በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሐቀኝነት በእርግጥ ከሁሉ የተሻለ መመሪያ ነውን?

ሐቀኝነት በእርግጥ ከሁሉ የተሻለ መመሪያ ነውን?

ምዕራፍ 27

ሐቀኝነት በእርግጥ ከሁሉ የተሻለ መመሪያ ነውን?

እንድትዋሹ የሚያደርጋችሁ ኃይለኛ ግፊት ተሰምቷችሁ ያውቃልን? ዶናልድ ክፍሉን አጽድቶ እንደጨረሰ ለእናቱ ይነግራታል። እርሱ ግን ቆሻሻውን በሙሉ ወደ አልጋው ሥር ወረወረ እንጂ አላጸዳውም ነበር። ሪቻርድም በወላጆቹ ላይ ከዚህ ያላነሰ ዓይን ያወጣ የማጭበርበር ሙከራ አድርጓል። በፈተና የወደቀው ሳያጠና ቀርቶ ሳይሆን ‘መምህሩ ስለማይወደው’ እንደሆነ ነግሯቸዋል።

አብዛኛውን ጊዜ ወላጆችና ሌሎች ትልልቅ ሰዎች ጥፋትን ለመሸፋፈን የሚደረጉ እንደነዚህ የመሰሉትን ግልጽ ማጭበርበሪያዎች ማወቅ አያቅታቸውም። ሆኖም ብዙ ወጣቶች ሌሎች የሚያውቁባቸው መሆኑ ቢገባቸውም የሚጠቅማቸው ከመሰላቸው ቢያንስ ቢያንስ ለመዋሸት ከመሞከር፣ እውነቱን ከማጣመም፣ ወይም ቀጥተኛ ማታለል ከመፈጸም ወደኋላ አይሉም። መጀመሪያ ነገር ወላጆች አንድ ጥፋት ተሠርቶ ሲያገኙ ሁልጊዜ በዝምታ አያልፉም። እቤት መድረስ ከሚገባችሁ ጊዜ ሁለት ሰዓት አሳልፋችሁ ስትመጡ ጊዜው ሳታስቡት እንዳለፈባችሁ ገልጻችሁ በወቅቱ የሚያሳፍራችሁን እውነት ከመናገር ይልቅ በመንገዳችሁ ላይ ከባድ አደጋ እንዳጋጠማችሁ ለመናገር ትገፋፉ ይሆናል።

ትምህርት ቤት ደግሞ ሐቀኝነትን የሚፈታተን ሌላ ሁኔታ ሊደቅንባችሁ ይችላል። ብዙውን ጊዜ ተማሪዎች የቤት ሥራ እንደሚበዛባቸው ይሰማቸዋል። ብዙውን ጊዜም ጉሮሮ ለጉሮሮ የሚያስተናንቅ ፉክክር ይኖራል። በዩናይትድ ስቴትስ የተደረጉት ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከጠቅላላው ተማሪዎች ግማሽ የሚሆኑት በፈተና ያጭበረብራሉ ወይም አጭበርብረዋል። የሆነ ሆኖ መዋሸት ማራኪ መስሎ ሊቀርብና ማጭበርበር ደግሞ ቀላል ማምለጫ ሊመስል ቢችልም በእርግጥ ማታለል ያዋጣልን?

ውሸት የማያዋጣበት ምክንያት

ከቅጣት ለማምለጥ ብሎ መዋሸት ለጊዜው ጠቃሚ መስሎ ሊታይ ይችላል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “በሐሰት የሚናገር አያመልጥም” በማለት ያስጠነቅቃል። (ምሳሌ 19:​5) ውሸቱ የመጋለጡና ቅጣት የማስከተሉ አጋጣሚ በጣም ከፍተኛ ነው። እንግዲያስ ወላጆቻችሁ መጀመሪያ በሠራችሁት ጥፋት ብቻ ሳይሆን በመዋሸታችሁ ጭምር በጣም ይናደዳሉ!

