በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት ቢፈጸም ምናለበት?

ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት ቢፈጸም ምናለበት?

ምዕራፍ 23

ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት ቢፈጸም ምናለበት?

‘ከተዋደዳችሁ ሩካቤ ሥጋ ብትፈጽሙ ምንም ችግር የለውምን? ወይስ እስክትጋቡ ድረስ መቆየት ይኖርባችኋል?’ ‘እስካሁን ድረስ ገና ድንግል ነኝ። አንድ ዓይነት ጉድለት ይኖረኝ ይሆን?’ እንደዚህ ያሉት ጥያቄዎች በወጣቶች አካባቢ በብዛት ይሰማሉ።

ይሁን እንጂ አለን ጉትማኸር ኢንስቲትዩት በ1981 ዘገባው ላይ “በአፍላ የጉርምስና ዕድሜው ሳለ የጾታ ግንኙነት ያልፈጸመ ወጣት ቢገኝ ያልተለመደ ነገር ነው” በማለት ደምድሟል። “ከ10 ወንድ ወጣቶች ውስጥ ስምንቱና ከ10 ሴት ወጣቶች ውስጥ ሰባቱ ገና በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ክልል እያሉ ወሲባዊ ግንኙነት ፈጽመዋል።”

‘ታዲያ ምናለበት?’ ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል። ማንም ሰው ተወዳጅ እንደሆነ እንዲሰማው መፈለጉ በተፈጥሮ ያለ ስሜት ነው። በወጣትነት ዕድሜያችሁ ደግሞ ሐሳባችሁን እስከመበታተን የሚያደርስ የፍትወተ ሥጋ ስሜት ሊያይልባችሁ ይችላል። ከዚህም በላይ የእኩዮቻችሁ ተጽእኖ አለ። ከጋብቻ በፊት ሩካቤ ሥጋ መፈጸም አስደሳች ነገር እንደሆነና የምትወዱት ሰው ካለ ደግሞ ከዚያ ሰው ጋር መቀራረብ መፈለግ ተፈጥሯዊ ነገር እንደሆነ ይነግሯችሁ ይሆናል። እንዲያውም አንዳንዶቹ ሩካቤ ሥጋ መፈጸም የወንድነት ወይም የሴትነት ማረጋገጫ እንደሆነ ይናገሩ ይሆናል። እናንተም የተለያችሁ ሆናችሁ ለመታየት ስለማትፈልጉ ወሲባዊ ግንኙነትን ለመሞከር ግፊት ሊያድርባችሁ ይችላል።

ከተለመደው አስተያየት በተቃራኒ ድንግልናቸውን እንደዋዛ አሳልፈው ለመስጠት የሚቸኩሉት ሁሉም ወጣቶች አይደሉም። ለምሳሌ ያህል ኤስተር የተባለችውን ያላገባች ወጣት እንውሰድ። የሕክምና ምርመራ በምታደርግበት ጊዜ የሚመረምራት ሐኪም እንደዋዛ “ምን ዓይነት የወሊድ መከላከያ ነው የምትጠቀሚው?” ብሎ ጠየቃት። ኤስተር “ምንም የወሊድ መከላከያ አልጠቀምም” ብላ በመለሰችለት ጊዜ ሐኪሙ “ምነው! ማርገዝ ትፈልጊያለሽ? ምንም የወሊድ መከላከያ የማትጠቀሚ ከሆነ አላረግዝም ብለሽ እንዴት ታስቢያለሽ?” አላት። ኤስተርም “ወሲባዊ ግንኙነት ስለማልፈጽም ነው!” ብላ መለሰች።

ሐኪሙ በመጠራጠር አተኩሮ ተመለከታትና “ይህ የማይታመን ነገር ነው” አለ። “ዕድሜያቸው ገና 13 ዓመት የሆኑ ትናንሽ ልጆች እዚህ ይመጣሉ፣ ግን ድንግሎች አይደሉም። አንቺ የምትደነቂ ሰው ነሽ” አላት።

ኤስተርን “የምትደነቅ” ሰው ያደረጋት ምን ነበር? “ሰውነታችንን ለዝሙት [ከጋብቻ በፊት ለሚፈጸም ወሲብ ጭምር] ማዋል አይገባንም። . . . ስለዚህ ከዝሙት ራቁ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ስለተከተለች ነው። (1 ቆሮንቶስ 6:​13, 181980 ትርጉም) አዎን፣ ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት መፈጸም በአምላክ ላይ ከባድ ኃጢአት መሥራት እንደሆነ ተገንዝባለች! “የእግዚአብሔር ፈቃድ” ይላል 1 ተሰሎንቄ 4:​3 እንደ 1980 ትርጉም “እናንተ እንድትቀደሱና ከዝሙት እንድትርቁ ነው።” ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት መፈጸምን የሚከለክለው ለምንድን ነው?

