በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በጣም ዓይን አፋር የሆንኩት ለምንድን ነው?

በጣም ዓይን አፋር የሆንኩት ለምንድን ነው?

ምዕራፍ 15

በጣም ዓይን አፋር የሆንኩት ለምንድን ነው?

“ሁሉም ሰው በጣም ቆንጆ እንደሆንኩ ይነግረኛል” በማለት አንዲት ወጣት ሴት ለአንድ የጋዜጣ ዓምድ ጽፋለች። ሆኖም ቀጥላ “ከሰዎች ጋር ማውራት ያስቸግረኛል። ስናገር አንድን ሰው ዓይኑን ካየሁ ፊቴ ይቀላና በውስጤ የሚተናነቅ ስሜት ይይዘኛል። . . . በሥራ ቦታ ከማንም ሰው ጋር ስለማላወራ ‘ኩራተኛ’ ናት የሚል ብዙ ትችት ሲሰነዘር እሰማለሁ። . . . ኩራተኛ አይደለሁም፤ ዓይን አፋር ነኝ” ብላለች።

አንድ ጥናት ጥያቄ ከቀረበላቸው ሰዎች ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት በሕይወታቸው ውስጥ በአንድ ወቅት ዓይን አፋር እንደሆኑና 40 በመቶዎቹ ደግሞ አሁንም ዓይን አፋር ነን ብለው የሚያስቡ እንደሆኑ አሳይቷል። በእርግጥም ዓይን አፋርነት ከጥንት ጀምሮ ከሰው ጋር አብሮ የኖረ ችግር ነው። ሙሴ በዓይን አፋርነቱ ምክንያት በእስራኤል ሕዝብ ፊት የአምላክ ቃል አቀባይ ሆኖ ለመናገር እምቢ ብሎ እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዘጸአት 3:​11, 13፤ 4:​1, 10, 13) ክርስቲያን ደቀ መዝሙር የነበረው ጢሞቴዎስም ዓይን አፋር የነበረና ለመናገርና በሥልጣኑም በተገቢ መንገድ ለመጠቀም ፈራ ተባ ይል የነበረ ይመስላል። — 1 ጢሞቴዎስ 4:​12፤ 2 ጢሞቴዎስ 1:​6–8

ዓይን አፋርነት ምንድን ነው?

ዓይን አፋርነት ማለት በሰዎች ፊት ማለትም በእንግዶች፣ በባለ ሥልጣኖች፣ ተቃራኒ ፆታ ባላቸው ሰዎች ፊት ወይም በእኩዮች ፊትም እንኳን ሳይቀር የተዝናና መንፈስ የማጣት ስሜት ነው። ግለሰቦችን በተለያዩ መንገዶች የሚነካ ከልክ በላይ ስለ ራስ ከመጨነቅ የሚመነጭ ስሜት ነው። አንዳንዶች ሲያፍሩ ወደ መሬት ያቀረቅራሉ፣ ልባቸው ይመታል፣ መናገር ይሳናቸዋል። ሌሎች ደግሞ መረጋጋት ­አጥተው አለማቋረጥ ይለፈልፋሉ። ሌሎች ደግሞ ድምፃቸውን አውጥተው መናገርና አስተያየታቸውን ወይም ምርጫቸውን መግለጽ ይሳናቸዋል።

ይሁንና መጠነኛ የሆነ ዓይን አፋርነት ጠቃሚ ገጽታዎች አሉት። ይህ ዓይነቱ ዓይን አፋርነት አቅምን ከማወቅና ከትሕትና ጋር ዝምድና አለው። አምላክም ‘ከእርሱ ጋር ቦታችንን ጠብቀን እንድንመላለስ’ ይፈልጋል። (ሚክያስ 6:​8) ልባምና ትሑት ሆኖ መታየት፣ ሰው አክባሪ መሆን እንዲሁም ዓይን አውጣና ዕብሪተኛ አለመሆን ተጨማሪ ጥቅም አለው። ዓይን አፋር ሰው ብዙ ጊዜ በጥሩ አድማጭነቱ ይወደዳል። ይሁን እንጂ ዓይን አፋርነታችን ሙሉ ችሎታችንን እንዳንገነዘብ ካገደንና ከከለከለን እንዲሁም ከሰዎች ጋር ያለንን ዝምድና፣ ሥራችንንና ስሜታችንን በሚጎዳ መንገድ የሚነካ ከሆነ ከዚህ ጠባያችን ለመላቀቅ አንድ ነገር ማድረግ ይኖርብናል!