በትምህርት ቤት ፈተና አጭበርብሮ ስለማለፍስ ምን ሊባል ይቻላል? የትምህርት ቤት የፍትሕ ፕሮግራሞች ዲሬክተር የሆኑ አንድ ሰው እንደሚከተለው ይላሉ:- “ፈተና የሚሰርቅ ወይም የሚያጭበረብር ማንኛውም ተማሪ በወደፊት የትምህርትና የሥራ ዕድሉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያመጣል።”

እውነት ነው፣ ብዙዎች እያጭበረበሩ ከቅጣት የሚያመልጡ ይመስላል። በፈተና ማጭበርበር የማለፊያ ውጤት ሊያስገኝላችሁ ይችላል፤ ይሁን እንጂ ማጭበርበሩ የሚያስከትላቸው የረዥም ጊዜ ውጤቶች ምንድን ናቸው? የዋና ትምህርት የምትማሩ ብትሆኑ የሚሰጣችሁን ፈተና አታልላችሁ ለማለፍ መሞከር ትልቅ ሞኝነት እንደሚሆን አለጥርጥር ትስማማላችሁ። ለምን ቢባል ሁሉ ሰው ደስ ብሎት ሲዋኝ መሬት ላይ ቁጭ ብሎ ለመመልከት የሚፈልግ የለማ! ወደ መዋኛው ኩሬ ተገፍታችሁ ብትጣሉ ደግሞ አጭበርባሪነታችሁ እስከ መስጠም ያደርሳችኋል!

ይሁን እንጂ በሒሳብ ትምህርት ወይም በንባብ ፈተና ላይ አጭበርብራችሁ ብታልፉስ? እውነት ነው፣ በእነዚህ ፈተናዎች ላይ ማጭበርበራችሁ በዋና ትምህርት ላይ ማጭበርበራችሁ የሚያስከትለውን የመሰለ ግልጽ ጉዳት አያስከትልባችሁ ይሆናል። ይሁን እንጂ መሠረታዊ የሆኑ የትምህርት ችሎታዎችን ካላዳበራችሁ በሥራ ዓለም ውስጥ “ልትሰጥሙ” ትችላላችሁ! በማታለል የተገኘ ዲፕሎማ ከመስጠም አያድንም። መጽሐፍ ቅዱስ “በሐሰተኛ ምላስ መዝገብ ማከማቸት የሚበንን ጉም ነው” ይላል። (ምሳሌ 21:​6) በሐሰት የሚገኙ ማናቸውም ጥቅሞች በቅጽበት በንኖ እንደሚጠፋ ጉም ናቸው። በትምህርት ቤት ሳላችሁ አጭበርብራችሁ ለማለፍ ከመሞከር ይልቅ አእምሮአችሁን ለሥራ አሰባስባችሁ ጠንክራችሁ ብታጠኑ ምንኛ የተሻለ ይሆናል! ምሳሌ 21:​5 “የትጉህ አሳብ ወደ ጥጋብ ያደርሳል” ይላል።

መዋሸትና ሕሊናችሁ

ሚሸል የተባለች አንዲት ወጣት ልጃገረድ ወላጆችዋ ይወዷቸው የነበሩትን ጌጣጌጦች የሰበረው ወንድሟ እንደሆነ በውሸት ለወላጆቿ ተናገረች። በኋላ ግን ውሸት መናገሯን ለወላጆችዋ ለመናዘዝ ተገፋፋች። “በእርግጥ ከፍተኛ ሐዘን ተሰማኝ” በማለት ትገልጻለች “ወላጆቼ ሲያምኑኝ እኔ ግን እንደጠበቁኝ ሳልሆን ቀረሁ።” የዚህች ወጣት ሁኔታ አምላክ በሰው ልጆች ውስጥ የሕሊናን ስጦታ ማስቀመጡን አሳምሮ ያሳያል። (ሮሜ 2:​14, 15) የሚሸል ሕሊና በበደለኛነት ስሜት እንድትሠቃይ አድርጓታል።

እርግጥ አንድ ሰው ሕሊናውን ችላ ለማለት ሊመርጥ ይችላል። ይሁን እንጂ መዋሸትን ልማድ ባደረገ መጠን ‘ሕሊናው በጋለ ብረት እንደተተኮሰ ያህል ሆኖ ስለሚደነዝዝ’ ለጥፋቱ ይበልጥ ደንታ ቢስ እየሆነ ይመጣል። (1 ጢሞቴዎስ 4:​21980 ትርጉም) ታዲያ የደነዘዘ ሕሊና እንዲኖራችሁ ትፈልጋላችሁን?

