በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የፈተና ውጤቴን ማሻሻል የምችለው እንዴት ነው?

የፈተና ውጤቴን ማሻሻል የምችለው እንዴት ነው?

ምዕራፍ 18

የፈተና ውጤቴን ማሻሻል የምችለው እንዴት ነው?

ቁጥራቸው በርካታ የሆነ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ‘በጣም የሚያስጨንቃችሁ ነገር ምንድን ነው?’ ተብለው ሲጠየቁ 51 በመቶዎቹ “የፈተና ውጤት”! በማለት መልሰዋል።

በወጣቶች ዘንድ ዋናው የጭንቀት መንስኤ በትምህርት ቤት የሚያገኙት ውጤት መሆኑ ምንም አያስደንቅም። ከትምህርት ቤት መመረቅና አለመመረቅ፣ ጥሩ ደመወዝ የሚያስገኝ ሥራ ማግኘትና አለማግኘት፣ በወላጆች መመስገንና አለመመስገን የሚወሰነው በፈተና ውጤት ነው። የፈተና ውጤቶችና ፈተናዎች ተገቢ ቦታ እንዳላቸው አይካድም። ኢየሱስ ክርስቶስም እንኳ ደቀ መዛሙርቱ አንዳንድ ነገሮችን መረዳታቸውን ለመፈተን ብሎ ጥያቄ ያቀርብላቸው ነበር። (ሉቃስ 9:​18) ሜዠርመንት ኤንድ ኢቫልዌሽን ኢን ዘ ስኩልስ የተሰኘ መጽሐፍ እንደተናገረው “የፈተና ውጤቶች የነፍስ ወከፍ ተማሪዎችን ጥንካሬና ድክመት ለማሳወቅ ከመቻላቸውም በላይ ወደፊት ለሚደረግ ጥናት ማነቃቂያ ይሆናሉ።” በተጨማሪም የፈተና ውጤቶቻችሁ ወላጆቻችሁ ስለ ትምህርት ቤት እንቅስቃሴያችሁ እንዲያውቁ ያስችላቸዋል። ጥሩ እድገት በማድረግ ላይ መሆናችሁንና አለመሆናችሁን ይጠቁማቸዋል።

ሚዛን መጠበቅ

ስለ ፈተና ውጤቶች ከልክ በላይ መጨነቅ ግን ጥረታችሁን ሁሉ የሚያመክን ጭንቀት ሊፈጥርባችሁና በከረረ ውድድር ውስጥ እንድትገቡ ሊያደርጋችሁ ይችላል። ስለ ጉርምስና የተጻፈ አንድ የመማሪያ መጽሐፍ በተለይ ኮሌጅ የመግባት እቅድ ያላቸው ተማሪዎች “እውቀት ከማግኘት ይልቅ የፈተና ውጤትንና በክፍል ውስጥ ባለ ማዕረግ መሆንን አጋንኖ በሚመለከት መውጫ የሌለው የውድድር ማጥ ውስጥ የሚገቡ” መሆናቸውን ገልጿል። በዚህም ምክንያት ዶክተር ዊልያም ግላሰር የተናገሩትን ብንጠቅስ ተማሪዎች “ገና ትምህርት እንደ ጀመሩ በፈተና ላይ ምን እንደሚመጣ መጠየቅን ስለሚለምዱ . . . በፈተና ላይ ይመጣል የተባሉትን ነገር ብቻ ያጠናሉ።”

ንጉሡ ሰሎሞን “ሰዎች የተመኙትን ለማግኘት ተግተው በመሥራት ምን ያህል እንደሚደክሙ ተመለከትሁ፤ ይህንንም የሚያደርጉት በባልንጀሮቻቸው ላይ በመቅናት መሆኑን ተረዳሁ፤ ይህም ሁሉ ከንቱ ስለሆነ ነፋስን እንደመጨበጥ ነው” በማለት አስጠንቅቋል። (መክብብ 4:​41980 ትርጉም) ለቁሳዊ ሀብትም ይሁን ወይም የትምህርት ቤት ሽልማት ለማግኘት ተብሎ የሚደረግ የጋለ ፉክክር ከንቱ ነው። ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወጣቶች በትምህርታቸው መትጋት እንደሚያስፈልጋቸው ይገነዘባሉ። ይሁን እንጂ ትምህርትን በሕይወታቸው ውስጥ ከሁሉ የሚበልጥ ነገር ከማድረግ ይልቅ ቁሳዊ ፍላጎቶቻቸውን አምላክ እንደሚያሟላላቸው በመተማመን መንፈሳዊ ነገሮችን ይከታተላሉ።​— ማቴዎስ 6:​33፤ የሥራ መስክ ስለ መምረጥ የሚገልጸውን ምዕራፍ 22ን ተመልከቱ።

