በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አልፎ አልፎ መዝናናት አልችልም?

አልፎ አልፎ መዝናናት አልችልም?

ምዕራፍ 37

አልፎ አልፎ መዝናናት አልችልም?

ፓሊን * በየሳምንቱ ዐርብ ማታ ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ትሄድ ነበር። በስብሰባው ላይ የሚደረገው ውይይት ያስደስታታል። ይሁን እንጂ የትምህርት ቤት ጓደኞቿ በሚዝናኑበት ሰዓት እሷ ግን በስብሰባ ላይ መሆኗ አንዳንድ ጊዜ ቅር ያሰኛት ነበር።

ፓሊን ስብሰባው ሲያልቅ በቤቷ አካባቢ በአፍላ ጉርምስና ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች ተኮልኩለው በሚዝናኑበት ሥፍራ በኩል ታልፍ ነበር። እንዲህ በማለት ታስታውሳለች:- “በዚያ በኩል በምናልፍበት ጊዜ በከፍተኛ ድምፅ በሚጮኸው ዘፈንና በሚንቦገቦገው መብራት በመማረክ ተንጠራርቼ በመስኮቱ በኩል እመለከታቸውና ምን ዓይነት የደስታ ጊዜ እንደሚያሳልፉ በማሰብ እጓጓ ነበር።” ከጊዜ በኋላ ከጓደኞቿ ጋር ለመደሰት ያላት ምኞት በሕይወቷ ውስጥ ከሁሉ የሚበልጥ ጉዳይ ሆነ።

እናንተም ክርስቲያኖች በመሆናችሁ ምክንያት እንደ ፓሊን የቀረባችሁ ነገር እንዳለ ይሰማችሁ ይሆናል። ሌሎች ሁሉ በአድናቆት የሚያወሩለትን የቴሌቪዥን ፕሮግራም ለማየት ትፈልጋላችሁ። ወላጆቻችሁ ግን ፕሮግራሙ ዓመፅ የሞላበት ስለሆነ ማየት የለባችሁም ይሉአችኋል። እናንተ መንገድ ዳር ወጥታችሁ ከሌሎች የትምህርት ቤት ጓደኞቻችሁ ጋር ለመጫወት ትፈልጋላችሁ፤ ወላጆቻችሁ ግን ልጆቹ “መጥፎ ባልንጀሮች” ናቸው ይሏችኋል። (1 ቆሮንቶስ 15:​33) የትምህርት ቤት ጓደኞቻችሁ በሙሉ ወደሚገኙበት ፓርቲ ለመሄድ ትፈልጋላችሁ፤ አባባና እማማ ግን አይቻልም ይሏችኋል።

የትምህርት ቤት ጓደኞቻችሁ እንደፈለጉ ቢወጡና ቢገቡ፣ በሙዚቃ ትርኢቶች ላይ ቢገኙና ጎሕ እስኪቀድ ድረስ ሲደንሱ ቢያድሩ ወላጆቻቸው ምንም አይሏቸውም። በመሆኑም እነሱ ባላቸው ነፃነት ልትቀኑ ትችላላችሁ። መጥፎ ነገር ለማድረግ ስለምትፈልጉ አይደለም። ብቻ አልፎ አልፎ ለመዝናናት ትፈልጋላችሁ።

አምላክ ስለ መዝናኛ ያለው አመለካከት

ራሳችሁን ለማስደሰት መፈለግ ምንም ስህተት እንደሌለው እርግጠኞች ሁኑ። ይሖዋም “ደስተኛ አምላክ” ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:​11 አዓት) ሰሎሞን በተባለው ጠቢብ ሰው አማካኝነትም “አንተ ጎበዝ፣ በጉብዝናህ ደስ ይበልህ፣ በጉብዝናህም ወራት ልብህን ደስ ይበለው፣ በልብህም መንገድ ዓይኖችህም በሚያዩት ሂድ” ይላል። ይሁን እንጂ ቀጥሎ “ዳሩ ግን ለምታደርገው ነገር ሁሉ እግዚአብሔር የሚፈርድብህ መሆኑን አስታውስ” በማለት አስጠንቅቋል።​— መክብብ 11:​9, 10 ቱደይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን

