በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አደንዛዥ ዕፅ መውሰድ እምቢ መባል የሚኖርበት ለምንድን ነው?

አደንዛዥ ዕፅ መውሰድ እምቢ መባል የሚኖርበት ለምንድን ነው?

ምዕራፍ 34

አደንዛዥ ዕፅ መውሰድ እምቢ መባል የሚኖርበት ለምንድን ነው?

ማይክ የተባለው የ24 ዓመት ወጣት “ገና በስሜት ያልበሰልኩ ሕፃን ነኝ” ይላል። “አንዳንድ ጊዜ በጣም እፈራለሁ። እኩዮቼ የሆኑ ልጆች እንኳን ያስፈራሩኛል። የመንፈስ ጭንቀትና ያለመረጋጋት መንፈስ አለብኝ። አንዳንድ ጊዜ ራሴን ለመግደል እንኳን አስባለሁ።”

የ36 ዓመቷ አን ስለራሷ ስትገልጽ “ለራሴ ያለኝ አክብሮት በጣም ዝቅተኛ ነው። በስሜት ያልበሰልኩ ጨቅላ ነኝ” ብላለች። ቀጥላም “ጤናማ ሕይወት መኖር በጣም አስቸጋሪ ሆኖብኛል” ብላለች።

ማይክና አን ገና ልጆች ሳሉ አደንዛዥ ዕፆችን ለመሞከር ያደረጉት ውሳኔ ያስከተለባቸውን መዘዝ እያጨዱ ነው። በዛሬው ጊዜ በሚልዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች ተመሳሳይ ነገር እያደረጉ ነው። እንደ ኮኬይንና ማሪዋና ያሉትን የተለያዩ አደንዛዥ ዕፆች በመርፌ ይወጋሉ፣ ይውጣሉ፣ በአፍንጫቸው ይስባሉ ወይም ያጨሳሉ። አንዳንድ ወጣቶች አደንዛዥ ዕፆችን የሚወስዱት ከሚያጋጥማቸው ችግር ለመሸሽ ነው። ሌሎች ደግሞ በአደንዛዥ ዕፅ የሚጠመዱት አዲስ ነገር ለመሞከርና ለማወቅ ባላቸው ጉጉት ተነሳስተው ነው። ሌሎች ደግሞ የሚሰማቸውን የመንፈስ ጭንቀት ወይም የመሰላቸት ስሜት ለማጥፋት ብለው አደንዛዥ ዕፆችን ይወስዳሉ። መውሰድ ከጀመሩ በኋላ ግን ብዙዎቹ ለሚሰጠው ደስታ ሲሉ ብቻ መውሰዳቸውን ይቀጥሉበታል። የ17 ዓመቱ ግራንት እንዲህ ይላል:- “ማሪዋና የማጨሰው ለሚሰጠኝ ስሜት ስል ብቻ ነው። ዘመናዊ ለመምሰል ወይም ማኅበራዊ ተቀባይነት ለማግኘት ስል አይደለም። . . . ስለ ፈለግሁ እንጂ እኩዮቼ ባሳደሩብኝ ተጽእኖ ምክንያት አጪሼ አላውቅም።”

ያም ሆነ ይህ ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ አደንዛዥ ዕፅ ለመውሰድ የምትፈተኑበት ወይም ደግሞ እንድትሞክሩ የምትጠየቁበት ጊዜ ያጋጥማችሁ ይሆናል። አንድ ወጣት “በትምህርት ቤታችን ያሉ ዘበኞችም እንኳ ማሪዋና ይሸጣሉ” ይላል። አደንዛዥ ዕፅ የሚወስዱ ሰዎች የሚጠቀሙባቸው ቁሳቁሶች በይፋ ተዘርግተው ይሸጣሉ። ይሁን እንጂ አደንዛዥ ዕፆችን መውሰድ ምንም ያህል የተለመደ ቢሆን እናንተ ዕፆችን ከመውሰድ ፈጽሞ እምቢ ለማለት የሚያስችላችሁ በቂ ምክንያት አለ። እንዴት?

