በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሥራ ላገኝ (እንዲሁም ቋሚ ልሆን) የምችለው እንዴት ነው?

ሥራ ላገኝ (እንዲሁም ቋሚ ልሆን) የምችለው እንዴት ነው?

ምዕራፍ 21

ሥራ ላገኝ (እንዲሁም ቋሚ ልሆን) የምችለው እንዴት ነው?

ሲኒየር ስኮላስቲክ በተሰኘ መጽሔት ላይ ታትሞ የወጣ አንድ ጥናት ለመመረቅ የተዘጋጁ የአሜሪካ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች “በጣም አስፈላጊ” አድርገው የሚቆጥሯቸው የሕይወት ግቦች የትኞቹ እንደሆኑ ጠይቋቸው ነበር። ሰማንያ አራት በመቶዎቹ “ቋሚ ሥራ ማግኘት መቻል” በማለት መልሰዋል።

ምናልባት የግል ወይም የቤተሰብ ወጪዎችን ለመደጎም እንድትችሉ ከትምህርት ሰዓት ውጪ የምትሠሩት ሥራ ለማግኘት ትፈልጉ ይሆናል። ወይም ደግሞ በሙሉ ጊዜ የወንጌላዊነት ሥራ ስታገለግሉ ራሳችሁን ለማኖር የሚያስችላችሁ የትርፍ ሰዓት ሥራ ትፈልጉ ይሆናል። (ምዕራፍ 22ን ተመልከቱ።) በዚያም ሆነ በዚህ በዓለም ዙሪያ የገንዘብ ዋጋ በማሽቆልቆሉና ትምህርት የሌላቸው ሠራተኞች የሚፈለጉበት የሥራ መስክ የተወሰነ በመሆኑ ምክንያት ወጣት ከሆናችሁ ሥራ ማግኘት አስቸጋሪ ሊሆንባችሁ ይችላል። ታዲያ ወደ ሥራ መስክ በቀላሉ ልትገቡ የምትችሉት እንዴት ነው?

ትምህርት ቤት የሥራ ሥልጠና የሚሰጥበት ቦታ ነው

ሠራተኛ በመቅጠር የብዙ ዓመታት ተሞክሮ ያላቸው ክሌቭላንድ ጆንስ የሚከተለውን ምክር ይሰጣሉ፦ “ጥሩ የሆነ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ይኑራችሁ። በጥሩ ሁኔታ መጻፍና ማንበብ እንዲሁም መናገር ያላቸውን ጥቅም ጎላ አድርጌ ለመግለጽ ቃላት ያጥሩኛል። በሥራ ዓለም የሚያጋጥሟችሁን ሰዎች በተገቢው መንገድ መያዝ እንድትችሉ አስፈላጊውን ሥርዓት ተማሩ።”

አንድ የአውቶቡስ ሾፌር የሚደርስበትንና የሚነሳበትን ሰዓት የሚገልጸውን የጊዜ ሰሌዳ ማንበብ መቻል አለበት። የፋብሪካ ሠራተኞች የሥራ አፈጻጸም ቅጾችን ወይም ተመሳሳይ ሪፖርቶችን እንዴት መሙላት እንደሚችሉ ማወቅ ያስፈልጋቸዋል። የሽያጭ ሠራተኞች የሒሳብ ስሌቶችን እንዲሠሩ ይጠበቅባቸዋል። በማንኛውም ዓይነት ሥራ ሐሳብን አሳክቶ የመግለጽ ችሎታ ተፈላጊ ነው። እነዚህ ሁሉ በትምህርት ቤት እያላችሁ ጠንቅቃችሁ ልታውቋቸው የምትችሏቸው ነገሮች ናቸው።

