በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቴሌቪዥን የማየት ልማዴን ልቆጣጠር የምችለው እንዴት ነው?

ቴሌቪዥን የማየት ልማዴን ልቆጣጠር የምችለው እንዴት ነው?

ምዕራፍ 36

ቴሌቪዥን የማየት ልማዴን ልቆጣጠር የምችለው እንዴት ነው?

ቴሌቪዥን ማየት ለብዙ ወጣቶች እንዲሁም ለአዋቂዎች ከባድ ሱስ ሆኗል። ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የአሜሪካ ወጣቶች 18 ዓመት እስኪሆናቸው ድረስ በአማካይ ለ15, 000 ሰዓቶች ቴሌቪዥን ይመለከታሉ! ቴሌቪዥን መመልከት ደንበኛ ሱስ እንዳለው ግልጽ የሚሆነው አዘውታሪ ተመልካቾች ልማዱን ለመተው በሚሞክሩበት ጊዜ ነው።

“ቴሌቪዥን መመልከት መተው ከአቅሜ በላይ ነው ለማለት እችላለሁ። አንድ ጊዜ ከተከፈተ መመልከቱን ችላ ብዬ ልተው አልችልም። ፈጽሞ ላጠፋው አልችልም። . . . ላጠፋው እጄን ስዘረጋ ክንዴ ይዝልብኛል። ስለዚህ ለብዙ ሰዓቶች ተደቅኜ እቀራለሁ።” ይህን የተናገረው ብስለት የሌለው ወጣት ነውን? አይደለም፣ አንድ የኮሌጅ እንግሊዝኛ አስተማሪ ነው! ይሁን እንጂ ወጣቶችም ቢሆኑ የቴሌቪዥን ሱሰኞች ሊሆኑ ይችላሉ። በአንድ ጥናት ለአንድ ሳምንት ያህል ቴሌቪዥን ላለመክፈት የተስማሙ አንዳንድ ሰዎች የተናገሩትን ልብ በሉ፦

“የመንፈስ ጭንቀት እየያዘኝ ነው። . . . ላብድ ተቃርቤያለሁ።” —የአሥራ ሁለት ዓመቷ ሱዛን

“ልማዱን ለመተው የምችል አይመስለኝም። ቴሌቪዥን በጣም እወዳለሁ።” —የአሥራ ሦስት ዓመቷ ሊንዳ

“ግፊቱ በጣም ኃይለኛ ነው። እንድከፍተው የሚወተውት ስሜት አለኝ። ይበልጥ አስቸጋሪ የሚሆነው ማታ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት እስከ አራት ሰዓት ባለው ጊዜ ነው።” — የአሥራ አንድ ዓመቱ ሉወስ

በዚህ “ቴሌቪዥን የማይከፈትበት ሳምንት” ተካፋይ ከሆኑት ወጣቶች የሚበዙት ሳምንቱ እንዳለቀ ቴሌቪዥን ለመክፈት መንደርደራቸው አያስደንቅም። ይሁን እንጂ የቴሌቪዥን ሱሰኛ መሆን የሚያስቅ ነገር ሳይሆን ብዙ አሳሳቢ ችግሮችን ይዞ የሚመጣ ነገር ነው። ከችግሮቹ ጥቂቶቹን ብቻ እንመልከት፦

የትምህርት ውጤት ማሽቆልቆልየአእምሮ ጤንነት ብሔራዊ ተቋም (የዩናይትድ ስቴትስ) ቴሌቪዥን ከልክ በላይ መመልከት “ዝቅተኛ የትምህርት ውጤት፣ በተለይም የንባብ ችሎታ መቀነስ” ሊያስከትል እንደሚችል ገልጿል። ዘ ሊትረሲ ሆክስ የተባለው መጽሐፍ በይበልጥ ቴሌቪዥን መመልከትን ሲወቅስ “ቴሌቪዥን ልጆች መማር ቀላል መሆን እንዳለበት፣ የግል ጥረት የማይጠይቅና አዝናኝ መሆን እንደሚኖርበት አድርገው እንዲያስቡ” ያደርጋቸዋል ብሏል። በመሆኑም አንድ የቴሌቪዥን ሱሰኛ ትምህርቱን የሚያጠናበትን ጊዜ እንደመከራ ጊዜ ይቆጥራል።