ከዚህም ሌላ ትምህርት ማለት በፈተና ከፍተኛ ውጤት ለማግኘት ከመንጠራራት የሚበልጥ ነገር ነው። ትምህርት ማለት ሰሎሞን “የማሰብ ችሎታ” [አዓት] ብሎ የጠራውን ጥሬ እውቀት ወደ አእምሮ አስገብቶ ጥሩና ተግባራዊ ድምዳሜ ላይ የመድረስ ብልሃት ማዳበር ነው። (ምሳሌ 1:​4) በግምት፣ በሽምደዳ ወይም በስርቆት የማለፊያ ውጤት የሚያገኝ ወጣት የማሰብ ችሎታውን ፈጽሞ ሊያዳብር አይችልም። የኋላ ኋላ የቼክ ደብተራችሁን ገቢና ወጪ ማስላት ካልቻላችሁ በሒሳብ ከፍተኛ ውጤት ማግኘቱ ምን ጥቅም አለው?

እንግዲያውስ የፈተና ውጤታችሁን መመልከት ያለባችሁ ራሱን እንደቻለ ግብ ሳይሆን በትምህርት ቤት የምታደርጉት እንቅስቃሴ የሚለካበት መመዘኛ እንደሆነ አድርጋችሁ መሆን ይኖርበታል። ይሁንና ትክክለኛ ችሎታችሁን የሚያሳይ ውጤት ለማግኘት የምትችሉት እንዴት ነው?

የመማርን ኃላፊነት ተቀበሉ!

መምህርት ሊንዳ ኔልሰን እንደተናገሩት ሰነፍ ተማሪዎች “ለደካማ [የትምህርት] ውጤታቸው የሚያመካኙት ከቁጥጥራቸው በላይ በሆኑ ነገሮች ላይ ነው፦ ፈተናው ከሚገባ በላይ ከባድ ነበር፣ አስተማሪው አይወደኝም፣ አይቀናኝም፣ ዕድል የለኝም፣ አየሩ መጥፎ ነበር ብለው ያሳብባሉ።” ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ “የታካች ሰው ነፍስ ትመኛለች፤ አንዳችም አታገኝም” ይላል። (ምሳሌ 13:​4) አዎን፣ ብዙውን ጊዜ ዝቅተኛ ውጤት የሚመጣበት ምክንያት ስንፍና ነው።

ጥሩ ተማሪዎች ግን የመማርን ኃላፊነት ይቀበላሉ። ቲን መጽሔት አንድ ጊዜ ከፍተኛ ውጤት ለሚያገኙ ጥቂት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ቃለ መጠይቅ አድርጎላቸው ነበር። ከፍተኛ ውጤት የሚያገኙበት ምሥጢር ምንድን ነው? አንዱ ተማሪ ሲናገር “የግል አነሳሽነት በትምህርትህ እንድትገፋ ይረዳሃል” ብሏል። ሌላው ደግሞ “ፕሮግራም አውጥቶ ጊዜን በተደራጀ መንገድ መጠቀም ይረዳል” ብሏል። “ለራስህ ግብ ማውጣት አለብህ” ብሏል ሌላው። አዎን፣ የውጤታችሁ ጥሩነት በአብዛኛው የሚመካው ከቁጥጥራችሁ በላይ በሆኑ ነገሮች ላይ ሳይሆን በእናንተው ላይ ነው። ምን ያህል ተግታችሁ ለማጥናትና በትምህርታችሁ ለመጎበዝ ባላችሁ ፈቃደኝነት ላይ የተመካ ነው።

ግን እኮ አጠናለሁ’

