በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ዓለምን የሚገዛው ማን ነው?

ዓለምን የሚገዛው ማን ነው?

ዓለምን የሚገዛው ማን ነው?

ብዙ ሰዎች ከላይ ለቀረበው ጥያቄ አምላክ ነው የሚል አጭር መልስ ይሰጣሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በየትኛውም ቦታ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስንም ሆነ አባቱን የዚህ ዓለም ገዥዎች አድርጎ አይጠቅሳቸውም። እንዲያውም በተቃራኒው ኢየሱስ:- “የዚህ ዓለም ገዥ ወደ ውጭ ይጣላል” በማለት ተናግሯል። አክሎም:- “የዚህ ዓለም ገዥ ይመጣልና፤ በእኔ ላይም አንዳች የለውም” ብሏል።—ዮሐንስ 12:31፤ 14:30፤ 16:11

ስለዚህ የዚህ ዓለም ገዥ የኢየሱስ ተቃዋሚ ነው። ይህ ገዥ ማን ሊሆን ይችላል?

የዓለም ሁኔታዎች የሚሰጡት ፍንጭ

ቅን አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች የተቻላቸውን ጥረት ቢያደርጉም ይህ ዓለም በታሪክ ዘመናት ሁሉ አስከፊ ሁኔታዎችን አሳልፏል። ይህ ጉዳይ የአንድ ርዕሰ አንቀጽ አዘጋጅ የነበሩትን ሟቹን ዴቪድ ሎውረንስ እንዳስገረመ ሁሉ ስለ ዓለም ሁኔታዎች የሚያስቡ ሰዎችንም ያስገርማቸዋል። እንዲህ አሉ:- “ማንኛውም ሰው ‘ሰላም በምድር ላይ እንዲሰፍን’ ይፈልጋል ማለት ይቻላል። ‘ለሰዎች መልካም ነገርን መመኘት’ የዓለም ሕዝብ በሙሉ አንዱ ለሌላው ያለው ስሜት ነው ቢባል ትክክል ነው። ታዲያ ችግሩ ምንድን ነው? የሰው ልጆች እነዚህን የመሰሉ ተፈጥሮአዊ ፍላጎቶች እያሏቸው ጦርነት የሰውን ልጅ ሕይወት ሊፈታተን የቻለው ለምንድን ነው?”

እርስ በርሱ የሚጋጭ ነገር ይመስላል፤ አይመስልም እንዴ? ሰዎች በተፈጥሮ ያላቸው ፍላጎት በሰላም መኖር ሆኖ ሳለ እርስ በእርሳቸው ይጠላላሉ፤ አሰቃቂ በሆነ መንገድም ይገዳደላሉ። ያላንዳች አዘኔታ የሚፈጸሙትን እጅግ የሚሰቀጥጡ የጭካኔ ድርጊቶች ይመልከቱ። ሰዎች ያለምንም ርኅራኄ እርስ በርሳቸው ለመገዳደልና ለመተራረድ በመርዘኛ ጋዞች የተሞሉ ክፍሎችን፣ የማጎሪያ ካምፖችን፣ እሳት የሚተፉ መሣሪያዎችን፣ የናፓልም ቦምቦችንና ሌሎች እጅግ የሚዘገንኑ መሣሪያዎችን ይጠቀማሉ።

ሰላምንና ደስታን የሚናፍቁት የሰው ልጆች በራሳቸው እንዲህ ያለ ለመናገር የሚቀፍ ግፍ በሌሎች ላይ ለመፈጸም ይችላሉ ብለው ያምናሉን? ሰዎች እንዲህ ያሉ የሚቀፉ ድርጊቶችን እንዲፈጽሙ የሚገፋፏቸው ወይም የሚሰቀጥጡ ሁኔታዎችን እንድፈጽም አስገድደውኛል ወደሚሏቸው መጥፎ ሁኔታዎች የሚከቷቸው ኃይሎች እነማን ናቸው? ሰዎች እንዲህ ያሉ የዓመፅ ድርጊቶችን እንዲፈጽሙ የሚገፋፋቸው አንድ ክፉ የሆነ በዓይን የማይታይ ኃይል ይኖር ይሆናል ብለው አስበው ያውቃሉን?