ደካማ የሆነ የማንበብ ልማድአንድን መጽሐፍ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው ካነበባችሁ ምን ያህል ጊዜ ሆኗል? አንድ የምዕራብ ጀርመን የመጻሕፍት ሻጮች ቃል አቀባይ የሚከተለውን እሮሮ አሰምተዋል፦ “አገራችን ከሥራ በኋላ ወደቤታቸው ሄደው በቴሌቪዥናቸው ፊት የሚያንቀላፉ ሕዝቦች አገር ሆናለች። የማንበብ ልማዳችን ከቀን ወደ ቀን እየቀነሰ ሄዷል።” ከአውስትራሊያ የመጣ አንድ ዘገባም በተመሳሳይ “አንድ አውስትራሊያዊ ልጅ በአማካይ ለንባብ ለሚያውለው ለእያንዳንዱ ሰዓት ሰባት ሰዓት ቴሌቪዥን በመመልከት ያሳልፋል” ብሏል።

ቤተሰብ በጋራ የሚያሳልፈው ጊዜ መቀነስአንዲት ክርስቲያን ሴት “ቴሌቪዥን በብዛት በመመልከቴ የተነሳ . . . በጣም ብቸኛና ከሰው የተነጠልኩ እንደሆንኩ ይሰማኛል። የራሴ ቤተሰቦች እንኳን እንግዶች እንደሆኑብኝ ያህል ነበር” በማለት ጽፋለች። እናንተም በተመሳሳይ ቴሌቪዥን በብዛት በማየታችሁ ምክንያት ከቤተሰባችሁ ጋር የምታሳልፉት ጊዜ በጣም አጭር እንደሆነባችሁ ተገንዝባችኋልን?

ስንፍናአንዳንድ ሰዎች ቴሌቪዥን ማየት ምንም ዓይነት ተሳትፎ የማይጠይቅ መሆኑ “[አንድ ወጣት] የሚያስፈልጉት ነገሮች አለምንም ጥረት እንደሚሟሉለት ተስፋ እንዲያደርግና በሕይወት ጉዳዮችም ዳር ቆሞ ተመልካች እንዲሆን ሊያደርገው እንደሚችል” ይሰማቸዋል።

ጤናማ ላልሆኑ ተጽእኖዎች መጋለጥአንዳንድ የኬብል ቴሌቪዥን ሥርጭቶች ወሲባዊ ፕሮግራሞችን ያቀርባሉ። መደበኛ የሆኑት ፕሮግራሞችም ቢሆኑ ብዙውን ጊዜ የመኪኖችን ግጭት፣ ፍንዳታዎችን፣ በጩቤ መገዳደልን፣ ጥይት መተኳኮስንና የካራቴ አመታቶችን የሚያሳዩ ናቸው። አንድ ጥናት እንደገለጸው በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ አንድ ወጣት ሰው 14 ዓመት እስኪሞላው ድረስ በቴሌቪዥን ላይ 18, 000 ግድያዎች ሲፈጸሙ እንደሚመለከት ይገመታል። ይህም በቡጢ መመታታትንና ዝርፊያን ሳይጨምር ነው።

ዊሊያም ቤልሰን የተባሉ እንግሊዛዊ ተመራማሪ ዓመፅ የሚያሳዩ የቴሌቪዥን ፊልሞችን እያዩ የሚያድጉ ልጆች “ከባድ በሆነ ዓመፅ የመካፈል” አጋጣሚያቸው ከፍ ያለ እንደሆነ ተገንዝበዋል። በተጨማሪም የዓመፅ ፊልሞችን በቴሌቪዥን መመልከት ወጣቶች “ተሳዳቢዎችና ተራጋሚዎች፣ በስፖርትና በጨዋታ ላይ እብሪተኞች፣ በሌሎች ላይ የሚዝቱና የሚያስፈራሩ እንዲሆኑና በግድግዳዎች ላይ መፈክር እንዲጽፉና መስኮቶችን እንዲሰብሩ” ሊያነሳሳ እንደሚችል ተናግረዋል። እንደነዚህ ባሉት ተጽዕኖዎች ልሸነፍ አልችልም ብላችሁ ልታስቡ ትችላላችሁ። ይሁን እንጂ የቤልሰን ጥናት እንዳሳየው ልጆች ዓመፅ የሚታይባቸውን የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች መመልከታቸው ሆን ብለው ወይም ፈልገው ስለ ዓመፅ ያላቸውን አመለካከት እንዲለውጡ አላደረጋቸውም። ዓመፅ የሚያሳዩ ፕሮግራሞችን አለማቋረጥ መመገባቸው የለወጠው ውስጠ ሕሊናቸውን ሲሆን ሕሊናቸው ሊኖረው የሚገባውን ዓመፅን የመከላከል ኃይል ሸርሽሮባቸዋል።

