በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያህል ማዘን የጤና ነውን?

ይህን ያህል ማዘን የጤና ነውን?

ምዕራፍ 16

ይህን ያህል ማዘን የጤና ነውን?

ሚቼል አባቱ የሞቱበትን ቀን ያስታውሳል፦ “በጣም ደንግጬ ነበር። . . . በልቤ ‘እውነት ሊሆን አይችልም’ እያልኩ ለራሴ እናገር ነበር።”

ምናልባት የምትወዱት ሰው፣ ወላጅ፣ ወንድም፣ እህት ወይም ጓደኛ ሞቶባችሁ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ኀዘን ብቻ ሳይሆን ንዴት፣ ግራ መጋባትና ፍርሃት ሊሰማችሁ ይችላል። ምንም ያህል ብትጥሩ እንባችሁን መግታት ያቅታችኋል። ወይም ደግሞ የኀዘኑን ሰቆቃ በልባችሁ አምቃችሁ ትይዙ ይሆናል።

በእርግጥም የምንወደው ሰው ሲሞት ስሜታችን በኀዘን መነካቱ ያለ ነገር ነው። ኢየሱስ ክርስቶስም እንኳ የቅርብ ወዳጁ መሞቱን ሲሰማ “እንባውን አፈሰሰ” እንዲሁም “በመንፈሱ አዘነ በራሱም ታወከ።” (ዮሐንስ 11:​33–36፤ ከ2 ሳሙኤል 13:​28–39 ጋር አወዳድሩ።) እናንተ የሚሰማችሁ ዓይነት ስሜት የተሰማቸው ሰዎች እንደነበሩ ማወቃችሁ ኀዘናችሁን በተሻለ ሁኔታ እንድትቋቋሙ ይረዳ ­ችኋል።

የሚወዱት ሰው መሞቱን ለመቀበል አሻፈረኝ ማለት

መጀመሪያ ላይ በኀዘኑ ምክንያት የመደንዘዝ ስሜት ይሰማችሁ ይሆናል። ምናልባትም በልባችሁ ክፉ ሕልም በማየት ላይ እንዳላችሁና አንድ ሰው መጥቶ ከእንቅልፋችሁ እንደሚቀሰቅሳችሁና ነገሮች እንደወትሯቸው እንደሚሆኑ ተስፋ ታደርጉ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል የሲንዲ እናት ባደረባት የካንሰር በሽታ ምክንያት ሞተች። ሲንዲ እንደሚከተለው በማለት ትገልጻለች፦ “በእርግጥ መሞቷን አምኜ ለመቀበል አልቻልኩም። ቀደም ሲል ከእርሷ ጋር ተነጋግረንበት የነበረ ነገር ሲያጋጥመኝ በልቤ ‘ቆይ ይህን ለእማዬ እነግራታለሁ’ እያልኩ አስባለሁ።”

የሚወዱት ሰው የሞተባቸው ሰዎች ወዳጃቸው ወይም ዘመዳቸው መሞቱን መቀበል ያቅታቸዋል። እንዲያውም ድንገት ሟቹን በመንገድ ላይ ሲሄድ ወይም በአውቶቡስ ላይ ሆኖ ሲያልፍ ያዩት ሊመስላቸው ይችላል። ከሟቹ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ሰው ውልብ ሲልባቸው ያ ሰው ሞቷል መባሉ ስህተት ሊሆን ይችላል የሚል ስሜት ሊቀሰቀስባቸው ይችላል። አምላክ ሰውን እንዲኖር እንጂ እንዲሞት እንዳልፈጠረው አስታውሱ። (ዘፍጥረት 1:​28፤ 2:​9) ስለዚህ ሞትን ለመቀበል መቸገራችን በተፈጥሮ ያለ ነገር ነው።

“እንዴት እንዲህ ታደርገኛለች?”

በሞተው ሰው ላይ የምትናደዱበት ጊዜ ቢያጋጥማችሁ አትደነቁ። ሲንዲ “እማዬ ስትሞት ‘ግን እኮ እንደምትሞቺ አልነገርሽንም። እንዲሁ ብቻ ሹልክ ብለሽ ሄድሽ’ እያልኩ የማስብባቸው ጊዜያት ነበሩ። እንደተከዳሁ ሆኖ ይሰማኝ ነበር” ብላለች።