አደንዛዥ ዕፆች እድገት ያቀጭጫሉ

ከችግር ለመሸሽ ብለው አደንዛዥ ዕፅ የሚወስዱትን እንደ ማይክና አን ያሉትን ወጣቶች እንውሰድ። ባለፈው ምዕራፍ ላይ እንደተገለጸው የስሜት እድገት የሚገኘው የሕይወትን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በመጋፈጥ፣ የኑሮ መሳካትም ሆነ ውድቀት ሲያጋጥም ሁሉንም እንደ ሁኔታው በመቀበል ነው። ከችግራቸው ለማምለጥ የኬሚካል ከለላ የሚፈልጉ ወጣቶች ግን ስሜታዊ እድገታቸው እንዲቀጭጭ ያደርጋሉ። ችግሮችን ተቋቁሞ ለመኖር የሚያስፈልገውን ችሎታ ሳያዳብሩ ይቀራሉ።

ችግሮችን መቋቋም እንደማንኛውም ችሎታ ልምምድ ይጠይቃል። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት፣ ጥሩ ችሎታ ያለው የእግር ኳስ ተጫዋች ተመልክታችሁ ታውቃላችሁን? በጭንቅላቱና በእግሩ አስደናቂ በሆነ መንገድ መጠቀም ይችላል! ሆኖም ይህ ተጫዋች ችሎታውን ያሳደገው እንዴት ነው? በርካታ ዓመታት የፈጀ ልምምድ በማድረግ ነው። ጥሩ ተጫዋች እስኪሆን ድረስ ኳሷን እንዴት እንደሚመታ፣ እንዴት አታልሎ እንደሚያልፍና እንዴት ቀምቶ እንደሚሮጥ ወዘተ ተለማምዷል።

ችግር የመቋቋም ችሎታም ከዚህ ጋር በጣም ተመሳሳይ ነው። ልምምድና ተሞክሮ ይጠይቃል! ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌ 1:​22 ላይ “እናንት አላዋቂዎች፣ [“ተሞክሮ የሌላችሁ” አዓት ]፣ እስከ መቼ አላዋቂነት ትወድዳላችሁ? . . . ሰነፎችም [እስከ መቼ] እውቀትን ይጠላሉ?” በማለት ይጠይቃል። በአደንዛዥ ዕፅ አማካኝነት የሚመጣውን የሚያስፈነድቅ ስሜት ከለላ የሚያደርግ ወጣት ‘ተሞክሮ የለሽነትን ይወዳል።’ የኑሮን ውጣ ውረድ ለመቋቋም የሚያስፈልገውን እውቀትና ችሎታ ሳያዳብር ይቀራል። ቶኪንግ ዊዝ ዩር ቲንኤጀር የተሰኘ መጽሐፍ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜያቸው አደንዛዥ ዕፆችን ስለሚወስዱ ወጣቶች ሲናገር “በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙትን ሥቃዮችና ችግሮች አለነዚህ አደንዛዥ ዕፆች ተቋቁሞ ማለፍ የሚቻል መሆኑን ሳይማሩ ይቀራሉ” ብሏል።

ከችግር ለመሸሽ በአደንዛዥ ዕፆች ትጠቀም የነበረችው አን “ለ14 ዓመታት ችግሮቼን ለመቋቋም ምንም ዓይነት ጥረት አላደረግሁም” በማለት አምናለች። ማይክም “ከ11 ዓመት ዕድሜዬ ጀምሮ በአደንዛዥ ዕፆች ስጠቀም ነበር። በ22 ዓመቴ በአደንዛዥ ዕፅ መጠቀም ሳቆም ገና ትንሽ ልጅ እንደሆንኩ ሆኖ ተሰማኝ። የሚሰማኝን የስጋትና የፍርሃት ስሜት ለማሸነፍ ሌሎች ሰዎችን የሙጥኝ አልኩ። ስሜታዊ እድገቴ አደንዛዥ ዕፆቹን መውሰድ በጀመርኩበት ጊዜ ላይ ቆሞ እንደቀረ ተገነዘብኩ” በማለት ከአን ጋር ተመሳሳይ የሆነ ነገር ገልጿል።

“በእነዚያ ሁሉ ዓመታት ላገኘው እችል የነበረውን እድገት አባከንኩት” በማለት ከ13 ዓመቱ ጀምሮ አደንዛዥ ዕፅ ይወስድ የነበረው ፍራንክ አክሏል። “ዕፅ መውሰድ ባቋረጥኩበት ጊዜ ኑሮን ለመቋቋም ፈጽሞ ያልተዘጋጀሁ መሆኔን ሳልወድ በግድ ተገነዘብኩ። አሁንም በዚህ ዕድሜዬ ማንኛውንም በጉርምስና ዕድሜ የሚገኝ ወጣት የሚያጋጥመው የስሜት መረበሽ የሚያስቸግረኝ የ13 ዓመት ልጅ ነኝ።”

አደንዛዥ ዕፆች ጤንነቴን ሊጎዱ ይችላሉን?

