በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የተሳካ ጥናታዊ ቅርርብ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?

የተሳካ ጥናታዊ ቅርርብ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?

ምዕራፍ 32

የተሳካ ጥናታዊ ቅርርብ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?

“አብዛኞቹ ጋብቻዎች ሳይሳኩ የሚቀሩት በጥናታዊ ቅርርብ አለመሳካት ምክንያት ነው። ይህ ነጥብ ከሚገባው በላይ ተደጋገመ ሊባል አይችልም።” እንዲህ በማለት የተናገሩት የቤተሰብ ሕይወት ጉዳይ ተመራማሪ የሆኑት ፖል ኤች ላንዲስ ናቸው። ሉዊዝ የዚህን አባባል ትክክለኛነት ልትመሰክር ትችላለች። እንዲህ በማለት ትገልጻለች:- “ትልቁ ስህተቴ አንዲ ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ ከማረጋገጤ በፊት በእርሱ ፍቅር መማረኬ ነበር። ጥናታዊ ቅርርባችን ብዙውን ጊዜ እኔና እርሱ ብቻ ሆነን በምናሳልፈው ጊዜ የተወሰነ ነበር። ከእነዚህ ‘አመቺ ናቸው’ ከሚባሉት ጊዜያት ውጭ ምን ዓይነት ጠባይ እንደሚያሳይ አይቼ አላውቅም።” ጋብቻቸው በፍቺ ፈረሰ። እንዲህ ዓይነቱን አሳዛኝ ሁኔታ ማስወገድ የሚቻልበት መፍትሔ ምንድን ነው? የተሳካ ጥናታዊ ቅርርብ ማካሄድ ነው!

ተቀጣጥሮ መጫወት ከመጀመር በፊት መደረግ ያለበት ነገር

“ብልህ [ሰው/ሴት] አካሄዱን ይመለከታል።” (ምሳሌ 14:​15) እምብዛም ለማታውቁት ሰው፣ ያ ሰው ማራኪ መስሎ ቢታያችሁ እንኳን፣ ለእሱ(ሷ) ያላችሁ ፍቅር እያደገ እንዲሄድ ማድረግ ችግር መጋበዝ ነው። በስሜቱና በግቦቹ ከእናንተ እጅግ በጣም ከራቀ ሰው ጋር ጋብቻ ወደመመሥረት ሊያደርሳችሁ ይችላል! ስለዚህ ይህን ሰው ምናልባትም በአንድ ዓይነት መዝናኛ ላይ ከበርካታ ሰዎች ጋር በሆናችሁበት ቦታና ሁኔታ ብታዩት አስተዋይነት ይሆናል።

“አስቀድሜ በጣም ከተቀራረብኩ ስሜቴ የማመዛዘን ችሎታዬን ሊጋርድብኝ እንደሚችል አውቅ ነበር” በማለት ደስተኛ ትዳር ከመሠረተ አሥር ዓመት የሆነው ዴቭ ገልጿል። “ስለዚህም ሮዝን ለእርሷ የተለየ ስሜት እንዳለኝ ከማወቋ በፊት ከርቀት እመለከታት ነበር። ለሰዎች ስለምታሳየው ጠባይ፣ ከሌሎች ጋር የመዳራት ፍላጎት የሌላት መሆኗን ለማየት እችል ነበር። ባደረግናቸው ተራ ጭውውቶች ሁኔታዋንና ግቧን ለማወቅ ቻልኩ።” በተጨማሪም ስለግለሰቡ ከሚያውቁ ሰዎች ጋር በመነጋገርና ግለሰቡ በምን ዓይነት ባሕርይ የታወቀ መሆኑን ጠይቆ በመረዳት ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ መገንዘብም ይጠቅማል።​— ከምሳሌ 31:​31 ጋር አወዳድሩ።

