በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የማስተርቤሽንን ግፊት መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

የማስተርቤሽንን ግፊት መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

ምዕራፍ 26

የማስተርቤሽንን ግፊት መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

“በጣም ኃይለኛ ሱስ ነው” ሲል ከማስተርቤሽን ጋር ከ15 ዓመት በላይ የታገለ አንድ ወጣት ሰው ተናግሯል። “እንደማንኛውም አደንዛዥ ዕፅ ወይም የአልኮል መጠጥ ሱስ ሊሆን የሚችል ነገር ነው።”

ይሁን እንጂ ሐዋርያው ጳውሎስ ፍላጎቶቹ እንደ ጨካኝ አለቃ እንዲገዙት አልፈቀደም ነበር። በተቃራኒው “ሰውነቴን [ሥጋዊ ፍላጎቴን] እንደባሪያ እየጎሰምኩ አስገዛዋለሁ” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 9:​27 አዓት) በራሱ ላይ ጨክኖ ነበር! ማንኛውም ሰው ተመሳሳይ ጥረት ቢያደርግ ከማስተርቤሽን ሊላቀቅ ይችላል።

“አእምሮአችሁን ለምትወስዱት እርምጃ አዘጋጁት”

ብዙ ሰዎች ማስተርቤሽን የሚፈጽሙት በውስጣቸው የሚፈጠረውን ውጥረት ወይም ጭንቀት ለማስታገሥ ነው። ይሁንና ማስተርቤሽንን እንደ ችግር መፍቻ መንገድ መውሰድ የሕፃንነት መንገድ ነው። (ከ1 ቆሮንቶስ 13:​11 ጋር አወዳድሩ።) ‘በሳል አስተሳሰብ’ በመያዝ ችግሩን ራሱን መዋጋት የተሻለ ይሆናል። (ምሳሌ 1:​4) ችግሮችና ብስጭቶች እያየሉ የመጡ በሚመስሉበት ጊዜ “የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ [በእግዚአብሔር] ላይ ጣሉት።”​— 1 ጴጥሮስ 5:​6, 7

ወሲባዊ ፍላጎታችሁን የሚያነሳሳ ነገር በድንገት ብታዩ ወይም ብትሰሙስ? መጽሐፍ ቅዱስ “አእምሮአችሁን ለሥራ አዘጋጁ፣ ራሳችሁን የምትገዙ ሁኑ” በማለት ይመክራል። (1 ጴጥሮስ 1:​13 ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን) አእምሮአችሁን አስገድዳችሁ የተቀሰቀሰባችሁን ከሥነ ምግባር ውጪ የሆነ አስተሳሰብ አሽቀንጥራችሁ አውጡ።

ይሁንና በተለይ አንድ ሰው ሌሊት ብቻውን በሚሆንበት ጊዜ የሚፈጠርበትን መጥፎ አስተሳሰብ አሽቀንጥሮ ማውጣት አስቸጋሪ ይሆናል። አንዲት ወጣት ሴት እንደሚከተለው ስትል መክራለች:- “አእምሮአችሁ ወደ ሌሎች ነገሮች እንዲያዘነብል ለማድረግ ከሁሉ ­የሚሻለው ነገር ከአልጋችሁ ወርዳችሁ አንድ ዓይነት ሥራ መሥራት ወይም ምናልባት ትንሽ ምግብ መብላት ሊሆን ይችላል።” አዎን፣ አእምሮአችሁ ‘ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፣ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፣ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ እንዲያስብ’ አስገድዱት።​— ፊልጵስዩስ 4:8

እንቅልፍ አልወስድ ሲላችሁ “በመኝታዬ ሁሉ አስታውስሃለሁ፣ ሌሊቱንም ሁሉ የአንተን ነገር አሰላስላለሁ” በማለት የጻፈውን ታማኙን ንጉሥ ዳዊትን ለመምሰል ጣሩ። (መዝሙር 63:​6 አዓት) አእምሮአችሁ በአምላክና በባሕሪዎቹ ላይ እንዲያሰላስል ማስገደድ ብዙውን ጊዜ ማስተርቤሽን እንድትፈጽሙ የሚገፋፋውን ስሜት ኃይል ይሰብራል። በተጨማሪም ዘወትር አምላክ ይህንን ንጹሕ ያልሆነ ልማድ እንዴት እንደሚመለከተው ማሰብ ይረዳችኋል።​— መዝሙር 97:​10