ለዚህም ጥሩ ጅምር የሚሆነው ችግሩን መረዳት ነው። (ምሳሌ 1:​5) ዓይን አፋርነት ማንነታችሁን ሳይሆን ጠባያችሁን፣ አንዳንድ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟችሁ የሚሰማችሁን ስሜት፣ ከሌሎች ጋር ባሳለፋችሁት ተሞክሮ በውስጣችሁ ሥር ሰድዶ የተቀረጸባችሁን አመለካከት የሚገልጽ ቃል ነው። ሌሎች ስለ እኔ ጥሩ አስተያየት አይሰጡም ወይም አይወዱኝም ብላችሁ ታስባላችሁ። ሌሎች ከእናንተ እንደሚሻሉ ወይም ከእናንተ የተሻለ እንከን የሌላቸው ናቸው ብላችሁ ታስባላችሁ። ከሌሎች ጋር ብትቀራረቡና ብትነጋገሩ ነገር ሁሉ የሚበላሽባችሁ ይመስላችኋል። ሁልጊዜ አይሳካልኝም ብላችሁ በማመናችሁ ምክንያት ውጥረት ስለሚኖርባችሁና ከእምነታችሁም ጋር የሚስማማ ነገር ስለምታደርጉ ብዙውን ጊዜ የምታደርጉት ነገር ሳይሳካላችሁ ይቀራል።

ዓይን አፋርነት ሕይወታችሁን የሚነካው እንዴት ነው?

ከሰዎች ጋር በመነጋገር ፈንታ ራሳችሁን ስታገሉ ወይም ለሌሎች ምንም ትኩረት መስጠት እስከማትችሉ ድረስ ስለ ራሳችሁ ስትጨነቁ የኩራት፣ ሰውን ያለመውደድ፣ ሰውን የመሰልቸት ወይም ለሰው ደንታ የማጣት ጠባይ ወይም ድንቁርና ያለባችሁ ሊያስመስልባችሁ ይችላል። ሐሳባችሁ በራሳችሁ ላይ ብቻ ካተኮረ አጠገባችሁ ያሉ ሰዎች በሚወያዩት ነገር ላይ ለማተኮር አዳጋች ይሆንባችኋል። ስለዚህ ከሚነገራችሁ ነገር ውስጥ የምታዳምጡት ጥቂቱን ብቻ ይሆናል። እንዲህ ከሆነ ደግሞ በጣም የምትፈሩት ነገር ይደርስባችኋል፤ ይኸውም ሞኝ መስላችሁ ትታያላችሁ።

በመሠረቱ በዓይን አፋርነት ወኅኒ ውስጥ ራሳችሁን ቆልፋችሁ ቁልፉን ወርውራችሁ ጥላችኋል ማለት ነው። አጋጣሚዎች እንዲያመልጧችሁ ታደርጋላችሁ። ለመናገር ወይም ሐሳባችሁን ለመግለጽ ስለምትፈሩ ብቻ የማትፈልጓቸውን ነገሮች ወይም ሁኔታዎች ትቀበላላችሁ። ከሰዎች ጋር ተገናኝታችሁ አዳዲስ ወዳጆች በማፍራት ወይም ለሕይወታችሁ ደስታ የሚጨምሩለትን ነገሮች በማድረግ የሚገኘው ደስታ ያመልጣችኋል። ሌሎች ሰዎችም የእናንተን እውነተኛ ማንነት ለማወቅ ሳይችሉ ስለሚቀሩ ከእናንተ ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም ሳያገኙ ይቀራሉ።