አምላክ ለውሸት ያለው አመለካከት

“ሐሰተኛ ምላስ” ‘ይሖዋ ከሚጠላቸው’ ነገሮች አንዱ ነበር፤ አሁንም ነው። (ምሳሌ 6:​16, 17) እንዲያውም “የሐሰት አባት” ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። (ዮሐንስ 8:​44) መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ውሸትን ነጭና ጥቁር ብሎ ለሁለት አይከፍልም፣ ወይም በሁለቱ መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት አያደርግም። ‘ውሸትም ሁሉ ከእውነት አይደለም።’​— 1 ዮሐንስ 2:​21

በመሆኑም ሐቀኝነት የአምላክ ወዳጅ ሊሆን ለሚፈልግ ለማንኛውም ሰው መመሪያው ሊሆን ይገባል። የመዝሙር መጽሐፍ 15ኛ ምዕራፍ “አቤቱ፣ [“ይሖዋ” አዓት] በድንኳንህ ውስጥ ማን ያድራል? በተቀደሰው ተራራህስ ማን ይኖራል?” በማለት ይጠይቃል። (ቁጥር 1) በሚቀጥሉት አራት ቁጥሮች የተሰጠውን መልስ እንመልከት:-

“በቅንነት የሚሄድ፣ ጽድቅንም የሚያደርግ፣ በልቡም እውነትን የሚናገር።” (ቁጥር 2) እንዲህ ያለው ሰው ከትላልቅ ሱቆች ዕቃ ሊሠርቅ ወይም አጭበርባሪ ሊሆን ይችላልን? ወላጆቹን የሚዋሽ ወይም ያልሆነውን ሆኖ ለመታየት የሚያስመስል ሰውስ ሊሆን ይችላልን? በጭራሽ! ስለዚህ የአምላክ ወዳጆች ለመሆን ከፈለጋችሁ በተግባራችሁ ብቻ ሳይሆን በልባችሁም ጭምር ሐቀኛ መሆን ያስፈልጋችኋል።

“የሌሎች ሰዎችን ስም የማያጠፋ፣ በጓደኞቹ ላይ ክፉ ነገር የማያደርግ፣ ጎረቤቶቹን የማያማ።” (ቁጥር 31980 ትርጉም) ስለ ሌሎች ሰዎች መጥፎና ክብር ነክ ነገር ከሚናገሩ ወጣቶች ጋር ተባብራችሁ ታውቃላችሁን? በእንዲህ ዓይነቱ ወሬ ለመካፈል እምቢ ለማለት የሚያስችል ጥንካሬ አዳብሩ!

“ኃጢአተኛ በፊቱ የተናቀ፣ እግዚአብሔርንም የሚፈሩትን የሚያከብር፣ ምንም ያህል ከባድ ቢሆን የገባውን ቃል ኪዳን የሚፈጽም” (ቁጥር 41980 ትርጉም) ከሚዋሹ፣ ከሚያታልሉ፣ ወይም ደግሞ ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ተግባር መፈጸማቸውን በጉራ ከሚናገሩ ሰዎች ጋር ጓደኞች አትሁኑ። ምክንያቱም እናንተም እንደነሱ እንድታደርጉ ይጠብቁባችኋል። ቦቢ የተባለ ወጣት እንደታዘበው “እንድትዋሹ የሚያደርግ ጓደኛ ችግር ውስጥ ያስገባችኋል። እንዲህ ዓይነቱ ሰው ልታምኑት የምትችሉት ጓደኛ አይደለም።” የሐቀኝነትን የአቋም ደረጃ የሚያከብሩ ጓደኞችን ፈልጉ።​— ከመዝሙር 26:​4 ጋር አወዳድሩ።

ይሖዋ የገቡትን ቃል ኪዳን የሚጠብቁ ሰዎችን እንደሚያደንቅ ወይም “እንደሚያከብር” አስተውላችኋልን? ምናልባት እናንተም በመጪው ቅዳሜ ወላጆቻችሁን በቤት ውስጥ ሥራ እንደምትረዱ ቃል ገብታችሁ ይሆናል። አሁን ግን በዚያ ዕለት ከሰዓት በኋላ የኳስ ጨዋታ እንድትመለከቱ ጓደኞቻችሁ ቢጋብዟችሁስ? የገባችሁትን ቃል እንደዋዛ በመቁጠር ወላጆቻችሁ አድካሚውን ሥራ ብቻቸውን እንዲሠሩ ትታችኋቸው ትሄዳላችሁ ወይስ ቃላችሁን ትጠብቃላችሁ?

