በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነተኛ ጓደኞች ላፈራ የምችለው እንዴት ነው?

እውነተኛ ጓደኞች ላፈራ የምችለው እንዴት ነው?

ምዕራፍ 8

እውነተኛ ጓደኞች ላፈራ የምችለው እንዴት ነው?

“በዚህ አካባቢ ስምንት ዓመት ሙሉ ትምህርት ቤት እየተመላለስኩ ስማር ቆይቻለሁ። ይሁን እንጂ አንድም ጓደኛ ላገኝ አልቻልኩም! አንድም ጓደኛ የለኝም።” እንዲህ ሲል እሮሮ ያሰማው ሮኒ የሚባል አንድ ወጣት ነው። ምናልባት እናንተም በተመሳሳይ ጓደኛ በማፍራት ረገድ ፍሬ ቢስ እንደሆናችሁ የተሰማችሁ ጊዜ ይኖር ይሆናል። ይሁን እንጂ እውነተኛ ጓደኞች ምንድን ናቸው? እውነተኛ ጓደኛ ለማግኘት የሚቻለውስ ምን በማድረግ ነው?

አንድ ምሳሌ “ወዳጅ ሁልጊዜ ይወድዳል፤ በመከራ ጊዜም ወንድም ይኖራል” ይላል። (ምሳሌ 17:​17 ዘ ባይብል ኢን ቤዚክ ኢንግሊሽ) ይሁን እንጂ የጓደኛ ጥቅም ችግር ተካፋይ መሆኑ ብቻ አይደለም። ማርቪያ የተባለች ወጣት እንደሚከተለው ትላለች:- “አንዳንድ ጊዜ ጓደኛ የምትሉት ሰው ወደ ችግር ያስገባችሁና ‘ይህ እንደሚደርስብህ አውቄ ነበር፤ ግን ስለ ፈራሁ አልነገርኩህም’ ይላችኋል። እውነተኛ ጓደኛ ግን ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ ስትጓዙ በሚያይበት ጊዜ የሚነግራችሁ ነገር እንደማያስደስታችሁ ቢያውቅም እንኳን ስህተታችሁን ለማስተካከል የምትችሉበት ጊዜ ከማለፉ በፊት አስቀድሞ ይነግራችኋል” በማለት ትናገራለች።

ታዲያ አንድ ሰው ስለሚያስብላችሁ እውነቱን ቢነግራችሁ አኩርፋችሁ ትርቁታላችሁን? ምሳሌ 27:​6 (የ1980 ትርጉም) “ወዳጅ ቢመታህም እንኳ ለመልካም ነው፤ ጠላት ግን አቅፎ ቢስምህም አትመነው” ይላል። ስለዚህ ለጓደኝነት የምትፈልጉት ሰው በአስተሳሰቡና በንግግሩ ቀጥተኛ የሆነ ሰው መሆን ይኖርበታል።

አስመሳይ ጓደኞችን ከእውነተኞቹ መለየት

የ23 ዓመቷ ፔጊ “ጥሩ ሰዎች እንድትሆኑ የሚያደርጓችሁ ሁሉም ‘ጓደኞች’ እንዳልሆኑ የራሴ ሕይወት ማስረጃ ነው” ትላለች። ፔጊ በአፍላ ጉርምስና ዘመኗ ከቤት እንድትወጣ ተገድዳ ነበር። ይሁን እንጂ ቢልና ሎይ የሚባሉ የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ ባልና ሚስት ጓደኞች ሆነዋት ነበር። ለፔጊም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመሩላት። “ከእነርሱ ጋር ያሳለፍኳቸው ወራት እውነተኛ ደስታ፣ እርካታና ሰላም የሰፈነባቸው ነበሩ” ትላለች ፔጊ። ሆኖም ከተዋወቀቻቸው አንዳንድ ወጣቶች ጋር ለመሆን መረጠችና ቢልንና ሎይን ተወቻቸው።

