በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ማስተርቤሽን—ምን ያህል አሳሳቢ ችግር ነው?

ማስተርቤሽን—ምን ያህል አሳሳቢ ችግር ነው?

ምዕራፍ 25

ማስተርቤሽን—ምን ያህል አሳሳቢ ችግር ነው?

“ማስተርቤሽን በአምላክ ዓይን ሲታይ ስህተት ይሆንን? እያልኩ አስባለሁ። ለወደፊቱ ባገባ አካላዊና/ወይም አእምሯዊ ጤንነቴን ይነካብኝ ይሆን?”​— የአሥራ አምስት ዓመት ወጣት የሆነችው መሊሳ

እንደዚህ ያሉ ሐሳቦች ብዙ ወጣቶችን ያስጨንቋቸዋል። ለምን? ምክንያቱም ማስተርቤሽን በጣም የተስፋፋ ስለሆነ ነው። እንደሚነገረው ከሆነ 97 በመቶ የሚሆኑ ወንዶችና ከ90 በመቶ የሚበልጡ ሴቶች ዕድሜያቸው 21 ዓመት እስኪሆን ድረስ ማስተርቤሽን ፈጽመዋል። በተጨማሪም ይህ ተግባር ለማንኛውም ዓይነት ደዌ፣ ኪንታሮትና የዓይን ቆብ መቅላት ጀምሮ እስከሚጥል በሽታና የአእምሮ ሕመም ድረስ፣ መንስኤ ነው ተብሎ ሲነገርለት የነበረ ነው።

የሃያኛው መቶ ዘመን የሕክምና ተመራማሪዎች ማስተርቤሽን እንደዚህ ያሉትን አስፈሪ ነገሮች ያመጣል ብለው መናገራቸውን ትተዋል። በእርግጥም በዛሬው ጊዜ ያሉት ሐኪሞች በማስተርቤሽን ምክንያት የሚመጣ ምንም ዓይነት አካላዊ የጤና መታወክ የለም ብለው ያምናሉ። ዊልያም ማስተርስና ቨርጂንያ ጆንሰን የተባሉ ተመራማሪዎች “ማስተርቤሽን የቱንም ያህል ቢዘወተር የሚያስከትለው የአእምሮ ሕመም ለመኖሩ የተረጋገጠ የሕክምና ማስረጃ የለም” በማለት ጨምረው ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ሌሎች ጎጂ ውጤቶች አሉት! ብዙ ክርስቲያን ወጣቶችም በዚህ ተግባር ረገድ የሚጨነቁበት ተገቢ ምክንያት አላቸው። “ለ[ማስተርቤሽን] በምሸነፍበት ጊዜ ይሖዋ አምላክን እንዳሳፈርኩት ይሰማኝ ነበር” በማለት አንድ ወጣት ጽፏል። “አንዳንድ ጊዜ በጣም አዝንና እተክዝ ነበር።”

ይሁንና ማስተርቤሽን ምንድን ነው? ምን ያህልስ አሳሳቢ ችግር ነው? ብዙ ወጣቶች ለመተው ከባድ ሆኖ ያገኙት ልማድ የሆነው ለምንድን ነው?

ወጣቶች በዚህ አድራጎት የሚጠቁበት ምክንያት

ማስተርቤሽን የወሲብ ስሜትን ለመቀስቀስ ሆን ተብሎ የሚደረግ በገዛ እጅ የራስን ፍላጎት ማነሳሳት ነው። በአፍላ ወጣትነት ዕድሜ ወሲባዊ ፍላጎት ያይላል። በመራቢያ ብልቶች ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ኃይለኛ ሆርሞኖች በሰውነት ውስጥ ይለቀቃሉ። በዚህ ምክንያት አንድ ወጣት እነዚህ ብልቶች አስደሳች ስሜቶችን ለመፍጠር እንደሚችሉ ይገነዘባል። አንዳንድ ጊዜም አንድ ወጣት ስለ ወሲብ ሳያስብ እንኳን ፍላጎቱ ሊቀሰቀስበት ይችላል።