አለመታከት ተፈላጊውን ውጤት ያስገኛል

ጆንስ “ትምህርታችሁን ጨርሳችሁ ሥራ በመፈለግ ላይ ከሆናችሁ ፈጽሞ ተስፋ አትቁረጡ” ይላሉ። “ለሁለት ወይም ለሦስት ቃለ መጠይቆች ከቀረባችሁ በኋላ እስክትጠሩ ድረስ እቤታችሁ ቁጭ ብላችሁ አትጠባበቁ። በዚህ ብቻ ሥራ ጀምሩ ተብላችሁ ላትጠሩ ትችላላችሁ።” ሳል የተባለ ወጣት ሥራ ከመቀጠሩ በፊት ሥራ በመፈለግ ሰባት ወራት አሳልፏል። “‘ሥራዬ ሥራ መፈለግ ነው’ እያልኩ ለራሴ እናገር ነበር” ብሏል። “ለሰባት ወራት በሳምንቱ ቀናት በሙሉ በየቀኑ ስምንት ሰዓት ሥራ በመፈለግ አሳልፍ ነበር። በየቀኑ ጠዋት ቀደም ብዬ እጀምርና ከሰዓት በኋላ አሥር ሰዓት እስከሚሆን ድረስ ‘እሠራ’ ነበር። ለብዙ ቀናት ማታ ማታ እግሬ ይቆስል ነበር። በሚቀጥለው ጧት እንደገና ሥራ ፍለጋዬን ለመቀጠል ‘ወኔዬን መቀስቀስ’ ያስፈልገኝ ነበር።”

ሳል ሥራ ፍለጋውን እንዳይተው ያደረገው ምን ነበር? “በአንድ የአስተዳደር ቢሮ በገባሁ ቁጥር ኢየሱስ “ተጋደሉ” ሲል የተናገረውን አስታውስ ነበር። አንድ ቀን ሥራ አገኝና ይህ ክፉ ጊዜ ያልፋል እያልኩ አስብ ነበር” ብሏል።​— ሉቃስ 13:24

ሥራ የሚገኝባቸው ቦታዎች

የምትኖሩት በገጠር አካባቢ ከሆነ ሥራ ፍለጋ የምትጀምሩት በአካባቢያችሁ ባለ የእርሻ ወይም የአትክልት ሥፍራ ሊሆን ይችላል። ወይም አንድ ዓይነት የግቢ ውስጥ ሥራ ልትፈልጉ ትችላላችሁ። የምትኖሩት በትላልቅ ከተሞች ከሆነ በጋዜጣ ላይ የሚወጡትን የሥራ ማስታወቂያዎች ተመልከቱ። እነዚህ ማስታወቂያዎች ለአንድ ዓይነት ሥራ ምን ዓይነት ብቃት እንደሚያስፈልግ ሊጠቁሟችሁ ስለሚችሉ ለቀጣሪው ባለሥልጣን የሚያስፈልገውን ብቃት የምታሟሉበትን ምክንያት ማስረዳት ትችላላችሁ። ወላጆች፣ መምህራን፣ ሥራ አስቀጣሪዎች፣ የፐርሶኔል ቢሮዎች፣ ጓደኞችና ጎረቤቶች ክፍት የሥራ ቦታ ስለሚገኝባቸው ቦታዎች ወሬ ልታገኙ የምትችሉባቸው ሌሎች ምንጮች ናቸው።

ሥራችሁ ላይ መቆየት

የሚያሳዝነው ነገር ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖዎች ሥራ አጥነት በሚፈጥሩበት ጊዜ ከሥራ ከሚባረሩት መካከል የመጀመሪያ የሚሆኑት ወጣት ሠራተኞች መሆናቸው ነው። ይሁን እንጂ ይህ በእናንተ ላይ እንዲደርስባችሁ አያስፈልግም። “ሥራቸው ላይ የሚቆዩ ሰዎች ለመሥራት ፈቃደኞች የሆኑና አሠሪው የሚጠይቃቸውን ሁሉ ለማድረግ የፈቃደኝነት ዝንባሌ የሚያሳዩ ናቸው” ይላሉ ሚስተር ጆንስ።

የእናንተ ዝንባሌ ደግሞ የአስተሳሰባችሁ ሁኔታ ማለትም ለሥራችሁና አብረዋችሁ ለሚሠሩት ሰዎች ያላችሁ ስሜት ማለት ነው። ይህም ዝንባሌያችሁ በምትሠሩት ሥራ ጥራት ላይ ይንጸባረቃል። አለቃችሁ የሚገመግማችሁ የሥራ ውጤታችሁን መሠረት በማድረግ ብቻ ሳይሆን በዝንባሌያችሁም ጭምር ነው።