ከተቃራኒ ጾታ ጋር የሚደረጉ የመጀመሪያ ቀጠሮዎች

አንዲት ሴት (አንድ ወንድ) ለእናንተ ተስማሚ የትዳር ጓደኛ እንደምትሆን (እንደሚሆን) ውሳኔ ላይ ከደረሳችሁ በኋላ ወደዚች ሴት (ወደዚህ ወንድ) ቀርባችሁ ስለ እርሷ (ስለ እርሱ) ይበልጥ ለማወቅ የምትፈልጉ መሆናችሁን ልትገልጹ ትችላላችሁ። * አዎንታዊ ምላሽ ካገኛችሁ የመጀመሪያው ቀጠሯችሁ የተንዛዛ መሆን አያስፈልገውም። ምናልባትም ምሳ አብራችሁ ለመብላት ወይም ደግሞ ሌሎች ሰዎች ባሉበት አብራችሁ ለመሆን ብትቀጣጠሩ በይበልጥ ለመተዋወቅና ከዚህች ሴት (ከዚህ ወንድ) ጋር የሚኖራችሁን ግንኙነት ልትቀጥሉ ትፈልጉ እንደሆነና እንዳልሆነ ለመወሰን ያስችላችኋል። በቀጠሯችሁ ወቅት የምታደርጓቸው ነገሮች ዘና የሚያደርጉ ቢሆኑ ሁለታችሁም በመጀመሪያ ሊሰማችሁ የሚችለውን መደናገጥና ውጥረት ሊያቃልልላችሁ ይችላል። በተጨማሪም ከሁለት አንዳችሁ በውጥናችሁ ለመግፋት ያላችሁ ፍላጎት የጠፋ እንደሆነ ኀፍረት ወይም ፈላጊ የማጣት ስሜት እንዳይሰማችሁ ቃል ለመግባት ወይም ውሳኔያችሁን ለማሳወቅ አትቸኩሉ።

ተቀጣጥራችሁ ለመጨዋወትና ለመጠናናት የመረጣችሁት ሁኔታ ምንም ዓይነት ቢሆን በሰዓቱ ለመገኘትና ንጹሕና ተገቢ የሆነ ልብስ ለብሳችሁ ለመቅረብ ሞክሩ። ጨዋታ የማድመቅ ጥሩ ችሎታ ይኑራችሁ። ንቁ አድማጮች ሁኑ። (ያዕቆብ 1:​19) እንዲህ አድርግ ወይም አታድርግ የሚሉ የማይሻሩና የማይለወጡ ደንቦች ባይኖሩም ወጣቱ ሰው በአካባቢው የተለመዱትን የጨዋነት ደንቦች ለመከተል ሊፈልግ ይችላል። እነዚህም የጨዋነት ደንቦች ለልጂቱ በር መክፈትን ወይም ደግሞ የምትቀመጥበትን ወንበር ማመቻቸትን ሊጨምሩ ይችላሉ። ወጣቷ ሴትም እንደ ልዕልት ተንከባከቡኝ የምትል ባትሆንም አብሯት ያለው ወንድ እሷን ለማስተናገድ ከሚያደርገው ጥረት ጋር በጨዋነት መተባበር ይኖርባታል። ወንዱና ሴቷ እርስ በርስ ሲከባበሩ ወደፊት የሚከተሉትን የአኗኗር ሥርዓት መለማመድ ይጀምራሉ። ባል ‘ደካማ ዕቃን በክብር እንደሚይዝ’ ሚስቱንም እንዲያከብር ታዟል። ሚስት ደግሞ “ለባሏ ጥልቅ አክብሮት” እንዲኖራት ያስፈልጋል።​— 1 ጴጥሮስ 3:​7፤ ኤፌሶን 5:​33 አዓት

እጅ ለእጅ መያያዝ፣ መሳሳም ወይም ደግሞ መተቃቀፍ ተገቢ ነውን? ከሆነስ መቼ? የፍቅር መግለጫዎች ከራስ ወዳድነት የመነጨ ወሲባዊ ፍላጎት መግለጫዎች ካልሆኑና የእውነተኛ መዋደድ መግለጫዎች ከሆኑ ንጹሕና ተገቢ ሊሆኑ ይችላሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው መኃልየ መኃልይ ሱነማይቱ ልጃገረድና የምትወደው እጮኛዋ የነበረው እረኛ ስለተለዋወጧቸው ተገቢ የሆኑ የፍቅር መግለጫዎች ይገልጻል። (መኃልየ መኃልይ 1:​2፤ 2:​6፤ 8:​5) ይሁን እንጂ ተጓዳኞች የሆኑ ወንድና ሴት እንደነዚህ ንጹሐን ወንድና ሴት የሚያደርጓቸው የፍቅር መግለጫዎች ርኩስ ወይም ከሥነ ምግባር ውጭ ወደሆነ የጾታ ብልግና እንዳያመሩ ተጨማሪ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። * (ገላትያ 5:​19, 21) እንደነዚህ ያሉት የፍቅር መግለጫዎች መደረግ ያለባቸው በመካከላቸው ያለው ግንኙነት ቁርጥ ያለ ቃል ኪዳን ወደመግባት ደረጃ ካደገ በኋላና ጋብቻቸው በቅርብ ጊዜ ውስጥ መፈጸሙ የማይቀር በሚሆንበት ጊዜ ቢሆን ምክንያታዊ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ራሳችሁን ብትቆጣጠሩ የተሳካ ጥናታዊ ቅርርብን ዋነኛ ዓላማ ለማከናወን ትችላላችሁ፤ የተሳካ ጥናታዊ ቅርርብ ዋና ዓላማም . . .