ይሁንና ከዚህ ይበልጥ አሳሳቢ የሚሆነው በቴሌቪዥን የዓመፅ ፊልሞችን ለመመልከት ሱሰኛ መሆን ‘ማንኛውንም ዓመፅ የሚወድ ሰው ከሚጠላው’ አምላክ ጋር ባላችሁ ዝምድና ላይ ሊያስከትል የሚችለው ውጤት ነው። — መዝሙር 11:​5

ቴሌቪዥን የመመልከት ልማዴን ልቆጣጠር የምችለው እንዴት ነው?

ይህ ማለት ግን ቴሌቪዥን በራሱ መጥፎ ነው ማለት ላይሆን ይችላል። ቫንስ ፓከርድ የተባሉት ደራሲ እንዳመለከቱት “በዩናይትድ ስቴትስ ቴሌቪዥን ብዙ ጠቃሚ ፕሮግራም ይቀርባል። . . . ከሌሊት ወፎችና ቢቨር ከሚባሉት እንስሳት እንቅስቃሴ ጀምሮ እንደጎሽና እሾኻማ ገላ እንዳላቸው ዓሦች የመሰሉ የተለያዩ ፍጥረታት እንቅስቃሴ የሚታይባቸው አስደናቂ የፎቶግራፍ አንሺነት ችሎታ ውጤቶች የሆኑ ፕሮግራሞች አሉ። በመንግሥት ጣቢያዎች የሚተላለፉ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች አስደናቂ የሆኑ ባሕላዊ ውዝዋዜዎችን፣ ኦፔራዎችንና የባንድ ሙዚቃዎችን ያቀርባሉ። ቴሌቪዥን ዐበይት ዜናዎችን ለመከታተል በጣም ጥሩ ነው። . . . አልፎ አልፎም እውቀት ሰጪ የሆኑ አስደናቂ ፊልሞችን ያቀርባል።”

ይሁን እንጂ ማንኛውም ጥሩ የሚባል ነገርም ቢሆን ከመጠኑ ሲያልፍ ጎጂ ሊሆን ይችላል። (ከምሳሌ 25:​27 ጋር አወዳድሩ።) ጎጂ ትዕይንቶችን ላለማየት ስትሉ ቴሌቪዥናችሁን እንድትዘጉ የሚያስችል ጥንካሬ እንደሌላችሁ ከተገነዘባችሁ “ምንም ነገር ባሪያ እንዲያደርገኝ አልፈቅድለትም” ያለውን የሐዋርያው ጳውሎስን ቃላት አስታውሱ። (1 ቆሮንቶስ 6:​12 ቱደይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን ) ታዲያ ለቴሌቪዥን ባሪያ ከመሆን ነፃ ልትወጡ የምትችሉትና ቴሌቪዥን የማየት ልማዳችሁን ልትቆጣጠሩ የምትችሉት እንዴት ነው?

ሊንዳ ኔልሰን የተባሉ ደራሲ “ራስን መግዛት የሚጀመረው ግብ ማውጣትን በመማር ነው” በማለት ገልጸዋል። መጀመሪያ ባሁኑ ጊዜ ያላችሁን ልማድ መርምሩ። ለአንድ ሳምንት ያህል የምታዩአቸው ፕሮግራሞች ምን ዓይነት እንደሆኑና በየቀኑ ቴሌቪዥን በማየት የምታሳልፉት ጊዜ ምን ያህል እንደሆነ ተከታተሉ። ወዲያው ቤታችሁ እንደገባችሁ ቴሌቪዥን ትከፍታላችሁን? የምታጠፉትስ መቼ ነው? “የግድ ማየት አለብኝ” የምትሏቸው ፕሮግራሞች ስንት ናቸው? ውጤቱ በጣም ያስደነግጣችሁ ይሆናል።