ሚስተር ጆንስ “ለአሠሪያችሁ መመሪያ መከተል እንደምትችሉ ብቻ ሳይሆን የዘወትር ቁጥጥር ሊደረግባችሁ ሳያስፈልግ ከሚጠበቅባችሁ በላይ ለመሥራት መቻላችሁን ጭምር አሳዩ” በማለት ቀጥለው ይመክራሉ። “ምክንያቱም በጣም በተጣበበው የሥራ ዓለም ሳይባረሩ የሚቆዩት የግዴታ በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ ለረዥም ጊዜ የቆዩት ሳይሆኑ ምርታማ የሆኑት ናቸው።”

ይህ እውነት መሆኑን ሳል ተገንዝቧል። እንዲህ ይላል፦ “ሁልጊዜ የአሠሪዬን ፍላጎት ለመፈጸም እጥር ነበር። አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ የሥራ ፕሮግራሜን ለመለወጥ፣ የሚሰጡኝን መመሪያዎች ለመከተልና ለበላይ ተቆጣጣሪዎቼ አክብሮት ለማሳየት ፈቃደኛ ነበርኩ።” ይህም “በቅን ልብ ጌታን እየፈራችሁ እንጂ፣ ለሰው ደስ እንደምታሰኙ ለታይታ የምትገዙ ሳትሆኑ፣ በሥጋ ጌቶቻችሁ ለሆኑ በሁሉ ታዘዙ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ያስታውሰናል።​— ቆላስይስ 3:22

ፍርሃትን ማስወገድ

ገና አዲስ ሥራ መጀመራችሁ ከሆነ ለመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት ፍርሃት ቢሰማችሁ በማንም ላይ የሚደርስ ስሜት ነው። ‘ይወዱኝ ይሆን? ሥራውን ልሠራው እችል ይሆን? ሥራዬን ይወዱልኝ ይሆን? መቸም ምንም የማላውቅ እንደማልመስል ተስፋ አደርጋለሁ’ እያላችሁ ታስቡ ይሆናል። እዚህ ላይ ጠንቃቆች ካልሆናችሁ ፍርሃታችሁ የነበራችሁን ገንቢ አመለካከት ሊያጠፋባችሁ ይችላል።

ስለምትሠሩበት ኩባንያ ይበልጥ ለማወቅ ጥረት በማድረግ ከሥራው ጋር ለመተዋወቅና ለመላመድ የምታደርጉትን ጥረት ለማፋጠንና መንፈሳችሁንም ለማረጋጋት ትችላላችሁ። ተመልከቱ፣ አዳምጡ፣ እንዲሁም አንብቡ። ተገቢ በሚሆንበት ጊዜም የቅርብ ተቆጣጣሪያችሁን ስለምትሠሩት ሥራና ስለ ሥራ አፈጻጸማችሁ ምክንያታዊ ጥያቄ ጠይቁት። ይህን ማድረጋችሁ ሞኞች አያስመስላችሁም። ‘እኔ የምሠራው ሥራ ከምሠራበት ክፍልና ከኩባንያው ጠቅላላ ዓላማ ጋር ያለው ዝምድና ምንድን ነው?’ እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ። ለእነዚህ ጥያቄዎች የምትሰጡት መልስ ጥሩ የሥራ ልምድ ለማዳበርና ከሥራችሁ እርካታ ለማግኘት ይረዳችኋል።

ከሥራ ባልደረቦቻችሁ ጋር ተስማሙ

ሁሉም የሥራ ዘርፎች ከሌሎች ሰዎች ጋር ማገናኘታቸው አይቀርም። በመሆኑም እንዴት ከሌሎች ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖራችሁ ማድረግ እንደምትችሉ ማወቃችሁ በሥራችሁ ላይ እንድትቆዩ የሚያስፈልጋችሁ ነገር ነው። “ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ።” (ሮሜ 12:​18) እንዲህ ማድረጋችሁ በሥራ ቦታችሁ ከማያስፈልግ ንትርክና መፋጠጥ እንድትርቁ ይረዳችኋል።