የሚያስከትላቸው መዘዞች

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመንም እንኳ ከጋብቻ ውጭ የጾታ ግንኙነት የፈጸሙ አንዳንድ ሰዎች ነበሩ። አንዲት መጥፎ ሥነ ምግባር ያላት ሴት አንድን ወጣት “ና ሌሊቱን ሙሉ በፍቅር እንርካ፤ በተወደደ መተቃቀፍም ደስ ይበለን” በማለት ትጋብዘው ይሆናል። (ምሳሌ 7:​181980 ትርጉም) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ዛሬ የምንደሰትባቸው ነገሮች ነገ ሥቃይ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል። “ከጋለሞታ ሴት ከንፈር ማር ይንጠባጠባልና፣ አፍዋም ከቅቤ የለሰለሰ ነውና” በማለት ሰሎሞን ተናግሯል። በመቀጠልም “ፍጻሜዋ ግን እንደ እሬት የመረረ ነው፣ ሁለት አፍ እንዳለው ሰይፍም የተሳለ ነው” ብሏል።​— ምሳሌ 5:​3, 4

አንዱ መዘዝ በወሲብ አማካኝነት በሚተላለፉ በሽታዎች መለከፍ ሊሆን ይችላል። አንድ ሰው የፈጸመው ሩካቤ ሥጋ የኋላ ኋላ መካንነትን ወይም ከባድ የጤና እክልን የመሰለ የማይሽር ጉዳት እንዳደረሰበት ቢገነዘብ የሚያጋጥመውን ጸጸት ገምቱት! ምሳሌ 5:​11 “በመጨረሻም ሥጋህና ሰውነትህ በጠፋ ጊዜ ታለቅሳለህ” በማለት ያስጠነቅቃል። ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት መፈጸም ዲቃላ መውለድን (ገጽ 184–5 ተመልከቱ።)፣ ፅንስ ማስወረድንና አለጊዜው ማግባትን የሚያስከትል ሲሆን እነዚህ ሁሉ መዘዞች የየራሳቸው ሥቃይ የተሞላበት ውጤት አላቸው። አዎን፣ ከጋብቻ በፊት ወሲብ የሚፈጽም ሰው በእርግጥም “በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል።”​— 1 ቆሮንቶስ 6:​18

እንደዚህ ያሉትን አደጋዎች በመገንዘብ ዶክተር ሪቻርድ ሊ፣ ዬል ጆርናል ኦቭ ባዮሎጂ ኤንድ ሜድስን በተሰኘ ጽሑፍ ላይ “ምንም ዋጋ የማይወጣበትንና ምንም መርዝነት የሌለውን፣ የእርግዝናም ሆነ የአባለ ዘር ችግር መከላከያ የሆነውን ከማንኛውም ነገር በላይ አስተማማኝና ፍቱን የሆነውን ጥንታዊ፣ ክቡርና ጤናማ የድንግልና ሥርዓት ችላ ብለን እርግዝናን መከላከልና የአባለ ዘር በሽታዎችን ማዳን እንችላለን ብለን ለወጣቶቻችን እንፎክራለን” በማለት ጽፈዋል።

የጥፋተኝነት ስሜትና ብስጭት

በተጨማሪም ብዙ ወጣቶች ከጋብቻ በፊት ወሲብ መፈጸም መራራ ብስጭት እንደሚያስከትል ተገንዝበዋል። ውጤቱስ? የጥፋተኝነት ስሜትና ለራሳቸው ያላቸው ክብር መቀነስ ነው። የሃያ ሦስት ዓመቱ ዴኒስ እንደሚከተለው በማለት አምኗል:- “በጣም ቅር የሚያሰኝ ነገር ነው። እንደጠበቅሁት ጥሩ ስሜት ወይም የፍቅር ሞቅታ አልሰጠኝም። በዚህ ፈንታ ድርጊቱ ምን ያህል ከባድ ኃጢአት መሆኑን ሙሉ በሙሉ መገንዘቤ ራሴን መታኝ። ራሴን መግዛት ባለመቻሌ በጣም አፍሬያለሁ።” አንዲት ወጣት ሴትም “ከነበርኩበት እንደ ሕልም ያለ ሁኔታ ስባንን በጣም ደስ የማይል ስሜት ተሰማኝ። . . . ፓርቲው አበቃ፣ እኔም ሕመም፣ ርካሽነትና ቆሻሻነት ተሰማኝ። ‘እዚህ ደረጃ ከመድረሳችን በፊት ለምን አልከለከልሽኝም?’ ሲለኝ ደግሞ ይብሱን አዘንኩ” በማለት ገልጻለች።