ከዚያ በኋላ ስትመለከቱአቸው የነበሩትን ፊልሞች በጥሞና መርምሩ። መጽሐፍ ቅዱስ “ምላስ መብልን እንደሚቀምስ፣ ጆሮ ቃልን የሚለይ አይደለምን?” በማለት ይጠይቃል። (ኢዮብ 12:​11) ስለዚህ አስተዋዮች በመሆንና ወላጆቻችሁ የሚሰጧችሁን ምክር በመከተል በእርግጥ ሊጠቅሙአችሁ የሚችሉት ፕሮግራሞች የትኞቹ እንደሆኑ አመዛዝናችሁ ምረጡ። አንዳንዶች ምን ፊልሞችን እንደሚመለከቱ አስቀድመው የወሰኑ በመሆናቸው ቴሌቪዥናቸውን የሚከፍቱት እነዚያን ፊልሞች ብቻ ለመመልከት ነው! ሌሎች ደግሞ ጠበቅ ያለ እርምጃ በመውሰድ በትምህርት ቀኖች ቴሌቪዥን ላለማየት ወይም በየቀኑ አንድ ሰዓት ብቻ ለመመልከት ለራሳቸው ሕግ ያወጣሉ።

ይሁን እንጂ በተዘጋ ቴሌቪዥን አጠገብ መቀመጥ የሚፈትናችሁ ቢሆንባችሁስ? አንድ ቤተሰብ ይህን ችግር በሚከተለው መንገድ ፈቷል፦ “ቴሌቪዥናችን ከፊታችን ገለል እንዲልልን በምድር ቤቱ አስቀመጥነው። . . . በምድር ቤቱ በመቀመጡ ወዲያው እቤት እንደገባን ለመክፈት አንፈተንም። አንድ ነገር ለማየት ብንፈልግ ረዘም ያለ ጉዞ ማድረግ ይጠይቅብናል።” ቴሌቪዥናችሁን በቁም ሣጥን ውስጥ ማስቀመጥ ወይም ሶኬቱን ነቅላችሁ መተውም ቢሆን የዚያኑ ያህል ውጤታማ ሊሆን ይችላል።

“ቴሌቪዥን የማይከፈትበት ሳምንት” ተሳታፊ የሆኑት ወጣቶች ሱስ የሆነባቸውን ነገር ለማግኘት አለመቻላቸው ያሠቃያቸው ቢሆንም ለቴሌቪዥን መተኪያ የሚሆኑ አንዳንድ ገንቢ ነገሮች አግኝተው ነበር። አንዲት ልጃገረድ “ከእናቴ ጋር አወራ ነበር። ትኩረቴ በእርሷና በቴሌቪዥኑ መካከል ስላልተከፋፈለብኝ በእኔ አመለካከት ከቴሌቪዥኑ ይበልጥ አስደሳች ሰው ሆና አገኘኋት” በማለት ታስታውሳለች። ሌላዋ ልጃገረድ ምግብ መሥራት በመለማመድ ጊዜዋን አሳልፋለች። ጄሰን የሚባል አንድ ወጣት ወደ መናፈሻ መሄድ ወይም ዓሣ ማጥመድ፣ ማንበብ ወይም ወደ ባሕር ዳር ሄዶ መናፈስ ቴሌቪዥን ከመመልከት ይበልጥ አስደሳች እንደሆነ ተገንዝቧል።

