በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የማነበው ነገር ሊጎዳኝ ይችላልን?

የማነበው ነገር ሊጎዳኝ ይችላልን?

ምዕራፍ 35

የማነበው ነገር ሊጎዳኝ ይችላልን?

ንጉሥ ሰሎሞን “ብዙ መጻሕፍትን ማድረግ ፍጻሜ የለውም፣ እጅግም ምርምር ሰውነትን ያደክማል” በማለት አስጠንቅቋል። (መክብብ 12:​12) ሰሎሞን መራጮች እንድንሆን እንጂ ማንበብ እንድንተው መምከሩ አልነበረም።

ርኔ ዴካርት የተባለው የአሥራ ሰባተኛው መቶ ዘመን ፈረንሳዊ ፈላስፋ እንዲህ ብሏል:- “አንድ ሰው ጥሩ መጻሕፍትን በሚያነብበት ጊዜ በቀድሞ ዘመን ከኖሩ ጨዋ ሰዎች ጋር እንደሚነጋገር ሊቆጠር ይችላል። እንዲያውም ደራሲው በጣም ምርጥ የሆኑትን አስተሳሰቦቹን የሚገልጽበት ልዩ ጭውውት ነው ሊባል ይችላል።” ይሁንና ሁሉም ደራሲዎች ‘ልናነጋግራቸው የሚገቡ’ አይደሉም። አስተሳሰባቸውም ቢሆን “የጨዋ ነው” ሊባል የሚችል አይደለም።

ስለዚህ “ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል” የሚለው አዘውትሮ የሚጠቀስ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት እዚህም ላይ ይሠራል። (1 ቆሮንቶስ 15:​33) አዎን፣ አብረህ የምትውላቸው ሰዎች ባሕርይህን ሊቀርጹ ይችላሉ። ያንተ የራስህ ድርጊት፣ ንግግር፣ አስተሳሰብም እንኳን ሳይቀር እንደ እርሱ መሆን እስኪጀምር ድረስ በርካታ ጊዜ አብሮህ ያሳለፈ ጓደኛ አለህን? መጽሐፍ ማንበብም ከመጽሐፉ ደራሲ ጋር ብዙ ሰዓቶችን እንደማሳለፍ የሚቆጠር ነው።

በመሆኑም በማቴዎስ 24:​15 ላይ የተገለጸውን መሠረታዊ ሥርዓት እዚህ ላይ ማንሳት ተገቢ ነው:- እሱም “አንባቢው ያስተውል” ይላል። የምታነቡትን ነገር ማመዛዘንና መመርመር ተማሩ። ሰዎች ሁሉ የተወሰነ አድሎአዊ አመለካከት ስለሚኖራቸው ትክክለኛውን ነገር በሐቀኝነት አያቀርቡም። ስለዚህ የምታነቡትን ወይም የምትሰሙትን ነገር ሁሉ ያለአንዳች ጥያቄ አትቀበሉ:- “የዋህ [“ተሞክሮ የሌለው” አዓት ] ቃልን ሁሉ ያምናል፤ ብልህ ግን አካሄዱን ይመለከታል።”​— ምሳሌ 14:​15

በተለይ ፍልስፍና ነክ ጽሑፎችን ስለ ማንበብ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋችኋል። ለምሳሌ ለወጣቶች የሚዘጋጁ መጽሔቶች ከተቃራኒ ጾታዎች ጋር ተቀጣጥሮ ከመጫወት ጀምሮ ከጋብቻ በፊት ወሲብ እስከመፈጸም ባሉ የተለያዩ ጉዳዮች ምክር ይሰጣሉ። እነዚህ ምክሮች ግን አንድ ክርስቲያን ሊከተላቸው የሚገቡ ላይሆኑ ይችላሉ። ከባድ ስለሆኑ የፍልስፍና ጥያቄዎች የሚናገሩ መጻሕፍትን ማንበብስ?

