በጣም የምጨነቀው ለምንድን ነው?
ምዕራፍ 13
በጣም የምጨነቀው ለምንድን ነው?
ሜላኒ 17 ዓመት እስኪሞላት ድረስ ምን ጊዜም እናቷን የምታስደስት እንከን የሌለባት ልጅ ነበረች። ከዚያ በኋላ ግን ትምህርቷን እንደ ቀድሞው በትጋት መከታተል አቆመች። ወደ ግብዣዎች እንድትሄድ የሚቀርብላትን ጥሪ መቀበል አቆመች። ውጤቷ ከA ወደ C ሲወርድ እንኳን ምንም ደንታ ያላት መስላ አልታየችም። ወላጆቿ ምን እንዳጋጠማት ረጋ ብለው ሲጠይቋት “ተዉኝ! ምንም አልሆንኩ” ብላ ተቆናጥራ ትወጣለች።
ማርክ 14 ዓመት ሲሆነው የግልፍተኝነት ጠባይ ያለው ችኩልና ሰው የሚጠላ ሆነ። በትምህርት ቤት ቀዥቃዣና በጥባጭ ሆነ። ሲበሳጭ ወይም ሲናደድ በሞተር ብስክሌቱ በረሐ አቋርጦ ይከንፍ ወይም ዥው ባለ ቁልቁለት ላይ በመንሸራተቻ መሣሪያው በከፍተኛ ፍጥነት ይንሸራተት ነበር።
ሜላኒ እና ማርክ ሁለቱም በአንድ ዓይነት በሽታ ማለትም በመንፈስ ጭንቀት ተይዘዋል። የናሽናል ኢንስቲትዩት ኦቭ ሜንታል ሄልዝ ሐኪም የሆኑት ዶክተር ዶናልድ ማክኒው በትምህርት ዓለም ላይ ከሚገኙት ወጣቶች መካከል ከ10 እስከ 15 በመቶ የሚሆኑት የስሜት ቀውስ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ይናገራሉ። አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ደግሞ ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ይይዛቸዋል።
አንዳንድ ጊዜ ችግሩ አካላዊ (ባዮሎጂያዊ) መንስኤ ይኖረዋል። አንዳንድ ኢንፌክሽኖች ወይም ሆርሞን አመንጪ ሕዋሶችን የሚነኩ ሕመሞች፣ ከወር አበባ ወርሐዊ ዑደት ጋር የተያያዘ የሆርሞን መለዋወጥ፣ በደም ውስጥ ሊኖር የሚገባው ስኳር ማነስ፣ አንዳንድ የመድኃኒት ዓይነቶች፣ መርዛማ ለሆኑ ብረቶች ወይም ኬሚካሎች መጋለጥ፣ ለነገሮች አለርጂ መሆን፣ ተመጣጣኝ ምግብ አለመመገብ፣ የደም ማነስ—እነዚህ ሁሉ የመንፈስ ጭንቀት ሊያመጡ ይችላሉ።
ለመንፈስ ጭንቀት መንስኤ የሚሆኑ ውጥረቶች
ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ የአፍላ ጉርምስና ዕድሜ ራሱ የጭንቀት ስሜት ያመጣል። አንድ ወጣት የኑሮን ውጣ ውረድ በመቋቋም ረገድ
ትልልቅ ሰዎች ያላቸው ተሞክሮ የሌለው በመሆኑ ማንም ሰው ለእርሱ ግድ እንደሌለው ሊሰማውና ተራ የሆኑ ችግሮች እንኳን በጣም ሊያስጨንቁት ይችላሉ።ሌላው የኀዘንና የትካዜ ምንጭ ወላጆች፣ አስተማሪዎች ወይም ጓደኞች እንደሚጠብቁት ሆኖ አለመገኘት ነው። ለምሳሌ ያህል ዶናልድ የተማሩ ወላጆቹን ለማስደሰት በትምህርት ቤት አንደኛ መውጣት እንዳለበት ተሰምቶት ነበር። ይህን ለማድረግ ባለመቻሉ ግን በጣም ተጨነቀና ራሱን የመግደል ፍላጎት አደረበት። ዶናልድ “ምንም ነገር በትክክል ሠርቼ አላውቅም። ማንንም ሰው ለማስደሰት የማልችል ነኝ” በማለት ኀዘኑን ገለጸ።