አንዳንድ ጊዜ አብረዋችሁ የሚሠሩት ሰዎች ከእናንተ በጣም የተለየ አስተዳደግና ባሕርይ ያላቸው ይሆናሉ። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ከእናንተ የተለየ ስለሆነ ብቻ ከእናንተ ያነሰ እንደሆነ አድርጋችሁ አታስቡ። የተለየ ለመሆን ያለውን መብት አክብሩለት። አክብሮት በጎደለው መንገድ እንዲይዙት የሚፈልግ ማንም የለም። አንድ ሰው አክብሮት በጎደለው መንገድ ከተያዘ ምንም የማይረባ ከንቱ ሰው እንደሆነ ይሰማዋል። ማንም ሰው ተፈላጊና ማንነቱ የታወቀ እንደሆነ ቢሰማው ይወዳል። ስለዚህ የሥራ ባልደረቦቻችሁንና አሠሪያችሁን በማክበር የእነርሱንም አክብሮት አትርፉ።

ሐሜትን ማስወገድ

“ሐሜት መጥፎ እንቅፋት ነው” ይላል ሳል። “ምክንያቱም ስለ አለቃችሁም ሆነ ስለ ሌሎች የተሳሳተ ግምት እንዲኖራችሁ ያደርጋል።” የስሚ ስሚ የሚመጣ ወሬ ትክክለኛ ላይሆን ይችላል። እንዲያውም ስም ለማጥፋት ተብሎ የሚነገር ሊሆን ይችላል። ሰዎች ስለ ሌሎች የሚያናፍሱት ሐሜት አብዛኛውን ጊዜ ከልክ በላይ የተጋነነና የሌሎችንም ሆነ የራሳችሁን መልካም ስም የሚያጎድፍ ነው። ስለዚህ ሐሜት ለመስማትም ሆነ ለመናገር የሚመጣባችሁን ግፊት አፍናችሁ አስቀሩት።

በተጨማሪም አጉረምራሚ የሆነን ሰው የሚወድ ማንም እንደሌለ አስታውሱ። በሥራ ላይ የሚያስቸግራችሁ ነገር ካለ ችግራችሁ በሐሜተኞች በኩል እንዲታወቅላችሁ አታድርጉ። ወደ አለቃችሁ ሂዱና አነጋግሩት። ይሁን እንጂ በቁጣ ገንፍላችሁ ቢሮውን በርግዳችሁ በመግባት በኋላ የምትጸጸቱበትን ቃላት በችኮላ አትናገሩ። በተጨማሪም ግለሰቡን ራሱን ከመዝለፍ ተቆጠቡ። የጉዳዩን ጭብጥ ብቻ ተናገሩ። ችግሩን በምታስረዱበት ጊዜ የተቻላችሁን ያህል ግልጽና ሐቀኞች ሁኑ። ምናልባት ንግግራችሁን ስትከፍቱ ‘እርዳታዎን እፈልጋለሁ። . . .’ ወይም ‘ተሳስቼ ሊሆን ይችላል፣ እኔ እንደሚሰማኝ ግን . . .’ በማለት ልትጀምሩ ትችላላችሁ።

ሰዓት አክባሪነት አስፈላጊ ነው

ሰዎች ከሥራ እንዲባረሩ የሚያደርጉ ሁለቱ ታላላቅ ምክንያቶች ዘግይቶ ሥራ መግባትና ከሥራ መቅረት ናቸው። የአንድ ትልቅ የኢንዱስትሪ ከተማ የቅጥርና የማሠልጠኛ ዲሬክተር ስለ ወጣት ሠራተኞች ሲናገሩ “ማለዳ መነሳትንና ትእዛዝ መቀበልን መልመድ ያስፈልጋቸዋል። እነዚህን ነገሮች መልመድ ካልቻሉ ውጤቱ የሥራ አጥነቱ ችግር ባለበት እንዲቀጥል ማድረግ ብቻ ነው” ብለዋል።

ሳል ሰዓት የማክበርን አስፈላጊነት የተማረው ከደረሰበት ችግር ነው። “ሰዓት አሳልፌ በመግባቴ ምክንያት ሦስት ወር ብቻ እንደሠራሁ ከመጀመሪያው ሥራዬ ተባረርኩ” በማለት በኀዘን ይገልጻል። “ይህ ደግሞ ሌላ ሥራ ለማግኘት የነበረኝን አጋጣሚ በጣም አዳጋች አድርጎብኝ ነበር።”