አምላክ ለምታደርጉት ሁሉ በኃላፊነት የሚጠይቃችሁ መሆኑን ማወቃችሁ ለመዝናኛ የተለየ አመለካከት እንዲኖራችሁ ያደርጋል። ምክንያቱም አምላክ መዝናናትን የማያወግዝ ቢሆንም ‘ተድላ አፍቃሪ’ የሆኑ ሰዎችን፣ ለመዝናናት ብቻ የሚኖሩ ሰዎችን ያወግዛል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1, 4) ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ንጉሥ ሰሎሞንን እንውሰድ። የነበረውን በጣም ብዙ ሀብት በመጠቀም ሰው ሊያስበው የሚችለውን ማንኛውም ዓይነት ሰብዓዊ ተድላ ቀምሷል። እንዲህ ይላል:- “ዓይኖቼንም ከፈለጉት ሁሉ አልከለከልኋቸውም፤ ልቤም በድካሜ ሁሉ ደስ ይለው ነበርና ልቤን ከደስታ ሁሉ አላራቅሁትም።” ውጤቱስ ምን ነበር? “እነሆ፣ ሁሉ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነበረ።” (መክብብ 2:​10, 11) አዎን፣ ተድላ በማሳደድ ላይ ብቻ የተመሠረተ ኑሮ የኋላ ኋላ ባዶና ብስጩ አድርጎ እንደሚያስቀር አምላክ ያውቃል።

በተጨማሪም አምላክ አደንዛዥ ዕፅ መውሰድንና ከጋብቻ በፊት ወሲብ መፈጸምን ከመሰሉ የሚያረክሱ ተግባሮች እንድትርቁ ይፈልጋል። (2 ቆሮንቶስ 7:​1) በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች ለደስታ ብለው የሚያደርጓቸው አብዛኞቹ ነገሮች ግን አንድ ወጣት በእነዚህ የሚያረክሱ ተግባሮች እንዲጠመድ ሊያደርጉ የሚችሉ ናቸው። ለምሳሌ ያህል አንዲት ልጃገረድ አንዳንድ የትምህርት ቤት ጓደኞቿ ባዘጋጁት ትላልቅ ሰዎች ያልተገኙበት ፕሮግራም ላይ ለመገኘት ወሰነች። “በጣም ግሩም የሆነ ሙዚቃ ተከፍቷል፣ ከፍተኛ ውዝዋዜ፣ አስደሳች መጠጦችና ልዩ ልዩ ቀላል ምግቦች፣ እንዲሁም ብዙ ሣቅ ነበር” በማለት ታስታውሳለች። ከዚያ በኋላ ግን “አንድ ሰው ሐሺሽ አመጣ። በኋላም የሚያሰክር መጠጥ መጣ። ነገሩ ሁሉ ትርምስምሱ የወጣው በዚህ ጊዜ ነበር።” ዝሙት ተፈጸመ። ልጅቷ ስትናዘዝ “ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ብስጩና በመንፈስ ጭንቀት የምሠቃይ ሆኛለሁ” ብላለች። አዋቂ ሰው ተገኝቶ የማይታዘባቸው እንዲህ ዓይነቶቹ ግብዣዎች በቀላሉ “ልቅ የሆኑ ግብዣዎች” ወይም ፈንጠዝያዎች ይሆናሉ!​— ገላትያ 5:​21 ባይንግተን

ስለዚህ ወላጆቻችሁ ትርፍ ጊዜያችሁን የምታሳልፉበት ሁኔታ በጣም የሚያሳስባቸው መሆኑና ምናልባትም ልትሄዱ የምትችሉበትን ቦታና ከእነማን ጋር አብራችሁ መዋል እንዳለባችሁ ገደብ ማድረጋቸው የሚገባ ነው። እንዲህ የሚያደርጉበት ምክንያት ምንድን ነው? “ሕፃንነትና ጉብዝና ከንቱዎች ናቸውና ከልብህ ኀዘንን አርቅ፣ ከሰውነትህም ክፉን ነገር አስወግድ” የሚለውን የአምላክ ማስጠንቀቂያ በተግባር እንድታውሉ ሊረዱአችሁ ብለው ነው።​— መክብብ 11:​10

በተድላ አሳዳጆች ትቀናላችሁን?

ይህን ሁሉ ረስቶ አንዳንድ ወጣቶች በሚሰጣቸው ነፃነት ለመቅናት ቀላል ነው። ፓሊን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መካፈል አቆመችና ተድላ አሳዳጅ ከሆኑት ብዙኃን ጋር ተባበረች። “መጥፎ ናቸው ተብለው የተነገሩኝን ነገሮች በሙሉ አደረግሁ” በማለት ታስታውሳለች። የፓሊን ተድላ አሳዳጅነት ተይዛ ወደ አስቸጋሪ ልጃገረዶች ጠባይ ማረሚያ እስከመግባት አደረሳት!

