በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልጆቹ የሚያስቸግሩኝ ለምንድን ነው?

ልጆቹ የሚያስቸግሩኝ ለምንድን ነው?

ምዕራፍ 19

ልጆቹ የሚያስቸግሩኝ ለምንድን ነው?

የልጁ አረማመድ ማንነቱን በደንብ የሚያሳውቅ ነው። የተጨነቀና በራሱ የማይተማመን፣ በግልጽ እንደሚታየውም በአዲሱ አካባቢው ግራ የተጋባ ነው። ከፍ ከፍ ያሉት ተማሪዎች በትምህርት ቤቱ አዲስ ገቢ መሆኑን ወዲያውኑ አወቁ። ከትንሽ ጊዜ በኋላ ወጣቶች ከበቡትና በጸያፍ አነጋገር ያጣድፉት ገቡ! ጆሮ ግንዱ በንዴት ቀልቶ ከእነርሱ በመሸሽ በአቅራቢያው ወዳለው መጸዳጃ ቤት ሊሸሸግ ሄደ። እዚያም ሆኖ ሳቃቸው ግድግዳውን ሰንጥቆ ሲያስተጋባ ይሰማው ነበር።

ማብሸቅ፣ በሰው መቀለድና ሌሎችን መሳደብ የብዙ ወጣቶች ጊዜ ማሳለፊያ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመንም እንኳን ሳይቀር አንዳንድ ወጣቶች እንዲህ ዓይነት ወራዳ ጠባይ አሳይተዋል። ለምሳሌ ያህል ትናንሽ ወንዶች ልጆች ነቢዩ ኤልሳዕን ለማብሸቅ ተሰብስበው ነበር። ወጣቶቹ ለኤልሳዕ የነቢይነት ሥራ ንቀት በማሳየት አክብሮት በጎደለው ሁኔታ “አንተ መላጣ፣ ውጣ፤ አንተ መላጣ፣ ውጣ ብለው አፌዙበት።” (2 ነገሥት 2:​23–25) ዛሬም በተመሳሳይ ብዙ ወጣቶች በሌሎች ሰዎች ላይ ስድብና ጎጂ አስተያየቶችን የመሰንዘር ዝንባሌ አላቸው።

ግሮዊንግ ፔይንስ ኢን ዘ ክላስሩም የተባለው መጽሐፍ ደራሲ እንደሚከተለው ብለዋል:- “ዘጠነኛ ክፍል ሳለሁ በክፍሉ ውስጥ የኔን ያህል አጭር ልጅ አልነበረም። በመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በክፍል ውስጥ ከሁሉም የበለጠ ጎበዝና አጭር ልጅ መሆን አበሳ መቁጠር ነው:- አጭር በመሆኔ ሊመቱኝ የማይፈልጉ ልጆች ጎበዝ በመሆኔ ሊመቱኝ ይፈልጉ ነበር። ‘አራት ዓይን’ ተብዬ ከመጠራት በተጨማሪ ‘ተንቀሳቃሽ መዝገበ ቃላት’ እና ሌሎች 800 ቅጽል ስሞች [የነቀፋ ቃላት] ተሰጥተውኝ ነበር።” ዘ ሎንሊነስ ኦቭ ችልድረን የተሰኘው መጽሐፍ ደራሲ “የአካል ጉድለት፣ የመናገር ችግር፣ ወይም ግልጽና ልዩ የሆኑ አካላዊና ባሕርያዊ ጉድለት ያላቸው ልጆች የሌሎች ልጆች መቀለጃ ለመሆን የተጋለጡ ናቸው” ብለዋል።