ያሰቡትን ለመፈጸም አለመቻል የመንፈስ ጭንቀት ሊያመጣ የሚችል መሆኑን አፍሮዲጡ በሚባል ክርስቲያን ላይ ከደረሰው በግልጽ ለመረዳት ይቻላል። ይህ ታማኝ ክርስቲያን በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለልዩ ተልእኮ ማለትም ታስሮ የነበረውን ሐዋርያው ጳውሎስን እንዲረዳ ተልኮ ነበር። ይሁን እንጂ ጳውሎስ ዘንድ በደረሰ ጊዜ ታመመና ጳውሎስን ከመርዳት ይልቅ እርሱ ራሱ የጳውሎስ ተረጂ ሆነ! በዚህ ጊዜ አፍሮዲጡ በጣም የማይረባ እንደሆነ ተሰምቶት “የተከዘበትን” ምክንያት ልትገምቱ ትችላላችሁ። ከመታመሙ በፊት ያከናወናቸውን ጥሩ ጥሩ ነገሮች ሁሉ ዘንግቶ እንደነበረ ግልጽ ነው።— ፊልጵስዩስ 2:25–30
የሚወዱትን ሰው ማጣት የሚያስከትለው የስሜት መጎዳት
ፍራንሲን ክላግስብሩን የተባሉ ሴት ቱ ያንግ ቱ ዳይ—ዩዝ ኤንድ ሱሳይድ በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ “በስሜት ቀውስ ምክንያት ለሚመጣው የመንፈስ ጭንቀት መንስኤው አብዛኛውን ጊዜ በጥልቅ ይወደድ የነበረን ሰው ወይም ነገር በማጣት ምክንያት የሚመጣ ከፍተኛ የስሜት መጎዳት ነው” ብለዋል። በመሆኑም በሞት ወይም በፍቺ ምክንያት ወላጅን ማጣት፣ ከሥራ መውጣት ወይም
አካላዊ ጤንነት ማጣትም እንኳን ሳይቀር የመንፈስ ጭንቀት ሊያስከትል ይችላል።ይሁንና ወጣት ለሆነ ሰው ከምንም በላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትልበት ፍቅር መነፈጉ፣ የማይፈለግ እንደሆነና ማንም ለእሱ ደንታ እንደሌለው ከተሰማው ነው። “እናቴ ትታን ስትሄድ እንደተከዳሁና ብቻዬን እንደቀረሁ ተሰማኝ” ትላለች ማሪ የምትባል አንዲት ወጣት ሴት። “በድንገት ሰማይ ምድሩ የተደፋብኝ መስሎ ታየኝ።”
እንግዲያውስ አንዳንድ ወጣቶች መፋታት፣ የአልኮል ሱሰኛነት፣ በቤተሰብ አባሎች ወይም በሥጋ ዘመዶች መካከል የሚደረግ የግብረ ሥጋ ግንኙነት፣ ሚስትን መደብደብ፣ ልጆችን ያለ አግባብ መያዝ የመሳሰሉት የቤተሰብ ችግሮች ሲያጋጥሟቸው ወይም ደግሞ በራሱ ችግር የተዋጠ ወላጅ ሊያገኙ የሚገባቸውን ትኩረት ሳይሰጣቸው ሲቀር የሚደርስባቸውን መደናገርና ሥቃይ አስቡ። “በመከራ ቀን ብትላላ [“ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ቢያድርብህ” አዓት] ጉልበትህ [የስሜት መረበሽን ለመቋቋም የሚያስችለው ኃይል ጭምር] ጥቂት ነው” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ እንዴት እውነት ነው! (ምሳሌ 24:10) አልፎ ተርፎም አንድ ወጣት በቤተሰቡ መካከል ለተነሳው ችግር መንስኤ እንደሆነ ተሰምቶት ራሱን ሊኮንን ይችላል።
ምልክቶቹን ለይቶ ማወቅ
የመንፈስ ጭንቀት የተለያየ መጠን አለው። አንድ ወጣት ለጊዜው በአንድ የሚያበሳጭ ነገር ቅስሙ ተሰብሮ ይሆናል። ይሁን እንጂ እንደዚህ ያለው ትካዜ ብዙም ሳይቆይ ይጠፋል።
የመንፈስ ጭንቀቱ የሚመላለስና ወጣቱ የዋጋ ቢስነት፣ የጭንቀትና የንዴት ስሜት፣ በጠቅላላው አፍራሽ ስሜት ካለው ይህ ሁኔታ ሐኪሞች መጠኑ አነስተኛ የሆነ ሥር የሰደደ የመንፈስ ጭንቀት በማለት ወደሚጠሩት ደረጃ ሊያድግ ይችላል። የማርክና ሜላኒ (በዚህ ምዕራፍ መጀመሪያ ላይ የተጠቀሱት ወጣቶች) ተሞክሮ እንደሚያሳየው የበሽታው ምልክቶች በጣም ሊለያዩ ይችላሉ። አንድ ወጣት የፍርሃትና የስጋት ስሜት ሊመላለስበት ይችላል። ሌላው