“የተሰወረውን የልብ ሰው” ማወቅ

አንድ የተመራማሪዎች ቡድን ጆርናል ኦቭ ማረጅ ኤንድ ዘ ፋምሊ በተሰኘው የግንቦት 1980 እትም ላይ የሚከተለውን ገልጿል:- “ሰዎች አንዳቸው ስለ ሌላው ውስጣዊ ማንነት በመጠኑም ቢሆን የተሟላ እውቀት አግኝተው የመሠረቷቸው ጋብቻዎች ከመፍረስ ተርፈው ለመለምለም ያላቸው አጋጣሚ በጣም ከፍተኛ ነው።” አዎን፣ የተጓዳኛችሁን “የተሰወረ የልብ ሰው” ማወቅ አስፈላጊ ነው።​— 1 ጴጥሮስ 3:​4

ሆኖም አንድ ሰው በውስጡ ያለውን የልብ አሳብ እንዲያወጣ ማድረግ ጥረትና ማስተዋል የሚጠይቅ ነገር ነው። (ምሳሌ 20:​5) ስለዚህ የተጓዳኛችሁን ውስጣዊ ማንነት ለማወቅ የበለጠ ሊረዷችሁ በሚችሉ የሥራ እንቅስቃሴዎች ለመካፈል እቅድ አውጡ። መጀመሪያ ላይ አብሮ ፊልም ወይም የሙዚቃ ትርኢት ማየት በቂ ሲሆን ይበልጥ ለመነጋገር በሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች መካፈል (ለምሳሌ እንደ ሸርተቴና ቦሊንግ ያሉትን ጨዋታዎች መጫወት፣ የአራዊት መጠበቂያ ቦታዎችን ማየት፣ ቤተ መዘክሮችንና የኪነ ጥበብ አዳራሾችን መጎብኘት) በተሻለ ሁኔታ እንድትተዋወቁ ሊረዷችሁ ይችላሉ።

ስለ ተጓዳኛችሁ ውስጣዊ ስሜቶች ፍንጭ ለማግኘት ‘ነፃ ጊዜህን/ጊዜሽን የምታሳልፈው/የምታሳልፊው እንዴት ነው?’ ‘ገንዘብ እንደልብ ብታገኝ/ብታገኚ ምን ማድረግ ትፈልግ/ትፈልጊ ነበር?’ ‘ከአምልኮ ሥራዎች መካከል ከሁሉ አስበልጠህ/አስበልጠሽ የምትወደው/የምትወጂው የትኛውን ነው? ለምንስ?’ የሚሉትን የመሳሰሉ የውስጥን ሐሳብ አለገደብ ለመግለጽ የሚያስችሉ ጥያቄዎች ለመጠየቅ ሞክሩ። እነዚህ ጥያቄዎች ተጓዳኛችሁ ከልብ የሚወደውን/የምትወደውን ነገር እንድታውቁ የሚረዷችሁን ጥልቀት ያላቸው መልሶች ያስገኛሉ።