ይህ አንዳንድ ወጣቶች የሚሉት ነው። ላባቸው እስኪንጠፈጠፍ ድረስ እንደሚሠሩ ግን ምንም ውጤት እንዳላገኙ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ ከጥቂት ዓመታት በፊት 770 ለሚያህሉ ተማሪዎች ቃለ መጠይቅ ያደረጉ የስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ (ዩ ኤስ ኤ) ተመራማሪዎች ተማሪዎቹ ለትምህርት ቤት ሥራቸው ምን ያህል ጥረት እንደሚያደርጉ ጠይቀው ነበር። የሚገርመው ነገር ዝቅተኛ ውጤት ያላቸው ተማሪዎችም እንደማንኛውም ተማሪ ተግተው የሠሩ መስሏቸዋል! ይሁን እንጂ የአጠናን ልማዳቸው ሲመረመር ከፍተኛ ውጤት የሚያመጡት የትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው ከሚሠሩት እጅግ በጣም ያነሰ መሆኑ ተደርሶበታል።

ከዚህ የምታገኙት ትምህርት ምንድን ነው? ምናልባት እናንተም እናጠናለን ብላችሁ የምታስቡትን ያህል ተግታችሁ እያጠናችሁ ላይሆን ስለሚችል አንዳንድ ለውጦችን ማድረግ ያስፈልጋችኋል። ጆርናል ኦቭ ኤዱኬሽናል ሳይኮሎጂ በተሰኘ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ “የቤት ሥራ ለመሥራት የሚውለውን ጊዜ መጨመሩ ብቻ እንኳን አንድ ተማሪ በትምህርት ቤት በሚያገኘው ውጤት ላይ ገንቢ ውጤት እንደሚያስገኝ” ገልጿል። እንዲያውም “ዝቅተኛ ችሎታ ያለው አንድ ተማሪ በሳምንት ውስጥ ከ1 እስከ 3 ሰዓት ለሚያክል ጊዜ የቤት ሥራ ቢሠራ አማካይ ችሎታ ካለው የቤት ሥራ የማይሠራ ተማሪ ጋር እኩል የሆነ ውጤት ሊያገኝ ይችላል።”

ሐዋርያው ጳውሎስ ወደሚፈልገው ግብ ለመድረስ በምሳሌያዊ አነጋገር ‘ራሱን መጎሰም’ አስፈልጎታል። (1 ቆሮንቶስ 9:​27) እናንተም በተመሳሳይ፣ በተለይ ቴሌቪዥን ወይም ሌሎች ሐሳባችሁን የሚበታትኑ ነገሮች ትኩረታችሁን ከትምህርታችሁ ላይ በቀላሉ ወደ ሌላ የሚቀለብሱባችሁ ከሆነ በራሳችሁ ላይ ጠንከር ያለ መመሪያ ልታወጡ ትችሉ ይሆናል። በቴሌቪዥኑ ላይ “የቤት ሥራ ተሠርቶ እስኪያልቅ ድረስ ቴሌቪዥን መክፈት የለም!” የሚል ምልክት ለማስቀመጥ ትችሉ ይሆናል።

የምታጠኑበት አካባቢ

አብዛኞቻችን ለጥናት የተመደበ ጸጥ ያለ ሥፍራ ቢኖረን እንጠቀማለን። መኝታ ቤታችሁ ውስጥ ሌላ ሰው አብሯችሁ የሚያድር ከሆነ ወይም በቤታችሁ ያለው ቦታ የተወሰነ ከሆነ መላ ፍጠሩ! ምናልባት ወጥ ቤቱ ወይም የሌላ ሰው የመኝታ ክፍል በየዕለቱ ለአንድ ሰዓት ወይም ከዚያ በላይ ለሆነ ጊዜ የጥናት ክፍል ሊሆንላችሁ ይችላል። ወይም ደግሞ ሌላ አማራጭ ካጣችሁ የሕዝብ መጻሕፍት ቤቱን ወይም የጓደኛችሁን ቤት ለጥናት ለመጠቀም ሞክሩ።