የዚህ ዓለም ገዢዎች እነማን እንደሆኑ ተገልጸዋል

መጽሐፍ ቅዱስ የማሰብ ችሎታ ያለው አንድ በዓይን የማይታይ አካል ሰዎችንም ሆነ ብሔራትን እንደሚቆጣጠር በግልጽ ስለሚያሳይ በዚህ ጉዳይ ላይ ግምታዊ ሐሳብ መስጠት አያስፈልግም። እንዲህ ይላል:- “ዓለምም በሞላው በክፉው” ተይዟል። መጽሐፍ ቅዱስ “ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፣ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው” በማለት ለይቶ ይገልጸዋል።—1 ዮሐንስ 5:19፤ ራእይ 12:9

ኢየሱስ ‘በዲያብሎስ በተፈተነበት’ ወቅት ሰይጣን የዚህ ዓለም ገዥ ስለመሆኑ ጥያቄ አላስነሣም። መጽሐፍ ቅዱስ በወቅቱ የሆነውን ሁኔታ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ዲያብሎስ እጅግ ረጅም ወደሆነ ተራራ ወሰደው፣ የዓለምንም መንግሥታት ሁሉ ክብራቸውንም አሳይቶ:- ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ አለው። ያን ጊዜ ኢየሱስ:- ሂድ አንተ ሰይጣን . . . አለው።”—ማቴዎስ 4:1, 8–10

እስቲ ስለዚህ ጉዳይ ያስቡ። “የዓለምን መንግሥታት ሁሉ” ልስጥህ በማለት ሰይጣን ኢየሱስን ፈትኖታል። ታዲያ ሰይጣን የዚህ ዓለም ገዥ ባይሆን ኖሮ ሰይጣን ልስጥህ ብሎ ያቀረበው ነገር እውነተኛ ፈተና ይሆን ነበርን? አይሆንም፤ ፈጽሞ ሊሆን አይችልም ነበር። ኢየሱስ እነዚህ ዓለማዊ መንግሥታት በሙሉ የሰይጣን መሆናቸውን እንዳልካደም ልብ ይበሉ። ሰይጣን በእነርሱ ላይ ስልጣን ባይኖረው ኖሮ ግን ኢየሱስ ምን ሥልጣን አለህና ማለቱ አይቀርም ነበር። እንግዲያው ሰይጣን ዲያብሎስ የማይታየው የዚህ ዓለም ገዥ መሆኑ ምንም አያከራክርም! እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “የዚህ ዓለም አምላክ” ብሎ ይጠራዋል። (2 ቆሮንቶስ 4:4) ነገር ግን እንዲህ ያለ ክፉ አካል ይህን ከፍተኛ ሥልጣን ሊጨብጥ የቻለው እንዴት ነው?

በኋላ ሰይጣን የሆነው ይህ አካል በፊት በአምላክ የተፈጠረ መልአክ ነበር፤ ይሁን እንጂ በአምላክ ቦታ ቅናት አደረበት። የአምላክን የመግዛት መብት ተገዳደረ። የመጀመሪያዋን ሴት ሔዋንን በማታለል ዓላማውን ዳር ለማድረስ ሲል እባብን እንደ አንደበት አድርጎ ተጠቀመበት። እንዲህ በማድረግም ሔዋን እሷንና ባሏን አዳምን ለአምላክ ከመታዘዝ ይልቅ የእሱን ፍላጎት እንዲፈጽሙ ለማድረግ ቻለ። (ዘፍጥረት 3:1–6፤ 2 ቆሮንቶስ 11:3) በተጨማሪም ገና ያልተወለዱትን የአዳምና የሔዋን ዘሮች በሙሉ ከአምላክ ማራቅ እችላለሁ ሲል ፎከረ። ስለዚህ ሰይጣን ፉከራውን በተግባር ለማረጋገጥ እንዲሞክር አምላክ ጊዜ ሰጠው፤ ይሁን እንጂ ሰይጣን አልተሳካለትም።—ኢዮብ 1:6–12፤ 2:1–10