ሌላው ቴሌቪዥን መመልከትን ለመቆጣጠር ቁልፍ የሆነ ነገር ‘የጌታ ሥራ እንዲበዛልን ማድረግ’ እንደሆነ የዋየንት ተሞክሮ ያሳያል። (“የቴሌቪዥን ሱሰኛ ነበርኩ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) (1 ቆሮንቶስ 15:​58) እናንተም ከአምላክ ጋር የቅርብ ዝምድና ብትመሠርቱ፣ በአሁኑ ጊዜ ተዘጋጅተው በሚቀርቡልን ጥሩ ጥሩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ረዳትነት መጽሐፍ ቅዱስን ብታጠኑና የአምላክ ሥራ የሚበዛላችሁ ብትሆኑ ቴሌቪዥን የማየት ሱሳችሁን ማሸነፍ ቀላል ይሆንላችኋል። (ያዕቆብ 4:​8) እውነት ነው፣ ቴሌቪዥን በማየት ልማዳችሁ ላይ ገደብ ማድረጋችሁ ከምትወዱአቸው አንዳንድ ፕሮግራሞች መነጠል ሊሆንባችሁ ይችላል። ይሁን እንጂ እያንዳንዱን ፕሮግራም በመከታተልና ራሳችሁን የቴሌቪዥን ባሪያዎች በማድረግ ጊዜያችሁን በሙሉ ቴሌቪዥን ለመመልከት የምታውሉት ለምንድን ነው? (1 ቆሮንቶስ 7:​29, 31ን ተመልከቱ።) “ሥጋዬን እየጎሰምሁ [“እንደ ባሪያ” አዓት] አስገዛዋለሁ” በማለት እንደተናገረው እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ በራሳችሁ ላይ ‘ብትጨክኑ’ ይሻላችኋል። (1 ቆሮንቶስ 9:​27) እንዲህ ማድረግ የቴሌቪዥን ባሪያ ከመሆን አይሻልምን?

የመወያያ ጥያቄዎች

◻ ቴሌቪዥን መመልከት ለአንዳንድ ወጣቶች ሱስ ሆኖባቸዋል ሊባል የሚቻለው ለምንድን ነው?

◻ ከልክ በላይ ቴሌቪዥን መመልከት ከሚያስከትላቸው ጎጂ ውጤቶች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

◻ ቴሌቪዥን የማየትን ልማድ መቆጣጠር ከሚቻልባቸው መንገዶች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

◻ ቴሌቪዥን ከማየት ይልቅ ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ?

[በገጽ 295 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“የመንፈስ ጭንቀት እየያዘኝ ነው። . . . ላብድ ተቃርቤያለሁ።” —የአሥራ ሁለት ዓመቷ ሱዛን፣ “ቴሌቪዥን የማይከፈትበት ሳምንት” ተሳታፊ

[በገጽ 292, 293 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የ‘የቴሌቪዥን ሱሰኛ ነበርኩ’​— ቃለ መጠይቅ

ጠያቂ፦ ከቴሌቪዥን ጋር መቆራኘት የጀመርከው ስንት ዓመት ሲሆንህ ነበር?

ዋየንት፦ ወደ አሥር ዓመት ገደማ ሲሆነኝ ነበር። ከትምህርት ቤት እንደተመለስኩ ቴሌቪዥን እከፍታለሁ። መጀመሪያ፣ የካርቱን ፊልሞችንና የልጆችን ፕሮግራም እመለከታለሁ። ቀጥሎ ዜና ይመጣል። . . . ከዚያም ወደ ወጥ ቤት እሄድና የምበላው ነገር እፈልጋለሁ። ከዚያ በኋላ ወደ ቴሌቪዥኑ ተመልሼ እንቅልፌ እስኪመጣ ድረስ ስመለከት እቆያለሁ።

ጠያቂ፦ ታዲያ ከጓደኞችህ ጋር ለመጫወት ጊዜ የሚኖርህ መቼ ነው?

ዋየንት፦ ጓደኛዬ ቴሌቪዥን ነበር።

ጠያቂ፦ እንዲህ ከሆነማ ለጨዋታም ሆነ ለስፖርት ጊዜ ኖሮህ አያውቅም ማለት ነው?

ዋየንት፦ [እየሳቀ] የስፖርት ችሎታ የለኝም። ምክንያቱም ጊዜዬን የማሳልፈው ሁልጊዜ ቴሌቪዥን በመመልከት ስለሆነ የስፖርት ችሎታዬን አላዳበርኩም። ቅርጫት ኳስ መጫወት አልችልም። በሰውነት ማሠልጠኛ ክፍለ ጊዜ ለመመረጥ ሁልጊዜ የመጨረሻ ነበርኩ። የስፖርት ችሎታዬን ከዚህ በተሻለ ሁኔታ አዳብሬ ቢሆን ኖሮ ደስ ይለኝ ነበር። እንዲህ ነኝ ብዬ ለመፎከር ባልችል እንኳን ራሴን ለማስደሰት እችል ነበር።

ጠያቂ፦ የትምህርት ውጤትህስ እንዴት ነበር?