የሚቻል ከሆነ የምትሠሩባቸውን መጻሕፍትና ደብተሮች ሊያዘረጋ የሚችል በቂ ስፋት ያለው ዴስክ ወይም ጠረጴዛ ተጠቀሙ። አሁንም አሁንም መነሳት እንዳያስፈልጋችሁ እርሳስና ወረቀት የመሳሰሉትን መሣሪያዎች አዘጋጅታችሁ አቅርቡ። ባጠቃላይ ሲታይ በምታጠኑበት ወይም የቤት ሥራችሁን በምትሠሩበት ጊዜ የስልክ ጥሪና ለመጠየቅ የሚመጣ ሰው ከሥራችሁ እንደሚያስተጓጉላችሁ ሁሉ ቴሌቪዥን ወይም ሬዲዮ መክፈት በጥናታችሁ ላይ እንዳታተኩሩ ያደርጋል።

በተጨማሪም በቂና ዓይን የማይወጋ ብርሃን እንዲኖራችሁ አድርጉ። ጥሩ ብርሃን ቶሎ እንዳትደክሙ ከማስቻሉም በላይ ለዓይናችሁ ጤንነትም ጥሩ ነው። ከተቻለም የክፍሉ አየር የተናፈሰ እንዲሆንና ሙቀቱ የተስተካከለ እንዲሆን አድርጉ። ቀዝቀዝ ያለ ክፍል ከሞቃት ክፍል ይልቅ ለጥናት የሚያበረታታ አካባቢ ይፈጥራል።

ፈጽሞ የማጥናት ፍላጎት ባይኖራችሁስ? ሕይወት ለስሜቶቻችን ተገዢዎች የመሆንን ቅንጦት እምብዛም አይሰጠንም። በዓለማዊ ሥራ ላይ የመሥራት ፍላጎት ኖራችሁም አልኖራችሁ በየቀኑ መሥራት ያስፈልጋችኋል። ስለዚህ የቤት ሥራችሁን መሥራታችሁ ራሳችሁን ለመገሠጽ እንደሚያለማምዳችሁና የኋላ ኋላ ለሚያጋጥማችሁ የሥራ ሁኔታ እንደሚያሠለጥናችሁ አድርጋችሁ ተመልከቱት። ሥራዬ ብላችሁ ያዙት። አንድ አሠልጣኝ እንደሚከተለው በማለት ይመክራሉ፦ “ከተቻለ ጥናቱ በየቀኑ በአንድ የተወሰነ ቦታና ጊዜ መደረግ ይኖርበታል። እንዲህ በማድረግም አዘውትሮ ማጥናት ልማድ ይሆንና . . . ለማጥናት ያለባችሁን ዳተኛነት ልትቀንሱ ትችላላችሁ።”

የጥናት ልማዳችሁ

በፊልጵስዩስ 3:​16 (አዓት) ላይ ጳውሎስ ክርስቲያኖችን “በደረስንበት የእድገት ደረጃ በዚያው ልማድ በሥርዓት መመላለሳችንን እንቀጥል” በማለት አበረታቷቸዋል። ጳውሎስ እዚህ ላይ የተናገረው ስለ ክርስቲያናዊ አኗኗር ልማድ ነበር። ይሁን እንጂ ልማድ ወይም የአሠራር ሥርዓት ለአጠናን ዘዴያችሁ አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ያህል ለማጥናት የምትፈልጉትን ነገር ለማደራጀት ሞክሩ። ተመሳሳይ ትምህርቶችን (ለምሳሌ ሁለት የውጭ ቋንቋዎችን) በተከታታይ ከማጥናት ተቆጠቡ። በተለይ ተደራራቢ የቤት ሥራ ካለባችሁ በምታጠኗቸው ትምህርቶች መካከል አጠር ያለ እረፍት አድርጉ።