ከረዥም ዘመን በፊት የመዝሙር 73 ጸሐፊ ከፓሊን ጋር የሚመሳሰል ስሜት ተሰምቶት ነበር። “የኃጢአተኞችን ሰላም አይቼ በዓመፀኞች ቀንቼ ነበርና” በማለት ተናዟል። የጽድቅ መስፈርቶችን ጠብቆ የመኖርን ጥቅም እንኳን ተጠራጥሮ ነበር። “በውኑ ልቤን በከንቱ አጸደቅሁ፣ እጆቼንም በንጽሕና በከንቱ አጠብሁ” ብሏል። ይሁን እንጂ ወዲያው ጥልቀት ያለው ማስተዋል አገኘ:- ክፉ ሰዎች “በድጥ ሥፍራ” ላይ፣ በጥፋት አፋፍ ላይ ተንጠልጥለው እንደሚገኙ ተገነዘበ።​— መዝሙር 73:​3, 13, 18

ፓሊን ይህን ሐቅ ከደረሰባት መከራ ተምራለች። ከተዘፈቀችበት ዓለማዊ አኗኗር ከወጣች በኋላ የአምላክን ሞገስ መልሳ ለማግኘት በሕይወትዋ ውስጥ ከፍተኛ የሆኑ ለውጦች አደረገች። እናንተ ግን ‘መዝናናት’ እጅግ ከባድ መዘዝ እንደሚያመጣ ለመገንዘብ በእስረኝነት ተይዛችሁ መሠቃየት፣ በአባለ ዘር በሽታዎች መለከፍ፣ ወይም የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኛ መሆን አያስፈልጋችሁም። እንደነዚህ ያሉትን አደጋዎች የማያስከትሉና ራሳችሁን ማስደሰት የምትችሉባቸው ብዙ ጤናማና ገንቢ የሆኑ መንገዶች አሉ። ከእነዚህ መንገዶች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

ጤናማ የሆኑ መዝናኛዎች

በአሜሪካ ወጣቶች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች “አልፎ አልፎ ከቤተሰብ ጋር በሚደረጉ ሽርሽሮችና እንቅስቃሴዎች እንደሚደሰቱ” ገልጿል። ቤተሰብ በሙሉ አንድ ላይ ሆኖ የሚያደርጋቸው ነገሮች መኖራቸው አስደሳች ከመሆኑም በላይ የቤተሰብ አንድነት ያጠናክራል።

እንዲህ ሲባል ግን አንድ ላይ ሆኖ ቴሌቪዥን መመልከት ብቻ ይበቃል ማለት አይደለም። አንቶኒ ፒየትሮፒንቶ እንዳሉት “ቴሌቪዥን የመመልከት መጥፎነት ከሌሎች ጋር ሆኖ ሊታይ የሚችል ቢሆንም ሌሎችን የማያሳትፍ መሆኑ ነው። . . . ቤተሰቡ ቴሌቪዥን በመመልከት ጊዜውን ከሚያባክን ይልቅ በቤት ውስጥ ጨዋታዎች፣ በጓሮ አጥር ግቢ ውስጥ በሚደረጉ ስፖርቶች፣ ምግብ በማብሰል፣ የእጅ ጥበብ የሚጠይቅ ሥራ በመሥራት፣ ጮክ ብሎ በማንበብና በመሳሰሉት የጊዜ ማሳለፊያ ተግባራት ቢያሳልፍ ሐሳብ ለሐሳብ ለመለዋወጥ የሚያስችል አጋጣሚ ከማግኘቱም በላይ የትብብርና ለትምህርት የመነቃቃት አጋጣሚ ሊያገኝ ይችላል።” የሰባት ልጆች አባት የሆነው ጆን እንደተናገረው ‘አጥር ግቢውን ማጽዳት ወይም ቤቱን ቀለም መቀባት እንኳን ቤተሰብ አንድ ላይ ሆኖ ከሠራው አስደሳች ሊሆን ይችላል’ ብሏል።

ቤተሰባችሁ ከዚህ ቀደም እንደዚህ ያሉትን ነገሮች አንድ ላይ ሆኖ የማይሠራ ከነበረ እናንተ ራሳችሁ ቅድሚያ ወስዳችሁ ለወላጆቻችሁ ሐሳብ አቅርቡ። ቤተሰባችሁ በአንድነት እንዲንሸራሸር ወይም አንዳንድ ነገሮችን እንዲሠራ ጥሩና ስሜት የሚያነቃቁ ሐሳቦችን ለማቅረብ ሞክሩ።