ደግሞ ሁልጊዜ ድካም ሊሰማው፣ የምግብ ፍላጎት ሊያጣ፣ የእንቅልፍ ችግር ሊያጋጥመው፣ ክብደቱ ሊቀንስ ወይም ተደጋጋሚ የመውደቅ አደጋ ሊደርስበት ይችላል።አንዳንድ ወጣቶች በየግብዣ ቦታዎች መዞርን፣ የሩካቤ ሥጋ ልክስክስነትን፣ ውንብድናን፣ ከባድ ጠጪነትንና የመሳሰሉትን ሥራዬ ብለው በመያያዝ ያለባቸውን የመንፈስ ጭንቀት ለመደበቅ ይሞክራሉ። አንድ የ14 ዓመት ወጣት “ለምን ሁልጊዜ ከቤት ውጭ መሆን እንደምፈልግ በእርግጥ አላውቀውም” በማለት ገልጿል። “የማውቀው ነገር ቢኖር ብቻዬን ከሆንኩ በጣም መጥፎ ስሜት እንደሚሰማኝ ብቻ ነው።” ነገሩ መጽሐፍ ቅዱስ “በሳቅ መሃልም እንኳን ልብ እያዘነ ሊሆን ይችላል” በማለት እንደገለጸው ነው።— ምሳሌ 14:13 አዓት
ነገሩ ከተራ ትካዜ የበለጠ በሚሆንበት ጊዜ
መጠኑ አነስተኛ የሆነ ሥር የሰደደ የመንፈስ ጭንቀት በአግባቡ ካልተያዘ ከበድ ወዳለ ሕመም፣ ማለትም ወደ ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ሊሸጋገር ይችላል። (ገጽ 107ን ተመልከት።) “ዘወትር በውስጤ ‘በድን’ የሆንኩ መስሎ ይሰማኝ ነበር” በማለት ከባድ የመንፈስ ጭንቀት የነበረባት ማሪ ገልጻለች። “የምኖረው ደስ የሚል ስሜት ሳይሰማኝ ነበር። ያለማቋረጥ ፍርሃት ፍርሃት ይለኝ ነበር።” ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ሲያጋጥም የትካዜው ስሜት ፋታ የማይሰጥ ከመሆኑም በላይ ለወራት ሊቀጥል ይችላል። በዚህም ምክንያት አሁን በብዙ አገሮች እንደ “ድብቅ ወረርሽኝ” ለሚቆጠረው በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች የራሳቸውን ሕይወት ማጥፋት ዋነኛ ምክንያት ይህ ዓይነቱ የመንፈስ ጭንቀት ሆኗል።
ከከባድ የመንፈስ ጭንቀት ጋር ተያይዞ የሚከሰተው የማይለቅና እጅግ አደገኛ የሆነ ስሜት ተስፋ የማጣት ስሜት ነው። ፕሮፌሰር ጆን ኢ ማክ ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ሰለባ ስለሆነች ቪቪየን የተባለች የ14 ዓመት ልጃገረድ ጽፈዋል። ከላይ ለሚያያት ሁሉ የሚያስቡላት ወላጆች ያሏት እንከን የማይወጣላት ወጣት ናት። ሆኖም በጥልቅ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ተውጣ ራሷን ሰቅላ ገደለች! ፕሮፌሰር ማክ “ቪቪየን ራሷን ለመግደል እንድትወስን ያደረጋት ትልቁ ምክንያት የመንፈስ ጭንቀቷ እንደሚለቃት፣ ከሥቃይዋ የመገላገል ተስፋ እንዳላት ለማየት አለመቻሏ ነው” በማለት ጽፈዋል።
በከባድ የመንፈስ ጭንቀት የተጠቁ ሰዎች ደህና የሚሆኑበት ጊዜ የማይመጣ፣ ነገ የሚባል ቀን የሌላቸው መስሎ ይሰማቸዋል። ጠበብቶች እንደሚሉት እንዲህ ያለው ተስፋ ቢስነት ብዙውን ጊዜ ራስን ወደ መግደል ይመራል።
ይሁን እንጂ ራስን መግደል መፍትሔ አይደለም። ሕይወቷ የቀን ቅዠት ሆኖባት የነበረችው ማሪ “በእርግጥ ራሴን የመግደል ሐሳብ ይመጣብኝ ነበር። ይሁን እንጂ ራሴን እስካልገደልኩ ድረስ ምንጊዜም ተስፋ እንደሚኖረኝ ተገንዝቤ ነበር” በማለት ገልጻለች። በእርግጥ ራስን መግደል ለምንም ነገር መፍትሔ አይሆንም። የሚያሳዝነው ነገር ግን ብዙ ወጣቶች ተስፋ የማጣት ስሜት ሲያጋጥማቸው ምንም አማራጭ ሊኖር እንደማይችል ወይም ችግራቸውን ሊወጡ እንደሚችሉ ሊሰማቸው አለመቻሉ ነው። ስለዚህ ማሪ ራስዋን ሄሮይን የሚባለውን አደንዛዥ ዕፅ በመርፌ በመውጋት ችግሯን ለመደበቅ ትሞክር ነበር። “የዕፁ ስሜት ከሰውነቴ እስኪለቅ ድረስ ከፍተኛ የሆነ በራስ የመተማመን ስሜት ይሰማኛል” ብላለች።