የመከላከያ እርምጃ ውሰዱ

“ብልህ ሰው መከራ ሲመጣ አይቶ ይሸሸጋል፣ ተሞክሮ የጎደለው ሰው ግን ወደ መከራ ከገባ በኋላ ቅጣቱን ይቀበላል” በማለት ጠቢቡ ሰው በመንፈስ ተገፋፍቶ ጽፏል። (ምሳሌ 22:​3 አዓት) አርቃችሁ በማሰብ ብልህ መሆናችሁን ልታሳዩ ትችላላችሁ። ለምሳሌ ያህል በአንዳንድ እንቅስቃሴዎች መካፈል፣ የሚያጣብቁ ልብሶችን መልበስ፣ ወይም ደግሞ አንዳንድ ምግቦችን መብላት የወሲብ ፍላጎት እንዲቀሰቀስባችሁ የሚያደርግ መሆኑን ከገነዘባችሁ እንዲህ የመሰለውን ነገር በተቻለ መጠን አስወግዱ። ለምሳሌ ያህል የአልኮል መጠጦች አንድ ሰው የይሉኝታ ስሜት እንዳይሰማው ሊያደርጉና ራሱን መግዛት ከባድ እንዲሆንበት ሊያደርጉ ይችላሉ። በተጨማሪም የወሲብ ፍላጎት የሚያነሳሳ መልእክት ያላቸውን የሚነበቡ ነገሮች፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ወይም ፊልሞች እንደ ወረርሽኝ ሽሿቸው። “ከንቱ ነገርን እንዳያዩ ዓይኖቼን መልስ” በማለት መዝሙራዊው ጸልዮአል።​— መዝሙር 119:37

በተለይ ራሳችሁን መቆጣጠር አስቸጋሪ በሚሆንባችሁ ጊዜያት የመከላከያ እርምጃዎች መውሰድ ትችላላችሁ። አንዲት ወጣት ሴት ወሲባዊ ፍላጎቷ በወሩ ውስጥ በተወሰኑ ቀናት በጣም ኃይለኛ እንደሚሆን ልትገነዘብ ትችላለች። ወይም ደግሞ አንድ ሰው በስሜት የሚጎዳበት ወይም ትካዜ የሚሰማው ጊዜ ሊኖር ይችላል። “በመከራ ቀን ብትላላ ጉልበትህ [“ኃይልህ” አዓት] ጥቂት ነው” በማለት ምሳሌ 24:​10 ያስጠነቅቃል። ስለዚህ እንደዚህ ባሉት ጊዜያት ለረጅም ጊዜ ብቻችሁን አትሁኑ። አእምሮአችሁ ችሎታውን በሚፈታተኑ ውጥኖች እንዲጠመድ የሚያደርጉ የሚያንጹ ሥራዎችን በመሥራት ከሥነ ምግባር ውጭ ወደ ሆኑ የብልግና አስተሳሰቦች እንዳያዘነብል የሚያደርገው አጋጣሚ እንዳያገኝ አድርጉ።

መንፈሳዊ የማጥቂያ መሣሪያ

ከ11 ዓመቱ ጀምሮ ከዚህ ልማድ ጋር ሲታገል የኖረ አንድ የ27 ዓመት ሰው በመጨረሻ በልማዱ ላይ ድል ለማግኘት ችሏል። “ልማዱን ለመዋጋት የጥቃት እርምጃ የመውሰድ ጉዳይ ነው” ሲል ገልጿል። “መጽሐፍ ቅዱስን ሳላሰልስ በእያንዳንዷ ቀን ቢያንስ ሁለት ሁለት ምዕራፍ አነብ ነበር።” ይህንንም ያለማቋረጥ ከሦስት ዓመት በላይ አድርጎታል። አንድ ሌላ ክርስቲያን ደግሞ እንደሚከተለው በማለት ይመክራል:- “ወደ መኝታ ከመሄዳችሁ በፊት ከመንፈሳዊ ነገሮች ጋር የሚዛመድ አንድ ነገር አንብቡ። በቀኑ መጨረሻ መንፈሳዊ ነገር እያሰባችሁ መተኛታችሁ በጣም አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም በዚህ ሰዓት መጸለይ እጅግ በጣም ይረዳል።”