ይሁን እንጂ ራሳችሁን ለማስደሰት ሁልጊዜ የግድ ከሌሎች ጋር መሆን አያስፈልጋችሁም። አብረዋት የሚውሉትን ወጣቶች በጥንቃቄ የምትመርጠው ሜሪ ለብቻዋ በምታሳልፈው ጊዜ እንዴት መደሰት እንደምትችል ተምራለች። “ፒያኖና ቫዮሊን እጫወታለሁ። ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ እነዚህን የሙዚቃ መሣሪያዎች እለማመዳለሁ” ትላለች። በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ የምትገኝ መሊሳ የተባለች ሌላ ልጃገረድም በተመሳሳይ “አንዳንድ ጊዜ ተረቶችንና ግጥሞችን እየጻፍኩ ጊዜዬን አሳልፋለሁ” ትላለች። እናንተም እንደዚሁ ማንበብ፣ አናፂነት፣ ወይም የሙዚቃ መሣሪያ መጫወት የመሳሰሉትን ችሎታዎች በመለማመድ ጊዜያችሁን ውጤት ባለው ሥራ ላይ እንዴት ማዋል እንደምትችሉ ልትማሩ ትችላላችሁ።

ክርስቲያናዊ የመዝናኛ ፕሮግራሞች

አልፎ አልፎ ከወዳጆች ጋር ተገናኝቶ መጫወትም ያስደስታል። በብዙ አካባቢዎች ልትደሰቱ የምትችሉባቸው ጤናማ የሆኑ በርካታ እንቅስቃሴዎች አሉ። ቦሊንግ፣ ሸርተቴ፣ ብስክሌት መንዳት፣ ቤዝቦልና ቅርጫት ኳስ በሰሜን አሜሪካ የተለመዱ መዝናኛዎች ናቸው። አለበለዚያም ቤተ መዘክሮችን ወይም የአራዊት መጠበቂያ ሥፍራዎችን ልትጎበኙ ትችላላችሁ። ከሌሎች ክርስቲያን ወጣቶች ጋር ሆኖ ሙዚቃ ማዳመጥና ጤናማ የሆነ የቴሌቪዥን ፕሮግራም መመልከትም ተገቢ የሚሆንባቸው ጊዜያት አሉ።

ከዚህም በላይ ወላጆቻችሁ ቀደም ያለ ዝግጅት የተደረገበት የጊዜ ማሳለፊያ ፕሮግራም ለማዘጋጀት እንዲረዷችሁ ልትጠይቁ ትችላላችሁ። በእነዚህ ዝግጅቶች ላይ የቡድን ጨዋታዎችንና መዝሙሮችን የመሰሉ ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎች እንዲኖሩ በማድረግ አስደሳች ጊዜ አሳልፉ። ከጓደኞቻችሁ አንዳንዶቹ የሙዚቃ ችሎታ ካላቸው ምናልባት ትንሽ እንዲጫወቱላችሁ ልታደፋፍሩአቸው ትችሉ ይሆናል። ጥሩ የምግብ ዝግጅት እንዲኖር ማድረግም ለምታሳልፉት ጊዜ ጣዕም ይጨምርለታል፤ ይሁን እንጂ በጣም የተቀናጣ ወይም ውድ የሆነ ምግብ ማዘጋጀት አስፈላጊ አይደለም። ተጋባዦቹ የተለያዩ ምግቦች ይዘው ሊመጡ የሚችሉባቸው ጊዜያት ሊኖሩ ይችላሉ።

በአካባቢያችሁ ኳስ ለመጫወት ወይም ለመዋኘት የሚያስችል ቦታ ይኖራልን? ሽርሽር ለመሄድ ለምን እቅድ አታወጡም? እዚህም ላይ ቢሆን በማንም ላይ የገንዘብ ወጪ እንዳይበዛ የተለያዩ ቤተሰቦች ምግብ ይዘው ሊሄዱ ይችላሉ።