ዝምድናችሁ ጥልቀት እያገኘ ሲሄድና ሁለታችሁም ስለ መጋባት ማሰብ ስትጀምሩ ይበልጥ አሳሳቢ ስለሆኑ ጉዳዮች፣ ለምሳሌም በሕይወታችሁ ውስጥ ከፍተኛ ግምት ስለምትሰጧቸው ነገሮች፣ የትና እንዴት እንደምትኖሩ፣ ስለ ገንዘብ ጉዳዮች፣ ሁለታችሁም ከቤት ውጭ መሥራት ያስፈልጋችሁ እንደሆነና እንዳልሆነ፣ ስለ ልጆች፣ ስለ ወሊድ መከላከያ፣ እያንዳንዳችሁ በትዳሩ ውስጥ የሚኖራችሁን የሥራ ድርሻ ስለሚመለከቱ ጉዳዮች እንዲሁም የአጭርና የረዥም ጊዜ ግቦቻችሁን እነዚህም ግቦቻችሁ ላይ ለመድረስ የሚያስችላችሁን እቅድ እንዴት እንደምታወጡና ስለመሳሰሉት ነገሮች መወያየት አስፈላጊ ይሆናል። ብዙ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን ይሆናሉ። ካገቡም በኋላ ቢሆን በዚሁ አገልግሎት ለመቀጠል ይፈልጋሉ። የሁለታችሁም መንፈሳዊ ግቦች የሚጣጣሙ መሆናቸውን ማረጋገጥ የሚኖርባችሁ በዚህ ጊዜ ነው። በተጨማሪም ምናልባት ባለፈው ሕይወታችሁ ያደረጋችኋቸውና በትዳራችሁ ላይ ተጽእኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ነገሮች ካሉ ስለ ጉዳዩ መግለጽ የሚኖርባችሁ በዚህ ጊዜ ነው። ይህም ከበድ ያለ ዕዳን ወይም የገባችሁትን ግዴታ ሊጨምር ይችላል። ጤንነትን የሚመለከቱ ጉዳዮች፣ ለምሳሌ ከባድ በሽታ መኖሩና ሊያስከትል የሚችለው መዘዝ ውይይት ሊደረግበት ይገባል።

እንደዚህ ባሉት ውይይቶች ወቅት “የልቤን ቀጥታ እናገራለሁ፣ የምናገረውም በቅንነት ነው” በማለት የተናገረውን የኤሊሁን ምሳሌ ተከተሉ። (ኢዮብ 33:​3 ዘ ሆሊ ባይብል ኢን ዘ ላንጉዊጅ ኦቭ ቱደይ የተባለው በዊልያም ቤክ የተዘጋጀ ትርጉም) ኤስተር ያካሄደችው ጥናታዊ ቅርርብ የኋላ ኋላ ደስተኛ ትዳር ሊሆን ለበቃው ጋብቻዋ እንዴት እንዳዘጋጃት ስትገልጽ “ጄይ ከሚናገረው ነገር የተለየ ሐሳብ በሚኖረኝ ጊዜ ለማስመሰል ወይም ከእርሱ ጋር እንደተስማማሁ ለመናገር ሞክሬ አላውቅም። እስካሁንም እንዲህ አላደርግም። ሁልጊዜ ሐቀኛ ለመሆን እጥራለሁ” በማለት ተናግራለች።

ተጓዳኛችሁን እንዳታስከፉ በመፍራት የሚከነክኑ ጉዳዮችን ሸፋፍናችሁ ወይም አድበስብሳችሁ አትለፉ። ቤስ ከጆን ጋር ባደረገችው ጥናታዊ ቅርርብ ወቅት ይህን ስህተት ፈጽማለች። ቤስ ለወደፊቱ የሚሆን ገንዘብ በመቆጠብ እንጂ ገንዘብ በማባከን እንደማታምን ተናገረች። ጆንም በዚህ ጉዳይ ከእርሷ ጋር እንደሚስማማ ተናገረ። ቤስ በዚህ ጉዳይ እንደሚስማሙ በመገመት ተጨማሪ ጥያቄ አልጠየቀችም። ይሁን እንጂ ጆን ገንዘብ ለመቆጠብ ይፈልግ የነበረው የስፖርት መኪና ለመግዛት ነበር! ከተጋቡ በኋላ ገንዘባቸውን እንዴት ማውጣት እንዳለባቸው ሊስማሙ እንደማይችሉ ግልጽ ሆነ።

