በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአጉል የወረት ፍቅር ልላቀቅ የምችለው እንዴት ነው?

ከአጉል የወረት ፍቅር ልላቀቅ የምችለው እንዴት ነው?

ምዕራፍ 28

ከአጉል የወረት ፍቅር ልላቀቅ የምችለው እንዴት ነው?

“ለአብዛኞቹ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ለሚገኙ ወጣቶች” ይላል አንድ በወጣቶች ጉዳይ ላይ የሚያተኩር መጽሔት፣ “በአጉል የወረት ፍቅር መያዝ በጉንፋን የመያዝን ያህል በጣም የተለመደ ነገር ነው።” ሁሉም ወጣቶች ለማለት ይቻላል፣ አጉል የወረት ፍቅር ይይዛቸዋል። አብዛኞቹም የያዛቸውን አጉል የወረት ፍቅር አሸንፈው ክብራቸውንና ለዛቸውን እንደጠበቁ ወደ አዋቂነት ዕድሜ ይደርሳሉ። ይሁን እንጂ በአጉል የወረት ፍቅር ተተብትቦ መታሰር የሚያስደስት ነገር አይደለም። “በጣም ተበሳጭቼ ነበር” ይላል አንድ ወጣት ሲያስታውስ፣ “ምክንያቱም ይህ የያዘኝ ፍቅር የትም የሚያደርሰኝ አልነበረም። በዕድሜ በጣም ትበልጠኝ ነበር፤ ሆኖም ወደድኳት። በእርግጥ በዚህ የተነሳ ከሰውነት ተራ ወጥቼ ነበር።”

አጉል የወረት ፍቅር የሚይዘው እንዴት ነው?

አንድን ግለሰብ መውደድ ከሥነ ምግባር ውጭ እስካልሆነ ድረስ (ለምሳሌ ያህል ያገባ ካልሆነ) ምንም ስህተት የለውም። (ምሳሌ 5:​15–18) የሆነ ሆኖ በወጣትነት ዘመናችሁ በአብዛኛው አስተሳሰባችሁንና ድርጊታችሁን የሚገዛው “የጎልማሳነት ምኞት” ነው። (2 ጢሞቴዎስ 2:​22) በጉርምስና ምክንያት በውስጡ የሚፈጠሩትን አዳዲስና ኃይለኛ የሆኑ ፍላጎቶች መቆጣጠር በመልመድ ላይ ያለ ወጣት በውስጡ በሚቀሰቀሱ የፍቅር ስሜቶች ተወጥሮ ሊያዝ ይችላል። ግን ስሜቱን የሚወጣበት የፍቅር ጓደኛ አይኖረውም።

በተጨማሪም “ልጃገረዶች ከወንዶች ልጆች ይልቅ አስቀድመው የበሰሉና በቀላሉ ማኅበራዊ ግንኙነት ለመመሥረት የሚችሉ ይሆናሉ።” በዚህም ምክንያት “ብዙውን ጊዜ የክፍል ጓደኞቻቸው የሆኑት ወንዶች ከመምህሮቻቸው” ወይም ሊያገኙአቸው ከማይችሉ ሌሎች ትልልቅ ሰዎች ጋር ሲወዳደሩ ብስለት የሌላቸውና የማይማርኩ ሆነው ያገኟቸዋል። (ሰቨንቲን መጽሔት) በመሆኑም አንዲት ልጃገረድ የምትወደው አስተማሪ፣ ዘፋኝ፣ ወይም የምታውቀው በዕድሜ ትልቅ የሆነ ሰው “በጣም የሚወደድ” ሆኖ ሊታያት ይችላል። ወንዶች ልጆችም በተመሳሳይ ብዙ ጊዜ በአጉል የወረት ፍቅር ይያዛሉ። ይሁን እንጂ እንደዚህ ላሉ ሊያገኙአቸው ለማይችሉ ሰዎች የሚኖራቸው የፍቅር ስሜት በእውነታ ላይ ሳይሆን በቅዠት ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ግልጽ ነው።