በነዚህ ዝግጅቶች ሁሉ ዋነኛው አስፈላጊ ነገር ልከኝነት ነው። ሙዚቃ አስደሳች እንዲሆን የጆሮ ታንቡር እስኪበጥስ ድረስ ጮክ ማለት አያስፈልገውም። ውዝዋዜም አስደሳች እንዲሆን መረን የለቀቀ ወይም ወሲባዊ ስሜት የሚያነሳሳ መሆን አያስፈልገውም። ከቤት ውጭ የሚደረጉ ጨዋታዎች የከረረ የፉክክር መንፈስ ሳይታይባቸው አስደሳች ሊሆኑ ይችላሉ። አንድ ወላጅ ግን “አንዳንድ ወጣቶች ለመደባደብ ትንሽ እስኪቀራቸው ድረስ የሚጨቃጨቁበት ጊዜ አለ” ብሏል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘እርስ በርስ መፎካከርን’ እንድታስወግዱ የሚሰጠውን ምክር በመከተል እንዲህ ዓይነቶቹ እንቅስቃሴዎች አስደሳች እንዲሆኑ አድርጉ።​— ገላትያ 5:​26

መጋበዝ የሚኖርባችሁ እነማንን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ለመላው የወንድማማቾች ማኅበር ፍቅር ይኑራችሁ” ይላል። (1 ጴጥሮስ 2:​17 አዓት) የመዝናኛ ፕሮግራማችሁ ለእኩዮቻችሁ ብቻ የተወሰነ እንዲሆን ለምን ታደርጋላችሁ? ሰፋ አድርጉትና የተለያየ ዕድሜ ያላቸውን ሰዎች እንዲያካትት አድርጉ። (ከ2 ቆሮንቶስ 6:​13 ጋር አወዳድሩ።) አንድ ወላጅ “በዕድሜ ገፋ ያሉት በአንዳንዶቹ እንቅስቃሴዎች መሳተፍ ባይችሉም መጥተው የሚካሄደውን ጨዋታ ቢመለከቱ ደስ ይላቸዋል” በማለት ገልጿል። ብዙውን ጊዜ በዕድሜ ተለቅ ያሉ ሰዎች መኖራቸው ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆኑ ለመከላከል ይረዳል። ይሁን እንጂ በማንኛውም የመዝናኛ ፕሮግራም ላይ ‘መላውን የወንድማማች ማኅበር’ መጋበዝ አይቻልም። ከዚህም በላይ የመዝናኛውን ፕሮግራም መቆጣጠር የሚቻለው የተጋባዦቹ ቁጥር አነስተኛ ሲሆን ነው።

ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችም እርስ በርስ በመንፈሣዊ ለመተናነጽ የሚቻልባቸው ጥሩ አጋጣሚዎች ናቸው። እውነት ነው፣ አንዳንድ ወጣቶች መንፈሳዊ ፕሮግራም የታከለበት የመዝናኛ ፕሮግራም አስደሳችነቱ እንደሚቀንስ ይሰማቸዋል። አንድ ክርስቲያን ወጣት “ለመዝናናት በምንሰባሰብበት ጊዜ ‘ቁጭ በሉና መጽሐፍ ቅዱሳችሁን ይዛችሁ የመጽሐፍ ቅዱስ ጨዋታ ተጫወቱ’ እንባላለን” በማለት አማሯል። ይሁን እንጂ መዝሙራዊው “በይሖዋ ሕግ የሚደሰት ሰው . . . ደስተኛ ነው” ብሏል። (መዝሙር 1:​1, 2 አዓት) በመሆኑም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያተኮሩ ውይይቶች፣ ወይም ጨዋታዎች በጣም አስደሳች ሊሆኑ ይችላሉ። ምናልባት በጨዋታው ይበልጥ መሳተፍ እንድትችሉ የቅዱሳን ጽሑፎች እውቀታችሁን ማሻሻል ያስፈልጋችሁ ይሆናል።

አብረዋችሁ ከተሰባሰቡት መካከል አንዳንዶቹ እንዴት ክርስቲያኖች እንደሆኑ ተሞክሮአቸውን እንዲናገሩ ማድረግ ሌላው አማራጭ ነው። አለበለዚያም አንዳንዶች አስቂኝ ቀልዶችንና ታሪኮችን እንዲናገሩ በመጋበዝ ለስብሰባችሁ ሞቅታና ሳቅ ልትጨምሩ ትችላላችሁ። ብዙውን ጊዜም እነዚህ ቀልዶችና ታሪኮች ጠቃሚ ትምህርት ያስተምራሉ። በዚህ መጽሐፍ አንዳንድ ምዕራፎች ላይ የተመሠረተም በጣም አስደሳች የሆነ የጋራ ውይይት ማድረግ ይቻላል።