ዶክተር ጄይ ሲግል እንደተናገሩት እንደዚህ ያሉት ስሜቶች አልፎ አልፎ ብቻ የሚያጋጥሙ አይደሉም። የ2,436 የኮሌጅ ተማሪዎችን ወሲባዊ ድርጊት ካጠኑ በኋላ “በመጀመሪያ ጊዜ [ወሲባዊ ግንኙነት በመፈጸማቸው] ምክንያት ቅር የተሰኙትና ያዘኑት ቁጥር ከረኩትና ደስ ከተሰኙት በእጥፍ ይበልጣል። ወንዶችም ሆኑ ሴቶች እንደጠበቁት ሆኖ ባለማግኘታቸው ከፍተኛ የቅሬታ ስሜት እንደተሰማቸው ያስታውሳሉ” በማለት ደምድመዋል። በወሲባዊ ግንኙነት ረገድ የተጋቡ ሰዎችም እንኳ ሳይቀር አንዳንድ ጊዜ ችግር እንደሚያጋጥማቸው አይካድም። ይሁን እንጂ በጋብቻ ውስጥ እውነተኛ ፍቅርና አሳቢነት ስለሚኖር እንደዚህ ያሉት ችግሮች አብዛኛውን ጊዜ መፍትሔ ያገኛሉ።

ዝሙት የሚያስከፍለው ዋጋ

አንዳንድ ወጣቶች ወሲባዊ ግንኙነት በመፈጸማቸው ምንም የጥፋተኝነት ስሜት ስለማይሰማቸው ከተለያዩ ሰዎች ጋር በመልከስከስ ስሜታዊ እርካታ ለማግኘት ቆርጠው ይነሳሉ። ሮበርት ሶርንሰን የተባሉ ተመራማሪ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ በሚገኙ ወጣቶች ወሲባዊ ባሕርይ ላይ ባደረጉት ጥናት እንደዚህ ያሉት ወጣቶች ይህ ሴሰኝነታቸው ከባድ ዋጋ እንደሚያስከፍላቸው ተናግረዋል። ሶሬንሰን ሲጽፉ “በግል ባደረግንላቸው ቃለ መጠይቅ ላይ ብዙ [ሴሰኛ ወጣቶች] . . . ይህን ድርጊት የሚፈጽሙት አለምንም ዓላማና እርካታ መሆኑን እንደሚያምኑ ገልጸዋል” በማለት ጽፈዋል። ከእነዚህ ወጣቶች ውስጥ አርባ ስድስት በመቶዎቹ “በዚህ ከቀጠልኩ አብዛኞቹ ችሎታዎቼ መበላሸታቸው ነው” ብለዋል። በተጨማሪም ሶሬንሰን እነዚህ ሴሰኛ ወጣቶች “በራሳቸው እንደማይተማመኑና ለራሳቸውም ያላቸው ግምት በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ” መናገራቸውን ተገንዝበዋል።

ነገሩ ልክ ምሳሌ 5:​9 እንደሚናገረው ነው። በጾታ ብልግና የሚካፈሉ ሰዎች ‘ክብራቸውን ለሌላ ይሰጣሉ።’

በማግስቱ የሚኖረው ስሜት

አንድ ወንድና አንዲት ሴት ሕገ ወጥ የጾታ ግንኙነት ከፈጸሙ በኋላ አንዳቸው ለሌላው ያላቸው አመለካከት ይለወጣል። ወንዱ ለሴቲቱ ያለው የጋለ ስሜት ከበፊቱ እንደቀነሰበት ሊገነዘብ ይችላል። እንዲያውም እንደበፊቱ ላትማርከው ትችላለች። በሌላ በኩል ደግሞ ሴቲቱ መጠቀሚያ እንደተደረገች ሊሰማት ይችላል። ወጣቱ አምኖን ድንግሊቱን ትዕማርን ወዶ ምን ያህል እንደታመመ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ አስታውሱ። ሆኖም ከእርሷ ጋር ወሲባዊ ግንኙነት ከፈጸመ በኋላ “ፈጽሞ ጠላት።”​— 2 ሳሙኤል 13:​15

ማሪያ የተባለች ልጃገረድ ተመሳሳይ ተሞክሮ ደርሶባታል። ወሲባዊ ግንኙነት ከፈጸመች በኋላ “(ድክመት በማሳየቴ) ራሴን ጠላሁት፤ የወንድ ጓደኛዬንም ጠላሁት። እንዲያውም ያቀራርበናል ብለን ያሰብነው ወሲባዊ ግንኙነት የጓደኝነታችን ፍጻሜ ሆነ። ከዚያ በኋላ ላየው እንኳን አልፈለግሁም” በማለት ተናግራለች። አዎን፣ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ከጋብቻ በፊት ወሲባዊ ግንኙነት ሲፈጽሙ እንደገና ሊመለሱበት የማይችሉትን መሥመር ጥሰው ይሄዳሉ!