አጉል የወረት ፍቅር ጎጂ የሚሆንበት ምክንያት

ብዙዎቹ የአጉል ወረት ፍቅር አጋጣሚዎች የሚቆዩት በጣም አጭር ለሆነ ጊዜ ቢሆንም በአንድ ወጣት ላይ ብዙ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ። መጀመሪያ ነገር በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ የሚገኝ ወጣት የሚያፈቅራቸው ብዙ ነገሮች ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው አይደሉም። አንድ ጠቢብ ሰው “ሞኝነት ከፍተኛ ቦታ ይሰጠዋል” ብሏል። (መክብብ 10:​6 አዓት) በመሆኑም አንድ ዘፋኝ የሚወደደው ጥሩ ድምፅ ወይም የሚያምር መልክ ስላለው ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ባለው ሥነ ምግባር ረገድ ሊመሰገን የሚገባው ሰው ነውን? ራሱን ለአምላክ የወሰነና “በጌታ” ያለ ክርስቲያን ነውን?​— 1 ቆሮንቶስ 7:​39

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል እንዲሆን አታውቁምን?” በማለት ያስጠነቅቃል። (ያዕቆብ 4:​4) አምላክ የሚያወግዘው አኗኗር ባለው ሰው ላይ ልባችሁን መጣላችሁ ከአምላክ ጋር ያላችሁን ወዳጅነት በአደጋ ላይ አይጥለውምን? በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “ከጣዖታት ራሳችሁን ጠብቁ” በማለት ያዝዛል። (1 ዮሐንስ 5:​21) አንድ ወጣት የክፍሉን ግድግዳ በእውቅ ዘፋኞች ፎቶግራፎች ከዳር እስከ ዳር ቢሞላ ይህ ድርጊቱ ምን ይባላል? “ጣዖት” አምልኮ ነው ቢባል ትክክል አይሆንም? ይህስ አምላክን እንዴት ሊያስደስተው ይችላል?

እንዲያውም አንዳንድ ወጣቶች ቅዠታቸው የማሰብ ችሎታቸውን እንዲጋርድባቸው ይፈቅዳሉ። አንዲት ወጣት ሴት ስትናገር “ስለ እኔ ምን እንደሚሰማው ስጠይቀው ምንም ስሜት የለኝም በማለት ይክዳል። ነገር ግን ከአኳኋኑና ከአስተያየቱ ውሸቱን እንደሆነ ልመለከት እችላለሁ” ብላለች። ይህ እሷ የምትለው ወጣት ለእርሷ ምንም ዓይነት ፍላጎት እንደሌለው በደግነት ሊገልጽላት ሞክሮ ነበር። እርሷ ግን የእምቢታ መልሱን ለመቀበል አልፈቀደችም።

አንዲት ልጃገረድ ከአንድ ታዋቂ ዘፋኝ ጋር ስለያዛት የወረት ፍቅር ስትጽፍ ‘የወንድ ጓደኛዬ እንዲሆን እፈልጋለሁ። ይህ ምኞቴ እውን እንዲሆንልኝም ጸልያለሁ! በቅርቤ የማገኘው ነገር የዘፈን ካሴቱ አልበም በመሆኑ አቅፌው ስተኛ ቆይቻለሁ። ላገኘው ካልቻልኩ ራሴን እገድላለሁ የምልበት ደረጃ ላይ ደርሻለሁ’ ብላለች። ታዲያ እንዲህ ዓይነቱ አእምሮ ቢስ ወረት ‘በጤናማ አእምሮ’ እንድናገለግለው የሚያዘንን አምላክ ያስደስታልን?​— ሮሜ 12:​3

መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌ 13:​12 ላይ “የምትዘገይ ተስፋ ልብን ታሳዝናለች” ይላል። በመሆኑም ሊገኝ ከማይችል ሰው ጋር በፍቅር ለመቆራኘት ተስፋ ማድረግ ጤናማ ካለመሆኑም በላይ ዛሬ ሐኪሞች ተቀባይ ያላገኘ ፍቅር የትካዜ፣ የጭንቀትና የመብሰክሰክ . . . የእንቅልፍ ማጣት ወይም የመልፈስፈስ፣ የደረት ውጋት ወይም የትንፋሽ ቁርጥ ቁርጥ ማለት መንስኤ እንደሆነ ይናገራሉ። (ከ2 ሳሙኤል 13:​1, 2 ጋር አወዳድሩ።) አንዲት የወረት ፍቅር የያዛት ልጃገረድ “ምግብ አይበላልኝም። . . . ትምህርቴንም መከታተል አልቻልኩም . . . የማልመው ሁሉ ስለ እርሱ ነው። . . . በጣም ብስጩ ሆኜአለሁ” በማለት የደረሰባትን ተናግራለች።