የቤት ሥራችሁ ብዙ ማንበብን የሚጠይቅ ከሆነ የሚከተለውን ዘዴ ለመከተል ልትሞክሩ ትችሉ ይሆናል። በመጀመሪያ የምታነቡትን ነገር ቃኙ። እንድታነቡ ስለተሰጣችሁ ክፍል ጠቅለል ያለ ሐሳብ እንዲኖራችሁ በውስጡ ያሉትን ንዑሳን ርዕሶች፣ ሠንጠረዦችና የመሳሰሉትን እየገለጣችሁ አየት አየት አድርጉ። ቀጥሎ የየምዕራፎቹን ርዕሶች ወይም የየአንቀጾቹን ሐሳብ ጠቅለል አድርገው የሚይዙ ዐረፍተ ነገሮችን ተመርኩዛችሁ ጥያቄዎችን አውጡ። (ይህ ዘዴ አእምሯችሁ በምታነቡት ነገር ላይ እንዲያተኩር ይረዳችኋል።) አሁን ደግሞ ላወጣችኋቸው ጥያቄዎች መልስ እየፈለጋችሁ አንብቡ። እያንዳንዱን አንቀጽ ወይም ክፍል ስትጨርሱ ያነበባችኋቸውን ነጥቦች መጽሐፉን ሳታዩ ድገሙ። መላውን የቤት ሥራ ከጨረሳችሁ በኋላ እያንዳንዱን ርዕስ በዓይናችሁ እየቃኛችሁና ከያንዳንዱ ክፍል ያገኛችሁትን ነጥብ በቃል ለማስታወስ በመሞከር ከልሱ። ይህ ዘዴ ተማሪዎች ከሚያነቡት ነገር ውስጥ 80 በመቶውን ያህል እንዲይዙ እንደረዳቸው አንዳንድ ሰዎች ይናገራሉ!

በተጨማሪም አንድ መምህር እንዲህ ብለዋል፦ “አንድ መረጃ ሁልጊዜ ከሌሎች መረጃዎች ጋር ተዛምዶ እንደሚኖር እንጂ ለብቻው ተነጥሎ እንደማይኖር ተማሪው እንዲገነዘብ ማድረግ አስፈላጊ ነው።” ስለዚህ የምታጠኑትን ነገር ከዚህ በፊት ከምታውቁትና ካጋጠማችሁ ነገር ጋር ለማገናዘብ ጣሩ። የምትማሩት ነገር የሚሰጠውን ተግባራዊ ጥቅም መርምሩ።

በዚህ ረገድ ፈሪሃ አምላክ ያለው ወጣት ከሌሎች የተሻለ አጋጣሚ ይኖረዋል። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” ይላል። (ምሳሌ 1:​7) ለምሳሌ ያህል የፊዚክስ ሕጎችን ማጥናት አሰልቺ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ በፍጥረት አማካኝነት የአምላክ ‘የማይታየው ባሕርይ በግልጽ እንደሚታይ’ ማወቅ ለምትማሩት ነገር ትርጉም ይጨምርለታል። (ሮሜ 1:​20) በተመሳሳይም ታሪክ ብዙውን ጊዜ የይሖዋ ዓላማዎች ስለ ተፈጸሙበት ሁኔታ ያስተምራል። ስለ ሰባቱ የዓለም ኃይሎች (አሁን ያለውን አንግሎ አሜሪካን ጨምሮ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም ተብራርቷል!​— ራእይ 17:​10፤ ዳንኤል ምዕራፍ 7

የምትማሩትን ነገር ከምታውቁት ወይም ከክርስቲያናዊ እምነታችሁ ጋር ማዛመድ ለምትማሯቸው ነገሮች ትርጉም ከመስጠቱም በላይ እውቀታችሁ ወደ ማስተዋል እያደገ ይሄዳል። ሰሎሞን እንደተናገረው “ለአስተዋይ ግን እውቀትን ማግኘት አያስቸግረውም።”​— ምሳሌ 14:​6

በሚመጣው ሳምንት ፈተና ይኖራል’

እነዚህ ቃላት ሊያሸብሯችሁ አይገባም። ከሁሉ አስቀድሞ ፈተናው ምን ዓይነት እንደሚሆን፣ ማለትም ግለጽ የሚል ይሁን ወይም ምርጫ፣ አስተማሪያችሁ ከሚሰጡት አስተያየት ለመረዳት ሞክሩ። ከፈተናው በፊት ባሉት ቀናት ደግሞ ምን ዓይነት ጥያቄዎች ፈተናው ላይ እንደሚመጡ ፍንጭ ለማግኘት በጥሞና አዳምጡ። (“ቀጥሎ ያለው ነጥብ በጣም አስፈላጊ ነው”፣ ወይም “ልታስታውሱት የሚገባው ነገር ደግሞ” የሚሉትን የመሳሰሉ አነጋገሮች ዓይነተኛ ፍንጭ ሰጪዎች ናቸው ይላል ሲኒየር ስኮላስቲክ የተሰኘው መጽሔት።) ቀጥሎም የጻፋችኋቸውን ማስታወሻዎች፣ የመማሪያ መጽሐፎችና የቤት ሥራ የሠራችሁባቸውን ደብተሮች ከልሱ።