እንዲህ ዓይነቶቹ አለመግባባቶች እንዳይደርሱ ማድረግ ይቻላል። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሉዊዝ ጥናታዊ ቅርርቧን መለስ ብላ በማስታወስ እንደሚከተለው ብላለች:- “‘ባረግዝና አንተ ግን ልጅ እንዲኖርህ ባትፈልግ ምን ታደርጋለህ?’ ‘ዕዳ ቢኖርብንና እኔ ደግሞ ቤት ውዬ ለልጃችን እንክብካቤ ማድረግ ብፈልግ ምን ታደርጋለህ?’ የሚሉትንና የመሳሰሉትን ብዙ ጥያቄዎች መጠየቅ ነበረብኝ። የሚሰጠውን መልስ በጥንቃቄ ማጤን ነበረብኝ።” እንዲህ ዓይነቶቹ ውይይቶች ከጋብቻ በፊት ጥርት ብለው መታየት የሚኖርባቸውን የልብ ባሕርያት ይፋ እንዲወጡ ማስቻል ይኖርባቸዋል።

በዕለታዊ ተግባሮች ላይ እንዳሉ ተመልከቷቸው

“ሁለታችሁ ብቻ አብራችሁ በምትሆኑባቸው ጊዜያት ሰውዬው በጣም ደግ ሆኖ ሊታያችሁ ይችላል” በማለት ኤስተር ገልጻለች። “በሌሎች ሰዎች መካከል ሲሆን ግን ያልተዘጋጀበት ሁኔታ ሊያጋጥመው ይችላል። ከጓደኞቻችሁ አንዱ የማያስደስተው ነገር ሊናገረው ይችላል። አሁን እንዲህ ባለ ተጽእኖ ሥር ሲሆን የሚያሳየውን ምላሽ ለመመልከት ትችላላችሁ። ተጓዳኛችሁ የኃይል ቃል ይናገረው ወይም በአሽሙር ወጋ ያደርገው ይሆን?” ንግግሯን ስትቋጭም “በጥናታዊ ቅርርባችን ወቅት ከጓደኞቻችንና ከቤተሰቦቻችን ጋር መሆናችን በጣም ረድቶናል” ብላለች።

ከመዝናኛ በተጨማሪ አንዳንድ ሥራዎችን አብራችሁ ሥሩ። የአምላክን ቃል እንደ ማጥናትና በክርስቲያናዊ አገልግሎት እንደመሳተፍ ባሉ ክርስቲያናዊ ሥራዎች ተካፈሉ። በተጨማሪም የትዳር የዕለት ተዕለት ኑሮ ክፍል የሚሆኑትን እንደ ቀለብ መሸመት፣ ምግብ ማብሰል፣ የምግብ ዕቃዎችን ማጠብ፣ ቤት ማጽዳት ያሉትን ሥራዎች አብራችሁ ሥሩ። እውነተኛ ሕይወት በሚንጸባረቅባቸው ሁኔታዎች፣ ተጓዳኛችሁ ውበቱን/ውበቷን መጠበቅ በማይችሉበት ሁኔታ ላይ ሆነው ጭምር፣ አብራችሁ ስትሆኑ ከማንኛውም በውጭ አምሮ ለመታየት ከሚደረግ መሸፋፈኛ አልፋችሁ ለማየት ትችላላችሁ።

በመኃልየ መኃልይ ላይ የተገለጸው እረኛ የሚወዳት ልጃገረድ ባዘነችበት ወይም በሚያቃጥለው ፀሐይ ስትለፋ ቆይታ ደክሟትና አልቧት ሳለ የነበራትን ሁኔታ ተመልክቷል። (መኃልየ መኃልይ 1:​5, 6፤ 2:​15) የባለጠጋውን የንጉሥ ሰሎሞንን ማባበያዎች በታማኝነት እንዴት እንደተቋቋመች ከተመለከተ በኋላ “ውዴ ሆይ! ሁለንተናሽ ውብ ነው፤ ምንም እንከን የለብሽም” በማለት በአድናቆት ተናግሯል። (መኀልየ መኀልይ 4:​71980 ትርጉም) ፍጹም ናት ማለቱ እንዳልነበረ ግልጽ ነው። ምንም ዓይነት መሠረታዊ የሆነ የሥነ ምግባር ጉድለት ወይም እንከን አልነበረባትም ማለቱ ነበር። ከነበረባት ማንኛውም ዓይነት ድክመት አመዝኖ የሚታየው ሥነ ምግባራዊ ጥንካሬዋ አካላዊ ውበቷን ጨምሮላታል።​— ከኢዮብ 31:​7 ጋር አወዳድሩ።