እውን ሊሆን የማይችል ቅዠት ሕይወታችሁን እንዲገዛው በምትፈቅዱበት ጊዜ በራሳችሁ ላይ ምን ዓይነት ጥፋት እንደሚደርስ አስቡ። ዶክተር ሎረንስ ባውማን ከቁጥጥር ውጭ የሆነ የወረት ፍቅር የመጀመሪያ ምልክቶች ከሆኑት ነገሮች ውስጥ አንዱ “ለትምህርት የሚደረገው ጥረት መቀነስ” እንደሆነ ተናግረዋል። ሌላው የተለመደ ውጤት ደግሞ ከጓደኞችና ከቤተሰብ ራስን ማግለል ነው። በተጨማሪም የእፍረት ስሜት ሊሰማ ይችላል። ደራሲው ጊል ሽቫርዝ “በዚህ ሁኔታ ላይ ወድቄ እንደነበረ መቀበል ያሳፍረኛል። ከጁዲ ጋር የወረት ፍቅር ይዞኝ በነበረ ጊዜ በጣሙን ተጃጅዬ ነበር” ሲሉ ጽፈዋል። አጉል የሆነው የወረት ፍቅር ካለፈ ከረዥም ጊዜ በኋላ እንኳን ያ ወይም ያች ልጅ በሄደበት ወይም በሄደችበት ሁሉ ስትከተሉ የነበራችሁት፣ ገበናችሁ በሰው ፊት መውጣቱና ባጠቃላይም ራሳችሁን ማጃጃላችሁ ትዝ ሊላችሁ ይችላል።

እውነታውን መቀበል

በምድር ላይ ከኖሩት ጠቢብ ሰዎች አንዱ የነበረው ንጉሥ ሰሎሞን ለፍቅሩ ምንም ምላሽ ካልሰጠች አንዲት ልጃገረድ ጋር የወረት ፍቅር ይዞት ነበር። ለዚህች ልጃገረድ “እንደ ጨረቃ የተዋበች፣ እንደ ፀሐይም የጠራች” እያለ እጅግ ውብ ግጥሞች አዥጎድጉዶ ነበር። ነገር ግን ልትሸነፍለት አልቻለችም!​— መኃልየ መኃልይ 6:​10

ይሁን እንጂ ሰሎሞን በመጨረሻ እርሷን ለማግባባት ያደርግ የነበረውን ሙከራ እርግፍ አድርጎ ትቷል። እናንተም እንደ ሰሎሞን ስሜታችሁን ለመቆጣጠር የምትችሉት እንዴት ነው? “በገዛ ልቡ የሚታመን ሰው ሰነፍ [“ሞኝ” አዓት] ነው” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ምሳሌ 28:​26) በተለይ ይህ አባባል በአጉል የወረት ፍቅር ቅዠት በተያዛችሁበት ጊዜ እውነት ይሆናል። ይሁን እንጂ “በጥበብ የሚሄድ ግን ይድናል።” ይህ ማለት ነገሮችን በትክክለኛ መልካቸው ማየት ማለት ነው።

“መሠረት ያለውን ተስፋ መሠረት ከሌለው ተስፋ ለይታችሁ ልታውቁ የምትችሉት እንዴት ነው?” በማለት ዶክተር ሃወርድ ሃልፐርን ጠይቀዋል። “ሐቁን በጥንቃቄና በእርጋታ በመመዘን ነው።” እስቲ አስቡት:- ከዚህ ወይም ከዚህች ሰው ጋር እውነተኛ ፍቅር ለመመሥረት የምትችሉበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላልን? የወደዳችሁት ሰው ዝነኛ ከሆነ ምናልባት ጭራሹንም ልትገናኙ አትችሉ ይሆናል። ግለሰቡ በዕድሜ የሚበልጣችሁ ከሆነ፣ ለምሳሌ አስተማሪያችሁ ከሆነ በመካከላችሁ እውነተኛ ፍቅር ሊመሠረት የሚችልበት አጋጣሚ ያንኑ ያህል የመነመነ ነው።