ፔጊ በመቀጠል “ከአዳዲሶቹ ‘ጓደኞቼ’ ብዙ ነገር ተማርኩ፤ የሙዚቃ ማጫወቻዎችን መስረቅ፣ የተጭበረበሩ ቼኮችን መመንዘር፣ ማሪዋና ማጨስንና በመጨረሻም በየቀኑ 200 ዶላር የሚጠይቅብኝን የአደንዛዥ ዕፅ ሱሴን ለማርካት እንዴት ገንዘብ ማግኘት እንደምችል ተማርኩ” በማለት ፔጊ ትዘረዝራለች። በ18 ዓመትዋ የምትፈልጋቸውን አደንዛዥ ዕፆች በሙሉ በነጻ ከሚሰጣት ሬይ የሚባል አንድ ወጣት ጋር ተዋወቀች። “አሁን ከችግር ተላቀቅሁ ብዬ አሰብኩ። ከእንግዲህ መስረቅና ማጭበርበር አያስፈልገኝም” ብላ አስባ ነበር። ይሁን እንጂ ሬይ ዝሙት አዳሪነትን አስለመዳት። በመጨረሻም ፔጊ ከከተማውና ከወሮበላ “ጓደኞቿ” ሸሽታ ሄደች።

ፔጊ በአዲሱ መኖሪያዋ ሳለች አንድ ቀን ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ሊያነጋግሯት መጡ። “ላቅፋቸው ስጠጋ ምክንያቱ ስላልገባቸው የተደናገጡትን ሁለት ሴቶች ስስም የደስታ እንባ በጉንጬ ላይ ይወርድ ነበር” ትላለች ፔጊ። “የቀድሞ ‘ጓደኞቼ’ ግብዝነት በጣም አስጠልቶኝ ነበር። እውነተኞቹ ሰዎች ግን እነዚህ ነበሩ።” ፔጊ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቷን እንደገና ቀጠለች።

ይሁንና ሕይወቷን ከአምላክ መንገዶች ጋር ማስማማት ቀላል አልሆነላትም። በተለይ ማጨስ ለማቆም በጣም ከብዷት ነበር። ይሁን እንጂ ምሥክር የሆነች ጓደኛዋ “ካጨስሽ በኋላ ከመጸለይና ይቅርታ ከመለመን ይልቅ አስቀድመሽ የማጨስ ፍላጎት ሲመጣብሽ ኃይል እንዲሰጥሽ ለምን አትጸልይም?” ብላ መከረቻት። “ይህ በደግነት የተሰጠ ተግባራዊ ምክር ጠቅሞኛል። . . . ከብዙ ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በውስጤ ንጹሕ እንደሆንኩ ተሰማኝና ራስን ማክበር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ተረዳሁ” ትላለች ፔጊ።

የፔጊ ተሞክሮ በምሳሌ 13:​20 ላይ የሚገኙትን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት እውነተኛነት ያጎላል:- “ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል።” ፔጊ ስትናገር “አምላክን ከሚወዱ ከእነዚያ ሰዎች [ቢልና ሎይ] ጋር የነበረኝን ጓደኝነት አጥብቄ ይዤ ቢሆን ኖሮ አሁን አስቀያሚ ትዝታ የሆኑብኝ ነገሮች ሁሉ አይደርሱብኝም ነበር” ትላለች።

ጓደኛ ማግኘት

አምላክን የሚወዱ ጓደኞች ልታገኙ የምትችሉት የት ነው? በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ነው። ጓደኛ ስትመርጡ እምነት እንዳላቸው በአፍ ብቻ የሚናገሩትን ሳይሆን እምነታቸውንና ለአምላክ ማደራቸውን የሚያስረዳ ተግባር የሚፈጽሙትን ወጣቶች ፈልጉ። (ከያዕቆብ 2:​26 ጋር አወዳድሩ።) እንደዚህ ያሉ ወጣቶች ማግኘት አስቸጋሪ ከሆነባችሁ በዕድሜ ከሚበልጧችሁ ክርስቲያኖች ጋር ተዋወቁ። የዕድሜ ልዩነት ለመወዳጀት ዕንቅፋት መሆን የለበትም። መጽሐፍ ቅዱስ በዳዊትና በዮናታን መካከል የነበረውን በአርአያነት ሊጠቀስ የሚችል ወዳጅነት ይነግረናል። ዮናታን ደግሞ ዳዊትን ሊወልደው በሚያስችል ዕድሜ ይበልጠው ነበር!​— 1 ሳሙኤል 18:​1

ይሁንና ወዳጅነት ልትጀምሩ የምትችሉት እንዴት ነው?