ለምሳሌ ያህል በልዩ ልዩ ጭንቀቶች፣ ሥጋቶች ወይም ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች የሚፈጠሩት ውጥረቶች የአንድን ወንድ ልጅ በቀላሉ የሚቆጡ የነርቭ ሥርዓቶች ሊነኩበትና ወሲባዊ መነሳሳትን ሊያስከትሉበት ይችላሉ። የወንዴ ዘር ተሸካሚ የሆነው ፈሳሽ ክምችትም የወሲብ ስሜቱ ተቀስቅሶ ከእንቅልፉ እንዲባንን ሊያደርገው ይችላል። አለበለዚያም በእንቅልፍ ላይ እንዳለ አብዛኛውን ጊዜ ሩካቤ ሥጋ የሚፈጽምበት ሕልም አይቶ ዘሩ ሊፈስበት ይችላል። በተመሳሳይም አንዳንድ ወጣት ልጃገረዶች ሳያስቡት የወሲብ ፍላጎታቸው ይቀሰቀስባቸው ይሆናል። ብዙዎቹ የወር አበባቸው ከመምጣቱ በፊት ወይም ካለፈ በኋላ ከፍተኛ የሆነ ወሲብ ፍላጎት ይኖራቸዋል።

ስለዚህ በዚህ ዓይነት የወሲብ ፍላጎታችሁ ቢቀሰቀስ ምንም የምትረበሹበት ምክንያት የለም። ይህ የወጣት ሰውነት ጤናማ ባሕርይ ነው። እንደዚህ ያሉት ስሜቶች በጣም ኃይለኛ ቢሆኑም እንኳ ­በአብዛኛው የሚቀሰቀሱት አለፍላጎታችሁ በመሆኑ ከማስተርቤሽን ጋር አንድ አይደሉም። እያደጋችሁ ስትሄዱ ደግሞ የእነዚህ አዳዲስ ስሜቶች ኃይል እየቀነሰ ይሄዳል።

የሆነ ሆኖ አንዳንድ ወጣቶች ለማወቅ ባላቸው ጉጉትና በእነዚህ ስሜቶች አዲስነት ምክንያት የጾታ ብልቶቻቸውን ሆን ብለው በገዛ እጃቸው ይቀሰቅሳሉ ወይም ይጫወቱባቸዋል።

ማስተርቤሽን ለመፈጸም ‘የሚቀሰቅሱ’

መጽሐፍ ቅዱስ አንዲት ሴሰኛ ሴት ስለገጠመችው አንድ ወጣት ሰው ይገልጻል። ሳመችውና “ና ሌሊቱን ሙሉ በፍቅር እንርካ” አለችው። ከዚያስ ምን ሆነ? “ወዲያውኑ እርስዋን ተከትሎ ሄደ፤ በሬ ወደሚታረድበት ሥፍራ እንደሚነዳ።” (ምሳሌ 7:​7–221980 ትርጉም) በግልጽ እንደሚታየው የዚህ ወጣት ወሲባዊ ፍላጎት የተቀሰቀሰው በሆርሞኖቹ ምክንያት ሳይሆን ባየውና በሰማው ነገር ምክንያት ነበር።

በተመሳሳይም አንድ ወጣት ሰው እንደሚከተለው ሲል አምኗል:- ‘እቅጩን ለመናገር ከማስተርቤሽን ጋር የነበረኝ ጠቅላላ ችግር መንስኤ ወደ አእምሮዬ የማስገባው ነገር ነው። የብልግና ድርጊቶች የሚታዩባቸውን የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እርቃነ ሥጋ የሚያሳዩ ፕሮግራሞችን በኬብል ቴሌቪዥን ላይ እመለከት ነበር። እንዲህ ዓይነቶቹ ትርዒቶች በጣም አስደንጋጭ ከመሆናቸው የተነሳ ልትረሷቸው አትችሉም። ደጋግመው ወደ አእምሮዬ ስለሚመጡ ማስተርቤሽን እንድፈጽም ይቀሰቅሱኝ ነበር።’