አንዳንድ ጊዜ ወጣቶች እርስ በርስ በመሰዳደብ (ብዙውን ጊዜም የሌላውን ወላጆች ክብር የሚነካ ስድብ በመሰንዘር) ራሳቸውን ለመከላከል በሚያደርጉት ሙከራ በከረረ የስድብ ውድድር ውስጥ ይገባሉ። ይሁን እንጂ ብዙ ወጣቶች እኩዮቻቸው ተሰብስበው ሲያበሽቋቸው ምንም ነገር ማድረግ ይሳናቸዋል። አንድ ወጣት በአንድ ወቅት የክፍል ጓደኞቹ ከሆኑ ወጣቶች በደረሰበት ፌዝና ንዝነዛ ምክንያት በጣም ከመፍራቱና ከማዘኑ የተነሳ ‘የማቅለሽለሽ ስሜት ይሰማው እንደነበረ ያስታውሳል።’ ሌሎች ተማሪዎች ስለሚያደርጉበት ነገር ከመጠን በላይ ይጨነቅ ስለነበረ በትምህርቱ ላይ ማተኮር አልቻለም።

የሚያስቅ ነገር አይደለም

እኩዮቻችሁ በሆኑ ጨካኝ ወጣቶች መሳለቂያ ሆናችሁ ታውቃላችሁን? እንዲህ ከሆነ አምላክ ይህን ጉዳይ እንደሚያስቅ ነገር አድርጎ እንደማይመለከተው ስታውቁ ትጽናኑ ይሆናል። የአብርሃም ልጅ ይስሐቅ ጡት በጣለበት ጊዜ ስለተዘጋጀው ድግስ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውሰዱ። የአብርሃም የመጀመሪያ ልጅ የነበረው እስማኤል ይስሐቅ ሊቀበል ስለነበረው ርስት በመቅናት ይመስላል፣ በይስሐቅ ላይ ‘ማሾፍ’ ጀምሮ ነበር። ይሁን እንጂ ማሾፉ ገራገር ቀልድ ከመሆን የራቀ ስለነበር እንደ ‘ስደት’ ተቆጥሯል። (ገላትያ 4:​29) የይስሐቅ እናት ሣራ በቀልዱ ውስጥ የጠላትነት መንፈስ እንደነበረ ተገነዘበች። ሣራ ይህን ነገር ይሖዋ በልጅዋ በይስሐቅ በኩል “ዘር” ወይም መሢሕ ለማስገኘት ያለውን ዓላማ ማቃለል እንደሆነ አድርጋ ተመለከተች። ሣራ ባቀረበችው ጥያቄም እስማኤልና እናቱ ከአብርሃም ቤተሰብ ተባረሩ።​— ዘፍጥረት 21:​8–14

በተመሳሳይም ወጣቶች ጭካኔ በተሞላበት መንገድ እየተሳደቡ ሲያስቸግሯችሁ፣ በተለይም ደግሞ ይህን የሚያደርጉባችሁ ከመጽሐፍ ቅዱስ የአቋም ደረጃዎች ጋር ተስማምታችሁ ለመኖር በመጣራችሁ ምክንያት ከሆነ፣ ይህ የሚያስቅ ነገር አይደለም። ለምሳሌ ክርስቲያን ወጣቶች እምነታቸውን ለሌሎች በማካፈል የታወቁ ናቸው። ይሁን እንጂ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች የተሰባሰቡበት አንድ ቡድን እንደተናገረው “በትምህርት ቤት ያሉት ልጆች ከቤት ወደ ቤት በመስበካችን ምክንያት ይቀልዱብንና ያዋርዱን ነበር” ብሏል። አዎን፣ በጥንት ዘመን እንደነበሩት የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች ብዙ ክርስቲያን ወጣቶችም ‘መዘበቻ በመሆን ፈተና’ ተፈትነዋል። (ዕብራውያን 11:​36) እንዲህ ዓይነቱን ነቀፋ ታግሠው ለመጽናት ስላሳዩት ድፍረት ሊመሰገኑ ይገባቸዋል!