ስለ ሌሎች ሁኔታ ማሰብ

ኢየሱስ ክርስቶስ ለእርሱ ሲሉ ለመሞትም እንኳን ፈቃደኞች የሆኑ ጥሩ ወዳጆች ነበሩት። ለምን? መጀመሪያ ነገር ኢየሱስ ስለ ሰዎች ሁኔታ ያስብ ነበር። ለችግራቸው ይደርስላቸውና ይረዳቸው ነበር። በሰዎች ችግር ገብቶ ለመርዳት ‘ይፈልግ’ ነበር። (ማቴዎስ 8:​3) በእርግጥም ስለ ሌሎች ሁኔታ ማሰብ ወዳጆችን ለማፍራት የሚያስችል የመጀመሪያ እርምጃ ነው።

ለምሳሌ ያህል ዴቪድ የተባለ ወጣት “ለሰዎች እውነተኛ ፍቅር ስላለውና ስለ ሌሎች ሁኔታ የሚያስብ በመሆኑ” ጥሩ ወዳጆችን በማፍራት እንደተሳካለት ይናገራል። ዴቪድ በመቀጠል “አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች አንዱ የሰውዬውን ስም ማወቅ ነው። ሰዎች ብዙውን ጊዜ ስለ እነርሱ አስባችሁ ስማቸውን ለማስታወስ በመቻላችሁ ይደነቃሉ። በዚህም ምክንያት አንዳንድ ያጋጠሟቸውን ነገሮች ወይም ችግሮች ያካፍሏችሁና ወዳጅነት ይመሠረታል” ብሏል።

ይህ ማለት ግን ለታይታ ብቻ ጠብ እርግፍ ማለት አለባችሁ ማለት አይደለም። ኢየሱስ “በልቡ ትሑት” ነበረ እንጂ ይታወቅልኝ ወይም ልታይ ልታይ የሚል ሰው አልነበረም። (ማቴዎስ 11:​28, 29) ሰዎችን የሚስበው ለእነርሱ እውነተኛ ስሜት ማሳየት ነው። ብዙውን ጊዜ ምግብ አብሮ መብላት ወይም ሥራ ማገዝ የመሳሰሉ ጥቃቅን ነገሮች ጥልቅ ወዳጅነት ለመገንባት ሊያገለግሉ ይችላሉ።

እንዴት እንደምትሰሙ”

ኢየሱስ “እንዴት እንደምትሰሙ ተጠንቀቁ” በማለት አሳስቧል። (ሉቃስ 8:​181980 ትርጉም) ኢየሱስ ይህን ሲናገር በአእምሮው ይዞት የነበረው የአምላክን ቃል የማዳመጥን ጥቅም ቢሆንም መሠረታዊ ሥርዓቱ ከሰዎች ጋር ያለንን ዝምድና ስለ ማዳበርም ይሠራል። ጥሩ ወዳጅነት ለማዳበር ጥሩ አድማጭ መሆን ያስፈልጋል።

ሌሎች የሚናገሩትን ነገር ለማዳመጥ ልባዊ ፍላጎት ካሳየን አብዛኛውን ጊዜ ወደ እኛ ይቀርባሉ። ይህን ለማድረግ ግን ‘የራሳችሁን ጥቅም [ምናልባትም እናንተ ለመናገር የምትፈልጉትን] ብቻ ሳይሆን የሌላውንም ሰው ጥቅም ማሰብን’ ይጠይቃል።​— ፊልጵስዩስ 2:​41980 ትርጉም

በወዳጅነታችሁ ጽኑ

ኢየሱስ ወዳጆቹን ፈጽሞ አልከዳም። ‘እስከ መጨረሻው ወዷቸዋል።’ (ዮሐንስ 13:​1) ጎርዶን የሚባል አንድ ወጣት ለወዳጆቹ ተመሳሳይ አመለካከት አለው። “የጓደኛ ዋና ተፈላጊ ባሕርይ ሁልጊዜ ከእናንተ ጎን ቆሞ መገኘቱ ነው። ችግር በሚያጋጥማችሁ ጊዜ አይለያችሁምን? ሰዎች ስለ እኔም ሆነ ስለ ጓደኛዬ መጥፎ ነገር ሲናገሩብን አንዳችን ለሌላው እንቆማለን። በእርግጥ የማንነጣጠል ሆነናል። ይሁን እንጂ አንዳችን ለሌላው የምንቆመው ትክክለኛ ነገር ሲሆን ብቻ ነው” ብሏል።

አስመሳይ ጓደኞች ግን አንድ ላይ በማይሆኑበት ጊዜ ወዳጃቸውን በግብዝነት ሲቦጫጭቁ ምንም አያሳፍራቸውም። ምሳሌ 18:​24 (አዓት) “አንዳቸው ሌላውን የማነካከት ዝንባሌ ያላቸው ጓደኛሞች አሉ” ይላል። እናንተስ በጎጂ ሐሜት የጓደኛችሁን ስም “ታጠፉታላችሁ?” ወይስ በታማኝነት ትቆሙለታላችሁ?