በቤተሰብ ሕይወት መስክ የተከበሩ ተመራማሪ የሆኑት ፖል ኤች ላንዲስ “[ከጋብቻ በፊት ወሲባዊ ግንኙነት] ጊዜያዊ ውጤቱ ዝምድናውን ማጠናከር ሊሆን ይችላል፤ የረዥም ጊዜ ውጤቱ ግን ከዚህ በጣም የተለየ ሊሆን ይችላል” በማለት ተናግረዋል። በእርግጥም ወሲባዊ ግንኙነት የሚፈጽሙ ወንድና ሴት ዝምድናቸውን የማቋረጥ ዕድላቸው ከማይፈጽሙት ይበልጣል! ምክንያቱስ ምንድን ነው? ሕገ ወጥ ወሲባዊ ግንኙነት ቅንዓትንና አለመተማመንን ስለሚያስከትል ነው። አንድ ወጣት ሲናገር “አንዳንድ ወጣቶች ወሲባዊ ግንኙነት ከፈጸሙ በኋላ ‘ከእኔ ጋር ልትፈጽመው ከቻለች ከሌላ ሰው ጋርም ፈጽማ ሊሆን ይችላል’ ብለው ያስባሉ። ለነገሩ እኔም እንደዚህ ተሰምቶኛል። . . . በጣም ቀናተኛና ተጠራጣሪ ነበርኩ” በማለት አምኗል።

ይህ ደግሞ “አይቀናም፤ . . . የማይገባውን አያደርግም፣ የራሱንም አይፈልግም” ከተባለለት እውነተኛ ፍቅር ምን ያህል የራቀ ነው! (1 ቆሮንቶስ 13:​4, 5) ዘለቄታዊ ዝምድና የሚገነባው ፍቅር በዕውር ወረት ወይም በወሲብ ላይ የተመሠረተ አይደለም።

ድንግልና ለራሳችሁ አክብሮት እንዲኖራችሁና ሰላም እንድታገኙ ያስችላችኋል

ይሁን እንጂ ድንግልና የከፋ መዘዝ እንዳያጋጥም ከመርዳት የበለጠ ጥቅም አለው። መጽሐፍ ቅዱስ ለወንድ ጓደኛዋ የጋለ ፍቅር ቢኖራትም ንጹሕ ሆና ስለቆየች አንዲት ወጣት ልጃገረድ ይናገራል። በዚህም ምክንያት “እኔ ቅጥር ነኝ ጡቶቼም እንደ ግንብ ናቸው” በማለት በኩራት ለመናገር ችላለች። የጾታ ግፊት ሲደርስባት በቀላሉ ‘እንደሚከፈትና ማንም ዘው ብሎ እንደሚገባበት በር’ አልነበረችም። በሥነ ምግባር ረገድ ሰው ሊደርስበት የማይችል ግንብ እንዳለው ትልቅ የቅጥር ምሽግ በመሆን ጽኑ ሆና ቆማለች! “ንጽሕት” ተብላ መጠራት የተገባት ስለነበረች ስለወደፊቱ ባሏ ስትናገር “በዚያን ጊዜም በፊቱ ሰላምን እንደምታገኝ ሆንሁ” በማለት ልትናገር ችላለች። የነበራት የአእምሮ ሰላም በሁለቱ መካከል ለነበረው እርካታ ምክንያት ሆኖአል።​— መኃልየ መኃልይ 6:​9, 10፤ 8:​9, 10

ንጽሕናዋን ጠብቃ የኖረችው ቀደም ሲል የጠቀስናት ኤስተር እንዲህ ያለው ውስጣዊ ሰላምና ለራስዋ ጥሩ ግምት ነበራት። እንዲህ ብላለች:- “ስለ ራሴ ጥሩ ስሜት ነበረኝ። የሥራ ባልደረቦቼ ሲያፌዙብኝ እንኳን ድንግልናዬን የምመለከተው ውድ ዋጋ እንዳለው ዕንቁ አድርጌ ነበር። ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ ድንግልና በብዛት የማይገኝ ነገር ሆኗል።” በተጨማሪም እንደ ኤስተር ያሉ ወጣቶች በጥፋተኝነት ስሜት የተረበሸ ሕሊና አያስጨንቃቸውም። ስቴፋን የተባለው የ19 ዓመት ክርስቲያን ወጣት “በይሖዋ አምላክ ፊት ንጹሕ ሕሊና ይዞ ከመኖር የበለጠ ጥሩ ነገር የለም” ብሏል።

‘ይሁን እንጂ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ወሲባዊ ግንኙነት ካላደረጉ እንዴት እርስ በርስ ሊተዋወቁ ይችላሉ?’ በማለት አንዳንድ ወጣቶች ይጠይቃሉ።