የሚቀልዱበትና የሚያሾፉበት ምክንያት

ይሁን እንጂ የሚያስቸግሯችሁ ልጆች እንዴት እንዲተዉአችሁ ለማድረግ እንደምትችሉ ያሳስባችሁ ይሆናል። ከሁሉ አስቀድሞ በእናንተ ላይ የሚቀልዱበትን ምክንያት ተገንዘቡ። መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌ 14:​13 [አዓት ] ላይ “በሳቅ መሃልም እንኳን ልብ እያዘነ ሊሆን ይችላል” ይላል። ወጣቶች አንድ ላይ ሆነው ሌላውን ሰው ሲያበሽቁ ከት ብለው ይስቃሉ። ይሁን እንጂ የሚያወኩት ‘ከልባቸው ደስታ የተነሣ’ አይደለም። (ኢሳይያስ 65:​14) ብዙውን ጊዜ የሚስቁት በውስጣቸው ያለውን የስሜት መረበሽ ለመሸፈን ነው። ከጀብደኝነት ድንፋታቸው ሽፋን ሥር በእርግጥ ‘ራሳችንን አንወደውም፤ ሌላውን ሰው ማዋረድ ግን ስለ ራሳችን የተሻለ ስሜት እንዲሰማን ያደርጋል’ እያሉ ይሆናል።

በተጨማሪም ቅናት እንዲያበሽቋችሁ ሊያነሳሳቸው ይችላል። አባቱ ከሌሎቹ ልጆቹ አብልጦ ስለወደደው የገዛ ወንድሞቹ ተነስተውበት ስለነበረው ስለ ዮሴፍ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ አስታውሱ። በገዛ ወንድማቸው ላይ የነበራቸው ከፍተኛ ቅንዓት በቃላት ስድብ ብቻ ተወስኖ ሳይቀር ሊገድሉት እስከማሰብ አድርሷቸዋል! (ዘፍጥረት 37:​4, 11, 20) በአሁኑ ጊዜም በተመሳሳይ በብልህነቱ ከሌሎቹ ልቆ የሚታይ ወይም በአስተማሪዎቹ ዘንድ ተወዳጅ የሆነ ተማሪ የእኩዮቹን ቅንዓት ሊያነሳሳ ይችላል። እርሱን ‘ወደ ራሳቸው ደረጃ ለማዋረድ’ መፍትሔው ስድብ ይመስላቸዋል።

ብዙውን ጊዜ በሰው ለማሾፍ ምክንያት የሚሆኑት ነገሮች በራስ አለመተማመን፣ ቅናትና ራስን ዝቅ አድርጎ መመልከት ናቸው። ታዲያ አንድ በራሱ የማይተማመን ወጣት ለራሱ ጥሩ ግምት ስለ ሌለው በሚያደርገው ነገር ለራሳችሁ ያላችሁ ግምት ዝቅ ሊል ይገባዋልን?

ችግሩን ማስቆም

መዝሙራዊው “በፌዘኞች ወንበር የማይቀመጥ የተባረከ ነው” ይላል። (መዝሙር 1:​11980 ትርጉም። ) ፌዘኞቹ የሚሰነዝሩት ዘለፋ እናንተን ትቶ በሌሎች ላይ እንዲያነጣጥር ለማድረግ ብላችሁ ከፌዘኞቹ ጋር ብትተባበሩ የስድቡን ዑደት ከማራዘም ውጭ የሚፈይደው ነገር አይኖርም። “ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ . . . ክፉውን በመልካም አሸንፍ።”​— ሮሜ 12:​17–21