የወንድም ወይም የእህት መሞትም እንደዚህ የመሰሉትን ስሜቶች ሊቀሰቅስ ይችላል። “በሞተ ሰው መናደድ ተገቢ አይደለም ለማለት ያስደፍራል” ትላለች ካረን ስትገልጽ፣ “እህቴ ስትሞት ግን በጣም አናደደችኝ። ‘እንዴት ብቻዬን ትታኝ ትሞታለች? ምን በደልኳትና እንዲህ አደረገችኝ?’ የሚለውን የመሰሉ ሐሳቦች በጭንቅላቴ ውስጥ ይመላለሱ ነበር።” አንዳንዶች የእህታቸው ወይም የወንድማቸው ሞት ባስከተለባቸው ኀዘን ምክንያት በሟቹ ይናደዳሉ። አንዳንዶች ደግሞ ወንድማቸው ወይም እህታቸው ከመሞቱ ወይም ከመሞቷ በፊት የወላጆቻቸው ጊዜና ትኩረት ሁሉ በሕመምተኛው ወይም በሕመምተኛዋ ላይ ስለዋለ እነርሱ ችላ እንደተባሉ ሊሰማቸውና ምናልባትም ቅሬታ ሊያድርባቸው ይችላል። በኀዘን የቆሰሉት ወላጆች ሌላው ልጃቸው እንዳይሞትባቸው በመፍራት ከልክ በላይ ስለሚቆጣጠሩት በሟቹ ላይ የጥላቻ ስሜት ሊቀሰቅስበት ይችላል።

“ . . . ቢሆን ኖሮ”

ብዙ ጊዜ የበደለኛነት ስሜት ያጋጥማል። ጥያቄዎችና ጥርጣሬዎች ወደ አእምሮ ይጎርፋሉ። ‘ልናደርግ የምንችለው ነገር ይኖር ነበረን? ሌላ ሐኪም ማማከር ይገባን ነበረን?’ ከዚያም ነገሩ ሁሉ እንዲህ ቢሆን ኖሮ ወይም እንዲህ ባይሆን ኖሮ ብቻ ይሆናል። ‘ያንን ያህል ባንጣላ ኖሮ።’ ‘ደግ ብሆንለት ወይም ብሆንላት ኖሮ።’ ‘ወደ ሱቅ እሱ ከሚሄድ ወይም እርሷ ከምትሄድ እኔው ሄጄ ቢሆን ኖሮ።’

ሚቼል “አባቴን ይበልጥ ብታገሠውና ስሜቱን ብረዳለት ኖሮ ወይም ከሥራ ሲመለስ ዕረፍት እንዲያገኝ በቤት ውስጥ አንዳንድ ነገሮችን ብሠራለት ኖሮ እንዲህ አይሆንም ነበር” ብሏል። ኤሊሳ ደግሞ “እናቴ ታማ በድንገት ከመሞቷ በፊት እርስ በርስ የተቃቃርንባቸው ነገሮች ነበሩ። አሁን ከፍተኛ የበደለኛነት ስሜት ይሰማኛል። ምን ማለት እንደነበረብኝ፣ ምን ማለት እንዳልነበረብኝ፣ ምን በደል እንደሠራሁ አስባለሁ” ብላለች።

አልፎ ተርፎም ለደረሰው ነገር ምክንያት እንደሆናችሁ ይሰማችሁ ይሆናል። ሲንዲ “ከእርሷ ጋር ስለተጨቃጨቅነው ነገር ሁሉ፣ ስላስከተልኩባት ጭንቀት ሁሉ የበደለኛነት ስሜት ይሰማኛል። ያስከተልኩባት ጭንቀት ሁሉ ለሕመሟ ምክንያት ሆኖ ይሆናል ብዬ አስባለሁ” ብላለች።

ለጓደኞቼ ምን ብዬ እነግራቸዋለሁ?”

ባሏ የሞተባት አንዲት ሴት ስለ ወንድ ልጅዋ ስትናገር “ጆኒ አባቱ እንደሞተ ለሌሎች ልጆች መናገር ያስጠላዋል፣ ያሳፍረዋል፣ ማፈሩ ደግሞ ያናድደዋል” ብላለች።

ዴዝ ኤንድ ግሪፍ ኢን ዘ ፋምሊ የተሰኘው መጽሐፍ እንደሚከተለው ተናግሯል፦ “‘ለጓደኞቼ ምን ብዬ እነግራቸዋለሁ?’ የሚለው ጥያቄ ወንድም ወይም እህት ለሞተባቸው ልጆች ከሁሉ ይበልጥ የሚያሳስብ ጥያቄ ነው። ብዙውን ጊዜም የደረሰባቸውን ጭንቀት ጓደኞቻቸው እንደማይረዱላቸው ይሰማቸዋል። ኀዘናቸውን ለመግለጽ ለሚያደርጉት ሙከራ ከሌሎች የሚያገኙት ምላሽ አፍጥጦ መመልከትና እርስ በርስ በጥያቄ ዓይን መተያየት ሊሆን ይችላል። . . . በዚህም ምክንያት ወንድም ወይም እህት የሞተበት ወጣት ተቀባይነትን እንዳጣ፣ ከሌሎች የተገለለ አንዳንድ ጊዜም የሚቃዥ ሊመስለው ይችላል።”