የውስጥ ስሜታችሁን ገልጣችሁ ተናገሩ

ኢየሱስ ተወዳጅ የሆነበት ሌላ መንገድ የውስጥ ስሜቱን ገልጦ በመናገር ነው። አንዳንድ ጊዜ ‘ማዘኑ፣’ ‘መውደዱ’ ወይም ‘በጣም መከፋቱ’ እንዲታወቅ አድርጓል። ቢያንስ አንድ ጊዜ ‘እንባውን አፍስሷል።’ ኢየሱስ ለሚያምናቸው ሰዎች የልቡን አውጥቶ መናገር አያሳፍረውም ነበር።​— ማቴዎስ 9:​36፤ 26:​38፤ ማርቆስ 10:​21፤ ዮሐንስ 11:​35

እርግጥ ይህ ማለት ለምታገኙት ሰው ሁሉ የልባችሁን ገልጣችሁ መናገር አለባችሁ ማለት አይደለም! ይሁን እንጂ ለሁሉም ሰው ሐቀኛ ልትሆኑ ትችላላችሁ። አንድን ሰው ማወቅና ማመን ስትጀምሩ ደግሞ ቀስ በቀስ ውስጣዊ ስሜታችሁን ልትገልጡለት ትችላላችሁ። በተጨማሪም ከሌሎች ሰዎች ጋር ትርጉም ያለው ዝምድና እንዲኖር የሌላውን ሰው ችግር እንደ ራስ ችግር ማየትና “የወንድማማች መዋደድ” ያስፈልጋል።​— 1 ጴጥሮስ 3:​8 አዓት

ፍጽምና አትጠብቁ

ጥሩ ጅምር ያለው ጓደኝነት ለመመስረት ብትችሉም እንኳን ፍጽምና አትጠብቁ። “ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለንና፤ በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር እርሱ ሥጋውን ሁሉ ደግሞ ሊገታ የሚችል ፍጹም ሰው ነው።” (ያዕቆብ 3:​2) በተጨማሪም ጓደኝነት የጊዜና የስሜት ወጪ ያስከትላል። ፕሬስሊ የሚባል አንድ ወጣት ሲናገር “ለመስጠት ፈቃደኛ መሆን አለባችሁ” ብሏል። “የጓደኝነት ትልቁ ክፍል ይህ ነው። ስለ አንዳንድ ነገሮች የራሳችሁ አመለካከት ቢኖራችሁም ለጓደኛችሁ ስሜትና አስተያየትም ቦታ ለመስጠት ፈቃደኞች መሆን ይኖርባችኋል።”

ይሁን እንጂ ወዳጅነት የሚያስከትለው የጊዜና የስሜት ኪሣራ ፍቅር አልባ የሆነ ባዶ የብቸኝነት ሕይወት መምራት ከሚያስከትለው ኪሣራ ጋር ሊወዳደር አይችልም። ስለዚህ ለራሳችሁ ወዳጆች አፍሩ። (ከሉቃስ 16:​9 ጋር አወዳድሩ።) ራሳችሁን ለሌሎች ስጡ። ሌሎች ሲናገሩ አዳምጡ፣ እንዲሁም እውነተኛ አሳቢነት አሳዩአቸው። እንዲህ ካደረጋችሁ እናንተም እንደ ኢየሱስ “እናንተ ወዳጆቼ ናችሁ” የምትሏቸው ብዙ ወዳጆች ሊኖሯችሁ ይችላሉ።​— ዮሐንስ 15:​14

የመወያያ ጥያቄዎች

◻ እውነተኛ ጓደኛን ለይታችሁ ልታውቁ የምትችሉት እንዴት ነው? አስመሳይ ጓደኞች ምን ዓይነት ናቸው?

◻ ጓደኞች ልታገኙ የምትችሉት የት ነው? ጓደኞች አድርጋችሁ የምትመርጧቸው ሰዎች ሁልጊዜ በዕድሜ እኩዮቻችሁ መሆን አለባቸውን?