ይህ ደግሞ ሌላው የሚያሳስብ ነገር ነው። አብዛኞቹ ወጣቶች ከባድ የሚባሉት አደንዛዥ ዕፆች ሊገድሉ እንደሚችሉ ይገነዘባሉ። እንደማሪዋና ያሉት ለስለስ ያሉ ናቸው የሚባሉት አደንዛዥ ዕፆችስ? ስለ እነዚህ ዕፆች ሲነገሩ የምትሰሟቸው ማስጠንቀቂያዎች በሙሉ ሰዎችን ለማስፈራራት ሲባል ብቻ የሚነገሩ ናቸውን? የዚህን መልስ ለማግኘት ማሪዋና በሚባለው አደንዛዥ ዕፅ ላይ ብቻ እናተኩር።

ማሪዋና (ፖት፣ ሪፊር፣ ጋንጃ፣ ግራስ ወይም ዊድ በሚባሉ ሌሎች የእንግሊዝኛ አጠራሮች የሚታወቀው ዕፅ ነው) ስለጉዳዩ ጥናት ያደረጉ ሊቃውንት ብዙ ክርክር ያደረጉበት ዕፅ ነው። ስለዚህ አደንዛዥ ዕፅ ገና ያልታወቀ ብዙ ነገር እንዳለ ይታመናል። መጀመሪያ ነገር ማሪዋና በጣም ውስብስብ የሆነ ዕፅ ነው። አንድ የማሪዋና ሲጋራ ከ400 በላይ የሆኑ የኬሚካል ውህዶች ይገኙበታል። ዶክተሮች የሲጋራ ጭስ ካንሰር እንደሚያመጣ ለማወቅ ከ60 ዓመታት በላይ ፈጅቶባቸዋል። የማሪዋና 400 ኬሚካላዊ ውህዶች ደግሞ በሰው አካል ላይ ምን ጉዳት እንደሚያመጡ በእርግጠኝነት ለማወቅ ብዙ አሥርተ ዓመታት ሊወስድባቸው ይችላል።

ይሁን እንጂ እውቅ የሆነው የዩናይትድ ስቴትስ ኢንስቲትዩት ኦቭ ሜዲስን ጠበብቶች ቡድን በሺዎች የሚቆጠሩ የጥናት ሪፖርቶችን ካጠና በኋላ ከሚከተለው ድምዳሜ ላይ ደርሷል:- “እስካሁን ታትመው የወጡ ሳይንሳዊ መረጃዎች ማሪዋና በርካታ የሆኑ ሥነ ልቦናዊና ባዮሎጂያዊ ውጤቶች እንዳሉትና ከእነዚህም አንዳንዶቹ ቢያንስ ቢያንስ በአንዳንድ ሁኔታዎች ለጤና ጎጂ መሆናቸውን ያመለክታሉ።” ከእነዚህ ጎጂ ውጤቶች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

ማሪዋና በሰውነታችሁ ላይ የሚያስከትለው ጠንቅ

ለምሳሌ ያህል ሳንባን እንውሰድ። ማሪዋናን አጥብቀው የሚደግፉ ሰዎች እንኳን ሳይቀሩ የማሪዋና ሲጋራ ጭስ መሳብ ጥሩ ሊሆን እንደማይችል ያምናሉ። የማሪዋና ጭስ እንደ ትንባሆ ጭስ ታርን የመሰሉ በርካታ መርዛማ ነገሮች ይገኙበታል።

ዶክተር ፎረስት ኤስ ቴናንት ጁንየር ማሪዋና በሚወስዱ 492 የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮች ላይ ጥናት አድርገው ነበር። ከእነዚህ ውስጥ 25 በመቶ የሚያህሉት “ማሪዋና በማጨሳቸው ምክንያት የጉሮሮ መቁሰል የደረሰባቸው ሲሆን 6 በመቶ የሚያህሉት ደግሞ የአየር መተላለፊያ ቧንቧ ሕመም ደርሶባቸዋል።” በአንድ ሌላ ጥናት ከ30 የማሪዋና ተጠቃሚዎች ውስጥ 24ቱ “ካንሰር የመያዝ የመጀመሪያ ምልክት የሆነው የአየር መተላለፊያ ቧንቧ ቁስለት እንደያዛቸው ተደርሶበታል።”