መዝናኛን በሚዛናዊነት መያዝ

ኢየሱስ ክርስቶስ አልፎ አልፎ መዝናናትን የሚጠላ ሰው አልነበረም። መጽሐፍ ቅዱስ በቃና በተደረገ ሠርግ ላይ ተገኝቶ እንደነበረ ይናገራል። በሠርጉ ላይ ደግሞ ምግብ፣ ሙዚቃ፣ ውዝዋዜና የሚያንጽ ጭውውት እንደነበረ አያጠራጥርም። እንዲያውም ኢየሱስ በተአምራዊ መንገድ ወይን ጠጅ በማቅረብ የሠርጉ ድግስ የተሳካ እንዲሆን አስተዋጽኦ አድርጓል!​— ዮሐንስ 2:​3–11

ይሁን እንጂ የኢየሱስ ሕይወት በድግስ ላይ ብቻ ያተኮረ አልነበረም። የሚበዛውን ጊዜውን ያሳለፈው መንፈሳዊ ነገሮችን በመከታተልና ለሰዎች የአምላክን ፈቃድ በማስተማር ነበር። “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 4:​34) የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ለኢየሱስ ጊዜያዊ የሆነ መዝናኛ ከሚያስገኘው ደስታ እጅግ በጣም የላቀና ዘላቂ የሆነ ደስታ አምጥቶለታል። በአሁኑ ጊዜም ‘በጌታ ሥራ ብዙ’ የሚሠራ ነገር አለ። (1 ቆሮንቶስ 15:​58፤ ማቴዎስ 24:​14) ይሁን እንጂ አልፎ አልፎ መዝናኛ እንደሚያስፈልጋችሁ ሲሰማችሁ ሚዛናዊና ጤናማ በሆነ መንገድ ተዝናኑ። አንድ ጸሐፊ እንደገለጸው:- “ሕይወት ሁልጊዜ በሥራና በውጥረት የተጨናነቀ ሊሆን አይችልም። እንዲህ ቢሆን ኖሮ በድካም ተዝለፍልፋችሁ ትወድቁ ነበር!”

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 እውነተኛ ስሟ አይደለም።

የመወያያ ጥያቄዎች

◻ አንዳንድ ክርስቲያን ወጣቶች በዓለም ወጣቶች የሚቀኑት ለምንድን ነው? እናንተስ እንዲህ ተሰምቶአችሁ ያውቃልን?

◻ አምላክ ለወጣቶች ጠባያቸውን በተመለከተ ምን ማስጠንቀቂያ ይሰጣል? ይህስ የመዝናኛ አመራረጣቸውን እንዴት ሊነካ ይገባል?

◻ የአምላክን ሕግና ሥርዓት በሚጥሱ ወጣቶች መቅናት ሞኝነት የሆነው ለምንድን ነው?

◻ ጤናማ በሆኑ መዝናኛዎች (1) ከቤተሰብ አባሎች ጋር፣ (2) ለብቻችሁና (3) ከመሰል ክርስቲያን ወጣቶች ጋር በመሆን መደሰት የሚቻልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?

◻ ኢየሱስ ክርስቶስ መዝናኛን በተመለከተ ጥሩ ምሳሌ የተወልን እንዴት ነው?

[በገጽ 297 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“በዚያ በኩል በምናልፍበት ጊዜ በከፍተኛ ድምፅ በሚጮኸው ዘፈንና በሚንቦገቦገው መብራት በመማረክ ተንጠራርቼ በመስኮቱ በኩል እመለከታቸውና ምን ዓይነት የደስታ ጊዜ እንደሚያሳልፉ በማሰብ እጓጓ ነበር”

[በገጽ 302 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“አንድ ሰው ሐሺሽ አመጣ። በኋላም የሚያሰክር መጠጥ መጣ። ነገሩ ሁሉ ትርምስምሱ የወጣው በዚህ ጊዜ ነበር”

[በገጽ 299 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመጽሐፍ ቅዱስን ሥርዓቶች የሚከተሉ ወጣቶች በእርግጥ ብዙ ደስታ እያመለጣቸው ነውን?

[በገጽ 300 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በትርፍ ጊዜያችን የሚያስደስቱንን ነገሮች መሥራት ጊዜአችንን ጤናማ በሆነ መንገድ የምናሳልፍበት ነው

[በገጽ 301 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ክርስቲያኖች ለመዝናናት አንድ ላይ የሚሰበሰቡባቸው ጊዜያት ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎች የሚደረጉበትና የተለያየ ዕድሜ ያላቸው የሚገኙበት ሲሆን ይበልጥ አስደሳች ይሆናል