◻ ጓደኛችሁ ከባድ ችግር ላይ ቢወድቅ ምን ማድረግ ይኖርባችኋል?

◻ ጓደኛ ለማፍራት የሚረዱ አራቱ መንገዶች ምንድን ናቸው?

[በገጽ 66 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ከአዳዲሶቹ ‘ጓደኞቼ’ ብዙ ነገር ተማርኩ፤ የሙዚቃ ማጫወቻዎችን መስረቅ፣ የተጭበረበሩ ቼኮችን መመንዘር፣ ማሪዋና ማጨስንና በመጨረሻም በየቀኑ 200 ዶላር የሚጠይቅ የአደንዛዥ ዕፅ ሱሴን ለማርካት እንዴት ገንዘብ ማግኘት እንደምችል ተማርኩ”

[በገጽ 68, 69 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ጓደኛዬን ማጋለጥ ይኖርብኛልን?

ጓደኛቻሁ ሞቅ እንዲለው ብሎ አደንዛዥ ዕፆች እንደሚወስድ፣ ዝሙት እንደሚፈጽም፣ እንደሚያጭበረብር ወይም እንደሚሰርቅ ብታውቁ ኃላፊነት ላለው ሰው ትናገራላችሁን? አብዛኞቹ ብዙውን ጊዜ ወጣቶች አጥብቀው የሚከተሉትን የዝምታ ደንብ በማክበር ዝም ይላሉ።

አንዳንዶቹ “ሾካካ” የሚል ስያሜ እንዳይሰጣቸው ይፈራሉ። ሌሎች ደግሞ ዓላማውን የሳተ ታማኝነት ያሳያሉ። እርማትና ተግሣጽ መቀበልን እንደ ጎጂ ነገር አድርገው በመመልከት የጓደኛቸውን መጥፎ ድርጊት ቢሸፍኑለት የጠቀሙት ይመስላቸዋል። በተጨማሪም የወጣቶችን የዝምታ ደንብ ቢጥሱ ለእኩዮቻቸው መዘባበቻነት ሊጋለጡና ጓደኞቻቸውንም ሊያጡ ይችላሉ።

ይሁን እንጂ ሊ የሚባል አንድ ወጣት ክሪስ የሚባለው ጓደኛው እንደሚያጨስ ባወቀ ጊዜ እርምጃ ለመውሰድ ወሰነ። ሊ ሲናገር “ጉዳዩ ለሚመለከተው ሰው መናገር እንዳለብኝ ስለማውቅ ሕሊናዬ እረፍት ነሳኝ!” ይላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመንም አንድ ወጣት ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። “ዮሴፍ የአሥራ ሰባት ዓመት ልጅ በሆነ ጊዜ ከወንድሞቹ ጋር በጎች ይጠብቅ ነበር፤ . . . ዮሴፍም የክፋታቸውን ወሬ ወደ አባታቸው አመጣ።” (ዘፍጥረት 37:​2) ዮሴፍ ሳይናገር ቢቀር የወንድሞቹ መንፈሳዊ ደህንነት አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል ያውቅ ነበር።

ኃጢአት ሰዎችን የሚያበላሽ፣ የሚበክል ኃይል ነው። በተሳሳተ ጎዳና ላይ የሚገኘው ጓደኛ እርዳታ፣ ምናልባትም ጠንከር ያለ ቅዱስ ጽሑፋዊ ተግሣጽ ካላገኘ ወደባሰ ክፋት እያዘቀጠ ሊሄድ ይችላል። (መክብብ 8:​11) ስለዚህ የጓደኛን ኃጢአት መሸፈን ምንም ጥቅም የማያመጣ ከመሆኑም ሌላ የኋላ ኋላ ሊጠገን የማይችል ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።

ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ “ወንድሞች ሆይ፣ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ፣ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት [“አስተካክሉት” አዓት]” በማለት አጥብቆ ያሳስባል። (ገላትያ 6:​1) በተሳሳተ ጎዳና ላይ የሚገኘውን ጓደኛችሁን ለማስተካከል የሚያስችል መንፈሳዊ ብቃት ያላችሁ ሆኖ ላይሰማችሁ ይችላል። ይሁን እንጂ ጉዳዩ እርዳታ ለመስጠት ብቃት ላለው ሰው እንዲነገር ማድረግ አስተዋይነት አይሆንምን?