በተጨማሪም መክብብ 7:​9 “በነፍስህ ለቁጣ ችኩል አትሁን፣ ቁጣ በሰነፍ ብብት ያርፋልና” ይላል። አዎን፣ እናንተን ለማብሸቅ ተብሎ የሚሰነዘረውን ዘለፋ ለምን ከቁም ነገር ትቆጥራላችሁ? እርግጥ ነው፣ አንድ ሰው በሰውነት ቁመናችሁ ላይ ቢያሾፍ ወይም በፊታችሁ ገጽታ ላይ አንድ ጉድለት በመኖሩ ቢስቅባችሁ ቅር ያሰኛችኋል። ይሁን እንጂ የተሰነዘሩት አስተያየቶች ደስ ባይሉም ጎጂ ላይሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ አንድ ሰው በየዋህነት ወይም ሆን ብሎ እናንተን ለማናደድ በጉድለታችሁ ገብቶ ቁስላችሁን ቢነካ ለምን ቅስማችሁ ይሰበራል? የተነገረው ነገር ጸያፍ ወይም አልባሌ ካልሆነ እንደ ቀልድ ውሰዱት። “ለመሳቅ ጊዜ” ስላለው ለጨዋታ ተብሎ በሚነገር ፌዝ መቀየም ተገቢ ላይሆን ይችላል።​— መክብብ 3:​4

ይሁን እንጂ ፌዙ የጭካኔ አልፎ ተርፎም የተንኮል ከሆነስ? አሿፊው በእናንተ ምላሽ ለመደሰትና በእናንተ ብሽቀት ለመፈንጠዝ ፈልጎ መሆኑን አስታውሱ። በንዴት አጸፌታውን መመለስ፣ ማኩረፍ ወይም ማልቀስ በማበሳጨት ተግባሩ እንዲቀጥል ሊያበረታታው ይችላል። ታዲያ እንዲህ ላለው ሰው ስትናደዱ ዓይቶ የመደሰት ዕድል ለምን ትሰጡታላችሁ? ብዙውን ጊዜ ስድብን ለመመከት ከሁሉ የተሻለው መንገድ በግዴለሽነት ስቆ ማለፍ ነው።

ንጉሥ ሰሎሞን “ባሪያህ ሲረግምህ እንዳትሰማ በሚጫወቱበት ቃል ሁሉ ልብህን አትጣል [“ሰዎች ለሚናገሩት ነገር ሁሉ ትኩረት አትስጥ” ቱደይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን ] አንተ ደግሞ ሌሎችን እንደ ረገምህ ልብህ ያውቃልና” ብሏል። (መክብብ 7:​21, 22) አሿፊዎች በሚናገሩት መርዘኛ አስተያየት ላይ ‘ልብህን መጣል’ ስለ እነርሱ አስተያየት ከልክ በላይ መጨነቅ ማለት ይሆናል። ይሁን እንጂ እነርሱ የሚሰጡት አስተያየት ትክክል ነውን? ሐዋርያው ጳውሎስ በእርሱ ላይ ቅንዓት ካደረባቸው እኩዮቹ ተገቢ ያልሆነ አስተያየት ተሰንዝሮበት ነበር፤ እርሱ ግን ‘ስለ እኔ የሆነ እንደሆነ እናንተም ብትፈርዱብኝ ወይም ሌላ ሰው ቢፈርድብኝ ምንም ግድ የለኝም፤ . . . ነገር ግን በእኔ ላይ የሚፈርድ እግዚአብሔር ብቻ ነው’ በማለት መልስ ሰጥቷል። (1 ቆሮንቶስ 4:​3, 4) ጳውሎስ ከአምላክ ጋር የነበረው ዝምድና በጣም ጠንካራ ስለ ነበረ ተገቢ ያልሆኑ አስተያየቶችን ለመቋቋም በራሱ የመተማመን መንፈስና ውስጣዊ ጥንካሬ ነበረው።