ቀለል ያለ ጭንቀትን መቋቋም
የመንፈስ ጭንቀትን ለመቋቋም የሚረዱ ጠቃሚ መንገዶች አሉ። “አንዳንድ ሰዎች በረሃብ ምክንያት የመንፈስ ጭንቀት ሊሰማቸው ይችላል” በማለት በኒው ዮርክ የመንፈስ ጭንቀት ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ናታን ኤስ ክላይን ተናግረዋል። “አንድ ሰው ቁርሱን ሳይበላ ሊወጣና ምሳውንም በአንዳንድ ምክንያቶች ሳይበላ ሊቀር ይችላል። ከዚያም ዘጠኝ ሰዓት ላይ ለምን ጥሩ ስሜት እንደማይሰማው ማሰብ ይጀምራል።”
የምትበሉት ምግብም ልዩነት ሊያመጣ ይችላል። የተስፋ መቁረጥ ስሜት የወረራት ዴቢ የምትባል አንዲት ወጣት “ትርኪ ምርኪ ምግብ መጥፎ ስሜት እንዲሰማኝ ሊያደርግ እንደሚችል አልተገነዘብኩም ነበር። እሱኑ አግበሰብስ ነበር። ጣፋጭ ምግቦች መብላቴን ስቀንስ የተሻለ ስሜት እንደሚሰማኝ አሁን አስተውያለሁ” በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች። ሌሎች ጠቃሚ እርምጃዎችም አሉ:- አንዳንድ የሰውነት እንቅስቃሴ ዓይነቶች መንፈሳችሁን ሊያነቃቁ ይችላሉ። የመንፈስ ጭንቀት የአካላዊ ሕመሞች ምልክት ሊሆን ስለሚችል የሕክምና ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ ሊሆን የሚችልበት ጊዜ ይኖራል።
የአእምሮን ውጊያ ማሸነፍ
ብዙውን ጊዜ የመንፈስ ጭንቀት የሚመጣው ወይም የሚባባሰው ስለ ራሳችሁ አፍራሽ አስተሳሰብ ሲኖራችሁ ነው። “ብዙ ሰዎች ሲያንቋሽሿችሁ ምንም ዋጋ እንደሌላችሁ እንድታስቡ ያደርጋችኋል” በማለት የ18 ዓመቷ ኤቭሊን ብሶቷን አሰምታለች።
እስቲ አስቡት:- ማንነታችሁን መለካት ያለባቸው ሌሎች ሰዎች ናቸውን? በሐዋርያው ጳውሎስም ላይ ተመሳሳይ የሆነ ብዙ 2 ቆሮንቶስ 10:7, 10, 17, 18
የማንቋሸሽ አስተያየት ተሰንዝሮበት ነበር። አንዳንዶች ኮሳሳና ንግግሩም የተናቀ ነው በማለት ተናግረዋል። ታዲያ ይኼ ጳውሎስን ዋጋ ቢስ እንደሆነ እንዲሰማው አድርጎታልን? በፍጹም አላደረገውም! ጳውሎስ አስፈላጊው ነገር የአምላክን የአቋም መመዘኛ ማሟላት እንደሆነ ያውቅ ነበር። ሌሎች የፈለጉትን ቢያወሩም እርሱ ግን በአምላክ እርዳታ ስላከናወናቸው ነገሮች ሊመካ ችሏል። እናንተም በአምላክ ዘንድ ጥሩ አቋም ያላችሁ መሆኑን ከተገነዘባችሁ ያደረባችሁ የትካዜ ስሜት ሊለቃችሁ ይችላል።—የመንፈስ ጭንቀት ያደረባችሁ አንድ ዓይነት ድካም ስላላችሁ ወይም አንድ ዓይነት ኃጢአት በመሥራታችሁ ምክንያት ከሆነስ? አምላክ ለእስራኤላውያን “ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንደ አመዳይ ትነጻለች” ብሏቸዋል። (ኢሳይያስ 1:18) የሰማያዊ አባታችንን ርሕራኄና ትዕግሥት ፈጽሞ አትዘንጉ። (መዝሙር 103:8–14) ይሁን እንጂ እናንተም ችግራችሁን ለማስወገድ እየጣራችሁ ነውን? አእምሯችሁን ከበደለኛነት ስሜት ለማላቀቅ ከፈለጋችሁ እናንተም የበኩላችሁን ማድረግ አለባችሁ። የምሳሌ መጽሐፍ እንደሚለው “ኃጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤ የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል።”— ምሳሌ 28:13