እንግዲያስ ወደ ጓደኛችሁ ቀርባችሁ ስህተቱን ገልጦ መናገር አስፈላጊ ነው። (ከማቴዎስ 18:​15 ጋር አወዳድሩ።) ይህን ለማድረግ ጉብዝናና ድፍረት ይጠይቃል። ኃጢአቱን በተመለከተ አሳማኝ ማስረጃ በመስጠት፣ በተለይም ደግሞ የምታውቁትንና እንዴት ልታውቁ እንደቻላችሁ ግልጥልጥ አድርጋችሁ በመናገር ጽኑ አቋም ውሰዱ። (ከዮሐንስ 16:​8 ጋር አወዳድሩ።) ለማንም አልነግርም የሚል ቃል አትግቡ። ምክንያቱም እንዲህ ዓይነቱ ቃል ኪዳን በደልን መሰወርን በሚያወግዘው አምላክ ፊት ዋጋ ቢስ ነው።​— ምሳሌ 28:​13

ምናልባት ጓደኛችሁ ኃጢአቱን ሳይናገር የቀረው በደንብ ያልገባው ነገር ስላለ ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 18:​13) ይህ ካልሆነና በእርግጥ ኃጢአት ተፈጽሞ ከሆነ ችግሩ ገሐድ በመውጣቱ ጓደኛችሁ እፎይታ ሊያገኝ ይችላል። ጥሩ አድማጭ ሁኑ። (ያዕቆብ 1:​19) ስሜቱን በሚገልጥበት ጊዜ “እንዲህ ማድረግ አልነበረብህም!” በማለት ኮናኝ አነጋገሮችን ወይም “እንዴት እንዲህ ልታደርግ ቻልክ!” የሚሉ የድንጋጤ አነጋገሮችን በመጠቀም ንግግሩን አታቋርጡ። ራሳችሁን በጓደኛችሁ ቦታ አድርጋችሁ ተመልከቱ፣ ስሜቱንም ተረዱለት።​— 1 ጴጥሮስ 3:​8

ብዙውን ጊዜ ሁኔታው እናንተ ልትሰጡ ከምትችሉት እርዳታ የበለጠ ነገር የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ከሆነ ጓደኛችሁ ጥፋቱን ለወላጆቹ ወይም ኃላፊነት ላላቸው ሌሎች ሰዎች እንዲገልጥ ደጋግማችሁ ጠይቁት። ጓደኛችሁ ጥፋቱን ለመናገር አሻፈረኝ ቢልስ? በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ጉዳዩን ገልጦ ካልተናገረ እውነተኛ ጓደኛ እንደመሆናችሁ ራሳችሁ ለመናገር እንደምትገደዱ አስታውቁት።​— ምሳሌ 17:​17

መጀመሪያ ላይ ጓደኛችሁ እንዲህ ዓይነቱን እርምጃ የምትወስዱበት ምክንያት ላይገባው ይችላል። ምናልባትም ሊናደድና ነገሩን ሳያመዛዝን ጓደኝነታችሁን ሊሰርዝ ይችላል። ይሁን እንጂ ሊ እንደሚከተለው ብሏል:- “ለሚመለከተው ሰው በመናገሬ ትክክለኛ ነገር እንዳደረግሁ አውቃለሁ። አሁን ይሰማኝ የነበረው የሕሊና ጭንቀት በጣም ቀሎልኛል። ምክንያቱም ክሪስ የሚያስፈልገውን እርዳታ እያገኘ ነው። በኋላም ክሪስ መጥቶ ጥፋቱን በማጋለጤ እንዳልተበሳጨ ነገረኝ። ይህም ከጭንቀቴ ገላግሎኛል።”

ጓደኛችሁ የወሰዳችሁትን የድፍረት እርምጃ መቃወሙን ከቀጠለ መጀመሪያውኑም ቢሆን ጥሩ ጓደኛ ሊሆናችሁ አይችልም ነበር ማለት ነው። እናንተ ግን ለአምላክ ያላችሁን ታማኝነትና እውነተኛ ጓደኛ መሆናችሁን እንዳረጋገጣችሁ ስለምታውቁ እርካታ ታገኛላችሁ።

[በገጽ 67 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጓደኛ ማፍራት ያስቸግራችኋልን?

[በገጽ 70 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስለ ሌሎች ሁኔታ አሳቢነት ማሳየት ጓደኝነት ለመጀመር የሚያስችል ዋና ቁልፍ ነው