“ብረት ብረትን ይስለዋል፣ ሰውም ባልንጀራውን ይስላል” በማለት ሰሎሞን ያሳስበናል። (ምሳሌ 27:​17) ምናልባት ጓደኛችሁ ወይም ከወላጆቻችሁ አንዱ ጥያቄ እየጠየቀ ወይም በክፍል ውስጥ የተማራችሁትን ነገር በቃላችሁ ስትደግሙ በማዳመጥ ሊያለማምዳችሁ ይችል ይሆናል። ከዚያ በኋላም ከፈተናው በፊት ባለው ምሽት መንፈሳችሁን ለማዝናናትና ጥሩ እንቅልፍ ለማግኘት ሞክሩ። ኢየሱስ “ለመሆኑ ከእናንተ በማሰብና በመጨነቅ በዕድሜው ላይ አንድ ቀን እንኳ መጨመር የሚችል ማን ነው?” በማለት ጠይቋል።​— ማቴዎስ 6:​271980 ትርጉም

በፈተና መውደቅ

በፈተና መውደቅ፣ በተለይ ለማለፍ ከፍተኛ ጥረት አድርጋችሁ ከነበረ፣ ለራሳችሁ ያላችሁን አክብሮት ሊደመስስባችሁ ይችላል። ይሁን እንጂ መምህር ማክስ ራፌርቲ “በሕይወት እስካለን ድረስ የምንለካው በምናውቀው ነገር፣ በምናገኘው ውጤት መሠረት ነው። . . . ልጆች የሕይወት ብሩሕ ጎን ብቻ እንዲታያቸው የሚያደርግ ትምህርት ቤት የሕልም ማምረቻ ፋብሪካ እንጂ ትምህርት ቤት አይደለም” ብለዋል። በፈተና መውደቅ የሚያስከትለው ውርደት ካለፈው ስህተታችሁ በመማር ለወደፊቱ እንድታሻሽሉ የሚያነሳሳችሁ ከሆነ መውደቃችሁ ጥሩ ነው።

ይሁን እንጂ ደስ የማያሰኘውን ሪፖርት ካርዳችሁን ይዛችሁ ወላጆቻችሁ ፊት የምትቀርቡት እንዴት ነው? ይህ ዓይነቱ ፍርሃት አንዳንድ ጊዜ በረቀቁ ዘዴዎች መጠቀምን ያስከትላል። አንድ ወጣት “ሪፖርት ካርዴን በምግብ ቤቱ ጠረጴዛ ላይ አስቀምጥና ፎቅ ላይ ወጥቼ እስከማግሥቱ ጧት እተኛለሁ” ብሏል። ሌላው ደግሞ “እኔ ደግሞ በተቻለ መጠን ሪፖርት ካርዴን ለእናቴ ሳላሳይ ዘግይቼ ጧት ሥራ ልትሄድ ስትነሳ እሰጣትና ‘ይኸውልሽ፣ ፈርሚ’ እላታለሁ። ቢያንስ በጊዜው ከእኔ ጋር ለመጨቃጨቅ ጊዜ አይኖራትም” ይላል። አንዳንድ ወጣቶች አልፎ ተርፎ በሪፖርት ካርዳቸው ላይ የተጭበረበሩ የውሸት ውጤቶችን ጽፈው ያሳያሉ!