ትካዜን ለመዋጋት የሚቻልበት ሌላው መንገድ ለራሳችሁ የምታወጧቸው ግቦች ሊደረስባቸው የሚችሉ እንዲሆኑ ማድረግ ነው። የተሳካ ኑሮ ለመኖር በትምህርት ቤት አንደኛ መውጣት አያስፈልጋችሁም። (መክብብ 7:16–18) በሕይወት ውስጥ ያሰቡት ነገር ሳይፈጸም መቅረቱ የተለመደ መሆኑን ተቀበሉ። ያሰባችሁት ሳይሳካላችሁ በሚቀርበት ጊዜ ‘ምንም ነገር ቢደርስብኝ ለእኔ ደንታ ያለው ሰው የለም፣ አይኖርምም’ ብላችሁ ከማሰብ ይልቅ ‘ልወጣው እችላለሁ’ ብላችሁ ለራሳችሁ ንገሩ። ስቅስቅ ብላችሁ ብታለቅሱም ምንም ስህተት የለበትም።
ውጤት ያለው ሥራ መሥራት ያለው ጥቅም
የደረሰባትን ተስፋ የመቁረጥ ስሜት በተሳካ ሁኔታ የተወጣችው ዳፍኒ “የተስፋ መቁረጥ ስሜት አለምንም ጥረት በራሱ አይለቅም” በማለት ትመክራለች። “አንድ የተለየ ነገር ማሰብ ወይም በጉልበት ሥራ መጠመድ አለባችሁ። አንድ ነገር ማድረግ መጀመር አለባችሁ።” ለምሳሌ ሊንዳ ትካዜ ሲሰማኝ “ልብስ መስፋት እጀምራለሁ። በስፌት ሥራዬ ላይ ሳተኩር ያስጨንቀኝ የነበረውን ነገር እረሳዋሁ። ይህ በእርግጥ ረድቶኛል” ብላለች። ጥሩ አድርጋችሁ ልትሠሩ
የምትችሏቸውን ነገሮች መሥራት ለራሳችሁ ያላችሁን ግምት ከፍ ሊያደርገው ይችላል። ምክንያቱም የመንፈስ ጭንቀት በሚያጋጥምበት ጊዜ ለራሳችሁ ያላችሁ ግምት በጣም ዝቅ ይላል።በተጨማሪም ደስ የሚያሰኟችሁን ነገሮች በማድረግ መጠመድ ጠቃሚ ነው። ደስ የሚሏችሁን ነገሮች ለመግዛት፣ አንዳንድ ጨዋታዎችን ለመጫወት፣ የምትወዱትን ምግብ ለመሥራት፣ ወደ መጻሕፍት መደብር ሄዳችሁ መጻሕፍትን ለማገላበጥ፣ ምግባችሁን ከቤት ውጭ ለመብላት፣ ለማንበብና በንቁ! መጽሔት ላይ እንደሚወጡት ያሉ የቃላት ጨዋታ እንቆቅልሾችን ለመፍታት ሞክሩ።
ዴቢ አጠር ያለ ጉዞ በማድረግ ወይም ለራሷ ትናንሽ ግቦችን በማውጣት የመንፈስ ጭንቀቷን ለመቋቋም እንደቻለች ተገንዝባለች። ይሁን እንጂ በጣም ከረዷት ነገሮች አንዱ ሌሎች ሰዎችን የሚረዳ ነገር ማድረግ ነበር። “የመንፈስ ጭንቀት በጣም ያጠቃትን አንዲት ወጣት ሴት አገኘሁና መጽሐፍ ቅዱስን እንድታጠና መርዳት ጀመርኩ” በማለት ዴቢ ትናገራለች። “እነዚህ ሳምንታዊ ውይይቶች የመንፈስ ጭንቀቷን እንዴት ልትወጣ እንደምትችል ለመንገር አጋጣሚ ሰጡኝ። መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ ተስፋ እንድታገኝ አስቻላት። ይህም እሷን ብቻ ሳይሆን እኔንም ረድቶኛል።” ነገሩ “ከመቀበል ይልቅ በመስጠት ብዙ ደስታ ይገኛል” በማለት ኢየሱስ እንደተናገረው ነው።— ሥራ 20:35 አዓት
ችግራችሁን ለምትቀርቡት ሰው ንገሩ