በተጨማሪም የወደዳችሁት ሰው እስካሁን ድረስ ለእናንተ ፍላጎት ያለው መሆኑን አሳይቷልን? ካልሆነ ነገሮች ለወደፊቱ ይለወጣሉ ብላችሁ እንድታምኑ የሚያደርጋችሁ እርግጠኛ ምክንያት አላችሁ ወይስ እንዲያው ግለሰቡ ወይም ግለሰቧ ከንጹሕ ስሜት የተናገሩትን ወይም ያደረጉትን እንደ ፍቅር መግለጫ አድርጋችሁ ስለ ወሰዳችሁ ነው? በአብዛኞቹ አገሮች አስቀድመው የፍቅር ጥያቄ የሚያቀርቡት ከሴቶች ይልቅ ወንዶች ናቸው። አንዲት ልጃገረድ ለእርሷ ምንም ፍላጎት የሌለውን ወንድ የሙጥኝ ብላ ብታሳድድ ራሷን ልታዋርድ ትችላለች።

በተጨማሪም ግለሰቡ ወይም ግለሰቧ ፍቅራችሁን ተቀብለው እሺ ቢሉ ምን ታደርጋላችሁ? ጋብቻ የሚያስከትለውን ኃላፊነት ለመቀበል ተዘጋጅታችኋልን? ዝግጁ ካልሆናችሁ የቅዠት አሳባችሁን ከአእምሮአችሁ አውጥታችሁ “ከልብህ ኀዘንን አርቅ” የሚለውን ምክር ተቀበሉ። “ለመውደድ ጊዜ አለው።” ይህ ጊዜ የሚመጣው ደግሞ በርካታ ዓመታት አልፈው በዕድሜ ከበሰላችሁ በኋላ ሊሆን ይችላል።​— መክብብ 3:​8፤ 11:​10

ስሜታችሁን መመርመር

ዶክተር ቻርልስ ዛስትሮ ሲናገሩ “የወረት ፍቅር የሚይዘው አንድ ሰው የወደደውን ሰው ‘ፍጹም የሆነ አፍቃሪ’ አድርጎ ሲመለከት ነው፤ ይህም ማለት የወረት ፍቅር የያዘው ሰው የተወደደው ሰው ከፍቅር ተጓዳኝ የሚፈለጉት ባሕርያት በሙሉ አሉት ብሎ ይደመድማል ማለት ነው” ብለዋል። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነት “ፍጹም አፍቃሪ” ሊኖር አይችልም። “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል።”​— ሮሜ 3:​23

ስለዚህ ራሳችሁን እንደሚከተለው እያላችሁ ጠይቁ:- ይህን ልቤን የጣልኩበትን ሰው ምን ያህል አውቀዋለሁ? ፍቅር የያዘኝ ሐሳቤ ከወለደው ሰው ጋር ነውን? ጉድለቶቹን እንዳልመለከት ዓይኔን አሳውሬያለሁን? የወደዳችሁትን ሰው ትክክለኛ በሆነና ባልተዛባ አመለካከት ብታዩ ካላችሁበት የወረት ድንዛዜ ልትነቁ ትችላላችሁ! በተጨማሪም ለወደዳችሁት ሰው የሚሰማችሁ ፍቅር ምን ዓይነት እንደሆነ ብትመረምሩ ይረዳችኋል። ካቲ ማይክል ኮይ የተባሉ ጸሐፊ “በብስለት ላይ ያልተመሠረተ ፍቅር በቅጽበት ሊጀምርና ሊጠፋ ይችላል። . . . ትኩረት ያደረጋችሁት በራሳችሁ ላይ ሲሆን ፍቅር የያዛችሁም በፍቅር ከመያዝ ሐሳብ ጋር ነው። . . . በብስለት ላይ ያልተመሠረተ ፍቅር ሙጭጭ የሚል፣ ለኔ ብቻ የሚልና ቀናተኛ ነው። . . . በብስለት ላይ ያልተመሠረተ ፍቅር ፍጽምና ይጠብቃል” ብለዋል።​— ከ1 ቆሮንቶስ 13:​4, 5 ጋር አነጻጽሩ።