ይሁንና ወላጆቻችሁ በትምህርት ቤት ያገኛችሁትን ትክክለኛ ውጤት ማወቅ መብታቸው ነው። ውጤታችሁ ካላችሁ ችሎታ ጋር የሚመጣጠን እንዲሆን ይፈልጋሉ። በዚህም ምክንያት ውጤታችሁ ከወትሮው ያነሰ ከሆነ ተገቢ ተግሣጽ እንደሚሰጣችሁ ልትጠብቁ ትችላላችሁ። ስለዚህ ለወላጆቻችሁ ሐቀኞች ሁኑ። በተጨማሪም “የአባትህን ምክር ስማ፣ የእናትህንም ሕግ አትተው።” (ምሳሌ 1:​8) ከአቅማችሁ በላይ እንደጠበቁባችሁ ከተሰማችሁ ከእነርሱ ጋር ተነጋገሩበት። — በምዕራፍ 2 ላይ “ለወላጆቼ እንዴት ልነግራቸው እችላለሁ?” በሚል ርዕስ የቀረበውን ክፍል ተመልከቱ።

የፈተና ውጤቶች በጣም አስፈላጊ ቢሆኑም የማንነታችሁ የመጨረሻ መለኪያዎች አይደሉም። ይሁን እንጂ በትምህርት ቤት የምታሳልፉትን ጊዜ በሚገባ ተጠቀሙበትና የሚቻላችሁን ያህል ተማሩ። ትምህርታችሁን ለመከታተል የምታደርጉት ጥረት እናንተንም ሆነ ወላጆቻችሁን ሊያስደስትና ሊያረካ የሚችል ውጤት ያስገኝላችኋል።

የመወያያ ጥያቄዎች

◻ የፈተና ውጤቶች ለምን ዓላማ ያገለግላሉ? ለውጤቶች ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው?

◻ በትምህርታችሁ ረገድ የግል ኃላፊነት ሊሰማችሁ የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?

◻ ከትምህርት ሰዓት ውጭ የሚሠሩ ሥራዎችን ስትሠሩ ልታስቡባቸው የሚገቡ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

◻ የፈተና ውጤቶቻችሁን ልታሻሽሉ የምትችሉባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?

◻ ለፈተና መዘጋጀት የምትችሉት እንዴት ነው?

◻ በፈተና መውደቅን እንዴት ልትመለከቱት ይገባል? በፈተና ብትወድቁ ከወላጆቻችሁ መደበቅ ይኖርባችኋልን?

[በገጽ 141 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በግምት፣ በሽምደዳ ወይም በስርቆት የማለፊያ ውጤት የሚያገኝ ወጣት የማሰብ ችሎታውን ሊያዳብር አይችልም

[በገጽ 144, 145 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ከትምህርት ሰዓት ውጭ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችስ?

ብዙ ወጣቶች ከትምህርት ሰዓት ውጭ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መካፈል በሥራ ውጤታቸው ኩራት እንዲሰማቸው እንደሚያደርግ ተገንዝበዋል። በቦልቲሞር ሜሪላንድ (ዩ ኤስ ኤ) የሚኖር አንድ ልጅ “በሁሉም ክበቦች ውስጥ ገብቼ ነበር” በማለት ይናገራል። “የምወዳቸውን ነገሮች መሥራት ያስደስተኝ ነበር። ከመኪናዎች ጋር የተያያዙ ነገሮችን መሥራት ደስ ይለኝ ስለነበረ አውቶሞቲቭ ክበብ ውስጥ ገባሁ። ኮምፒዩተሮች እወዳለሁ፤ ስለዚህም ኮምፒዩተር ክበብ ውስጥ ገባሁ። ድምፅ አስተላላፊ መሣሪያዎችን ስለምወድ በኦዲዮ ክበብ ውስጥም ገባሁ።” በተለይ ኮሌጅ የመግባት ግብ ያላቸው ተማሪዎች ከትምህርት ሰዓት ውጭ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንዲካፈሉ ማበረታቻ ይሰጣቸዋል።