አዎን፣ ብዙውን ጊዜ ማስተርቤሽን ለመፈጸም የሚያነሳሳው አንድ ሰው የሚያነበው፣ የሚመለከተው ወይም የሚያዳምጠውና እንደዚሁም ደግሞ የሚያወራውና የሚያሰላስለው ነገር ነው። አንዲት የ25 ዓመት ሴት እንደተናገረችው “ልማዱን በጭራሽ ማቆም የምችል አይመስለኝም ነበር። ይሁን እንጂ የፍቅር ልብ ወለድ መጻሕፍት አነብ ስለነበር ይህ ደግሞ ለችግሬ ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል” ብላለች።

“ማስታገሻ መድኃኒት”

የዚህች ወጣት ሴት ተሞክሮ ልማዱን ለመተው በጣም ከባድ የሚሆንበትን ትልቅ ምክንያት በማያጠራጥር ሁኔታ ያሳያል። በመቀጠልም እንዲህ ብላለች:- “ብዙውን ጊዜ ማስተርቤሽን እፈጽም የነበረው ግፊት፣ ውጥረት ወይም ጭንቀት በሚያጋጥመኝ ጊዜ እነዚህን ስሜቶች ለመወጣት ነበር። ከዚህ ድርጊት አገኝ የነበረው ቅጽበታዊ ደስታ አንድ የአልኮል መጠጥ የሚያዘወትር ሰው ጭንቀቱን ለማስታገስ ብሎ አልኮል ሲጠጣ የሚሰማውን ስሜት የሚመስል ነበር።”

ሱዛንና ኧርቪንግ ሳርኖፍ የተባሉ ተመራማሪዎች እንደሚከተለው በማለት ጽፈዋል:- “ለአንዳንድ ሰዎች ማስተርቤሽን ተቀባይነት ሲያጡ ወይም በአንድ ነገር ጭንቀት ሲሰማቸው መጽናኛ ለማግኘት ዘወር የሚሉበት ልማድ ይሆንባቸዋል። ይሁን እንጂ ሌሎች ይህን አድራጎት መሸሻ የሚያደርጉት አልፎ አልፎ በጣም ድንገተኛ የሆነ ስሜታዊ ውጥረት በሚደርስባቸው ጊዜ ብቻ ነው።” አንዳንዶች በሚበሳጩበት ጊዜ፣ ሲተክዙ፣ ብቸኝነት ሲሰማቸው ወይም ብዙ ጭንቀት ሲደርስባቸው ወደዚህ ልማድ ይመለሳሉ፤ ለእነርሱ ይህ አድራጎት ችግራቸውን እንደሚያስወግድ “ማስታገሻ መድኃኒት” ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

አንድ ወጣት “ማስተርቤሽን ምሕረት የማይደረግለት ኃጢአት ነውን?” በማለት ጠይቋል። ማስተርቤሽን አንድም ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጠቀሰም። * ይህ አድራጎት በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን በግሪክኛ ተናጋሪው ዓለም የተለመደ ነበር። ስለዚህም ይህን አድራጎት ለመግለጽ የሚያገለግሉ ብዙ የግሪክኛ ቃላት አሉ። ይሁን እንጂ ከእነዚህ ቃላት አንዱም እንኳን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተጠቀሰም።

ማስተርቤሽን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በቀጥታ ያልተወገዘ መሆኑ ምንም ጉዳት የለውም ማለት ነውን? በጭራሽ አይደለም! ምንም እንኳን ዝሙትን ከመሳሰሉት ከባድ ኃጢአቶች ጋር ያልተመደበ ቢሆንም ማስተርቤሽን ርኩስ ልማድ መሆኑ ጥርጥር የለውም። (ኤፌሶን 4:​19) በመሆኑም በአምላክ ቃል ውስጥ የተገለጹት መሠረታዊ ሥርዓቶች ይህንን ርኩስ ልማድ ጠንክራችሁ መቋቋም ‘እንደሚጠቅማችሁ’ ያመለክታሉ።​— ኢሳይያስ 48:​17