ዘላቂ የሆነ የቅርብ ግንኙነት መገንባት

ወሲብ ብቻውን ዘለቄታዊ ዝምድና ሊመሠርት አይችልም። መሳሳምን የመሳሰሉት የፍቅር መግለጫዎችም ቢሆኑ እንደዚያው ናቸው። አን የተባለች ወጣት ሴት “አንዳንድ ጊዜ በችኮላ ከመጠን ያለፈ አካላዊ ቅርርብ ሊደረግ እንደሚቻል ከተሞክሮዬ ተገንዝቤያለሁ” በማለት ታስጠነቅቃለች። አንድ ወንድና አንዲት ሴት አለመጠን እርስ በርስ ተቀራርበው ፍቅራቸውን በሚገላለጹበት ጊዜ በመካከላቸው ትርጉም ያለው የሐሳብ መለዋወጥ ሊኖር አይችልም። በመሆኑም ከጋብቻ በኋላ ብቅ ሊሉ የሚችሉ ከባድ ልዩነቶቻቸው ሊሸፈኑ ይችላሉ። አን ከጊዜ በኋላ ከአንድ ሰው ማለትም አሁን ካገባችው ሰው ጋር እየተቀጣጠረች መጫወት ስትጀምር ከመጠን ያለፈ አካላዊ ቅርርብ ላለማድረግ ትጠነቀቅ ነበር። አን “ጊዜያችንን የምናሳልፈው ችግሮችን በመፍታትና በሕይወታችን ስለሚኖረን ግብ በመወያየት ነበር። የማገባው ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ ለማወቅ ቻልኩ። ከተጋባን በኋላ ያጋጠመን ያልጠበቅነው አስደሳች ነገር ብቻ ነበር” በማለት ገልጻለች።

አንና የወንድ ጓደኛዋ እንዲህ ዓይነቱን ራስ መግዛት ለማሳየት አስቸጋሪ ሆኖባቸው ነበርን? “አዎን፣ አስቸጋሪ ነበር!” በማለት አን አምናለች። “እኔ በተፈጥሮዬ ሰው ወዳድ ነኝ። ይሁን እንጂ ራሳችንን አለመግዛት ስለሚያስከትልብን አደጋ እንነጋገር ስለነበር እርስ በርሳችን እንረዳዳ ነበር። ሁለታችንም አምላክን ለማስደሰትና ወደፊት የምናደርገውን ጋብቻችንን ላለማበላሸት አጥብቀን እንመኝ ነበር።”

ይሁን እንጂ አንድ አዲስ ያገባ ሰው ወይም አዲስ ያገባች ሴት ከዚህ በፊት ወሲባዊ ተሞክሮ ቢኖረው ወይም ቢኖራት አይረዳቸውምን? አይረዳቸውም። እንዲያውም በተቃራኒው የጋብቻ ቅርርባቸውን እንደሚቀንስባቸው ብዙ ጊዜ ታይቷል! ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት ሲፈጸም ዋናው ትኩረት የራስን ስሜት በማርካት ላይ፣ ማለትም በወሲብ አካላዊ ገጽታ ላይ ነው። በመካከላቸው ሊኖር የሚገባው መከባበር ከቁጥጥር ውጭ በሆነ ፍትወት ይመነምናል። እንዲህ ያለው የራስ ወዳድነት ባሕርይ አንዴ ከተቀረጸ በኋላ ለማስወገድ ስለሚያስቸግር በመጨረሻ በዝምድናቸው ላይ አደጋ ያስከትላል።

ይሁን እንጂ በጋብቻ ውስጥ የሚኖረው ጤናማ የሆነ ቅርርቦሽ ራስን መግዛት ይጠይቃል። ትኩረት ሊሰጥ የሚገባው በመቀበል ላይ ሳይሆን በመስጠት ላይ፣ ‘ለትዳር ጓደኛ የጋብቻ ግዴታን በመፈጸም’ ላይ ነው። (1 ቆሮንቶስ 7:​3, 4) በድንግልና መቆየታችሁ እንዲህ ዓይነቱን ራስ መግዛት ለማዳበር ይረዳችኋል። ከራሳችሁ ስሜት በፊት ስለ ሌላው ሰው ደህንነት ራስ ወዳድነት የሌለበት አሳቢነት እንድታሳዩ ያስተምራችኋል። በተጨማሪም የጋብቻ እርካታ የሚገኘው አካላዊ ቅርርቦሽ በማድረግ ብቻ እንዳልሆነ አስታውሱ። ሲሞር ፊሸር የተባሉ ሶሲዮሎጂስት አንዲት ሴት ለሩካቤ ሥጋ የምታሳየው ምላሽ የሚመካው ለባሏ ባላት “የወዳጅነት ስሜት፣ የጠበቀ ቅርርብና የአለኝታነት ስሜት” ላይ እንደሆነና ባሏም “ሚስቱን እንደ ራሱ ለማየት ባለው ችሎታ ላይና . . . እርሷ በእርሱ ላይ ባላት የመተማመን ስሜት” ላይ እንደሆነ ይናገራሉ።