‘የጌታ ሥራ እንዲበዛላችሁ ማድረግ፣’ ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስን ለሌሎች ማስተማርን በመሰለ ሥራ መካፈልም ይረዳል። (1 ቆሮንቶስ 15:​58) የማስተርቤሽን ልማዷን ያሸነፈች አንዲት ሴት “ይህንን ልማድ ለማስወገድ በጣም እየረዳኝ ያለው ነገር የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ እንደመሆኔ መጠን አእምሮዬና ጉልበቴ በሙሉ ሌሎች በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ዝምድና እንዲመሠርቱ በመርዳቱ ሥራ መያዜ ነው” በማለት ተናግራለች።

እናንተም በጸሎት አማካኝነት አምላክ “ከተለመደው በላይ የሆነ ኃይል” እንዲሰጣችሁ ከልብ ልትለምኑት ትችላላችሁ። (2 ቆሮንቶስ 4:​7 አዓት) “ልባችሁን በፊቱ [በአምላክ ፊት] አፍስሱ።” (መዝሙር 62:​8) አንዲት ወጣት ሴት ስትናገር “ጸሎት አፋጣኝ ብርታት የሚያስገኝ ኃይል ነው። ፍላጎቱ በሚቀሰቀስበት ጊዜ መጸለይ በእርግጥ ይረዳል” ብላለች። በተጨማሪም ከእንቅልፍ እንደተነሳችሁና በቀኑ በሙሉ ይህን ልማድ ለመተው የቆረጣችሁ መሆናችሁን ለአምላክ በማስታወቅ ኃይል የሚሰጠውን መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጣችሁ ለምኑት።​— ሉቃስ 11:13

ከሌሎች የሚገኝ እርዳታ

በግል የምታደርጉት ጥረት ካልተሳካላችሁ ሊረዳችሁ ለሚችል ሰው፣ ለምሳሌ ለወላጃችሁ ወይም ለአንድ ክርስቲያን ሽማግሌ ተናገሩ። ወጣት ሴቶች ለጎለመሱ ክርስቲያን ሴቶች ችግራቸውን ማዋየት የሚረዳቸው ሆኖ ሊያገኙት ይችላሉ። (ቲቶ 2:​3–5) ተስፋ መቁረጥ ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረ አንድ ወጣት “አንድ ቀን ምሽት ለአባቴ ስለ ጉዳዩ ለብቻው በግልጽ ነገርኩት” በማለት ተናግሯል። “ለእርሱ ለመናገር በጣም ትልቅ ድፍረት ጠይቆብኛል። እያለቀስኩ ነገርኩት። ከፍተኛ እፍረት ተሰምቶኝ ነበር። ይሁን እንጂ የተናገረኝን ቃል ፈጽሞ አልረሳውም። እኔን በሚያረጋጋ ሁኔታ ፈገግ ብሎ ‘በጣም እንድኮራብህ አደረግኸኝ’ አለኝ። ለእርሱ ለመናገር ምን ያህል ድፍረትና ቁርጠኝነት እንደጠየቀብኝ አውቋል። ከዚህ ይበልጥ መንፈሴንና ቁርጠኝነቴን ሊያጠናክር የሚችል ቃል ሊገኝ አይችልም።

“ከዚያም አባቴ ልሻሻል የማልችልበት ደረጃ ላይ የደረስኩ አለመሆኔንና እፈጽም የነበረው መጥፎ ድርጊት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ እንድገነዘብ የሚያስችሉኝ አንዳንድ ጥቅሶች አሳየኝ” በማለት ወጣቱ ይናገራል። “ለተወሰነ ጊዜ ልማዴን አሸንፌ እንድቆይና ከዚያ በኋላ እንደገና እንድንወያይበት ነገረኝ። ምናልባት እንደገና ቢያገረሽብኝ ተስፋ እንዳልቆርጥና ዳግመኛ ለልማዴ ሳልሸነፍ ረዘም ያለ ጊዜ እንድቆይ መከረኝ።” ወጣቱ ሰው ችግሩን ሙሉ በሙሉ ካሸነፈ በኋላ እንደሚከተለው ብሏል:- “ሌላ ሰው ችግሬን እንዲያውቅና እንዲረዳኝ ማድረጌ ትልቅ ጥቅም ሰጥቶኛል።”