የወደዳችሁትን ሰው ከአእምሮአችሁ ማውጣት

በዓለም ያለው ምክንያት ሁሉ ቢቀርብላችሁ እንኳን የሚሰማችሁን ስሜት ሊፍቅላችሁ እንደማይችል የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ችግራችሁን የሚያባብስ ነገር ከማድረግ ልትቆጠቡ ትችላላችሁ። ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ ልብ ወለዶችን ማንበብ፣ የፍቅር ታሪክ የያዙ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን መመልከት፣ ወይም ደግሞ አንዳንድ የሙዚቃ ዓይነቶችን ማዳመጥ ብቻ እንኳን የብቸኝነት ስሜታችሁን ሊያባብስባችሁ ይችላል። ስለዚህ ሐሳባችሁ በዚህ ጉዳይ ላይ ብቻ እንዳያተኩር ተከላከሉ። “እንጨት ባለቀ ጊዜ እሳት ይጠፋል።”​— ምሳሌ 26:​20

የቅዠት ፍቅር ከልብ የሚወዱአችሁንና የሚያስቡላችሁን ሰዎች ሊተካላችሁ አይችልም። ስለዚህ ‘ራሳችሁን አታግልሉ።’ (ምሳሌ 18:​1) ወላጆቻችሁ በጣም ሊረዱአችሁ ይችሉ ይሆናል። ስሜታችሁን ለመደበቅ ምንም ያህል ሙከራ ብታደርጉም እንኳን አንድ ዓይነት የሚያብሰለስላችሁ ነገር እንዳለ አስተውለው ይሆናል። ታዲያ ለምን ቀርባችሁ በልባችሁ ውስጥ ያለውን አትገልጡላቸውም? (ከምሳሌ 23:​26 ጋር አወዳድሩ።) አንድ የጎለመሰ ክርስቲያንም በጥሞና ሊያዳምጣችሁ ይችላል።

“በሥራ ተጠመዱ” በማለት ኤስተር ዴቪዶዊዝ የተባሉ አንዲት ጸሐፊ ያሳስባሉ። በትርፍ ጊዜአችሁ መሥራት የምትወዱትን ነገር አድርጉ፣ አንድ ዓይነት የጉልበት ሥራ ሥሩ፣ ቋንቋ አጥኑ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ምርምር ፕሮጄክት ጀምሩ። ጠቃሚ በሆኑ ሥራዎች መጠመዳችሁ ከምትወዱት ሰው ጋር ለመሆን አለመቻላችሁ የሚያስከትልባችሁን የስሜት መቃወስ በጣም ሊያቃልልላችሁ ይችላል።

ከአጉል የወረት ፍቅር መላቀቅ ቀላል አይደለም። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ግን የሚሰማችሁ ሥቃይ እየቀነሰ ይሄዳል። ከዚህም ስለራሳችሁና ስለስሜታችሁ ብዙ ትምህርት ታገኛላችሁ። ለወደፊቱ እውነተኛ ፍቅር ቢያጋጥማችሁ እንዴት እንደምትይዙት በተሻለ ሁኔታ የተዘጋጃችሁ ትሆናላችሁ! ይሁን እንጂ ‘እውነተኛ ፍቅርን’ ለይታችሁ ለማወቅ የምትችሉት እንዴት ነው?

የመወያያ ጥያቄዎች

◻ አጉል የወረት ፍቅር በወጣቶች ዘንድ የተለመደ የሆነው ለምንድን ነው?

◻ ብዙውን ጊዜ የወጣትነት የቅዠት ፍቅር የሚይዛቸው እነማን ናቸው? ለምንስ?

◻ አጉል የወረት ፍቅር ጎጂ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

◻ አንድ ወጣት አጉል ከሆነ የወረት ፍቅር ለመላቀቅ ሊያደርግ የሚችላቸው አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

◻ አንድ ወጣት የያዘውን የቅዠት ፍቅር ከማባባስ ሊቆጠብ የሚችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 223 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

‘ምግብ አይበላልኝም። ትምህርቴንም መከታተል አልቻልኩም። የማልመው ሁሉ ስለ እርሱ ነው። በጣም ብስጩ ሆኜአለሁ’

[በገጽ 220 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከትላልቅና ሊገኙ ከማይችሉ ተቃራኒ ጾታ ያላቸው ሰዎች ጋር የወረት ፍቅር ማጋጠሙ በጣም የተለመደ ነገር ነው

[በገጽ 220 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የወደዳችሁትን ሰው በተረጋጋ መንፈስና ባልተዛባ አመለካከት ማየት ከፍቅር ስሜታችሁ የምትገላገሉበት ፈውስ ሊሆንላችሁ ይችላል