ይህን የመሰለ ግምገማ ለማድረግ ረዘም ያለ ጊዜ ያስፈልጋል። ስለዚህ በችኮላ የሚደረግን ጥናታዊ ቅርርብ አስወግዱ። (ምሳሌ 21:​5) ብዙውን ጊዜ ወንዶችና ሴቶች አንዳቸው ሌላውን ለመማረክ ይጣደፋሉ። በቂ ጊዜ ወስደው ቢጠናኑ ግን ደስ የማይሉ ልማዶችና ዝንባሌዎች ይፋ የሚወጡበት የራሳቸው መንገድ ይኖራቸዋል። በጥናታዊ ቅርርባቸው ወቅት ጊዜ መውሰድ ብቻ ሳይሆን የወሰዱትን ጊዜ በጥሩ መንገድ የሚጠቀሙ ተጓዳኞች ከተጋቡ በኋላ ተስማምተው ለመኖር ይቀላቸዋል። የሚነሱ አለመግባባቶችን ለመፍታት እንደሚችሉ በመተማመንና ብሩሕ አመለካከት በመያዝ ሊጋቡ ይችላሉ። የተሳካ ጥናታዊ ቅርርብ ለሰመረና ደስተኛ ለሆነ ጋብቻ አዘጋጅቷቸዋልና።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.8 ይህ ልማድ የሚያገለግለው ተቃራኒ ጾታ ያላቸው ሰዎች ተቀጣጥረው አብረው መጫወት በተለመደባቸውና ክርስቲያኖችም እንዲህ ቢያደርጉ ተገቢ እንደሆነ ተደርጎ በሚታይባቸው አገሮች ነው። አንድ ወጣት ሐሳቡን ለመግለጽ ዓይን አፋር ወይም ፈራ ተባ የሚል ከሆነ አንዲት ወጣት ሴት ጨዋነት ባልተለየው መንገድ ስሜቷን እንዳትገልጽ የሚያግዳት ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓት ባይኖርም ብዙውን ጊዜ ሐሳብ ለማቅረብ የመጀመሪያ የሚሆነው ወንዱ ነው።​— ከመኃልየ መኃልይ 8:​6 ጋር አወዳድሩ።

^ አን.10 “ከጋብቻ በፊት ወሲብ እንድፈጽም ብጠየቅ እንዴት እምቢ ማለት እችላለሁ?” የሚል ርዕስ ያለውን ምዕራፍ 24ን ተመልከቱ።

የመወያያ ጥያቄዎች

◻ የጥናታዊ ቅርርብ ዋና ዓላማ ምንድን ነው? ደስታ የሰፈነበት ትዳር ለመመሥረትስ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

◻ የሌላውን ሰው ‘ውስጣዊ ማንነት’ ለማወቅ ምን ሊረዳችሁ ይችላል?

◻ ለተሳካ ጥናታዊ ቅርርብ የሚረዱት ምን ዓይነት ጭውውቶች ናቸው?

◻ በተለያዩ ሁኔታዎች አንድ ላይ ሆኖ ጊዜ ማሳለፍ የሚጠቅመው ለምንድን ነው?

◻ አንድ ግንኙነት ችግር እንዳለበት የሚጠቁሙ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

◻ ጥናታዊ ቅርርቡ መሰረዝ የሚኖርበት መቼ ነው?

[በገጽ 255 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ሰዎች አንዳቸው ስለ ሌላው ውስጣዊ ማንነት በመጠኑም ቢሆን የተሟላ እውቀት አግኝተው የመሠረቷቸው ጋብቻዎች ከመፍረስ ተርፈው ለመለምለም ያላቸው አጋጣሚ በጣም ከፍተኛ ነው።”​—ጆርናል ኦቭ ማረጅ ኤንድ ዘ ፋምሊ

[በገጽ 256, 257 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

መለያየት ይኖርብን ይሆን?

በሁለት ተቃራኒ ጾታዎች መሐል ያለ ፍቅር ቁርጥ ያለ ውሳኔ ማድረግ አስፈላጊ በሚሆንበት ደረጃ ላይ ሲደርስ ጥርጣሬዎች መነሳታቸው ያልተለመደ ነገር አይደለም። እንደዚህ ያሉት ጥርጣሬዎች የተነሱት እየተቀጣጠራችሁ አብራችሁት የምትጫወቱት ሰው ከባድ ጉድለቶች ስላሉበት ወይም ጉድኝቱ ራሱ ጉድለት ስላለበት ቢሆን ምን መደረግ ይኖርበታል?