“ፍትወት”ን መቀስቀስ

“እንግዲህ በምድር ያሉትን ብልቶቻችሁን ግደሉ፣ እነዚህም ዝሙትና ርኩሰት ፍትወትም . . .” ናቸው በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠነቅቃል። (ቆላስይስ 3:​5) “ፍትወት” የሚያመለክተው የተለመደውን ተፈጥሯዊ የወሲብ ስሜት ሳይሆን ከቁጥጥር ውጭ የሆነውን የወሲብ ፍላጎት ነው። በመሆኑም “ፍትወት” አንድን ሰው ጳውሎስ በሮሜ 1:​26, 27 ላይ እንደገለጸው እጅግ መጥፎ ለሆነ ድርጊት ተገዢ እንዲሆን ሊያደርገው ይችላል።

ታዲያ ማስተርቤሽን እነዚህን ፍላጎቶች “አይገድላቸውምን?” አይገድላቸውም፤ እንዲያውም በተቃራኒ አንድ ወጣት እንደተናገረው “ማስተርቤሽን በምትፈጽሙበት ጊዜ ሐሳባችሁን በተሳሳቱ ምኞቶች ላይ ታሳርፋላችሁ። ይህ ደግሞ ለእነዚህ ድርጊቶች ያላችሁን ምኞት ይጨምራል” ብሏል። ብዙውን ጊዜ በማስተርቤሽን የሚገኘውን ወሲባዊ ደስታ ለመጨመር ከሌላ ሰው ጋር ሩካቤ ሥጋ እንደምትፈጽሙ ሆኖ እንዲታያችሁ ታደርጋላችሁ። (ማቴዎስ 5:​27, 28) ስለዚህ አንድ ግለሰብ ምቹ ሁኔታ ቢያጋጥመው ዝሙት መፈጸሙ አይቀርም። ይህም እንደሚከተለው በማለት በተናገረ አንድ ወጣት ላይ ደርሶበታል:- “ባንድ ወቅት ማስተርቤሽን ከሴት ጋር መገናኘት ሳያስፈልገኝ ጭንቀቴን የሚያስታግስልኝ ይመስለኝ ነበር። ሆኖም ከሴት ጋር ለመገናኘት ኃይለኛ ፍላጎት አደረብኝ።” ይህ ወጣት ዝሙት ፈጸመ። እንግዲያውስ አንድ ብሔር አቀፍ ጥናት ማስተርቤሽን ይፈጽሙ ከነበሩ ወጣቶች ውስጥ አብዛኞቹ ዝሙትም ጭምር ይፈጽሙ እንደነበረ መግለጹ አያስደንቅም። የእነርሱ ቁጥር ድንግሎች ከነበሩት በ50 በመቶ የሚበልጥ ነበር!

አእምሮንና ስሜትን የሚያረክስ ድርጊት

በተጨማሪም ማስተርቤሽን አእምሮን የሚያረክሱ አንዳንድ ዝንባሌዎች እንዲቀረጹ ያደርጋል። (ከ2 ቆሮንቶስ 11:​3 ጋር አወዳድሩ።) አንድ ሰው ማስተርቤሽን በሚፈጽምበት ጊዜ በራሱ ስሜት ላይ ብቻ ስለሚያተኩር ጨርሶ ራስ ወዳድ ይሆናል። ወሲብ ከፍቅር ተነጥሎ ውጥረትን እንደመወጫ ድርጊት ብቻ ተደርጎ ይታያል። አምላክ ግን ዓላማው ወሲባዊ ፍላጎቶች በባልና በሚስት መካከል ያለው ፍቅር በሚገለጥበት የጾታ ግንኙነት ብቻ እንዲረኩ ነበር።​— ምሳሌ 5:​15–19