ሐቀኛ የመሆን ጥቅም

የሠራተኞች ቅጥር ባለሥልጣን የሆኑት ጆንስ ሲናገሩ “ሐቀኝነት አንድ ሰው ሥራውን እንደያዘ እንዲቆይ ይረዳዋል” ብለዋል። ሐቀኛ መሆን ዕቃ ከመስረቅ መቆጠብን ብቻ ሳይሆን ከሚፈቀደው የእረፍት ሰዓት በላይ በመቆየት ጊዜ ከመስረቅ መቆጠብንም ይጨምራል። ሐቀኛ የሆነ ሠራተኛ ከፍ ያለ ግምት ይሰጠዋል፣ እምነትም ይጣልበታል። ለምሳሌ ያህል ልብስ ብቻ በሚሸጥበት ሱቅ የሚሠራ አንድ ወጣት የይሖዋ ምሥክር በሐቀኝነቱ ጥሩ ዝና አትርፎ ነበር።

“አንድ ቀን” ይላል ሲናገር “ሥራ አስኪያጁ በመጋዘኑ በሚገኝ ልብስ ውስጥ አንድ ዕቃ ተሸጉጦ አገኙ። ከሠራተኞቹ አንዱ ከሱቁ ሰርቆ ለማውጣት ያዘጋጀው ነበር። ከሥራ በምንወጣበት ሰዓት የሥራ አስኪያጁ ቢሮ ወዳለበት ፎቅ ስወጣ ሁሉም ሠራተኞች እዚያ ተኮልኩለው አገኘኋቸው። ሠራተኞቹ በሙሉ እዚያ የተወሰዱት ሊፈተሹ ነበር። ሳልፈተሽ የቀረሁት ሠራተኛ እኔ ብቻ ነበርኩ።”

ብዙ ክርስቲያን ወጣቶች ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ተሞክሮ አጋጥሟቸዋል። በሠራተኝነታቸውም ጥሩ ግምት አትርፈዋል። ስለዚህ ሥራ ለማግኘት ከልብ ጣሩ። አትሰልቹ። ተስፋ አትቁረጡ። ይህን ያህል ለፍታችሁ ያገኛችሁትን ሥራ ደግሞ እንደያዛችሁ ለመቆየት ጣሩ!

የመወያያ ጥያቄዎች

◻ በትምህርት ቤት የምትማሩት ነገር ሥራ ለማግኘት ያላችሁን ችሎታ ሊነካ የሚችለው እንዴት ነው?

◻ ሥራ በምትፈልጉበት ጊዜ አለመሰልቸት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

◻ ሥራ በምትፈልጉበት ጊዜ የምታጠያይቁባቸው ቦታዎች የትኞቹ ናቸው? የምታማክሯቸው ሰዎችስ እነማን ናቸው?

◻ ለሥራ ቃለ መጠይቅ በምትቀርቡበት ጊዜ የሚረዷችሁ አንዳንድ ጠቃሚ ምክሮች ምንድን ናቸው?

◻ ከሥራ ከመባረር እንድትድኑ ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ?

[በገጽ 166 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“በጥሩ ሁኔታ መጻፍና ማንበብ እንዲሁም መናገር ያላቸውን ጥቅም ጎላ አድርጌ ለመግለጽ ቃላት ያጥሩኛል”

[በገጽ 170 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“‘ሥራዬ ሥራ መፈለግ ነው’ እያልኩ ለራሴ እናገር ነበር”

[በገጽ 168, 169 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ለሥራ ቃለ መጠይቅ ስትቀርቡ

“ለሥራ ቃለ መጠይቅ ከመቅረባችሁ በፊት ማስታወስ ያለባችሁ ነገር በጠያቂዎቻችሁ አእምሮ የምታሳድሩት የመጀመሪያ ግምት ዘላቂ የሆነ ግምት መሆኑን ነው” ይላሉ የሥራ አማካሪ የሆኑት ክሌቭላንድ ጆንስ። ለሥራ ቃለ መጠይቅ የሚቀርቡ ወጣቶች ጂንስ ልብሶችንና እስኒከር ጫማዎችን አድርገው እንዳይሄዱ ያስጠነቅቁና ንጹሕና ደስ የሚል አለባበስ እንዲኖራቸው አጥብቀው ያሳስባሉ። ብዙውን ጊዜ አሠሪዎች አንድ ሰው ሥራውን የሚያከናውንበት ሁኔታ ከአለባበሱ የተለየ እንደማይሆን ያስባሉ።