ልማዱ የሚያገረሽበትን ሁኔታ መቋቋም

አንድ ወጣት ልማዱን ለማሸነፍ ጠንክሮ ከጣረ በኋላ እንደገና አገረሸበት። እንደሚከተለው ሲል ችግሩን አምኗል:- “በጣም ከባድ ጭነት ሆኖብኝ ነበር። ምንም ዋጋ የሌለኝ ሰው ነኝ ብዬ አሰብኩ። ከዚያም ‘ከእንግዲህ ልሻሻል አልችልም። የይሖዋ ሞገስ የለኝም። ስለዚህ ይህን ያህል ራሴን የማስጨንቀው ለምንድን ነው?’ ብዬ አሳበብኩ።” ይሁን እንጂ አንድ ሰው ልማዱ አገረሸበት ማለት በትግሉ ተሸንፏል ማለት አይደለም። አንዲት የ19 ዓመት ልጃገረድ እንዲህ በማለት ታስታውሳለች:- “በመጀመሪያ ላይ በእያንዳንዱ ሌሊት ማለት ይቻላል የማስተርቤሽን ድርጊት እፈጽም ነበር። ከዚያም በይሖዋ ላይ በይበልጥ መመካት ጀመርኩና የመንፈሱን እርዳታ ስላገኘሁ በአሁኑ ጊዜ በዚህ ልማድ የምሸነፈው በዓመት ውስጥ ስድስት ያህል ጊዜ ብቻ ነው። ከተሸነፍኩ በኋላ በጣም አዝናለሁ። ይሁን እንጂ ባገረሸብኝ ቁጥር የሚቀጥለው ፈታኝ ሁኔታ ሲመጣ ይበልጥ ጥንካሬ አገኛለሁ።” ስለዚህ ቀስ በቀስ ትግሏን ማሸነፍ ጀምራለች።

የማስተርቤሽን ልማድ በሚያገረሽበት ጊዜ ወደዚህ ያደረሳችሁ ነገር ምን እንደሆነ አጢኑ። አንድ ወጣት እንዲህ ብሏል:- “ሳነበው ወይም ሳስበው የነበረውን ነገር ለማስታወስ እሞክራለሁ። ብዙውን ጊዜ እንደገና ወደዚህ ልማድ የተንሸራተትኩበትን ምክንያት ለይቼ ለማወቅ እችላለሁ። በዚህ መንገድም ልማዱ እንዲያገረሽብኝ ያደረገውን ነገር ላለመድገም እርምት እወስዳለሁ።”

በቆራጥነት መታገል የሚያስገኛቸው ጥቅሞች

የማስተርቤሽንን ልማድ ያሸነፈ አንድ ወጣት እንዲህ አለ:- “ችግሩን ካሸነፍኩ ወዲህ በይሖዋ ፊት ንጹሕ ሕሊና ለማግኘት ችያለሁ። ይህ ደግሞ በምንም ነገር የማልለውጠው ነገር ነው!”

አዎን፣ ንጹሕ ሕሊና ማግኘት፣ ስለ ራስ ጥሩ ግምት እንዲኖር ማስቻል፣ ከፍተኛ የሆነ የሥነ ምግባር ጥንካሬና ከአምላክ ጋር የተቀራረበ ዝምድና መመሥረት፣ እነዚህ ሁሉ ማስተርቤሽንን ለመቋቋም ጥሩ ትግል ከማድረግ የሚገኙ ሽልማቶች ናቸው። በመጨረሻ ማስተርቤሽንን ያሸነፈች አንዲት ወጣት ሴት:- “በዚህ ልማድ ላይ የምታገኙት ድል ማንኛውም ጥረት ሊደረግለት የሚገባው ነው” ብላለች።

የመወያያ ጥያቄዎች

◻ ፍትወተ ሥጋን የሚቀሰቅሱ አስተሳሰቦችን ማሰላሰል አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው? ወጣቶች ሐሳባቸውን ወደሌላ ነገር ለማዘንበል ምን ማድረግ ይችላሉ?

◻ አንድ ወጣት ማስተርቤሽን ለመፈጸም በሚፈተንበት ጊዜ ይህን ግፊት ለመቀነስ ምን የመከላከያ እርምጃዎች ሊወስድ ይችላል?

◻ መንፈሳዊ መከላከያ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

◻ ጸሎት ይህንን ልማድ በማሸነፍ ረገድ ምን ድርሻ ያበረክታል?

◻ የማስተርቤሽንን ልማድ ተዋግታችሁ በማሸነፍ ረገድ ችግር ካጋጠማችሁ ለሌላ ሰው ችግራችሁን ማዋየት የሚረዳችሁ ለምንድን ነው?

[በገጽ 208, 209 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ወሲባዊ ሥዕሎችና ጽሑፎች፣ ሱስ የሚያስይዙና አደገኛ ናቸው!