ዓይን አፋርነትን ማሸነፍ

ጊዜና ጥረት ከታከለበት ጠባይ ሊለወጥ ይችላል። ከሁሉ በፊት ሌላ ሰው ይታዘበናል ብላችሁ አትጨነቁ። ይታዘበናል ብላችሁ የምትፈሩት ሰው ራሱ ስለ ራሱ በማሰብና ምን ልናገር፣ ምን ልሥራ በሚል ሐሳብ ተውጦ ይሆናል። ይህ ሰው የልጅነት መንፈስ ኖሮት ቢሳለቅባችሁ ችግር ያለበት መሆኑን ተረዱ። “ወዳጁን የሚንቅ እርሱ አእምሮ የጎደለው ነው።” (ምሳሌ 11:​12) የእናንተን ውስጣዊ ማንነት ሳይመለከቱ ውጪያዊ መልካችሁን አይተው የሚፈርዱ ሰዎች ጥሩ ጓደኞች ወይም ወዳጆች ሊሆኗችሁ አይችሉም።

በተጨማሪም አዎንታዊ አስተሳሰብ እንዲኖራችሁ ጣሩ። ፍጹም የሆነ ሰው የለም፤ ሁላችንም የየራሳችን ጠንካራና ደካማ ጎኖች አሉን። ሁልጊዜ የአመለካከት ልዩነት እንደሚኖር አስታውሱ። ሰዎች በሚወዷቸውና በሚጠሏቸው ነገሮች ረገድ ይለያያሉ። ሰዎች ከእናንተ የተለየ አስተያየት ቢኖራቸው እናንተን ንቀዋችኋል ማለት አይደለም።

በተጨማሪም ሌሎችን በሚዛናዊነት መመልከትን ተማሩ። ቀደም ሲል ዓይን አፋር የነበረ አንድ ወጣት እንዲህ ብሏል:- “ስለ ራሴ ሁለት ነገሮችን ተገንዝቤአለሁ። . . . አንደኛ፣ ከሚገባው በላይ ስለ ራሴ እጨነቅ ነበር። ሰዎች ስለተናገርኩት ነገር ምን ተሰምቷቸው ይሆን እያልኩ አስብ ነበር። ሁለተኛ፣ ሌሎች ለሚያደርጉት ነገር ሁሉ መጥፎ ትርጉም እሰጥ፣ እጠራጠራቸውና ይንቁኛል ብዬ አስብ ነበር።”

ይህ ወጣት ሰው በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ተገኘ። “በስብሰባው ላይ የሰማሁት ንግግር በእርግጥ ረድቶኛል” ይላል። ‘ተናጋሪው ፍቅር ከሰው ጋር ተግባቢ እንደሆነ፣ ፍቅር ካለን ስለ ሰዎች የምናስበው ክፉ ክፉውን ሳይሆን ጥሩ ጥሩውን እንደሚሆን አመልክቶ ነበር። ስለዚህ እኔም ሰዎች መጥፎ ናቸው ብዬ ማሰቤን መተው ጀመርኩ። “ችግሬ ይገባቸዋል፣ ደግ ይሆኑልኛል፣ ያስቡልኛል” ብዬ ማሰብ ጀመርኩ። ሰዎችን ማመን ጀመርኩ። አንዳንዶች ስለ እኔ የተሳሳተ ግምት ሊኖራቸው እንደሚችል አውቃለሁ፤ ቢሆንም የራሳቸው ጉዳይ ነው ብዬ ማሰብ ጀምሬአለሁ።’