“ሰውን የልቡ ኀዘን [ጭንቀት] ያዋርደዋል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል።” (ምሳሌ 12:25) ችግራችሁን ሊረዳላችሁ ከሚችል ሰው የሚሰነዘር “መልካም ቃል” በጣም ትልቅ ትርጉም አለው። ልባችሁን ሊያነብ የሚችል ሰው ስለማይኖር ለምታምኑትና ሊረዳችሁ ለሚችል ሰው ልባችሁን አፍስሱ። በምሳሌ 17:17 መሠረት “ወዳጅ ሁልጊዜ ይወድዳል፣ ለመከራ ጊዜም እንደ ወንድም ይሆናል።” (ዘ ባይብል ኢን ቤዚክ ኢንግሊሽ) የ22 ዓመቷ ኢቫን “ችግራችሁን አምቃችሁ ብትይዙ ብቻችሁን አንድ ትልቅ ሸክም እንደመሸከም ይሆንባችኋል” ብላለች። “እርዳታ ለመስጠት ብቃት ላለው ሰው ስታካፍሉት ግን በጣም ይቀልላችኋል።”
‘ይህንማ ከአሁን በፊትም ሞክሬያለሁ፤ ያገኘሁት ግን የሕይወትን ምሳሌ 27:5, 6
ብሩሕ ገጽታ እንድመለከት የሚያሳስብ ንግግር ብቻ ነው’ ትሉ ይሆናል። ታዲያ ችግራችሁን የሚረዳላችሁ አድማጭ ብቻ ሳይሆን ያልተዛባ ሚዛናዊ ምክር ጭምር ሊሰጣችሁ የሚችል ሰው ልታገኙ የምትችሉት የት ነው?—እርዳታ ማግኘት
እንዲህ ያለውን እርዳታ ለማግኘት ለወላጆቻችሁ ‘ልባችሁን በመስጠት’ ጀምሩ። (ምሳሌ 23:26) ወላጆቻችሁ ከማንም ሰው ይበልጥ ያውቋችኋል። ብዙውን ጊዜም አጋጣሚውን ከሰጣችኋቸው ሊረዷችሁ ይችላሉ። ችግሩ በጣም ከባድ ሆኖ ካገኙት የባለሞያ እርዳታ እንድታገኙ ዝግጅት ሊያደርጉ ይችላሉ። *
ሌላው የእርዳታ ምንጭ የክርስቲያን ጉባኤ አባሎች ናቸው። ማሪ “ባለፉት ዓመታት ሁሉ ደስተኛ መስዬ ለመታየት ብዙ ጥረት አደርግ ስለነበር ምን ያህል የመንፈስ ጭንቀት እንዳለብኝ የሚያውቅ ሰው አልነበረም” ትላለች። “በኋላ ግን በጉባኤ ውስጥ ካሉት በዕድሜ የገፉት ሴቶች ለአንዷ ምሥጢሬን ነገርኳት። የሰው ችግር በጣም የሚገባት ሴት ነበረች! በእኔ ላይ ከደረሱት ሁኔታዎች አንዳንዶቹ በእርስዋም ላይ ደርሰውባት ነበር። ስለዚህ ሌሎች ሰዎችም እንደ እኔው ያለ ችግር አሳልፈው ነጥረው የወጡ መሆናቸውን በመገንዘቤ ተጽናናሁ።”
ያም ሆኖ የማሪ የመንፈስ ጭንቀት ወዲያውኑ አልተዋትም። ከአምላክ ጋር ያላት ዝምድና ጥልቅ እየሆነ ሲሄድ ግን ቀስ በቀስ ስሜቶቿን መቋቋም ጀመረች። እናንተም በይሖዋ እውነተኛ አምላኪዎች መካከል ስለ ደህንነታችሁ ከልብ የሚያስቡ ወዳጆችና “ቤተሰብ” ልታገኙ ትችላላችሁ።— ማርቆስ 10:29, 30፤ ዮሐንስ 13:34, 35
ከተለመደው በላይ የሆነ ኃይል
ይሁን እንጂ ትካዜን ለማስወገድ የሚረዳው ከሁሉ የበለጠ ጠንካራ እርዳታ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ታላቅ ኃይል’ [“ከተለመደው በላይ የሆነ ኃይል” አዓት] በማለት የጠራው ከአምላክ የሚገኝ ኃይል ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:7) በአምላክ ከተማመናችሁ የመንፈስ ጭንቀትን ተዋግታችሁ እንድታሸንፉ ሊረዳችሁ ይችላል። (መዝሙር 55:) በመንፈስ ቅዱሱ አማካኝነት ከተለመደው ኃይላችሁ በላይ የሆነ ኃይል ይሰጣችኋል። 22
ከአምላክ ጋር የምትመሠርቱት ወዳጅነት ያጽናናችኋል። ጆርጂያ የተባለች ወጣት “በማዝንበት ጊዜ ብዙ እጸልያለሁ። ምንም ያህል ከባድ ችግር ቢኖርብኝ ይሖዋ መውጫውን እንደሚያዘጋጅልኝ አውቃለሁ” ብላለች። ዳፍኒም “ማንኛውንም ነገር ለይሖዋ ልትነግሩት ትችላላችሁ። ልባችሁን ለእርሱ ብታፈስሱ ስሜታችሁን ሊረዳላችሁ የሚችል ሰው ባይኖር እንኳን እርሱ በእርግጥ ይረዳላችኋል፣ ስለ እናንተም ያስባል” በማለት ጆርጂያ ከተናገረችው ጋር የሚስማማ ሐሳብ ሰጥታለች።