ይሁንና አንዳንድ ጊዜ ሌሎች ላዘነ ጓደኛቸው ምን እንደሚሉ እንደማያውቁና በዚህም ምክንያት ምንም ሳይናገሩ ዝም እንደሚሉ መገንዘብ ይገባችኋል። በእናንተ ላይ የደረሰው ኀዘን እነርሱም የሚወዱትን ሰው በሞት ሊያጡ እንደሚችሉ ሊያሳስባቸው ይችላል። ይህን ለማሰብ ስለማይፈልጉም ሊሸሿችሁ ይችላሉ።

ኀዘኑን መጋፈጥ

የምትወዱት ሰው ስለሞተባችሁ ማዘናችሁ በተፈጥሮ ያለ ነገር መሆኑን ማወቅ ኀዘኑን እንድትቋቋሙት የሚረዳ ትልቅ ነገር ነው። የደረሰውን ነገር አለመቀበል ግን ኀዘኑን ከማራዘም በስተቀር የሚፈይደው ነገር አይኖርም። አንዳንድ ጊዜ የሞተው የቤተሰብ አባል ገበታ ላይ ቀርቦ የሚበላ ይመስል ባዶ ሥፍራ ይተውለታል። ይሁንና አንድ ቤተሰብ ከዚህ የተለየ ነገር ለማድረግ መርጧል። እናቲቱ እንዲህ ትላለች፦ “ከዚያ ወዲያ በማድ ቤቱ ገበታ ላይ እንደ ቀድሞው አቀማመጣችን ተቀምጠን አናውቅም። ባለቤቴ የዴቪድን መቀመጫ ስለያዘ የተፈጠረውን ክፍት ቦታ ለመሙላት ችለናል” ትላለች።

ማድረግና መናገር የነበረባችሁና ያልነበረባችሁ ነገሮች ሊኖሩ ቢችሉም አብዛኛውን ጊዜ የምትወዱት ሰው የሞተው በዚህ ምክንያት እንዳልሆነ መገንዘብ ይረዳችኋል። በተጨማሪም “ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለን።”​— ያዕቆብ 3:​2

የሚሰማችሁን ስሜት ለሌሎች ማካፈል

ዶክተር ኧርል ግሮልማን የሚከተለውን ምክር ሰጥተዋል፦ “እርስ በርሱ የሚካሰሰውን ስሜታችሁን ለይታችሁ ማወቅ ብቻውን አይበቃም። በግልጽ ልትቋቋሙት ይገባል። . . . ይህ ጊዜ ስሜታችሁን ለሌሎች ማካፈል የሚገባችሁ ጊዜ ነው።” በዚህ ጊዜ ራሳችሁን ከሌሎች ማግለል የለባችሁም።​— ምሳሌ 18:​1

ኀዘን የደረሰባችሁ መሆኑን ብትክዱ “ሰቆቃው ለረዥም ጊዜ እንዲቆይ ከማድረግና ኀዘኑን ከማራዘም በቀር ምንም አትፈይዱም” በማለት ዶክተር ግሮልማን ይመክራሉ። “የሚሰሟችሁ ብዙ ስሜቶች ከደረሰባችሁ መራራ ኀዘን አንጻር በማንም ላይ የሚደርሱ መሆናቸውን የሚረዳላችሁ ጥሩ አድማጭ ጓደኛ ፈልጉ” በማለት ይመክራሉ። ብዙውን ጊዜ ወላጅ፣ ወንድም፣ እህት፣ ጓደኛ ወይም በክርስቲያን ጉባኤ ያለ ሽማግሌ እውነተኛ ድጋፍ ሊሰጣችሁ ይችላል።

አልቅስ አልቅስ የሚል ስሜት ቢመጣባችሁስ? ዶክተር ግሮልማን በመጨመር “ለአንዳንዶቹ ወንዶችና ሴቶች እንዲሁም ልጆች እንባ ማፍሰስ የደረሰባቸውን የስሜት ጭንቀት የሚፈውስ ከሁሉ የበለጠ ሕክምና ነው። ማልቀስ ጭንቀትን ለማቅለልና ኀዘንን ለመወጣት የሚያስችል ተፈጥሮአዊ መንገድ ነው” ብለዋል።