ለቢሮ ሥራ ለመቀጠር ስታመለክቱ በሥራው ላይ ያለ ሰው እንደሚለብሰው ያለ አለባበስ ልበሱ። ለፋብሪካ ሥራ ስታመለክቱ ንጹሕና የተተኮሰ ሱሪና ሸሚዝ ከንጹሕ ጫማ ጋር ልበሱ። ሴት ከሆንሽ ልከኛ ልብስ መልበስ ያለብሽ ከመሆኑም በላይ መኳኳያዎችን አታብዢ። የምታመለክቺው የቢሮ ሥራ ለማግኘት ከሆነ የሚያስከብር ልብስና ከልብሱ ጋር የሚስማማ ስቶኪንግና ጫማ አድርጊ።

ለሥራ ቃለ መጠይቅ በምትቀርቡበት ጊዜ ሁልጊዜ ብቻችሁን እንድትሄዱ ጆንስ ያስጠነቅቃሉ። ወደ ቃለ መጠይቁ እናታችሁን ወይም ጓደኛችሁን ይዛችሁ ብትሄዱ አሠሪው በአእምሮ ገና ያልበሰላችሁ ናችሁ ብሎ ሊደመድም ይችላል።

‘ምናልባት ቀጣሪው ባለ ሥልጣን ከዚህ በፊት የሥራ ልምድ እንዳለኝ ቢጠይቀኝ ምን መልስ መስጠት ይኖርብኛል?’ ብላችሁ ታስቡ ይሆናል። ዋሽታችሁ ለማሞኘት አትሞክሩ። ችሎታችሁን ከልክ በላይ አጋንናችሁ ከተናገራችሁ ቀጣሪዎች ብዙውን ጊዜ ያጋነናችሁ መሆናችሁን ማወቃቸው አይቀርም። ስለዚህ ሐቀኞች ሁኑ።

“ዘላቂ የሆነ” ሥራ ስትፈልጉ ይህ የመጀመሪያ ጊዜያችሁ ይሆናል እንጂ ቀደም ያለ የሥራ ልምድ ሳይኖራችሁ አይቀርም። ትምህርት ቤት ሲዘጋ የክረምት ሥራ ይዛችሁ ታውቃላችሁን? ወይም የሕፃናት ሞግዚት ሆናችሁ ነበርን? በቤታችሁ ውስጥ ዘወትር እንድታከናውኑ የተመደበላችሁ ቋሚ ሥራ ኖሯችሁ ያውቃል? በአምልኮ ቦታችሁ የምታከናውኑት ኃላፊነት ተሰጥቷችሁ ያውቃል? በሕዝብ ፊት የመናገር ሥልጠና ተሰጥቷችሁ ያውቃል? እነዚህ ነገሮች ኃላፊነት መቀበል የምትችሉ መሆናችሁን ስለሚያመለክቱ ለቃለ መጠይቅ በምትቀርቡበት ጊዜ ልትጠቅሷቸው ወይም በማመልከቻችሁ ላይ ልትገልጿቸው ትችላላችሁ።

ቀጣሪዎች ለማወቅ የሚፈልጉት ሌላው ዋና ነገር በኩባንያቸው ውስጥ ለመቀጠርና የሚሰጣችሁን ሥራ ለማከናወን ምን ያህል ፍላጎት እንዳላችሁ ነው። በእርግጥ የሚሰጧችሁን ሥራ ለመሥራት እንደምትፈልጉና ልትሠሩትም እንደምትችሉ ማሳመን አለባችሁ። “ሥራውን ይህን ያህልም አልፈልገውም” የሚል አመለካከት ካላችሁ ቃለ መጠይቅ የሚያደርግላችሁ ሰውም እናንተን ለመቅጠር ፍላጎት አይኖረውም።

የሙሉ ወይም የትርፍ ሰዓት ሥራ ለማግኘት ማመልከትና ለመቀጠር መቻል አስቸጋሪ ቢሆንም ሊሳካላችሁ ይችላል። የምታገኙት ሥራ ደግሞ ራሳችሁን ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ለመርዳት የሚያስችላችሁ መሆኑን ስትገነዘቡ ተጨማሪ እርካታ ታገኛላችሁ።