እንግዲያውስ የመንፈስ ጭንቀት ካለባችሁ ወደ አምላክ ጸልዩ። ስሜታችሁን ገልጣችሁ ልትነግሩት የምትችሉት ጠቢብና አስተዋይ ሰው ፈልጉ። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ጥበብ ያለበት ምክር የሚሰጡ “ሽማግሌዎች” ታገኛላችሁ። (ያዕቆብ 5:14, 15) እነዚህ ሽማግሌዎች ከአምላክ ጋር ያላችሁን ወዳጅነት ጠብቃችሁ እንድትኖሩ ሊረዷችሁ ዝግጁዎች ናቸው። አምላክ ራሱም ችግራችሁን ሊረዳላችሁ የሚችል በመሆኑ ጭንቀታችሁን በእርሱ ላይ እንድትጥሉ ጋብዟችኋል፤ “እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና።” (1 ጴጥሮስ 5:6, 7) መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ “አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል” በማለት ቃል ገብቷል።— ፊልጵስዩስ 4:7
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.40 አብዛኞቹ የሕክምና ጠበብቶች ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው ሰዎች የገዛ ሕይወታቸውን የማጥፋት አደጋ ሊያጋጥማቸው ስለሚችል የባለ ሞያ እርዳታ እንዲያገኙ ይመክራሉ። ለምሳሌ ያህል በሕክምና ባለሞያ ትእዛዝ ብቻ የሚሰጥ መድኃኒት ሊኖር ይችላል።
የመወያያ ጥያቄዎች
◻ በአንድ ወጣት ላይ የመንፈስ ጭንቀት ሊያመጡ የሚችሉ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? እናንተስ የመንፈስ ጭንቀት ደርሶባችሁ ያውቃልን?
◻ መጠኑ አነስተኛ የሆነ ሥር የሰደደ የመንፈስ ጭንቀት ምልክቶች ምን እንደሆኑ ለይታችሁ ልትናገሩ ትችላላችሁን?
◻ ከባድ የመንፈስ ጭንቀት እንዴት ሊታወቅ እንደሚችል ታውቃላችሁን? ይህስ ከባድ ሕመም የሆነው ለምንድን ነው?
◻ ትካዜን ለመዋጋት የሚቻልባቸውን አንዳንድ መንገዶች ጥቀሱ። ትካዜን ለመዋጋት ይረዳሉ ተብለው ከቀረቡት ከእነዚህ ሐሳቦች ውስጥ እናንተ ሞክራችሁ የተጠቀማችሁበት አለን?
◻ ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ሲደርስባችሁ ችግራችሁን ገልጣችሁ መናገር ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
[በገጽ 106 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች የራሳቸውን ሕይወት እንዲያጠፉ ካደረጓቸው የተለመዱ ምክንያቶች በዋነኛነት የሚጠቀሰው ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ነው
[በገጽ 112 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ከአምላክ ጋር የግል ዝምድና ማበጀት ከባድ የመንፈስ ጭንቀትን ለመቋቋም ሊረዳችሁ ይችላል
[በገጽ 107 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ሊሆን ይችላልን?