“በተጨማሪም በተሟላ ሁኔታ ፍቅር የማሳየትን አስፈላጊነት፣ ማለትም ራሴን ለሌሎች መስጠትን ተማርኩ” በማለት ገልጿል። “ይህንንም በመጀመሪያ ከእኔ በዕድሜ በሚያንሱት ላይ ሞከርኩ። በኋላም ሌሎችን እቤታቸው ድረስ ሄጄ መጠየቅ ጀመርኩ። ችግራቸው እንዲሰማኝ ማድረግና ልረዳቸው የምችልበትን መንገድ ማሰብ ጀመርኩ።” ስለዚህ ኢየሱስ በሉቃስ 6:​37, 38 ላይ “አትፍረዱ አይፈረድባችሁምም፤ አትኮንኑ አትኮነኑምም። . . . ስጡ ይሰጣችሁማል፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ይሰፈርላችኋልና” በማለት የተናገራቸውን ቃላት እውነተኛነት ይህ ወጣት ተማረ።

የመጀመሪያ እርምጃ

ስለዚህ ተጫዋች መሆንን፣ ማለትም ሰላምታ መስጠትንና ጭውውት መጀመርን ልመዱ። ጭውውቱም ስለ አየሩ ሁኔታ አስተያየት መስጠትን የመሰለ ቀላል መግቢያ በመጠቀም ሊጀምር ይችላል። አስታውሱ:- ጭውውት በመጀመር ረገድ ከእናንተ የሚፈለገው የሥራ ድርሻ 50 በመቶ ብቻ ነው። ሌላው 50 በመቶ ደግሞ ልታጫውቱት የፈለጋችሁት ሰው ድርሻ ነው። በንግግራችሁ ላይ ብትሳሳቱ አትሸማቀቁ። ሌሎች ቢስቁባችሁ አብራችሁ መሳቅን ተማሩ። “ለማለት የፈለግሁት ይህን አልነበረም” ብትሉ የተዝናና መንፈስ እንዲኖራችሁና ጭውውቱን እንድትቀጥሉ ይረዳችኋል።

ዘና እንድትሉ የሚያስችሏችሁን ልብሶች ልበሱ፤ ሆኖም ልብሶቻችሁ ንጹሕና የተተኮሱ ወይም ያልተጨማደዱ መሆናቸውን አረጋግጡ። እንደሚያምርባችሁ ሲሰማችሁ በዚህ በኩል የሚሰማችሁ ፍርሃት ስለሚቀንስላችሁ በምትጨዋወቱት ነገር ላይ ለማተኮር ትችላላችሁ። ቀጥና ዘና ብላችሁ ቁሙ። የደስደስ ያላችሁና ፈገግተኞች ሁኑ። ከምታነጋግሩት ሰው ጋር በወዳጅነት ዓይን ፊት ለፊት እየተያያችሁ ሰውዬው ሲናገር ራሳችሁን በመነቅነቅ ወይም የቃል መልስ በመስጠት ስለሚናገረው ነገር ተከታተሉ።

በሌሎች ፊት ንግግር ማድረግን ወይም ሥራ ለመቀጠር ለቃል ፈተና መቅረብን የመሰለ ከበድ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥማችሁ የተቻላችሁን ያህል ተዘጋጅታችሁ ቅረቡ። የምትናገሩትን አስቀድማችሁ ተለማመዱ። የንግግር ችግሮች ልምምድ በማድረግ ሊወገዱ ወይም ሊቀንሱ ይችላሉ። ማንኛውንም ችሎታ ለማሻሻል ጊዜ እንደሚጠይቅ ሁሉ የንግግር ችሎታንም ለማሻሻል ጊዜ ይወስድ ይሆናል። ይሁን እንጂ ጥሩ ውጤት ማየት ስትጀምሩ ተጨማሪ ውጤት ለማግኘት ትበረታታላችሁ።

አምላክ የሚሰጠው እርዳታም ችላ ሊባል አይገባም። የጥንቱ የእሥራኤል ሕዝብ የመጀመሪያ ንጉሥ የነበረው ሳኦል መጀመሪያ ላይ በጣም ዓይን አፋር ነበር። (1 ሳሙኤል ምዕራፍ 9 እና 10) ይሁን እንጂ የኃይል እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ ሲደርስ “በሳኦል ላይ የእግዚአብሔር መንፈስ በኃይል ወረደ።” ሕዝቡንም መርቶ በማዋጋት ድል እንዲያገኙ ለማድረግ ቻለ!​— 1 ሳሙኤል ምዕራፍ 11