“ወሲባዊ ሥዕሎችና ጽሑፎች የትም ቦታ ይገኛሉ። በጎዳና ላይ ስትሄዱ በማስታወቂያ ሰሌዳዎች ላይ በግልጽ ተለጥፈው ታገኛላችሁ” በማለት የ19 ዓመቱ ሮናልድ ያስታውሳል። “እንዲያውም አንዳንድ አስተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ይዘውት ይመጡና የሚቀጥለው ክፍል ተማሪዎች እስኪገቡላቸው ድረስ በዴስካቸው ላይ ዘርግተው ያነቡታል።” አዎን፣ በተለያየ የዕድሜ ክልል፣ የአስተዳደግ ሁኔታና የትምህርት ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች ወሲባዊ ሥዕሎችንና ጽሑፎችን በጉጉት ይከታተላሉ። ማርክ የተባለ አንድ ወጣት እንዲህ ብሏል:- “በጣም አጫጭር ልብሶች የለበሱ ልጃገረዶች የተሳሉባቸውን መጽሔቶች በማነብበትና ፎቶግራፋቸውን በምመለከትበት ጊዜ ስሜቴ በጣም ይነሳሳል። . . . አንብቤ የጨረስኳቸውን መጽሔቶች እንደገና ማንበቡ በፊት ያገኘሁትን የደስታ ስሜት ስለማይሰጠኝ የመጽሔቶቹን አዳዲስ እትሞች ለማግኘት እፈልጋለሁ። ሱስ የሚያስይዝ ነገር ነው።” ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ ሱስ ጥሩ ነውን?

ወሲባዊ ሥዕሎችና ጽሑፎች ‘ወሲብ ዓላማው ራስን ማስደሰት ብቻ ነው’ የሚል መጥፎና ልከኝነት የጎደለው መልእክት ያስተላልፋሉ። ወሲባዊ ሥዕሎችና ጽሑፎች አብዛኛውን ጊዜ ሴቶችን አስገድዶ ስለ መድፈርና ሌሎችን በማሠቃየት ራስን ለማስደሰት ስለሚደረጉ ድርጊቶች የሚገልጹ ናቸው። ከወሲባዊ ጽሑፎችና ፊልሞች ተመልካቾች መካከል ብዙዎቹ “ልከኛ” ናቸው የሚባሉት ወሲባዊ ሥዕሎችና ጽሑፎች እንደቀድሞው ስሜታቸውን የማይቀሰቅሱ ስለሚሆኑባቸው በጣም ነውረኛ የሆኑትን ሥዕሎች ወይም ተንቀሳቃሽ ፊልሞች መፈለግ ይጀምራሉ። በኒው ዮርክ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ኧርነስት ቫን ዴን ሀግ እንደተናገሩት “ወሲባዊ ሥዕሎችና ጽሑፎች ሌሎችን እንደ ተራ ሥጋ፣ የራሳችን የተድላ ስሜት ማርኪያ እንደሆኑ ዕቃዎች አድርገን እንድንመለከታቸው ይጋብዙናል።”

ወሲባዊ ሥዕሎችና ጽሑፎች በተጨማሪም ስለ ወሲብ የተዛባና የተጋነነ አመለካከት እንዲኖር በማድረግ በጋብቻ ላይ ችግር ያስከትላል። አንዲት ወጣት ሚስት እንደሚከተለው ስትል ተናግራለች:- “ወሲባዊ ሥዕሎችንና ጽሑፎችን ማንበብ በመጽሐፎቹ ውስጥ በሥዕል የታዩትን ያልተለመዱ ነገሮች ከባሌ ጋር ለማድረግ እንድመኝ አድርጎኛል። ይህም ዘወትር ወደመበሳጨትና በወሲብ ወዳለመርካት አድርሶኛል።” ወንዶች ወሲባዊ ጽሑፎች ማንበባቸው ከሴቶች ጋር ባላቸው ግንኙነት ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ ለማወቅ በ1981 በሴቶች ላይ ጥናት ተደርጎ ነበር። ከሴቶቹ መካከል ግማሽ ያህል የሚሆኑት በጣም ከባድ ችግር እንዳስከተለባቸው ሪፖርት አድርገዋል። እንደ እውነቱ ከሆነ ወሲባዊ ሥዕሎችንና ጽሑፎችን ማንበብ አንዳንድ ጋብቻዎችን አፍርሷል ወይም የተጫጩ አንዳንድ ወጣቶችን አለያይቷል። አንዲት ሚስት እንደሚከተለው በማለት ምሬቷን ገልጻለች:- “[ባሌ] ወሲባዊ ፍላጎቱ በወሲባዊ ሥዕሎችና ጽሑፎች አማካኝነት መነሳሳት የሚያስፈልገው መሆኑንና ለእነዚህም ጽሑፎችና ሥዕሎች ያለውን ፍላጎት በምመለከትበት ጊዜ እኔ ወሲባዊ ፍላጎቱን ለማርካት ብቁ እንዳልሆንኩ ይሰማኛል። . . . ምነው አምላክ የምታረካው ዓይነት ሴት ባደረገኝ ብዬ አማርራለሁ። ይሁን እንጂ እርሱ ከእኔ ይልቅ ፕላስቲክና ወረቀት የሚመርጥ መሆኑ ማንነቴን በከፊል አበላሽቶብኛል። . . . ወሲባዊ ሥዕሎችና ጽሑፎች . . . የፍቅር ፀር ናቸው። . . . በጣም አስቀያሚ፣ ጨካኝና አጥፊ ናቸው።”