ማንኛውም ሰው ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ባይኖርበትም አልፎ አልፎ ከሚከተሉት ስሜቶች አንዱ ወይም ብዙው ሊሰማው ይችላል። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ምልክቶች ረዘም ላለ ጊዜ ቆይተውባችሁ ከሆነ ወይም አንዱም ቢሆን የተለመደ ተግባራችሁን ማከናወን እስኪሳናችሁ ድረስ ከባድ ከሆነባችሁ (1) አካላዊ ሕመም ሊኖርባችሁ ይችላልና የተሟላ የሕክምና ምርመራ ያስፈልጋችኋል ወይም (2) ከባድ የአእምሮ ሕመም ማለትም ከባድ የመንፈስ ጭንቀት ሊኖርባችሁ ይችላል።
ምንም ነገር አያስደስታችሁም። በአንድ ወቅት ትደሰቱባቸው በነበሩት ተግባሮች እንኳን መደሰት ያቅታችኋል። መንፈሳችሁ እየተሸበረ ለይምሰል ብቻ ወዲያና ወዲህ የምትንቀሳቀሱ በሕልም ውስጥ ያላችሁ መስሎ ይሰማችኋል።
ፈጽሞ ዋጋ ቢስ የመሆን ስሜት። የእናንተ ሕይወት ለሌላ ሰው የሚያበረክተው ጠቃሚ ነገር እንደሌለውና ጨርሶ ዋጋ ቢስ እንደሆነ ይሰማችኋል። ከፍተኛ የሆነ የበደለኛነት ስሜት ሊሰማችሁ ይችላል።
ከፍተኛ የሆነ የጠባይ ለውጥ። ባንድ ወቅት ተግባቢ ከነበራችሁ አሁን ግን ራሳችሁን የምታገልሉ ልትሆኑ ትችላላችሁ፤ ራሳችሁን የምታገልሉ ከነበራችሁ ደግሞ አሁን ተግባቢ ትሆናላችሁ። ብዙ ጊዜ ታለቅሱ ይሆናል።
ፈጽሞ ተስፋ ቢስ የመሆን ስሜት። ነገሮች በጣም መጥፎ እንደሆኑና ሁኔታችሁን ለመለወጥ ምንም ልታደርጉ እንደማትችሉ እንዲሁም መጥፎዎቹ ሁኔታዎች ፈጽሞ ሊሻሻሉ እንደማይችሉ ይሰማችኋል።
ሞት ትመኛላችሁ። የሚሰማችሁ ምሬት ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ብትሞቱ የሚሻላችሁ መስሎ ዘወትር ይሰማችኋል።
ሐሳባችሁን መሰብሰብና በአንድ ነገር ላይ ማተኮር ይሳናችኋል። አንድ ዓይነት ሐሳብ እየደጋገመ ይመጣባችኋል ወይም የምታነቡትን ነገር መረዳት ያቅታችኋል።
ያመጋገብ ወይም እዳሪ የመውጣት ልማድ መለወጥ። የምግብ ፍላጎት ማጣት ወይም ከልክ በላይ መብላት። አልፎ አልፎ ሆድ ድርቀትና ተቅማጥ ይፈራረቅባችኋል።
የእንቅልፍ ልማድ መለወጥ። በጣም ትንሽ ወይም ከልክ ያለፈ እንቅልፍ መተኛት። ብዙ ጊዜ ያቃዣችሁ ይሆናል።
የሕመም ስሜትና ውጋት። ራስ ምታት፣ ቁርጠት፣ የሆድና የደረት ውጋት ያሠቃያችኋል። ሁልጊዜ አለበቂ ምክንያት ድካም ይሰማችኋል።
[በገጽ 108 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንድ ወጣት ወላጆቹ እንደ ሚጠብቁበት ለመሆን አለመቻሉ የመንፈስ ጭንቀት እንዲያድርበት ሊያደርግ ይችላል
[በገጽ 109 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ችግራችሁን ለሌሎች መናገርና ልባችሁን ማፍሰስ የመንፈስ ጭንቀትን ለመቋቋም ከሚረዷችሁ ጥሩ መንገዶች አንዱ ነው
[በገጽ 110 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሌሎችን የሚጠቅም ነገር ማድረግ ትካዜን ለማሸነፍ የሚረዳ ሌላው መንገድ ነው