ብርሃናችሁ እንዲበራ ማድረግ

አንዳንድ ጊዜ በክርስቲያናዊ አኗኗራችሁ ምክንያት ይቀለድባችሁ ይሆናል። ኢየሱስ ክርስቶስም እንኳን እንዲህ ዓይነቱን “የተቃውሞ ንግግር” መታገሥ አስፈልጎታል። (ዕብራውያን 12:​3 አዓት ) ኤርምያስም የይሖዋን መልእክት በድፍረት በመናገሩ ምክንያት ‘ቀኑን ሁሉ መሳቂያ ሆኗል’። የሚሰነዘርበት መጥፎ ትችት የማያቋርጥ ከመሆኑ የተነሳ የይሖዋን መልእክት ለመናገር የነበረውን ድፍረት ለጊዜውም ቢሆን አጥቶ ነበር። “የእግዚአብሔርን ስም አላነሣም፣ ከእንግዲህ ወዲህም በስሙ አልናገርም” ብሎ ወስኖ ነበር። ይሁን እንጂ ለአምላክና ለእውነት የነበረው ፍቅር በመጨረሻ ፍርሃቱን እንዲያሸንፍ ገፋፍቶታል።​— ኤርምያስ 20:​7–9

በአሁኑ ጊዜም አንዳንድ ክርስቲያን ወጣቶች እንደ ኤርምያስ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ተሰምቷቸዋል። አንዳንዶች የሚደርስባቸውን ዘለፋ በመፍራት ክርስቲያኖች መሆናቸውን ለመደበቅ ሞክረዋል። ይሁን እንጂ እንደዚህ ያሉት ወጣት ክርስቲያኖች ብዙውን ጊዜ ለአምላክ ባላቸው ፍቅር ተነሳስተው ከፍርሃታቸው ለመላቀቅና ‘ብርሃናቸው እንዲበራ ለማድረግ’ ችለዋል! (ማቴዎስ 5:​16) ለምሳሌ ያህል በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ አንድ ወጣት እንደሚከተለው ብሏል:- “ዝንባሌዬ ተለወጠ። ክርስቲያን መሆኔን በግድ እንደተጫነብኝ ሸክም አድርጌ መመልከቴን ትቼ ልኮራበት እንደሚገባ ነገር አድርጌ መመልከት ጀመርኩ።” እናንተም ብትሆኑ አምላክን የማወቅና ሌሎችንም የመርዳት መብት በማግኘታችሁ “ልትኮሩ” ትችላላችሁ።​— 1 ቆሮንቶስ 1:​31

ይሁን እንጂ ሁልጊዜ ሌሎችን በመተቸት ወይም እናንተ ከእነርሱ እንደምትበልጡ የሚሰማችሁ መሆኑን የሚያመለክት ነገር በመናገር በገዛ እጃችሁ ጥላቻ አትጋብዙ። አጋጣሚ ስታገኙ እምነታችሁን አካፍሉ፤ ይሁን እንጂ “በየዋህነትና በጥልቅ አክብሮት” ይሁን። (1 ጴጥሮስ 3:​15 አዓት ) በመልካም ጠባያችሁ ያተረፋችሁት መልካም ስም በትምህርት ቤት በምትቆዩበት ጊዜ ሁሉ ከብዙ ችግር ሊያድናችሁ ይችላል። ያላችሁን የቆራጥነት አቋም ሌሎች ባይወዱትም ብዙውን ጊዜ እነርሱ እንደ እናንተ ለመሆን ባለመቻላቸው እየተቆጩ በዚህ አቋማችሁ ያከብሯችኋል።

ቫኔሳ የምትባለውን አንዲት ልጃገረድ ሌሎች ልጃገረዶች በቡድን ሆነው እየመቱ፣ ወዲያ ወዲህ እየገፈተሩና መጽሐፎቿን ከእጆቿ ላይ እየዘረገፉ ያስቸግሯት ነበር። ይህን ሁሉ የሚያደርጉት ጠብ ለመቀስቀስ ነበር። አልፈው ተርፈው በራሷ ላይና በንጹሕ ነጭ ቀሚሷ ላይ የቸኮላት ወተት አፈሰሱባት። ይሁን እንጂ በሚያደርጉት የጠብ አጫሪነት ድርጊት አልተበገረችም። ቫኔሳ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የልጃገረዶቹ ቡድን መሪ የነበረችውን ልጅ በይሖዋ ምሥክሮች ትልቅ ስብሰባ ላይ አገኘቻት! የረብሸኞች አውራ የነበረችው ልጅ ለቫኔሳ “እጠላሽ ነበር። . . . አንድ ጊዜ እንኳን ስትናደጂ ለማየት እመኝ ነበር” አለቻት። ይሁን እንጂ ቫኔሳ እንዴት ይህን ያህል ለመታገሥ እንደቻለች ለማወቅ ያላት ጉጉት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ እንድታጠና የቀረበላትን ግብዣ እንድትቀበል አደረጋት። “የተማርኩትን ነገር ወደድኩት” በመቀጠልም “ስለዚህም ነገ ልጠመቅ ነው” አለቻት።