ይሁን እንጂ መምህር የነበሩ አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ፌዴራላዊ መንግሥት ባለ ሥልጣን ለንቁ! መጽሔት እንደሚከተለው በማለት ተናግረው ነበር፦ “ተማሪዎቹ ይበልጡን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በትምህርታቸው ላይ ሳይሆን ከትምህርት ውጭ በሚደረጉት እንቅስቃሴዎች ላይ ይሆንና በፈተናዎች ጥሩ ውጤት ማግኘት አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል።” አዎን፣ ከትምህርት ውጪ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እየተካፈሉ ሚዛን መጠበቅ ቀላል አይደለም። በትምህርት ቤቷ የሶፍትቦል ቡድን ውስጥ ትጫወት የነበረች ካቲ የምትባል ልጃገረድ እንደሚከተለው ብላለች፦ “ከጨዋታው በኋላ በጣም ይደክመኝ ስለነበር ምንም ሌላ ነገር መሥራት አልችልም ነበር። የትምህርት ቤት ሥራዬ ተነካብኝ። ስለዚህ በዚህ ዓመት አልተመዘገብኩም።”

በተጨማሪም መንፈሳዊ አደጋዎችም አሉ። አንድ ክርስቲያን የአፍላ ጉርምስና ዕድሜውን መለስ ብሎ ሲያስብ “ሦስት ሥራዎችን ማለትም ትምህርቴን፣ የሩጫ ልምምዴንና መንፈሳዊ ሥራዎቼን ማስማማት የምችል መስሎኝ ነበር። ይሁን እንጂ ሦስቱ በሚጋጩበት ጊዜ ሁሉ መንፈሳዊ ሕይወቴ ይበደል ነበር” ብሏል።

በትምህርት ቤት የሁለት ስፖርት ቡድኖች አባል የሆነው ወጣት ቴሞን እንደሚከተለው ይላል፦ “ማክሰኞ፣ ሐሙስ፣ እንዲሁም ቅዳሜ ከከተማ ውጭ ወጥተን ስለምንለማመድና ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት እስኪሆን ድረስ ስለማንመለስ በ[መንግሥት] አዳራሹ ተገኝቼ [መንፈሳዊ ትምህርት] ለመከታተል አልቻልኩም ነበር።” “አካላዊ ልምምድ ለጥቂት ነገር ጠቃሚነት” ቢኖረውም “ለአምላክ ያደሩ መሆን ግን ለነገር ሁሉ” ጠቃሚ መሆኑን ማስታወስ አስፈላጊ ነው።​— 1 ጢሞቴዎስ 4:​8 አዓት

በተጨማሪም ሊያጋጥሟችሁ ስለሚችሉት ሥነ ምግባራዊ አደጋዎች አስቡ። ከትምህርት ሰዓት ውጪ በምታደርጉት እንቅስቃሴ ጊዜያችሁን የምታሳልፉት በእናንተ ላይ ጥሩ ሥነ ምግባራዊ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩ ጓደኞች ጋር ነውን? የጭውውታቸው ርዕስ ምንድን ነው? የቡድን ወይም የክበብ አባሎች ተጽእኖ በእናንተ ላይ ጎጂ ውጤት ሊኖረው ይችል ይሆን? 1 ቆሮንቶስ 15:​33 “ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል” ይላል።

በይሖዋ ምሥክሮች መካከል የሚገኙ ብዙ ወጣቶች ከትምህርት ሰዓት ውጭ ያላቸውን ጊዜ ከስፖርት ይልቅ እጅግ በጣም ጠቃሚ ለሆነ ነገር ይጠቀሙበታል። ሌሎች ስለ ፈጣሪያቸው እንዲያውቁ በመርዳት ለማሳለፍ መርጠዋል። ቆላስይስ 4:​5 (የ1980 ትርጉም) “በማንኛውም አጋጣሚ ጊዜ እየተጠቀማችሁ በማያምኑት ሰዎች ዘንድ በጥበብ ኑሩ” በማለት ይመክራል።

[በገጽ 143 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ለማጥናት የሚሰንፉ ተማሪዎች . . . ማለፊያ ማርክ ማግኘት ያቅታቸዋል

[በገጽ 146 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ከትምህርት ሰዓት ውጭ የምታደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች ከቤት ሥራችሁ ጋር ሚዛናቸውን እንዲጠብቁ ማድረግ ቀላል አይደለም

[በገጽ 148 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጆች መጥፎ ውጤት የሠፈረበትን ካርድ ሲመለከቱ እንደሚናደዱ የተረጋገጠ ነው። ይሁን እንጂ ከአቅማችሁ በላይ እንደጠበቁባችሁ ከተሰማችሁ ከእነርሱ ጋር ተነጋገሩ