እውነት ነው፣ እንደነዚህ ያሉት ሰዎች የኋላ ኋላ በካንሰር ይያዛሉ ብሎ በእርግጠኛነት ሊናገር የሚችል ሰው የለም። ይሁን እንጂ ሕይወታችሁን እንደዚህ ባለ አስጊ ሁኔታ ላይ ለመጣል ትፈልጋላችሁን? ከዚህም ሌላ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ “ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣል” ይላል። (ሥራ 17:​25) ሆን ብላችሁ ሳንባንና ጉሮሮን የሚያበላሽ ነገር የምታጨሱ ከሆነ ሕይወት ሰጪ ለሆነው አምላክ አክብሮት ታሳያላችሁን?

የሰው አንጎል በመክብብ 12:​6 ላይ በቅኔያዊ አነጋገር “የወርቅ ኩስኩስት” ተብሎ ተጠርቷል። ከእጃችሁ ጭብጥ ትንሽ በለጥ የሚለውና ከአንድ ኪሎ ግራም በላይ ክብደት ያለው አንጎላችሁ ውድ የሆነ የትውስታዎቻችሁ መከማቻ ብቻ ሳይሆን የመላው ሰውነታችሁ የነርቭ አውታሮች ትእዛዝ ሰጪ ማዕከል ነው። ይህን በአእምሮአችሁ ይዛችሁ ኢንስቲትዩት ኦቭ ሜዲስን የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ልብ በሉ:- “ማሪዋና በአንጎል ላይ ኬሚካላዊና ኤሌክትሮፊዚዮሎጂካዊ የሆኑ ለውጦችን ጨምሮ ኃይለኛ ውጤት እንደሚያስከትል በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን።” በአሁኑ ጊዜ ማሪዋና አንጎልን ለዘለቄታው እንደሚያበላሽ የተረጋገጠና የማያሻማ ማስረጃ የለም። ይሁን እንጂ ማሪዋና በአንድ ዓይነት መንገድ “የወርቅ ኩስኩስት” በሆነው አንጎላችሁ ላይ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል መሆኑ እንዲህ በቀላሉ ችላ ተብሎ ሊታለፍ የሚችል ሐቅ አይደለም።

አግብታችሁ ልጅ ለመውለድ ያላችሁ ተስፋስ? ኢንስቲትዩት ኦቭ ሜዲስን ማሪዋና “ለሙከራ የሚያገለግሉ እንስሳት በሚወልዷቸው ልጆች ላይ የአካል ጉድለት እንደሚያስከትል” የታወቀ መሆኑን ገልጿል። በሰዎች ላይ ተመሳሳይ ውጤት ይኖረውና አይኖረው እንደሆነ እስካሁን ድረስ አልተረጋገጠም። ይሁን እንጂ ማሪዋና የሚወስዱ ወላጆች በሚወልዷቸው ልጆች ላይ የሚደርሰው የአካል ጉድለት (ዲ ኢ ኤስ በሚባለው ሆርሞን እንደሚመጡት ጉድለቶች) የሚታወቁት ከበርካታ ዓመታት በኋላ ነው። ስለዚህ ማሪዋና አጫሾች የሚወልዱአቸው ልጆችና የልጅ ልጆች ወደፊት ምን እንደሚደርስባቸው ገና ወደፊት የሚታይ ነገር ነው። ዶክተር ጋብሪኤል ናሀስ ማሪዋና ማጨስ “ልጆች በሚኖራቸው የውርሰ ባሕርይ ቁማር መጫወት” ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል። ልጆችን እንደ ‘ይሖዋ ስጦታ’ የሚያይ ሰው እንዲህ ዓይነቱን አደገኛ እርምጃ ሊወስድ ይችላልን?​— መዝሙር 127:​3

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አደንዛዥ ዕፆች ያለው አመለካከት

እርግጥ ማሪዋና ከብዙ የታወቁ አደንዛዥ ዕፆች አንዱ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ ስለ ማሪዋና የተባለው ሁሉ ለደስታ ብሎ ማንኛውንም ዐቅልን የሚያስት ነገር መውሰድ አግባብ አለመሆኑን የሚያሳይ በቂ ማስረጃ አለ። መጽሐፍ ቅዱስ “የጎበዛዝት ክብር ጉልበታቸው ናት” ይላል። (ምሳሌ 20:​29) ወጣቶች እንደመሆናችሁ መጠን ጥሩ ጤንነት እንዳላችሁ የታወቀ ነው። ታዲያ ይህን ጤንነታችሁን ለምን አሽቀንጥራችሁ ለመወርወር ትሞክራላችሁ?