ስለዚህ እኩዮቻችሁ የሚናገሩት “የተቃውሞ ንግግር” ቅስማችሁን እንዲሰብረው አትፍቀዱ። ተገቢ ሆኖ ሲገኝ እንደ ቀልድ ቆጥራችሁ ችላ በሉት። ክፋትን በደግነት መልሱ። የጠቡን እሳት ለመቆስቆስ እምቢተኞች ሁኑ። ከጊዜ በኋላ የሚያስቸግሯችሁ ልጆች እናንተን የፌዝ ዒላማ በማድረግ መደሰታቸውን ሊተዉ ይችላሉ፤ ምክንያቱም “እንጨት ባለቀ ጊዜ እሳት ይጠፋል።”​— ምሳሌ 26:​20

የመወያያ ጥያቄዎች

◻ አምላክ በሌሎች ላይ በጭካኔ የሚቀልዱ ሰዎችን እንዴት ይመለከታል?

◻ ብዙውን ጊዜ ወጣቶች በሌሎች እንዲቀልዱ የሚያደርጋቸው ነገር ምንድን ነው?

◻ የሚደርስባችሁን ፌዝ ለመቀነስ ወይም ለማስቆም የምትችሉት እንዴት ነው?

◻ በትምህርት ቤት ሌሎች መቀለጃ በሚያደርጓችሁ ጊዜም እንኳ ሳይቀር ‘ብርሃናችሁ እንዲበራ ማድረግ’ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

◻ በትምህርት ቤት እንዳይደበድቧችሁ ራሳችሁን ለመጠበቅ ምን እርምጃዎችን መውሰድ ትችላላችሁ?

[በገጽ 155 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አሿፊዎች በጀብደኝነት ድንፋታቸው ሽፋን ሥር ‘ራሳችንን አንወደውም፤ ሰውን ማዋረድ ግን ስለ ራሳችን የተሻለ ስሜት እንዲሰማን ያደርጋል’ እያሉ ይሆናል

[በገጽ 152 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ልጆች እንዳይመቱኝ ማድረግ የምችለው አንዴት ነው?

ብዙ ተማሪዎች ‘ወደ ትምህርት ቤት ስትመጣ ነፍስህን በእጅህ ቋጥረህ መያዝ ይኖርብሃል’ ይላሉ። ይሁን እንጂ የጦር መሣሪያ መያዝ ሞኝነት ከመሆኑም ሌላ ችግር ያስከትላል። (ምሳሌ 11:​27) ታዲያ ራሳችሁን መጠበቅ የምትችሉት እንዴት ነው?

አደገኛ አካባቢዎችን አውቃችሁ ከእነዚህ አካባቢዎች ራቁ። በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች መተላለፊያዎች፣ ከፎቅ መወጣጫ ደረጃዎች ሥር የሚገኙ ሥርቻዎችና ልብስ መለወጫ ክፍሎች አደገኞች ናቸው። መጸዳጃ ቤቶች ለመደባደብና ዕፅ ለመውሰድ የሚያመቹ መሰባሰቢያ ሥፍራዎች መሆናቸው በሰፊው የታወቀ ከመሆኑ የተነሳ ብዙ ወጣቶች በእነዚህ ነገሮች ከመጠቀም ይልቅ ወደነዚህ ሥፍራዎች ባለመሄድ ምቾታቸውን ቢያጡ ይመርጣሉ።