ይሁን እንጂ ክርስቲያን ወጣቶችን ከሁሉ ይበልጥ የሚያሳስባቸው ወሲባዊ ሥዕሎችና ጽሑፎች አንድ ሰው በአምላክ ፊት ንጹሕ ለመሆን የሚያደርገውን ጥረት በቀጥታ የሚጻረሩ መሆናቸው ነው። (2 ቆሮንቶስ 6:​17 እስከ 7:​1) መጽሐፍ ቅዱስ በጥንት ዘመን የነበሩ አንዳንዶች “በእምቢተኝነታቸው ምክንያት . . . የሐፍረት ስሜታቸው ስለጠፋ ራሳቸውን ለክፉ ልማድ አስገዝተዋል፤ ስለዚህ ልዩ ልዩ ርኩሰትን ባለማቋረጥ ለማድረግ አጥብቀው ይመኛሉ” ብሏል። (ኤፌሶን 4:​18, 19 የ1980 ትርጉም) እንዲህ ዓይነት መበላሸት እንዲደርስባችሁ ትፈልጋላችሁን? አልፎ አልፎ እንኳን ወሲባዊ ሥዕሎችንና ጽሑፎችን መመልከት በአንድ ሰው ሕሊና ላይ የሚያደነዝዝ ውጤት ሊኖረው እንደሚችል አስታውሱ። አንዳንድ ክርስቲያን ወጣቶችን ማስተርቤሽንና ይባስ ብሎም የጾታ ብልግና ወደመፈጸም አድርሷቸዋል። እንግዲያስ ጥበብ የሆነው ነገር ከወሲባዊ ሥዕሎችና ጽሑፎች ርቆ ለመኖር መጣጣሩ ነው።

“ብዙ ጊዜ ወሲባዊ ሥዕሎችና ጽሑፎች እግረ መንገዴን ላያቸው በምችልባቸው ቦታዎች ተዘርግተው አገኛለሁ” ይላል ወጣቱ ዴሮል። “ስለዚህ መጀመሪያ ዓይኔን ወርወር ሳደርግ በግድ አየዋለሁ። ሁለተኛ ግን መለስ ብዬ አላየውም።” አዎን፣ ወሲባዊ ሥዕሎችና ጽሑፎች በግልጽ ሊታዩ በሚችሉባቸው ቦታዎች ቢለጠፉ እንኳን ለማየት እምቢተኞች ሁኑ። የትምህርት ቤት ጓደኞቻችሁም ቢሆኑ እንድታዩ ለሚያቀርቡላችሁ ውትወታ አትበገሩ። የ18 ዓመቷ ካረን እንዳለችው “ፍጹም ሰው ባለመሆኔ አእምሮዬን ንጹሕ በሆኑና በሚያስመሰግኑ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ማድረግ አስቸጋሪ ነው። ታዲያ ሆን ብዬ ወሲባዊ ሥዕሎችንና ጽሑፎችን ብመለከት አእምሮዬ ንጹሕ በሆኑና በሚመሰገኑ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ማድረግ ይበልጥ አስቸጋሪ አይሆንብኝምን?”

[በገጽ 206 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ጸሎት አፋጣኝ ብርታት የሚያስገኝ ኃይል ነው። ፍላጎቱ በሚቀሰቀስበት ጊዜ መጸለይ በእርግጥ ይረዳል”