በተጨማሪም ማስተርቤሽን የሚፈጽም ግለሰብ ተቃራኒ ጾታን እንደ ወሲብ ዕቃ፣ ማለትም ወሲባዊ እርካታ እንደሚሰጥ ዕቃ አድርጎ መመልከት ይቀናዋል። አንድ ሰው ማስተርቤሽን በመፈጸም የሚማራቸው ዝንባሌዎች ‘መንፈሱን’ ወይም ዋነኛ የአእምሮ ዝንባሌውን ያረክሱበታል። በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ በማስተርቤሽን ምክንያት የሚመጡ ችግሮች ከጋብቻ በኋላም እንኳ ሳይቀር ሳይጠፉ ይቀጥላሉ! እንግዲያውስ የአምላክ ቃል “ወዳጆች ሆይ፣ . . . ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ” በማለት የሚያሳስበው በቂ ምክንያት ስላለው ነው።​— 2 ቆሮንቶስ 7:​1

ለጥፋተኛነት ስሜት ሊኖር የሚገባው ሚዛናዊ አመለካከት

ይሁንና ባጠቃላይ ሲታይ ብዙ ወጣቶች ይህን መጥፎ ልማድ ለማሸነፍ ቢችሉም አልፎ አልፎ እንደገና የሚያገረሽባቸውና የሚሸነፉ አሉ። ደግነቱ አምላክ በጣም መሐሪ ነው። መዝሙራዊው “ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ጥሩና ይቅር ለማለት ዝግጁ ነህ” ብሏል። (መዝሙር 86:​5 አዓት) አንድ ክርስቲያን ለማስተርቤሽን በሚሸነፍበት ጊዜ የገዛ ልቡ ይኮንነዋል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነውና ሁሉንም ያውቃል” በማለት ይናገራል። (1 ዮሐንስ 3:​20) አምላክ ኃጢአታችንን ብቻ አይመለከትም። የእውቀቱ ታላቅነት ይቅርታ ለማግኘት የምናደርገውን ልባዊ ልመና በርሕራኄ እንዲሰማ ያስችለዋል። አንዲት ወጣት ሴት እንደጻፈችው “በመጠኑ የጥፋተኝነት ስሜት ተሰምቶኛል፣ ይሁንና ይሖዋ እንዴት ያለ አፍቃሪ አምላክ እንደሆነ፣ ልቤን ሊያነብ እንደሚችልና ጥረቴንና የልቤን አሳብ ሁሉ እንደሚያውቅ ማወቄ አልፎ አልፎ ለማስተርቤሽን ስሸነፍ ከልክ በላይ ትካዜ እንዳይሰማኝ ይጠብቀኛል” ብላለች። ማስተርቤሽን ለመፈጸም የሚመጣባችሁን ፍላጎት ከተዋጋችሁ ከባድ የሆነውን የዝሙት ኃጢአት ከመፈጸም ልትጠበቁ ትችላላችሁ።

የመስከረም 1, 1959 መጠበቂያ ግንብ እትም እንደሚከተለው ይላል:- “የቀድሞ አኗኗራችንን ካሰብነው በላይ በጥልቅ ያበላሸብን አንድ ዓይነት መጥፎ ልማድ ደጋግሞ እያሰናከለ እንደሚጥለን እንገነዘብ ይሆናል። . . . ቢሆንም ተስፋ አትቁረጡ። ምሕረት የማይገባው ኃጢአት እንደፈጸማችሁ አድርጋችሁ አትደምድሙ። ሰይጣን ምሕረት የማይገባው ኃጢአት እንደፈጸማችሁ አድርጋችሁ እንድታስቡ ይፈልጋል። ማዘናችሁና በራሳችሁ መናደዳችሁ ራሱ ልትስተካከሉ የማትችሉ አለመሆናችሁን የሚያሳይ ማስረጃ ነው። የአምላክን ምሕረት ለማግኘት፣ በእርሱ ፊት ንጹሕ ሆናችሁ ለመታየትና እርዳታውን ለማግኘት በመፈለግ በትሕትናና ከልብ ወደ እርሱ ከመቅረብ አትታክቱ። አንድ ልጅ ችግር ሲያጋጥመው ወደ አባቱ እንደሚሮጥ ሁሉ እናንተም በአንድ ዓይነት ድካም የቱንም ያህል በተደጋጋሚ የወደቃችሁ ብትሆኑ ወደ አምላክ ቅረቡ፣ ይሖዋ አምላክ ደግሞ ይገባናል በማንለው ደግነቱ ምክንያት እርዳታውን በልግስና የሚሰጣችሁ ከመሆኑም በላይ በቅንነት ከቀረባችሁት ንጹሕ ሕሊና እንድታገኙ ያስችላችኋል።”