ይሁን እንጂ ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሚሆነው መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለው አመለካከት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የማሰብ ችሎታህን ጠብቅ” ይለናል። (ምሳሌ 3:​21 አዓት) በተጨማሪም “በእግዚአብሔር ፍርሃት ቅድስናን ፍጹም እያደረግን ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ” በማለት ያሳስበናል። በእርግጥም አምላክ “እኔም እቀበላችኋለሁ፣ ለእናንተም አባት እሆናለሁ” የሚለው በአደንዛዥ ዕፅ አለ አግባብ መጠቀምን የመሰሉትን ልማዶች በማስወገድ ‘ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳቸውን ለሚያነጹ’ ሰዎች ብቻ ነው።​— 2 ቆሮንቶስ 6:​17 እስከ 7:​1

ይሁን እንጂ አደንዛዥ ዕፆችን አልወስድም በሚል አቋም መጽናት ቀላል ላይሆን ይችላል።

እኩያ ጓደኞችና የሚያደርሱት ተጽእኖ

የወንድማማች ልጆችና የቅርብ ጓደኞች የሆኑት ጆ እና ፍራንክ በአንድ ቀዝቀዝ ያለ የበጋ ምሽት ስምምነት አደረጉ። “ማንም ሰው የፈለገውን ቢያደርግ” አለ ከሁለቱ በዕድሜ የሚያንሰው ጆ፣ “በአደንዛዥ ዕፆች አካባቢ ፈጽሞ አንደርስም።” ሁለቱ ወጣቶች እጅ ለእጅ ተጨባብጠው ስምምነታቸውን አጸደቁ። ከአምስት ዓመታት በኋላ ጆ በአደንዛዥ ዕፅ ምክንያት በደረሰ አደጋ መኪናው ውስጥ ሞቶ ተገኘ። ፍራንክም የአደንዛዥ ዕፆች ከባድ ሱሰኛ ሆነ።

ግን ምን ነካቸው? መልሱን “አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል” ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ አጣዳፊ ማስጠንቀቂያ እናገኛለን። (1 ቆሮንቶስ 15:​33) ጆ እና ፍራንክ መጥፎ ባልንጀሮች አጋጠሟቸው። አደንዛዥ ዕፆች ከሚወስዱ ወጣቶች ጋር የነበራቸው ጓደኝነት እየጠነከረ ሲሄድ እነሱ ራሳቸውም አደንዛዥ ዕፆችን መቅመስ ጀመሩ።

ሰልፍ ዲስትራክቲቭ ቢሄቪየር ኢን ቺልድረን ኤንድ አዶለሰንትስ የተሰኘ መጽሐፍ እንዳለው:- “ወጣቶች አብዛኛውን ጊዜ ከልዩ ልዩ አደንዛዥ ዕፆች ጋር የሚተዋወቁት ወይም ‘በሱሱ የሚለከፉት’ በቅርብ ጓደኛቸው አማካኝነት ነው። . . . [የአለማማጁ ወጣት] ዓላማ ምናልባት አንድን ስሜት የሚቀሰቅስ ወይም አስደሳች ተሞክሮ ለሌሎች ማካፈል ሊሆን ይችላል።” በዚህ ምዕራፍ መጀመሪያ ላይ የተጠቀሰው ማይክ እንዲህ በማለት የዚህን እውነተኝነት አረጋግጧል:- “ከሁሉ በላይ መቋቋም ከብዶኝ የነበረው የእኩዮቼን ግፊት ነው። . . . ለመጀመሪያ ጊዜ ማሪዋና ያጨስኩት አብረውኝ የነበሩት ልጆች በሙሉ ያጨሱ ስለነበረና እኔም በእነርሱ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ስለፈለግሁ ነበር።”