መጽሐፍ ቅዱስ “እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፣ . . . በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ” በማለት ይመክራል። (ቆላስይስ 2:​8) መጽሐፍ ቅዱስና አሁን እንደምታነቡት ያሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች ከሁሉ የበለጠ ምክር ይሰጣሉ።​— 2 ጢሞቴዎስ 3:​16

ስለ ፍቅር የሚናገሩ ልብ ወለድ መጻሕፍት ቢነበቡ ጉዳት የላቸውምን?

የፍቅር ልብ ወለድ መጻሕፍትን ማንበብ በዩናይትድ ስቴትስ ለሚኖሩ ከ20 ሚልዮን በላይ ለሆኑ ሰዎች ሱስ ሆኖባቸዋል። እርግጥ የመፈቃቀርንና የመጋባትን ፍላጎት በወንዶችና በሴቶች ውስጥ እንዲኖር ያደረገው አምላክ ራሱ ነው። (ዘፍጥረት 1:​27, 28፤ 2:​23, 24) ስለዚህ በልብ ወለድ ታሪኮች ውስጥ ፍቅር ዋነኛ ሥፍራ መያዙ የሚያስደንቅ አይደለም። ይህም በራሱ መጥፎ ላይሆን ይችላል። እንዲያውም አንዳንድ የፍቅር ልብ ወለድ መጽሐፎች በጥሩ ሥነ ጽሑፍነታቸው አንቱታ አትርፈዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ የቆዩ ልብ ወለዶች በዘመናዊ መለኪያ ሲለኩ በስሜት ቀስቃሽነታቸው ለዘብ ያሉ እንደሆኑ ተደርገው ስለሚቆጠሩ የልብ ወለድ ጸሐፊዎች አዲስ ዓይነት የአጻጻፍ ስልት መከተል ይበልጥ አትራፊ ሆኖ አግኝተውታል። አንዳንዶቹ ለትረካቸው ትዕይንታዊ መልክና ስሜት ለመስጠት አሁንም ታሪካዊ ወይም የመካከለኛው ዘመን መቼት ይጠቀማሉ። ሌሎች ደግሞ የአጻጻፍ ዘዴያቸውና የሚጠቀሙበት መቼት ዘመናዊ ነው። የሆነ ሆኖ እነዚህ ዘመናዊ የፍቅር ልብ ወለድ ጸሐፊዎች ጥቃቅን ለውጦችን ያደርጉ እንደሆነ እንጂ የሚከተሉት ስልት አንድ ዓይነትና በቅድሚያ ሊታወቅ የሚችል ነው። ዋና ገጸባሕርያት የሆኑት ወንዶችና ሴቶች እምቡጥ በሆነው ፍቅራቸው ላይ የሚደቀኑባቸውን ከባድ እንቅፋቶች በአሸናፊነት ይወጣሉ።

በተለመደው የገጸ ባሕርይ አሳሳል ወንዱ ዋና ገጸ ባሕርይ በራሱ የሚተማመን፣ ጉልበተኛ፣ አልፎ ተርፎም እብሪተኛ የሆነ ሰው ነው። ሴቷ ዋና ገጸ ባሕርይ ግን ሆደ ባሻና ስሜቷ በቀላሉ የሚነካ፣ ብዙውን ጊዜም ዕድሜዋ ከወንዱ በ10 ወይም በ15 ዓመት የምታንስ ናት። ወንዱ ገጸ ባሕርይ በንቀት ዓይን የሚመለከታት ቢሆንም እሷ ግን እጅግ ስለምትወደው ከእርሱ መራቅ አይሆንላትም።

ብዙውን ጊዜ ሴቷን ገጸ ባሕርይ የሚያሽኮረምም የዋናው ገጸ ባሕርይ ተቀናቃኝ ይኖራል። ይኼኛው አፍቃሪዋ ደግና አሳቢ ቢሆንም ስሜቷን የማይቀሰቅስ ወይም ሊማርካት የማይችል ይሆናል። ስለዚህ በማራኪ መልኳ በመጠቀም ምንም ስሜት ያልነበረውን ጀግና አንበርክካ ለእርሷ ያለውን ዘላቂ ፍቅር በይፋ የሚያውጅ ልዝብ ነፍስ እንዲሆን ታደርገዋለች። ያለፉት አለመግባባቶች ሁሉ ተወግደው አስደሳች ጋብቻ መሥርተው በደስታ ይኖራሉ . . .