በቤተሰብ ደረጃ አንድ ላይ ተባብሮ መቋቋም

ኀዘን በሚደርስባችሁ ጊዜ ወላጆቻችሁ ከፍተኛ የእርዳታ ምንጭ ሊሆኑላችሁ ሲችሉ እናንተም እነርሱን ልትረዷቸው ትችላላችሁ። ለምሳሌ ያህል እንግሊዝ አገር የሚኖሩት ጄንና ሣራ፣ ዳራል የሚባለው የ23 ዓመት ወንድማቸው ሞተባቸው። ታዲያ ኀዘኑን የተቋቋሙት እንዴት ነበር? ጄን “አሁን አራት ስለሆንን እኔ የማደርገውን ማንኛውም ነገር ከአባቴ ጋር ሆኜ ስሠራ ሣራ ደግሞ ሁልጊዜ ­ከእማማ ጋር ትሠራለች። በዚህ መንገድ ማናችንም ብቻችንን አንሆንም ነበር” በማለት መልስ ትሰጣለች። በተጨማሪም ጄን “ከዚያ በፊት አባቴ ሲያለቅስ አይቼው አላውቅም ነበር። ወንድማችን ሲሞት ግን አንድ ሁለት ጊዜ ያህል አለቀሰ፤ ይህም ባንድ በኩል ጥሩ ነበር፤ አሁን መለስ ብዬ ሳስበው ባጠገቡ ሆኜ ላጽናናው መቻሌ አስደስቶኛል” ብላለች።

ኃይል የሚሰጥ ተስፋ

ዴቪድ የተባለ እንግሊዛዊ ወጣት ጃኔት የተባለች የ13 ዓመት እህቱ ሆጅኬንዝ በሚባል በሽታ ሞተችበት። እንዲህ ብሏል፦ “በጣም ከጠቀሙኝ ነገሮች አንዱ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ንግግር ላይ የተጠቀሰ አንድ ጥቅስ ነበር። እርሱም እንዲህ ይላል፦ ‘[አምላክ] ቀን ቀጥሮአልና፣ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፤ ስለዚህም [ኢየሱስን] ከሙታን በማስነሳቱ ሁሉን አረጋግጦአል [“ለሰው ሁሉ ዋስትና ሰጥቷል።” [አዓት ]’ ተናጋሪው ‘ዋስትና’ የሚለውን ቃል ጠበቅ አድርጎት ነበር። ይህ ንግግር ከቀብር ሥነ ሥርዓቱ በኋላ ከፍተኛ የሆነ የብርታት ምንጭ ሆኖልኛል።”​— ሥራ 17:​31፤ በተጨማሪም ማርቆስ 5:​35–42፤ 12:​26, 27፤ ዮሐንስ 5:​28, 29፤ 1 ቆሮንቶስ 15:​3–8ን ተመልከቱ።

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጸው የትንሣኤ ተስፋ ኀዘንን ጨርሶ አያጠፋም። የምትወዱትን በሞት የተለያችሁን ሰው ፈጽሞ ልትረሱት አትችሉም። ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች እውነተኛ መጽናኛ ለማግኘት በመቻላቸው ቀስ በቀስ ከደረሰባቸው ኀዘን ማገገም ጀምረዋል።

የመወያያ ጥያቄዎች

◻ የምትወዱት ሰው ሲሞትባችሁ ማዘን በተፈጥሮ ያለ ነገር መሆኑ ይሰማችኋልን?

◻ የሚወደው ሰው ሞቶበት ያዘነ ሰው ምን ዓይነት ስሜቶች ሊሰሙት ይችላሉ? ለምንስ?

◻ የሚወደው ሰው በሞት የተለየው ኀዘንተኛ ወጣት ስሜቶቹን መቋቋም የሚችልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?

◻ የሚወደው ሰው የሞተበትን ጓደኛችሁን ልታጽናኑ የምትችሉት እንዴት ነው?

[በገጽ 128 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“መሞቷን አምኜ መቀበል አልቻልኩም።. . . በልቤ ‘ቆይ ይህን ለእማዬ እነግራታለሁ’ እያልኩ አስባለሁ”

[በገጽ 131 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“እማማ ስትሞት  . . ‘ግን እኮ እንደምትሞቺ አልነገርሽንም። እንዲሁ ብቻ ሹልክ ብለሽ ሄድሽ’ እያልኩ አስብ ነበር። እንደተከዳሁ ሆኖ ይሰማኝ ነበር”

[በገጽ 129 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ይህ ነገር ሕልም ነው እንጂ በእርግጥ በእኔ ላይ አልደረሰብኝም!”

[በገጽ 130 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የምንወደው ሰው በሞት ሲለየን ርህሩህ የሆነ ሰው የሚሰጠን ማጽናኛ ያስፈልገናል