“ገንዘቡን በአራጣ የማያበድር፣ በንጹሑ ላይ መማለጃን የማይቀበል። እንዲህ የሚያደርግ ለዘላለም አይታወክም።” (ቁጥር 5) የማጭበርበርና የቃል አባይነት ዋናው ምክንያት ስግብግብነት መሆኑ እውነት አይደለምን? በፈተና ላይ የሚያጭበረብሩ ተማሪዎች ያላጠኑበትን ውጤት ለማግኘት የሚስገበገቡ ናቸው። ጉቦ የሚቀበሉ ሰዎች ከፍትሕ ይልቅ ለገንዘብ ከፍተኛ ግምት የሚሰጡ ናቸው።

አንዳንዶች፣ የፖለቲካና የትላልቅ ድርጅቶች መሪዎች እንኳን የግል ጥቅም ለማግኘት ሲሉ የሐቀኝነት ሕጎችን ያጣምሙ የለምን? ይሉ ይሆናል። ይሁን እንጂ የሐቀኝነትን ደንብ የሚያጣምሙ ሰዎች የሚያገኙት ውጤትና ጥቅም ምን ያህል አስተማማኝ ነው? መዝሙር 37:​2 “እንደ ሣር ፈጥነው ይደርቃሉና፣ እንደ ለመለመ ቅጠልም ይረግፋሉ” በማለት መልስ ይሰጣል። ሲያጭበረብሩ ተይዘው ባይዋረዱም እንኳን በመጨረሻ የይሖዋ አምላክ ፍርድ ይጠብቃቸዋል። የአምላክ ወዳጆች ግን “ከቶ አይናወጡም።” ዘላለማዊ የሆነው የወደፊት ሕይወታቸው አስተማማኝ ነው።

“ሐቀኛ ሕሊና” ማዳበር

እንግዲያውስ ማንኛውንም ዓይነት ውሸት እንድናስወግድ የሚገፋፋን ጠንካራ ምክንያት አለ አይደለምን? ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ራሱና ስለ ባልንጀሮቹ ሲናገር “ሐቀኛ ሕሊና እንዳለን እንተማመናለን” ብሏል። (ዕብራውያን 13:​18 አዓት) የእናንተስ ሕሊና እውነት ያልሆነ ነገር ይቆረቁረዋልን? የማይቆረቁረው ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስንና እንደ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! የመሳሰሉትን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች በማጥናት ሕሊናችሁን አሰልጥኑ።

ወጣቱ ቦቢ እንዲህ አድርጓል፤ ጥሩ ውጤትም አግኝቷል። ስሕተቶቹን በተተበተበ ውሸት አለመሸፈንን ተምሯል። ወደ ወላጆቹ ቀርቦ ነገሮችን በሐቀኝነት እንዲያወያያቸው ሕሊናው ይገፋፋዋል። ይህን ማድረጉ አንዳንድ ጊዜ ቅጣት አስከትሎበታል። ይሁን እንጂ ሐቀኛ በመሆኑ ‘በውስጡ ጥሩ ስሜት እንደሚሰማው’ አምኗል።

እውነቱን መናገር ሁልጊዜ ቀላል አይሆንም። ይሁን እንጂ እውነቱን ለመናገር ውሳኔ ያደረገ ሰው ጥሩ ሕሊና ይኖረዋል፣ ከሚወዳቸው ወዳጆቹ ጋር ጥሩ ዝምድና ይኖረዋል፤ ከሁሉ ይበልጥ ደግሞ በአምላክ ድንኳን ውስጥ ‘እንግዳ ሆኖ የማደር’ መብት ያገኛል! እንግዲያስ ሐቀኝነት ከሁሉ የተሻለ መመሪያ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ክርስቲያኖች ሊከተሉት የሚገባ ትክክለኛ መመሪያ ነው።

የመወያያ ጥያቄዎች

◻ ውሸት ለመናገር የሚፈትኑ አንዳንድ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?

◻ መዋሸት ወይም ማታለል የማያዋጣው ለምንድን ነው? ይህንንስ በግል የታዘባችሁትን ወይም ራሳችሁ ያጋጠማችሁን ምሳሌ በማድረግ ልታስረዱ ትችላላችሁን?

◻ ውሸታም ሰው ሕሊናውን የሚያበላሸው እንዴት ነው?

◻ መዝሙር 15ን አንብቡ። ቁጥሮቹ በሐቀኝነት ጉዳይ ላይ ተፈጻሚነት የሚኖራቸው እንዴት ነው?

◻ አንድ ወጣት ሐቀኛ ሕሊና ሊያዳብር የሚችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 212 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

‘ፈተና የሚሰርቅ ወይም የሚያጭበረብር ማንኛውም ተማሪ በወደፊት የትምህርትና የሥራ ዕድሉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያመጣል’

[በገጽ 216 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

መጽሐፍ ቅዱስ በውሸትና ነጭ ውሸት ተብለው በሚጠሩት መካከል ምንም ልዩነት አያደርግም

[በገጽ 214 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አብዛኛውን ጊዜ ልጆች ላለመታዘዝ የሚያቀርቡትን ሰንካላ ምክንያት ወላጆች ማወቃቸው አይቀርም