ፍቅር በፍቅር ታሪኮች ላይ እንደሚቀርበው ነውን?

እንዲህ ዓይነቶቹን በግምታዊ አስተሳሰብ ያሸበረቁ ታሪኮች ማንበብ በእውኑ ዓለም ያለውን ሁኔታ እንዳታዩ ዓይናችሁን ሊጋርድባችሁ ይችላልን? በ16 ዓመት ዕድሜዋ የፍቅር ልብ ወለዶችን ማንበብ የጀመረችው ቦኒ “የምመኘው ረዥም፣ ጠይምና ውብ፣ የኃይለኛነት ባሕርይ ያለው ስሜት የሚቀሰቅስ ወጣት ወንድ ለማግኘት ነበር” በማለት ታስታውሳለች። “ከአንድ ወጣት ጋር ተቀጣጥሬ ስጫወት ሊስመኝ ወይም ሊዳብሰኝ ካልፈለገ ደግና አሳቢ ቢሆንም እንኳ ለዛ ቢስና አሰልቺ ይሆንብኝ ነበር። የምመኘው በልብ ወለዶች ውስጥ ያነበብኩትን ዓይነት የስሜት መቀስቀስ ለማግኘት ነበር” በማለት አምናለች።

ቦኒ ካገባች በኋላም የፍቅር ታሪኮችን ማንበብ ቀጠለች። ስለዚህ እንዲህ ትላለች:- “ጥሩ ቤትና ቤተሰብ ነበረኝ። ግን ለምን እንደሆነ እንጃ አላረካኝም። . . . በልብ ወለድ መጻሕፍት ውስጥ ማራኪ በሆነ መንገድ የሚገለጸውን ጀብዱ፣ የስሜት መቀስቀስና ፍንደቃ ለማግኘት እመኝ ነበር። ትዳሬ የጎደለው ነገር እንዳለ ይሰማኝ ነበር።” ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ባል ለሚስቱ ከመልክና “ከስሜት መቀስቀስ” የበለጠ ነገር ማድረግ እንደሚኖርበት እንድትገነዘብ ረድቷታል። መጽሐፍ ቅዱስ “እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤ ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና፣ ነገር ግን . . . ይመግበዋል ይከባከበውማል” ይላል።​— ኤፌሶን 5:​28, 29

በፍቅር ልብ ወለዶች ውስጥ ታሪኩ አብዛኛውን ጊዜ ጥሩ ፍጻሜ የሚያገኝና የሚነሱ አለመግባባቶች በቀላሉ የሚፈቱ መሆናቸውስ? በገሐዱ እውነተኛ ዓለም ከሚያጋጥሙ ሁኔታዎች በጣም የተለዩ ናቸው። ቦኒ ስታስታውስ “ከባሌ ጋር አለመግባባት ሲያጋጥመኝ ፊት ለፊት ተነጋግሬ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ የልብ ወለድ ታሪክ ገጸ ባሕርይ የተጠቀመችውን ብልሃት እጠቀማለሁ። ባሌ የልብ ወለዱ ወንድ ገጸ ባሕርይ እንዳደረገው ሳያደርግ ከቀረ አኮርፋለሁ” ብላለች። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ ለሚስቶች “ሚስቶች ሆይ፣ በጌታ እንደሚገባ ለባሎቻችሁ ተገዙ” በማለት የሚሰጠው ምክር ይበልጥ ተግባራዊ ሊሆን አይችልምን?​— ቆላስይስ 3:​18