የሚገርመው ነገር በ177 ያገቡ ሴቶች ላይ በተደረገ ጥናት መሠረት ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት ፈጽመው ከነበሩት ውስጥ ሦስት አራተኛ የሚሆኑት ካገቡ በኋላ በነበሩት የመጀመሪያ ሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ወሲባዊ ችግር እንደገጠማቸው የገለጹ መሆናቸው ነው። ከዚህም በላይ ለረዥም ጊዜ የቆየ ወሲባዊ ችግር እንደነበረባቸው የገለጹት ሁሉ “ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት የፈጸሙ ናቸው።” በተጨማሪም የተደረገው ጥናት ያሳየው ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት የፈጸሙ ካገቡ በኋላ ምንዝር የመፈጸም አጋጣሚያቸው ካልፈጸሙት ቁጥር በእጥፍ የሚበልጥ መሆኑን ነው! እንግዲያስ “ዝሙት . . . ቀናውን አስተሳሰብ ያጠፋል” የሚሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ምንኛ እውነት ናቸው!​— ሆሴዕ 4:​11 አዓት

ስለዚህ ‘የምታጭዱት የዘራችሁትን ነው።’ (ገላትያ 6:​7, 8) ፍትወት ከዘራችሁ ብዙ የጥርጣሬና ያለመተማመን ምርት ታጭዳላችሁ። ራስን መግዛት ከዘራችሁ ግን ለትዳር ታማኝ መሆንንና መተማመንን ታመርታላችሁ። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ኤስተር አግብታ በደስታ መኖር ከጀመረች አያሌ ዓመታት አልፈዋል። ባሏ ሲናገር “እቤት ወደ ሚስቴ ስመጣ እሷ የእኔ ብቻ እኔም የእርሷ ብቻ መሆኔን ሳስበው የሚሰማኝን ደስታ መግለጽ አልችልም። ይህን የመተማመን ስሜት ሊተካው የሚችል ምንም ነገር የለም” ብሏል።

እስኪጋቡ ድረስ ወሲባዊ ግንኙነት ሳይፈጽሙ የሚቆዩ ሰዎች አምላክን ደስ እንደሚያሰኙ በማወቃቸው የአእምሮ ሰላም ያገኛሉ። ቢሆንም በዚህ ዘመን በንጽሕና መቆየት ቀላል አይደለም። ታዲያ በንጽሕና ለመቆየት እንድትችሉ ምን ሊረዳችሁ ይችላል?

የመወያያ ጥያቄዎች

◻ ከጋብቻ በፊት ወሲባዊ ግንኙነት መፈጸም በምታውቋቸው ወጣቶች ዘንድ ምን ያህል ተስፋፍቷል? ይህስ በእናንተ ላይ ችግር ወይም ተጽእኖ ያመጣባችኋልን?

◻ ከጋብቻ በፊት ወሲባዊ ግንኙነት መፈጸም ከሚያመጣቸው አሉታዊ መዘዞች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? እነዚህ መዘዞች የደረሱባቸው የምታውቋቸው ወጣቶች አሉን?

◻ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ለሚያጋጥማቸው እርግዝና መፍትሔው የወሊድ መቆጣጠሪያ ነውን?

◻ አንዳንዶች ሕገ ወጥ ወሲባዊ ግንኙነት ከፈጸሙ በኋላ የጥፋተኝነትና የቅሬታ ስሜት የሚሰማቸው ለምንድን ነው?

◻ ወሲባዊ ግንኙነት መፈጸም ያልተጋቡ ወንድና ሴት ይበልጥ እንዲቀራረቡ እንደሚረዳቸው ይሰማችኋልን? ለምን እንዲህ ብላችሁ ትመልሳላችሁ?

◻ አንድ ወንድና አንዲት ሴት እየተቀጣጠሩ በሚጫወቱበት ጊዜ እርስ በርስ ሊተዋወቁ የሚችሉት እንዴት ነው?

◻ እስከ ጋብቻ ድረስ ድንግል ሆኖ መቆየት ምን ጥቅሞች ያሉት ይመስላችኋል?