[በገጽ 171 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ለሥራ ቃለ መጠይቅ ስትቀርቡ ማድረግ ያለባችሁ ነገሮች

ጨዋዎችና በሥራ ላይ እንዳሉ ሰዎች ሁኑ። ለቀጣሪው ባለሥልጣን ተገቢ የሆነ የአክብሮት ሰላምታ ስጡ። “አቶ . . .” እያላችሁ ጥሩት እንጂ ባልንጀራችሁን በምትጠሩበት ዓይነት አጠራር አትጠቀሙ።

በወንበር ላይ ስትቀመጡ ቀጥ ብላችሁና ሁለቱንም እግሮቻችሁን ወለሉ ላይ ሙሉ ለሙሉ አሳርፋችሁ ተቀመጡ። ንቁዎች ሁኑ። ቅድመ ዝግጅት አድርጋችሁ ብትቀርቡ የተረጋጋ መንፈስ ሊኖራችሁና ዘና ልትሉ ትችላላችሁ።

የሚቀርብላችሁን ጥያቄ አስባችሁ መልሱ። ትሑቶች፣ ትክክለኞች፣ ሐቀኞችና ግልጾች ሁኑ። የተሟላ መልስ ስጡ። ጉረኞች አትሁኑ።

ትሠሯቸው የነበሩትን ሥራዎች፣ የሠራችሁበትን ጊዜ ርዝመት፣ ደመወዝ፣ ትሠሯቸው የነበሩትን የሥራ ዓይነቶችና የለቀቃችሁበትን ምክንያት የሚገልጽ ማስታወሻ ይዛችሁ ሂዱ።

ያገኛችሁት ሥልጠናና የሥራ ልምድ አሁን ለምትጠይቁት ሥራ ምን ያህል ብቁ እንደሚያደርጋችሁ ለማሳየት ዝግጁዎች ሁኑ።

ስለ እናንተ ሊናገሩ የሚችሉ ሰዎችን ስም እንድትሰጡ ከተጠየቃችሁ እናንተንና ሥራችሁን የሚያውቁ ሦስት የታመኑ ሰዎችን ስም (እንዲሁም ሙሉ አድራሻ ) ስጡ።

በራሳችሁ የምትተማመኑና ሞቅ ያለ መንፈስ ያላችሁ ሁኑ። ቢሆንም ያልሆናችሁትን ሆናችሁ ለመቅረብ አትሞክሩ። አነጋገራችሁ ግልጽና የተጣራ ይሁን። ብዙ አትናገሩ።

በጥንቃቄ አዳምጡ፤ ትሑቶችና ዘዴኞች ሁኑ። ከሁሉም በላይ የወደፊት አሠሪያችሁ ከሚሆነው ሰው ጋር ምንም ዓይነት ክርክር አትግጠሙ።

ቀጣሪው ባለሥልጣን ማወቅ የሚፈልገው ዋና ነገር ምን ያህል ለሥራው እንደምትስማሙ ነው። ስለዚህ ምንም ዓይነት የግል፣ የቤተሰብ ወይም የገንዘብ ችግር እንዳለባችሁ አትጥቀሱ።

ሥራውን የማታገኙት ሆኖ ከታየ ወደፊት በድርጅቱ ውስጥ ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ሌሎች የሥራ አጋጣሚዎች ምክር እንዲሰጣችሁ ቀጣሪውን ባለሥልጣን ጠይቁት።

ቃለ መጠይቅ ከተደረገላችሁ በኋላ ወዲያውኑ ለቀጣሪው ባለሥልጣን አጭር የምስጋና ደብዳቤ ላኩለት። *

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.65 ምንጭ፦ ሃው ቱ “ሴል ዩርሰልፍ” ቱ አን ኢምፕሎየር የተሰኘው የኒው ዮርክ የሥራ ቅጥር አገልግሎት ቢሮ ብሮሹር

[በገጽ 167 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በትምህርት ቤት የምትማሯቸው ትምህርቶች አንድ ቀን ሥራ ስትይዙ ጠቃሚ ሆነው ታገኟቸው ይሆናል