ዛሬም ክርስቲያን ወጣቶች ሌሎች ስለ አምላክና አምላክ አመጣለሁ ብሎ ቃል ስለገባው ጽድቅ የሚሰፍንበት አዲስ ዓለም እንዲማሩ የመርዳት ኃላፊነት አለባቸው። (ማቴዎስ 24:​14) ይህን ምሥራች በመያዝ በአጽናፈ ዓለሙ ውስጥ ከሁሉ የበለጠ ባለ ሥልጣን የሆነውን አምላክ ወክሎ መቆም በራስ የመተማመን ስሜትን እንደሚቀሰቅስና አንድ ሰው ከመጠን በላይ ስለ ራሱ እንዳይጨነቅ እንደሚረዳው የተረጋገጠ ነው። እንግዲያስ እናንተም አምላክን በታማኝነት ካገለገላችሁ እንደሚባርካችሁና ዓይን አፋርነታችሁን እንድታስወግዱ እንደሚረዳችሁ እርግጠኞች ልትሆኑ ትችላላችሁ።

የመወያያ ጥያቄዎች

◻ ዓይን አፋርነት ምንድን ነው? ዓይን አፋር የሆነ ሰው በሌሎች ፊት ምን ይሰማዋል? ይህ ዓይነቱ ጠባይ በእናንተም ላይ በመጠኑ ይታያልን?

◻ ዓይን አፋር የሆነ ሰው በሌሎች ፊት ሲሆን በራሱ መተማመን የማይችለው ለምንድን ነው?

◻ ዓይን አፋርነት አንድ ሰው ብዙ ነገሮች እንዲቀሩበት የሚያደርገው ለምንድን ነው?

◻ ዓይን አፋርነትን ለማስወገድ የሚረዱ አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው? ከእነዚህ መካከል እናንተ ተጠቅማችሁባቸው የረዷችሁ ይኖራሉን?

[በገጽ 121 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ዓይን አፋር የሆነ ሰው የሰዎችን ወዳጅነትና ጥሩ አጋጣሚዎችን ያጣል

[በገጽ 124 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በሚከተሉት መንገዶች ተጠቅማችሁ ዓይን አፋርነትን ለማስወገድ ትችላላችሁ

ለመለወጥ መፈለግና ለውጥ ማድረግ የሚቻል መሆኑን ማመን

አፍራሽ አስተሳሰቦችን ገንቢ በሆኑ እርምጃዎች መተካት

ለራሳችሁ ምክንያታዊና ትርጉም ያላቸው ግቦችን ማውጣት

የተዝናና መንፈስ እንዲኖራችሁ ለማድረግና ጭንቀትን ለመቋቋም የምትችሉበትን መንገድ ማወቅ

አስቀድሞ መለማመድ

በየጊዜው በሚገኙት የተሳኩ ውጤቶች አማካኝነት በራስ የመተማመን መንፈስ ማዳበር

የአስተያየት ልዩነቶች እንዳሉና ሌሎችም እንደ እናንተ እንደሚሳሳቱ ማስታወስ

ችሎታን ለማሳደግና አዳዲስ ችሎታዎችን ለመማር ልምምድ ማድረግ

ፍቅር ለማሳየትና ሌሎችን ለመርዳት መጣር

ለዛ ባለው መንገድ መልበስና የምታደርጉትን ነገር በልበ ሙሉነት ማድረግ

አምላክ በሚሰጠው እርዳታ መተማመን

በክርስቲያናዊ ስብሰባዎችና እምነታችሁን ለሌሎች በማካፈሉ ሥራ መጠመድ

[በገጽ 123 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ዓይን አፋር የሆነ ሰው ሌሎች የሚንቁት መስሎ ይታየዋል

[በገጽ 123 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ተጨዋች መሆንን፣ ፈገግ ማለትን፣ ሰላምታ መስጠትንና ጭውውት መቀጠልን ተማሩ