ወሲባዊ ይዘት

በወጣቶች ዘንድ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያላቸው ስለ ወሲብ ፍርጥርጥ አድርገው የሚገልጹ የፍቅር ልብ ወለድ መጻሕፍት ናቸው። እነዚህ መጻሕፍት በአንዳንድ ከተሞች በሕዝብ መጻሕፍት ቤቶች ውስጥ ይገኛሉ። ታዲያ እንደነዚህ ያሉት መጻሕፍት ሊጎዱአችሁ ይችላሉን? የ18 ዓመቷ ካረን “መጻሕፍቱ በእርግጥ ኃይለኛ የሆነ ወሲባዊ ስሜትና ጉጉት ቀስቅሰውብኛል። ዋናዋ ገጸ ባሕርይ ከዋናው ገጸ ባሕርይ ጋር ሩካቤ ሥጋ ስትፈጽም የተሰማት የደስታና የፍንደቃ ስሜት እኔም እነዚያን ስሜቶች እንድመኝ አድርገውኛል። ስለዚህ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ለመጫወት በምቀጣጠርበት ጊዜ” ትላለች በመቀጠል፣ “እነዚያን ስሜቶች በራሴ ላይ ለማየት ሞከርኩ። ይህም ዝሙት ወደመፈጸም አደረሰኝ።” ይሁን እንጂ የተሰማት ስሜት በፍቅር ልብ ወለድ ታሪክ ውስጥ የተገለጸችው ዋና ገጸ ባሕርይ የተሰማትንና ስታልመው የነበረውን የመሰለ ነበርን? ካረን የተገነዘበችው እውነት “እነዚህ ስሜቶች የጸሐፊዎቹ አእምሮ የፈጠሯቸው እንጂ በእውነተኛው ዓለም የሌሉ ስሜቶች” መሆናቸውን ነው።

በእርግጥም የአንዳንዶቹ ደራሲዎች ዓላማ ወሲባዊ ቅዠቶችን መቀስቀስ ነው። አንድ የመጻሕፍት አሳታሚ ለፍቅር ልብ ወለድ ደራሲያን የሰጠውን መመሪያ ተመልከቱ:- “ወሲባዊ ትረካዎች ዋናው ገጸ ባሕርይ በአሳሳሙና በአደባበሱ በሚቀሰቅሰው ፍትወትና ወሲባዊ ስሜት ላይ ማተኮር አለባቸው።” በተጨማሪም ጸሐፊዎቹ የፍቅር ታሪኮች “በአንባቢዎች ላይ የስሜት መነሳሳት፣ ውጥረትና ጥልቅ የሆነ የፍትወት መቀስቀስ የሚያስከትሉ መሆን ይኖርባቸዋል” የሚል ምክር ተሰጥቷቸዋል። እንዲህ ዓይነቶቹን ጽሑፎች ማንበብ አንድ ሰው “በምድር ያሉቱን ብልቶቻችሁን ግደሉ፣ እነዚህም ዝሙትና ርኩሰት ፍትወትም ክፉ ምኞትም ጣዖትንም ማምለክ የሆነ መጎምጀት ነው” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር እንዲከተል የሚረዱ እንዳልሆኑ ግልጽ ነው።​— ቆላስይስ 3:​5

መራጭ መሆን

እንግዲያስ ከሥነ ምግባር ውጭ የሆኑ ስሜቶችን ወይም በእውኑ ሕይወት የማይገኙ ፍላጎቶችን የሚቀሰቅሱ ጽሑፎችን ማስወገድ በጣም የተሻለ ይሆናል። የንባብ አድማሳችሁን ሰፋ በማድረግ እንደ ታሪክ፣ ወይም ሳይንስ የመሳሰሉትን ሌሎች መጻሕፍት ለማንበብ ለምን አትሞክሩም? አዝናኝ ብቻ ሳይሆን ትምህርት ሰጪ የሆኑ አንዳንድ ልብ ወለድ ጽሑፎችም ስላሉ ሁሉም ልብ ወለድ መጽሐፍ መጥፎ ነው ማለት አይቻልም። ይሁን እንጂ አንድ ልብ ወለድ መጽሐፍ ወሲባዊ ስሜትን፣ ጠበኝነትን ወይም ምትሐታዊ ተግባራትን የሚያጎላ ወይም ጨካኝና ስግብግብ የሆኑ ገጸ ባሕርያትን ከፍ አድርጎ የሚገልጽ ከሆነ እንዲህ ዓይነቱን ጽሑፍ በማንበብ ጊዜያችሁን ማባከን ይኖርባችኋልን?