ለምሳሌ ያህል እርስ በርሳቸው በሚዋደዱ ሰዎች መካከል እንኳን አንዳንድ ጊዜ አለመግባባት ሊፈጠር እንደሚችል የታወቀ ነው። (ከዘፍጥረት 30:​2​ና ከሥራ 15:​39 ጋር አወዳድሩ።) ይሁን እንጂ በምንም ነገር ላይ ለመስማማት የማትችሉ፣ እያንዳንዱ ውይይት ወደመጯጯህ የሚለወጥ፣ ወይም ግንኙነታችሁ ማለቂያ በሌለው የመፍረስና የመጠገን ዑደት ላይ የተገነባ ከሆነ ተጠንቀቁ! የ400 ሐኪሞችን አስተያየት ያጠናቀረ አንድ መጠይቅ የማያቋርጥ ጭቅጭቅ መኖሩ “ለጋብቻ የሚያበቃ ስሜታዊ ብስለት” እንደሌለ፣ ምናልባትም “በወንዱና በሴቷ መካከል ሊታረቅ የማይችል ልዩነት” እንዳለ የሚጠቁም ኃይለኛ ምልክት እንደሆነ ገልጿል።

ሌላው አሳሳቢ ነገር ልታገቡ ባሰባችሁት ሰው ላይ በቀላል የማይታዩ የባሕርይ ጉድለቶችን ማግኘታችሁ ሊሆን ይችላል። የቁጡነት ጠባይ ያለው ቢሆን ወይም ራስ ወዳድነትን፣ አለመብሰልን፣ ነጭናጫነትን፣ ወይም እልከኝነትን የሚያመለክቱ ጥቂት ፍንጮች ቢታዩ ቀሪ ሕይወታችሁን እንደዚህ ካለው ሰው ጋር ለማሳለፍ መፈለጋችሁ ያጠራጥራችሁ ይሆናል። ሆኖም ብዙ ሰዎች እንደዚህ ያሉትን ጉድለቶች ችላ ብለው ወይም ማለባበሻ ሰበብ በመስጠት የጀመሩትን ዝምድና እንደምንም ብሎ እንዲሰምር ለማድረግ ይጥራሉ። እንዲህ የሚሆነው ለምንድን ነው?

ጥናታዊ ቅርርብ በእውነተኛ ክርስቲያኖች ዘንድ ክብደት የሚሰጠው ጉዳይ በመሆኑ፣ መሆንም አለበት፣ አንዳንድ ክርስቲያኖች እየተቀጣጠሩ አብረውት የሚጫወቱትን ሰው የማግባት ግዴታ እንዳለባቸው ሊሰማቸው ይችላል። በተጨማሪም ከዚህ ሰው ጋር መፋጠጥ ወይም እርሱን ማሳዘን ሊያስፈራቸው ይችላል። ሌሎች ደግሞ የማገባው ሌላ ሰው አላገኝ ይሆናል ብለው ይፈራሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ምክንያቶች ብዙ ችግር ያለበትን ጥናታዊ ቅርርብ እንዲቀጥል ለማድረግ የሚበቁ አይደሉም።

ጥናታዊ ቅርርብ የሚደረግበት ዓላማ ከግለሰቡ ወይም ከግለሰቧ ጋር ጋብቻ መመሥረት ይቻል እንደሆነ ለመመርመር ነው። ስለዚህ አንድ ክርስቲያን ጥናታዊ ቅርርብን በጥሩ እምነት ጀምሮት በጥናታዊ ቅርርቡ ወቅት ጉድለት ቢያገኝ ግንኙነቱን እንዲቀጥልበት አይገደድም። በተጨማሪም ‘ምናልባት ሌላ ሰው አላገኝ ይሆናል’ በሚል ምክንያት እየተበላሸ የሄደውን ግንኙነት እንዲቀጥል ማድረግ ስህተትና ራስ ወዳድነት አይሆንምን? (ከፊልጵስዩስ 2:​4 ጋር አወዳድሩ።) ስለዚህ ሁለታችሁም አንድ ላይ ሆናችሁ ችግራችሁን ፊት ለፊት ተጋፈጡት እንጂ አትሽሹት። ልታገቡ ያሰባችሁትን ሰው በጥንቃቄና በሚዛናዊነት መርምሩት።