[በገጽ 182 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“በአፍላ የጉርምስና ዕድሜው ሳለ ወሲባዊ ግንኙነት ያልፈጸመ ወጣት ቢገኝ ያልተለመደ ነገር ነው።”​— የአለን ጉትማኸር ኢንስቲትዩት

[በገጽ 187 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“በጣም ቅር የሚያሰኝ ነገር ነው፤ እንደጠበቅሁት ጥሩ ስሜት ወይም የፍቅር ሞቅታ አልሰጠኝም”

[በገጽ 190 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አንድ ወንድና አንዲት ሴት ከጋብቻ በፊት ወሲባዊ ግንኙነት ሲፈጽሙ ዳግመኛ የማይመለሱበትን መሥመር ጥሰው ይሄዳሉ!

[በገጽ 184, 185 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

‘በእኔ ላይ ሊደርስ አይችልም!’—በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች እርግዝና

“በየዓመቱ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኙ 10 ወጣት ሴቶች መካከል ቢያንስ አንዷ ታረግዛለች፤ ይህም ቁጥር በጣም በመጨመር ላይ ነው። ሁኔታዎች ካልተለወጡ በቀር ከ10 ወጣቶች ውስጥ አራቱ ገና በአፍላ የጉርምስና ዕድሜያቸው ሳሉ ቢያንስ አንድ ጊዜ ያረግዛሉ።” እንዲህ በማለት የዘገበው ቲንኤጅ ፕሬግናንሲ: ዘ ፕሮብሌም ዛት ሃዝንት ጎን አዌይ (የወጣቶች እርግዝና:- አልለቅ ያለን ችግር) የተሰኘ ጽሑፍ ነው። ለመሆኑ የሚያረግዙት ምን ዓይነት ወጣቶች ናቸው? አዶለሰንስ የተሰኘው ጋዜጣ “በትምህርት ዕድሜያቸው ላይ እያሉ የሚያረግዙት ወጣቶች ከሁሉም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ክፍሎች የመጡ ናቸው። . . . ከሁሉም ዓይነት ዘሮች፣ እምነቶች፣ ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች፣ ከገጠርና ከከተማ የመጡ ናቸው።”

ማርገዝ ፈልገው የሚያረግዙ ወጣቶች በጣም ጥቂቶች ናቸው። ፍራንክ ፉርስቴንበርግ ጁኒየር ከ400 በላይ በሆኑ ያረገዙ ልጃገረዶች ላይ ባደረጉት ከፍተኛ ጥናት “አብዛኞቹ በተደረገላቸው ቃለ ምልልስ ላይ በተደጋጋሚ ‘በእኔ ላይ ይደርሳል’ ብዬ በጭራሽ አላሰብኩም ነበር” በማለት ሲናገሩ እንደተደመጡ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ አንዳንድ ወጣት ሴቶች ጓደኞቻቸው የሆኑ ጥቂት ወጣቶች ሩካቤ ሥጋ ቢፈጽሙም እንዳላረገዙ ሲመለከቱ እነርሱም እንደማያረግዙ ገምተዋል። በተጨማሪም ፉርስተንበርግ “የሚበዙቱ ‘ባንድ ጊዜ’ ማርገዝ የሚቻል እንዳልመሰላቸው ጠቅሰዋል። ሌሎች ደግሞ ‘አልፎ አልፎ ብቻ’ ወሲባዊ ግንኙነት ቢፈጽሙ እንደማያረግዙ አስበው ነበር። . . . ሳያረግዙ ብዙ በቆዩ መጠን ራሳቸውን ለአደጋ ለማጋለጥ የሚኖራቸው ድፍረት ይጨምራል” በማለት ይናገራሉ።

እንደ እውነቱ ከሆነ አንዲት ሴት ወሲባዊ ግንኙነት በፈጸመችበት በማንኛውም ጊዜ ልታረግዝ ትችላለች። (ጥናት ከተደረገባቸው 544 ወጣት ሴቶች መካከል ‘አንድ አምስተኛ የሚሆኑት ወሲባዊ ግንኙነት መፈጸም በጀመሩ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ አርግዘዋል።’) ብዙዎቹም ባል ሳታገባ ልጅ እንደወለደችው ሮቢን የተባለች ወጣት በወሊድ መከላከያ የማይጠቀሙት ሆን ብለው ነው። ሮቢን እንደብዙዎቹ ልጃገረዶች በወሊድ መከላከያ እንክብሎች መጠቀም ጤንነቷን እንዳይጎዳባት ትፈራ ነበር። ጨምራም “የወሊድ መከላከያ ለማግኘት ብሞክር ስህተት የሆነ ነገር እያደረግሁ መሆኔን አምኜ መቀበል ይሆንብኛል። ይህን ደግሞ ማመን አልፈልግም ነበር። ስለዚህ የማደርገው ስህተት እንዳይሰማኝ ኅሊናዬን ዘግቼ ምንም አይደርስብኝም ብዬ ተስፋ ማድረግ ጀመርኩ” በማለት የእምነት ቃሏን ሰጥታለች።