ታዲያ “ንጹሕ ሕሊና” ሊገኝ የሚችለው እንዴት ነው?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.20 አምላክ አውናንን በሞት የቀጣው ‘ዘሩን በምድር ላይ ስላፈሰሰ’ ነበር። ይሁን እንጂ እዚህ ላይ የተጠቀሰው ማስተርቤሽን ሳይሆን የተቋረጠ ወሲባዊ ግንኙነት ነው። በተጨማሪም አውናን በሞት የተቀጣው የሟች ወንድሙን ሚስት አግብቶ የወንድሙ ቤተሰባዊ መስመር እንዲቀጥል ለማድረግ በራስ ወዳድነት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ነበር። (ዘፍጥረት 38:​1–10) በዘሌዋውያን 15:​16–18 ላይ ስለተጠቀሰው ‘የዘር መፍሰስ’ ምን ሊባል ይቻላል? በግልጽ እንደሚታየው ይህ የሚያመለክተው ማስተርቤሽንን ሳይሆን ሌሊት በሕልም እንዲሁም በተጋቡ ሰዎች መካከል በሚደረገው ወሲባዊ ግንኙነት ወቅት ስለሚወጣው የዘር ተሸካሚ ፈሳሽ ነው።

የመወያያ ጥያቄዎች

◻ ማስተርቤሽን ምንድን ነው? እርሱንስ በሚመለከት በሰፊው የተዛመቱ አንዳንድ የተሳሳቱ አስተሳሰቦች ምንድን ናቸው?

◻ ብዙውን ጊዜ ወጣቶች ኃይለኛ ወሲባዊ ፍላጎት የሚሰማቸው ለምንድን ነው? ይህስ ስህተት ነው ብላችሁ ታስባላችሁን?

◻ ማስተርቤሽን ለመፈጸም የሚገፋፋውን ምኞት ሊያቀጣጥሉ የሚችሉ ነገሮች ምንድን ናቸው?

◻ ማስተርቤሽን መፈጸም አንድን ወጣት ሊጎዳው ይችላልን?

◻ ማስተርቤሽን የቱን ያህል ከባድ ኃጢአት ነው ብላችሁ ታስባላችሁ? አንድ ወጣት ይህን ልማድ እየተዋጋ ማሸነፍ ቢያቅተው ይሖዋ እንዴት ይመለከተዋል?

[በገጽ 200 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አንዳንዶች ውጥረት ሲኖርባቸው ወይም ሲጨነቁ፣ ብቸኛ ሲሆኑ ወይም ሲተክዙ ማስተርቤሽን ለመፈጸም ይገፋፋሉ

[በገጽ 202 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

‘እቅጩን ለመናገር ከማስተርቤሽን ጋር የነበረኝ የጠቅላላው ችግር መንስኤ ወደ አእምሮዬ የማስገባው ነገር ነው’

[በገጽ 204 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“[ማስተርቤሽን] ለመፈጸም በምሸነፍበት ጊዜ ይሖዋ አምላክን እንዳሳፈርኩት ይሰማኝ ነበር”

[በገጽ 198 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማስተርቤሽን ኃይለኛ የሆነ የጥፋተኝነት ስሜት ቢያስከትልም የአምላክን ምሕረት ለማግኘት የሚቀርብ ልባዊ ጸሎትና ልማዱን ለመቋቋም የሚደረግ ጥረት ለግለሰቡ ጥሩ ሕሊና ሊያስገኝለት ይችላል

በገጽ 203 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወሲባዊ ፊልሞች፣ መጻሕፍትና በቴሌቪዥን የሚታዩ የብልግና ድርጊቶች የማስተርቤሽን ‘መቀስቀሻ’ ናቸው