እውነቱን ፍርጥርጥ አድርገን እንነጋገርና ጓደኞቻችሁ በአደንዛዥ ዕፆች መጠቀም ከጀመሩ እናንተም ከእነርሱ ጋር ለመስማማትና ለመግጠም የሚያስገድድ ኃይለኛ የስሜት ግፊት ይሰማችኋል ማለት ነው። ጓደኞቻችሁን ካልቀየራችሁ እናንተም የኋላ ኋላ የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚ የመሆን አጋጣሚያችሁ ከፍተኛ ይሆናል።

‘ከጠቢባን ጋር መሄድ’

ምሳሌ 13:​20 “ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የሰነፎች [“የደደቦች” አዓት ] ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል” ይላል። ይህን ነጥብ በምሳሌ ለማስረዳት፣ ጉንፋን እንዳይዛችሁ እየፈለጋችሁ ጉንፋን ወደያዛቸው ሰዎች ትቀርባላችሁን? “በተመሳሳይ መንገድም” ይላል አዶለሰንት ፒር ፕሬሸር የተሰኘው መጽሐፍ፣ “አደንዛዥ ዕፅ ከመውሰድ ለመራቅ . . . ከፈለግን . . . ሁኔታዎቻችን ጤናማ ሚዛናቸውን እንዳያጡ ማድረግና ጎጂ ለሆኑ ተጽእኖዎች እንዳንጋለጥ መጠንቀቅ ያስፈልገናል።”

ስለዚህ አደንዛዥ ዕፆችን አልወስድም በሚለው አቋማችሁ ለመጽናት ትፈልጋላችሁ? እንግዲያስ ባልንጀሮቻችሁን በጥንቃቄ ምረጡ። ከአደንዛዥ ዕፆች ርቃችሁ ለመኖር ያደረጋችሁትን ቁርጥ ውሳኔ የሚደግፉላችሁ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ጓደኞች ፈልጉ። (ከ1 ሳሙኤል 23:​15, 16 ጋር አወዳድሩ።) በተጨማሪም በዘጸአት 23:​2 ላይ ያሉትን ቃላት ልብ በሉ። እነዚህ ቃላት የተነገሩት በመሐላ የተደገፈ ምሥክርነት ለሚሰጡ ምሥክሮች ቢሆንም ለወጣቶችም ጥሩ ምክር ይዘዋል። “ክፉውን ለማድረግ ብዙ ሰዎችን አትከተል” ይላል።

እኩዮቹን ያለ አንዳች ጥያቄ የሚከተል ሰው ከባሪያ በምንም አይሻልም። መጽሐፍ ቅዱስ በሮሜ 6:​16 ላይ “ለመታዘዝ ባሪያዎች እንድትሆኑ ራሳችሁን ለምታቀርቡለት፣ ለእርሱ ለምትታዘዙለት ባሪያዎች እንደ ሆናችሁ አታውቁምን?” ይላል። ወጣቶች ‘የማሰብ ችሎታቸውን’ እንዲያዳብሩ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያበረታታው ለዚህ ነው። (ምሳሌ 2:​10–12) ራሳችሁ አስባችሁ በወሰናችሁት ውሳኔ መመራትን ተለማመዱ፤ እንዲህ ካደረጋችሁ ጋጠ ወጥ ወጣቶችን ወደመከተል አታዘነብሉም።

እውነት ነው፣ ስለ አደንዛዥ ዕፆችና ስለሚያስከትሉት ውጤት ለማወቅ ጉጉት ሊያድርባችሁ ይችላል። ይሁን እንጂ አደንዛዥ ዕፆች በሰዎች ላይ የሚያደርሱትን ውጤት ለማወቅ አእምሮአችሁንና ሰውነታችሁን መበከል አያስፈልጋችሁም። እስቲ በእናንተ ዕድሜ የሚገኙትን አደንዛዥ ዕፆች የሚወስዱ ወጣቶች፣ በተለይም ለረዥም ጊዜ ሲወስዱ የቆዩትን፣ ተመልከቱአቸው። ንቁና አስተዋዮች ይመስላሉን? በትምህርታቸው የሚያገኙትን ውጤት ሳይቀንሱ ለመቀጠል ችለዋልን? ወይስ ደግሞ ፈዛዞች፣ ትጋት የሌላቸውና አንዳንድ ጊዜ በአካባቢያቸው የሚካሄደውን ነገር መገንዘብ እስኪሳናቸው ድረስ የፈዘዙ ናቸው? የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚዎቹ ራሳቸው እንደነዚህ ያሉትን ፈዛዞች “ፉዞ” ይሏቸዋል። ሆኖም ብዙዎቹ “ፉዞዎች” በአደንዛዥ ዕፆች መጠቀም የጀመሩት አዲስ ነገር ለማወቅ ባላቸው ጉጉት ተነሳስተው ሊሆን ይችላል። እንግዲያስ መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች ጤናማ ያልሆኑ ነገሮችን ለማወቅ ያላቸውን ጉጉት እንዲገቱና “ለክፋት ነገር ሕፃናት” እንዲሆኑ አጥብቆ መምከሩ ተገቢ ነው።​— 1 ቆሮንቶስ 14:​20