እንደዚህ ያለው አስተሳሰብ ከጋብቻ ውጭ ልጅ በወለዱ እናቶች ዘንድ የተለመደ ነው። በፉርስተንበርግ ጥናት ላይ “ጥናት ከተደረገባቸው ወጣቶች ውስጥ ግማሽ የሚያህሉት አንዲት ሴት ከማግባቷ በፊት ወሲብ መፈጸም እንደማይኖርባት ተናግረዋል። . . . በሚናገሩትና በሚያደርጉት ነገር መካከል ግልጽ የሆነ ልዩነት እንዳለ መካድ አይቻልም። . . . ከወረሷቸው የሥነ ምግባር መስፈርቶች በተለየ ሁኔታ መኖር ለምደዋል።” ይህ ዓይነቱ የስሜት ግጭት “ሴቶቹ ወሲባዊ ባሕሪያቸው የሚያስከትልባቸውን መዘዝ በትክክለኛው መንገድ እንዳይቋቋሙት ይበልጥ አስቸጋሪ ያደርግባቸዋል።”

የወሊድ መከላከያ መጠቀምም ቢሆን ከጋብቻ ውጭ ላለማርገዝ ዋስትና አይሆንም። ኪድስ ሃቪንግ ኪድስ የተሰኘው መጽሐፍ “ማንኛውም የወሊድ መከላከያ ዘዴ ተፈላጊውን ውጤት የማያስገኝበት የየራሱ ጉድለት አለው። . . . ያላገቡ ወጣቶች አለአንዳች ማሰለስ የወሊድ መከላከያ ዘዴዎችን ቢጠቀሙ እንኳን . . . [በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ] በየዓመቱ 500,000 የሚሆኑ ወጣት ሴቶች ማርገዛቸው አይቀርም” በማለት ያሳስበናል። ፓት የተባለች ከጋብቻ ውጭ ልጅ የወለደች የ16 ዓመት ወጣት “ [የወሊድ መከላከያ] እንክብሎችን በታማኝነት ሳላሰልስ እወስድ ነበር። በእውነቱ ሳልወስድ ያሳለፍኩት አንድም ቀን አልነበረም” በማለት የኀዘን እሮሮዋን አሰምታለች።

“አትሳቱ” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠነቅቃል። “እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና።” (ገላትያ 6:​7) እርግዝና አንድ ሰው ከዝሙት አሳዛኝ ምርቶችን ከሚያጭድባቸው መንገዶች አንዱ ብቻ ነው። ደግነቱ ከጋብቻ ውጭ ልጅ የወለዱ እናቶች በጾታ ብልግና ወጥመድ ውስጥ እንደሚወድቁት ሌሎች ሰዎች ሊመለሱና “ከበደሌ ፈጽሞ እጠበኝ፣ ከኃጢአቴም አንጻኝ” በማለት የጸለየውን የንጉሥ ዳዊትን የንስሐ ዝንባሌ በመያዝ ወደ አምላክ ሊቀርቡ ይችላሉ። (መዝሙር 51:​2) እንደዚህ ያሉት ንስሐ የገቡ ሰዎች ልጆቻቸውን “በጌታ ምክርና በተግሣጽ” ለማሳደግ የሚያደርጉትን ጥረት አምላክ ይባርክላቸዋል።​— ኤፌሶን 6:​4

ይሁንና ከጋብቻ በፊት ወሲብ ከመፈጸም መቆጠብ በጣም የተሻለ ነው! ከጋብቻ በፊት ወሲባዊ ግንኙነት ብትፈጽሙም አታረግዙም በሚሏችሁ ሰዎች ፈጽሞ አትታለሉ።

[በገጽ 183 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንዲት ወጣት የጾታ ብልግና ከፈጸመች በኋላ መጠቀሚያ እንደተደረገችና አልፎ ተርፎም ክብሯን እንደተገፈፈች ሊሰማት ይችላል

[በገጽ 186 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በወሲባዊ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች ብዙውን ጊዜ የሚመጡት ከጋብቻ በፊት በሚፈጸም ወሲብ ምክንያት ነው

[በገጽ 188 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከልክ ባለፈ ሁኔታ የፍቅር ስሜት መገላለጥ አንድን ወንድና አንዲትን ሴት ለሥነ ምግባር አደጋ ሊያጋልጥና ትርጉም ባለው ሁኔታ ሐሳባቸውን እንዳይለዋወጡ ሊያደርጋቸው ይችላል

[በገጽ 189 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጋብቻ ውስጥ የሚገኘው ደስታ የሚመካው ባልና ሚስቱ ከሚያደርጉት አካላዊ ግንኙነት በበለጠ ነገር ላይ ነው