ለምሳሌ ያህል ታዛዥና ባለሞያ ሚስት እንደምትሆን የሚያሳይ ማስረጃ አለን? (ምሳሌ 31:​10–31) ራሱን መሥዋዕት የሚያደርግ ፍቅር ያለውና ቤተሰቡ የሚያስፈልገውን የሚያቀርብ ሰው እንደሚሆን የሚያሳይ ማስረጃ አለን? (ኤፌሶን 5:​28, 29፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:​8) ግለሰቡ ወይም ግለሰቧ ቀናተኛ የአምላክ አገልጋይ እንደሆነ ወይም እንደሆነች ይናገሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህን አባባል የሚደግፍ ተግባር ይታይባቸዋልን?​— ያዕቆብ 2:​17, 18

እርግጥ በመካከላችሁ ያለው ግንኙነት እንዲጎለብት በርካታ የጊዜና የስሜት መሥዋዕትነት ከፍላችሁ ከነበረ ፍጹም አለመሆኑን ወይም አለመሆኗን ስለተገነዘባችሁ ብቻ ግንኙነታችሁን ለማቋረጥ መቸኮል የለባችሁም። (ያዕቆብ 3:​2) ምናልባትም ጉድለቶቹ ወይም ጉድለቶችዋ ችላችሁ የምታሳልፏቸው ዓይነት ሊሆኑ ይችላሉ።

ባይሆኑስ ምን ማድረግ ይኖርባችኋል? ጉዳዩን ተነጋገሩበት። በግቦቻችሁ ወይም ባመለካከቶቻችሁ ረገድ መሠረታዊ የሆኑ ልዩነቶች አሏችሁን? ያልተግባባችሁባቸው ነገሮች ስለኖሩ ብቻ ነውን? ምናልባት ሁለታችሁም ‘መንፈሳችሁን ተቆጣጥራችሁ’ ችግሮችን ከበፊቱ በበለጠ እርጋታ መፍታት መልመድ ስለሚያስፈልጋችሁ ይሆን? (ምሳሌ 25:​28) በተጓዳኛችሁ ላይ የምታዩት ለየት ያለ የሚያናድድ ባሕርይ አሳስቧችሁ ከሆነ ድክመቱን ወይም ድክመቷን በትሕትና በመቀበል ለመሻሻል ፍላጎት ያለው ወይም ያላት መሆኑን ያሳያል ወይም ታሳያለችን? በእናንተስ በኩል ይበልጥ ታጋሾችና በቀላሉ የማትቆጡ መሆን ያስፈልጋችሁ ይሆን? (መክብብ 7:​9) የጥሩ ጋብቻ ደመ ሕይወት ‘እርስ በርስ በፍቅር መቻቻል’ ነው።​— ኤፌሶን 4:2

ነገሮችን በግልጽ መነጋገር ዝምድናችሁን ከማበላሸት ይልቅ ወደፊት ይበልጥ ሊጎለብት የሚችል መሆኑን ሊያመለክት ይችላል። ይሁን እንጂ ውይይታችሁ ተስፋ አስቆራጭና ለምን ተነካሁ ባይነትን የሚያስከትል ከሆነ ይህ ውሎ አድሮ ችግር የሚያስከትል መሆኑን የሚያሳይ ግልጽ ምልክት ስለሆነ ችላ አትበሉት። (ምሳሌ 22:​3) ችግሮቹ ከጋብቻ በኋላም ላይሻሻሉ ይችላሉ። ጥናታዊ ቅርርባችሁን ማቋረጡ ለሁለታችሁም የሚበጅ ሊሆን ይችላል።

[በገጽ 253 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከሌሎች ሰዎች ጋር ሆናችሁ እርስ በርስ መተያየት በፍቅር ከመጠላለፋችሁ በፊት እንድትተዋወቁ ሊረዳችሁ ይችላል

[በገጽ 254 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአካባቢው የተለመዱትን የጨዋነት ደንቦችና የጥሩ ምግባር መግለጫዎች ማክበር ወደ ጋብቻም ሊያልፍ የሚችል የጋራ መከባበር ልምድ ይፈጥራል

[በገጽ 259 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጥናታዊ ቅርርቡ እንዳልተሳካ ግልጽ በሚሆንበት ጊዜ ፊት ለፊት ተወያይቶ ዝምድናው ለምን ማክተም እንዳለበት ግልጽ ማድረግ ትልቅ ደግነት ነው