እምቢ ለማለት ትችላላችሁ!

አደንዛዥ ዕፆችን ስለ መውሰድ የተዘጋጀ በዩ ኤስ ናሽናል ኢንስቲትዩት የሚታተም አንድ ቡክሌት ሲያሳስበን “አደንዛዥ ዕፅ እንድትወስዱ ስትጠየቁ እምቢ ማለት . . . መብታችሁ ነው። በዚህ ረገድ ያደረጋችሁትን ውሳኔ የሚጫኑ ጓደኞች የነፃነት መብታችሁን ይጋፉባችኋል” ብሏል። አንድ ሰው አደንዛዥ ዕፅ እንድትወስዱ ቢጠይቃችሁ ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ? እምቢ ለማለት ድፍረት ይኑራችሁ! ይህን ስታደርጉ አደንዛዥ ዕፆችን መውሰድ ስለሚያመጣቸው ክፉ ውጤቶች ረዥም መግለጫ መስጠት ላያስፈልጋችሁ ይችላል። ይኸው ቡክሌት “አይ፣ አመሰግናለሁ። ለማጨስ አልፈልግም” ወይም “እዚህ ጣጣ ውስጥ መግባት አልፈልግም” ወይም ደግሞ በቀልድ አነጋገር “ሰውነት በመበከሉ ልማድ የለሁበትም” ብቻ ብሎ መልስ መስጠት እንደሚቻል ሐሳብ ሰጥቷል። ካልወሰዳችሁ ብለው ድርቅ የሚሉባችሁ ከሆነ ጽኑ አቋም እንዳላችሁ በሚያንጸባርቅ መንገድ ጠበቅ አድርጋችሁ አልፈልግም ለማለት ትችላላችሁ! ክርስቲያኖች መሆናችሁን ማሳወቅም መከላከያ ሊሆንላችሁ ይችላል።

ማደግ ቀላል ሂደት አይደለም። ይሁን እንጂ በአደንዛዥ ዕፆች በመጠቀም ማደግ የሚያስከትላቸውን ችግሮች ለማስወገድ መሞከር ግን ኃላፊነት የሚሰማችሁ የበሰላችሁ ጎልማሳ ሰዎች ለመሆን የሚያስችላችሁን እድገት ሊቀጭባችሁ ይችላል። ችግሮችን ፊት ለፊት መጋፈጥን ተማሩ። ችግሮቹ ከአቅማችሁ በላይ ሆነው በሚታዩአችሁ ጊዜ ኬሚካሎችን በመጠቀም ከችግራችሁ ለመሸሽ አትሞክሩ። ነገሮችን በየፈርጃቸው ለያይታችሁ እንድታዩ ሊረዳችሁ ከሚችል ወላጅ ወይም ኃላፊነት ከሚሰማቸው ሌሎች ጎልማሳ ሰዎች ጋር ተነጋገሩ። በተጨማሪም “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር አስታውሱ።​— ፊልጵስዩስ 4:​6, 7

አዎን፣ ይሖዋ አምላክ እምቢ! ለማለት የሚያስችላችሁን ብርታትና ጥንካሬ ይሰጣችኋል። ሌሎች ሰዎች ይህን ቁርጥ ውሳኔያችሁን እንድታላሉ እንዲያደርጉአችሁ አትፍቀዱላቸው። ማይክ በጥብቅ እንደሚመክረው “አደንዛዥ ዕፆችን አትሞክሩ። ብትሞክሩ ቀሪ ሕይወታችሁን ስትሠቃዩ ትኖራላችሁ!”