ስለዚህ ጥንቃቄ አድርጉ። አንድን መጽሐፍ ከማንበባችሁ በፊት ሽፋኑንና ውስጠኛ ልባሱን መርምሩ። በመጽሐፉ ላይ አንዳች ተነቃፊ ነገር ይኖር እንደሆነ በጥንቃቄ እዩ። ይህን ሁሉ ጥንቃቄ ካደረጋችሁ በኋላ መጽሐፉ መጥፎ ሆኖ ካገኛችሁት ማንበባችሁን ለማቆም የሚያስችል ጥንካሬ ይኑራችሁ።

መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማንበብ ግን ይጠቅማችኋል እንጂ አይጎዳችሁም። ለምሳሌ ያህል አንዲት ጃፓናዊት ልጃገረድ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ የብዙ ወጣቶች ችግር ከሆነው ወሲባዊ ጉዳዮችን በአእምሮ ከማውጠንጠን ችግር እንደጠበቃት ትናገራለች። “መጽሐፍ ቅዱስን ከመኝታዬ ጎን አስቀምጥና ከመተኛቴ በፊት ሥራዬ ብዬ አነባለሁ” ትላለች። “አእምሮዬ ስለወሲብ ወደማሰብ የሚያዘነብለው ብቻዬን ስሆንና የምሠራው ነገር በማይኖረኝ ሰዓት (ለምሳሌ በመኝታ ሰዓት) ነው። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ በእርግጥ ይረዳኛል!” አዎን፣ ታሪካቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጻፈላቸው ሰዎች ጋር “መነጋገር” መቻል እውነተኛ የሆነ ሥነ ምግባራዊ ጥንካሬ ሊሰጣችሁና ደስታችሁን በእጅጉ ሊጨምርላችሁ ይችላል።​— ሮሜ 15:​4

የመወያያ ጥያቄዎች

◻ በምታነቡት ነገር ረገድ መራጮች መሆን ያለባችሁ ለምንድን ነው?

◻ ስለ ፍቅር የሚናገሩ ልብ ወለድ መጻሕፍት ለብዙ ወጣቶች በጣም ማራኪ የሆኑት ለምንድን ነው? ይሁን እንጂ እነዚህን መጻሕፍት ማንበብ ምን ዓይነት አደጋዎች ያስከትላል?

◻ ጥሩ የሚነበብ ጽሑፍ መምረጥ የምትችሉት እንዴት ነው?

◻ መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ከማንበብ የሚገኙ አንዳንድ ጥቅሞች ምንድን ናቸው?

[በገጽ 287 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ጥሩ ቤትና ቤተሰብ ነበረኝ፤ ግን ለምን እንደሆነ እንጃ አላረካኝም . . . በልብ ወለድ መጻሕፍት ውስጥ ማራኪ በሆነ መንገድ የሚገለጸውን ጀብዱ፣ ደስታና ፍንደቃ እመኝ ነበር። ትዳሬ የጎደለው ነገር እንዳለ ይሰማኝ ነበር”

[በገጽ 283 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ መጻሕፍት ስላሉ መራጮች መሆን አለባችሁ

[በገጽ 285 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

የፍቅር ልብ ወለዶችን ማንበብ የሚመስጥ ሊሆን ይችላል፤ ይሁን እንጂ ስለ ፍቅርና ስለ ጋብቻ ጤናማ የሆነ አመለካከት እንዲኖራችሁ ያስተምራሉን?