ዋየንት፦ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንደምንም ብዬ ለማለፍ ችዬአለሁ። የቤት ሥራዎቼን ቴሌቪዥን ስመለከት ካመሸሁ በኋላ በጥድፊያ እሠራ ነበር። ሁለተኛ ደረጃ ስገባ ግን ጥሩ የአጠናን ልማድ ስላልነበረኝ በጣም ከብዶኝ ነበር።

ጠያቂ፦ ያን ያህል ብዙ ጊዜ ቴሌቪዥን መመልከትህ ያስከተለብህ ችግር አለን?

ዋየንት፦ አዎን። አንዳንድ ጊዜ ከሰዎች ጋር ስሆን ሰዎቹ በቴሌቪዥን ውስጥ የምመለከታቸው ይመስለኝና በጭውውቱ በመሳተፍ ፈንታ ዝም ብዬ እመለከታቸዋለሁ። ከሰዎች ጋር ያለኝ ግንኙነት ከአሁኑ የተሻለ ቢሆን ደስ ይለኝ ነበር።

ጠያቂ፦ አሁን ባደረግነው ጭውውት ግን ጥሩ ተሳትፎ አድርገሃል። የቴሌቪዥን ሱስህን ያሸነፍክ ይመስላል።

ዋየንት፦ ከቴሌቪዥን መላቀቅ የጀመርኩት ሁለተኛ ደረጃ ስገባ ነው። . . . የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ ጓደኞች ፈለግሁና መንፈሳዊ መሻሻል ማድረግ ጀመርኩ።

ጠያቂ፦ ታዲያ ይኼ ቴሌቪዥን ከመመልከትህ ጋር ምን ግንኙነት አለው?

ዋየንት፦ ለመንፈሳዊ ነገሮች ያለኝ አድናቆት እያደገ ሲመጣ ስመለከታቸው የነበሩት ብዙ ፊልሞች በእርግጥ ክርስቲያኖች ሊያዩአቸው የማይገቡ መሆናቸውን ተገነዘብኩ። በተጨማሪም ከበፊቱ ይበልጥ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናትና ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መዘጋጀት እንዳለብኝ ተሰማኝ። ይህ ደግሞ እመለከተው ከነበረው የቴሌቪዥን ፕሮግራም አብዛኛውን እንድቀንስ አስገደደኝ። ይሁንና እንዲህ ማድረግ ቀላል አልነበረም። ቅዳሜ ጧት የሚተላለፉትን የካርቱን ፊልሞች እወዳቸው ነበር። ይሁን እንጂ በጉባኤው ያለ አንድ ክርስቲያን ወንድም ቅዳሜ ጧት ከቤት ወደ ቤት በሚያደርገው የስብከት ሥራ አብሬው እንድሄድ ጋበዘኝ። ይህም የቅዳሜ ጠዋት ቴሌቪዥን የማየት ልማዴን እንድተው አደረገኝ። ስለዚህ ቀስ በቀስ ቴሌቪዥን የመመልከት ልማዴን እንዴት እንደምቋቋም ተማርኩ።

ጠያቂ፦ ዛሬስ እንዴት ነህ?

ዋየንት፦ ዛሬም ቢሆን ቴሌቪዥን ከተከፈተ ምንም ነገር ልሠራ ስለማልችል ችግሩ አለብኝ። ስለዚህ ብዙውን ጊዜ አልከፍተውም። እንዲያውም ቴሌቪዥኔ ከጥቂት ወራት በፊት ተበላሽቶብኛል። ላሠራው አልፈለግሁም።

[በገጽ 291 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቴሌቪዥን ማየት ለአንዳንድ ሰዎች ከባድ ሱስ ሆኗል

[በገጽ 294 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቴሌቪዥኑ በማያመች ቦታ ከተቀመጠ እቤት እንደገቡ ለመክፈት የሚኖረው ፈተና ይቀንሳል