በጓደኛ አመራረጣችሁ ጥንቃቄ አድርጉ። ብዙውን ጊዜ አንድ ወጣት ድብድብ መሐል የሚገባው ከመጥፎ ባልንጀሮች ጋር በመዋሉ ብቻ ነው። (ምሳሌ 22:​24, 25ን ተመልከቱ።) በእርግጥ ለትምህርት ቤት ጓደኞቻችሁ ጀርባችሁን መስጠት ከእናንተ ሊያርቃቸው ወይም ጠላቶቻችሁ እንዲሆኑ ሊያደርጋቸው ይችላል። ለእነርሱ የወዳጅነት መንፈስ ካሳያችሁና ትሑቶች ከሆናችሁ እናንተን ምንም ላይሏችሁ ይችላሉ።

ከጠብ ሽሹ። ‘ይዋጣልን’ የሚል ጥያቄ ሲቀርብላችሁ ጥያቄውን አትቀበሉ። (ገላትያ 5:​26 የአዓት የግርጌ ማስታወሻ) ተደባድባችሁ ብታሸንፉም እንኳ ተጋጣሚያችሁ የሚያሸንፍበትን ምቹ ጊዜ ሊጠብቅ ይችላል። ስለዚህ በመጀመሪያ በጥሞና በማነጋገር ከጠቡ ለመውጣት ሞክሩ። (ምሳሌ 15:​1) ይህ ካልሠራ ከቦታው በመሄድ፣ አስፈላጊ ከሆነም ሮጣችሁ በማምለጥ ከተፈጠረው ፍጥጫ ሽሹ። ‘ያልሞተ ውሻ ከሞተ አንበሳ እንደሚሻል’ አስታውሱ። (መክብብ 9:​4) ምንም ዓይነት ሌላ አማራጭ ካጣችሁ ራሳችሁን ለመከላከል የሚያስችላችሁን አስፈላጊና ምክንያታዊ ዘዴ ተጠቀሙ።​— ሮሜ 12:​18

ለወላጆቻችሁ ተናገሩ። ወጣቶች “ወላጆቻቸው ፈሪ ናቸው ብለው እንዳያስቡ ወይም ወመኔዎቹን ለምን አልመከታችሁም ብለው እንዳይቆጧቸው በማሰብ በትምህርት ቤት የሚያጋጥማቸውን ሽብር ለወላጆቻቸው አይነግሩም።” (ዘ ሎንሊነስ ኦቭ ችልድረን ) ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ ችግሩን ለማቆም የሚያስችለው ብቸኛ መንገድ የወላጅ ጣልቃ ገብነት ነው።

ወደ አምላክ ጸልዩ። አምላክ አካላዊ ጉዳት አይደርስባችሁም ብሎ ዋስትና አይሰጥም። ይሁን እንጂ ያጋጠማችሁን የጠብ ፍጥጫ እንድትቋቋሙ የሚያስችላችሁን ድፍረትና ሁኔታውን ለማብረድ የሚያስፈልጋችሁን ጥበብ ሊሰጣችሁ ይችላል።​— ያዕቆብ 1:​5

[በገጽ 151 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብዙ ወጣቶች እኩዮቻቸው ያበሽቋቸዋል

[በገጽ 154 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሚያሾፍባችሁ ልጅ የሚፈልገው እናንተ ስትናደዱ በማየት ለመደሰት ነው። ከእርሱ ጋር መሰዳደብ ወይም ማልቀስ የባሰ እንዲያበሽቃችሁ ሊያበረታታው ይችላል

[በገጽ 156 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሲቀለድባችሁ እናንተን ለማናደድ የተነገረውን ነገር እንደ ቀልድ አይታችሁ ለማለፍ ሞክሩ