የመወያያ ጥያቄዎች

◻ ብዙ ወጣቶች የአደንዛዥ ዕፆች ሱሰኛ የሚሆኑት ለምንድን ነው?

◻ አደንዛዥ ዕፆችን መውሰድ ስሜታዊ እድገታችሁን የሚያቀጭጭባችሁ ለምንድን ነው?

◻ ማሪዋና በሰውነት ላይ የሚያስከትለውን ውጤት በሚመለከት ምን የታወቀ ነገር አለ?

◻ ለደስታ ብሎ አደንዛዥ ዕፆች መውሰድን በሚመለከት የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት ምንድን ነው?

◻ ከአደንዛዥ ዕፆች ርቆ ለመኖር ባልንጀሮችን በጥንቃቄ መምረጥ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

◻ አደንዛዥ ዕፆችን የመውሰድ ጥያቄ በሚቀርብበት ጊዜ እምቢ የሚባልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?

[በገጽ 274 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“በትምህርት ቤታችን ያሉ ዘበኞችም እንኳ ማሪዋና ይሸጣሉ” ይላል አንድ ወጣት

[በገጽ 279 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ስሜታዊ እድገቴ አደንዛዥ ዕፆችን መውሰድ በጀመርኩበት ጊዜ ላይ ቆሞ እንደቀረ ተገነዘብኩ።”​—የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኛ የነበረው ማይክ

[በገጽ 278 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ማሪዋና አዲሱ ታምረኛ ዕፅ ነውን?

ማሪዋና ግላኮማ ለተባለው የዓይን በሽታና ለአስም ሕመም እንዲሁም የካንሰር በሽተኞች በሚወስዷቸው መድኃኒቶች ምክንያት ለሚያስቸግራቸው የማቅለሽለሽ ስሜት መድኃኒት ሊሆን እንደሚችል ብዙ ሲለፈፍ ቆይቷል። አንድ የዩ ኤስ የሕክምና ተቋም የሰጠው ዘገባ እነዚህ አባባሎች ጥቂት እውነትነት እንዳላቸው አምኗል። ይሁን እንጂ ይህ ማለት ዶክተሮች በቅርቡ የማሪዋና ሲጋራዎችን ለሕመምተኞቻቸው ማዘዝ ይጀምራሉ ማለት ነውን?

አይመስልም። ምክንያቱም በማሪዋና ውስጥ ከሚገኙት ከ400 በላይ የሚሆኑ ኬሚካላዊ ውህዶች መካከል አንዳንዶቹ ጠቃሚ መሆናቸው ቢረጋገጥም እነዚህን መድኃኒቶች ለማግኘት ብሎ ማሪዋና ማጨስ ምክንያታዊ ሊሆን አይችልም። “በማሪዋና መጠቀም” ይላሉ ዶክተር ካርልተን ተርነር የተባሉት የታወቁ ጠበብት፣ “ሰዎች ፔኒሲሊን እንዲያገኙ ብሎ የሻገተ ዳቦ እንደመስጠት ነው።” ስለዚህ ከማሪዋና ውህዶች መካከል እውነተኛ መድኃኒት የሆነ ውህድ ቢገኝ ሐኪሞች የሚያዙት ከማሪዋና የተገኙ “ተዋጽኦዎችን” ወይም ከእነዚህ ተዋጽኦዎች ጋር “ተመሳሳይ የሆኑ” ሰው ሠራሽ ቅመሞችን ይሆናል። የዩ ኤስ የጤናና የሰብዓዊ አገልግሎቶች ጸሐፊ እንደሚከተለው ብለው መጻፋቸው ተገቢ ነው:- “ከማሪዋና ይገኛሉ ተብለው የሚታሰቡ የሕክምና ጥቅሞች ማሪዋና በጤንነት ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት በምንም መንገድ እንደማያሻሽለው ጠንከር ብሎ መገለጽ ይኖርበታል።”

[በገጽ 275 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አደንዛዥ ዕፆችን አልወስድም ለማለት ድፍረት ይኑራችሁ!

[በገጽ 276, 277 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

አሁን አደንዛዥ ዕፆች እየወሰዳችሁ ከችግሮቻችሁ ብታመልጡ . . . ጉልምስና ዕድሜ ላይ በምትደርሱበት ጊዜ ችግሮችን መጋፈጥ ይሳናችኋል