ሰይጣን ዓለምን የሚገዛው ብቻውን አይደለም። በአምላክ ላይ ባደረገው ዓመፅ አንዳንድ መላእክት ከጎኑ እንዲቆሙ ያደረገው ሙከራ ተሳክቶለታል። እነዚህ መላእክት አጋንንት በመሆን የእሱ መንፈሳዊ ግብረ አበሮች ሆኑ። መጽሐፍ ቅዱስ ለክርስቲያኖች ምክር ሲሰጥ ስለ እነርሱ እንዲህ ይላል:- “የዲያብሎስን ሽንገላ” ተቃወሙ። “መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፣  . . . ከዚህ ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ሥፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ።”—ኤፌሶን 6:11, 12

ክፉ መናፍስትን ተከላከሉ

እነዚህ በዓይን የማይታዩ ክፉ የዓለም ገዦች የሰውን ዘር በሙሉ ለማሳትና ከአምላክ አምልኮ ለማራቅ ቆርጠው ተነስተዋል። የአምላክ ቃል ሙታን አንዳች እንደማያውቁ በግልጽ የሚያመለክት ቢሆንም እንኳ ክፉ መናፍስት ቆርጠው የተነሱበትን ዓላማ የሚያከናውኑበት አንዱ መንገድ ነፍስ አትሞትም የሚለውን ሐሳብ በማስፋፋት ነው። (ዘፍጥረት 2:17፤ 3:19፤ ሕዝቅኤል 18:4፤ መዝሙር 146:3, 4 የ1879 ትርጉም፤ መክብብ 9:5, 10) ስለዚህ አንድ ክፉ መንፈስ የአንድን የሞተ ሰው ድምፅ አስመስሎ በመቅረብ በመናፍስት ጠሪ በመጠቀም ወይም ከማይታየው ዓለም በሚመጣ “ድምፅ” አማካኝነት በሕይወት ያሉትን ዘመዶቹን ወይም ጓደኞቹን ሊያነጋግር ይችላል። “ድምፁ” በሞት የተለየውን ሰው ድምፅ ሊመስል ይችላል፤ ሆኖም ድምፁ የአንድ ጋኔን ድምፅ ነው!

ስለዚህ እንዲህ ዓይነት “ድምፅ” ከሰሙ አይታለሉ። ምንም ነገር ቢልዎት አይቀበሉት፤ “ሂድ አንተ ሰይጣን”! የሚሉትንም የኢየሱስ ቃላት ያስተጋቡ። (ማቴዎስ 4:10፤ ያዕቆብ 4:7) ስለ መንፈሳዊው ዓለም ለማወቅ ያልዎት ጉጉት ከክፉ መናፍስት ጋር እንዲጠላለፉ እንዲያደርጉዎት አይፍቀዱለት። እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት መናፍስትነት ተብሎ ይጠራል፤ አምላክ ደግሞ አምላኪዎቹ ከየትኛውም ዓይነት የመናፍስትነት ድርጊት እንዲርቁ አስጠንቅቋቸዋል። “ሞራ ገላጭም፣ . . . መናፍስትንም የሚጠራ፣ ጠንቋይም፣ ሙታን ሳቢም በአንተ ዘንድ አይገኝ” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ዘዳግም 18:10–12፤ ገላትያ 5:19–21፤ ራእይ 21:8

መናፍስትነት አንድን ሰው በአጋንንት ቁጥጥር ሥር ስለሚያደርገው ምንም ያህል ጨዋታ ወይም አስደሳች ሊመስሉ ቢችሉም እንኳ ከመናፍስትነት ጋር ከተያያዙ ልማዶች በሙሉ ይራቁ። እነዚህ ልማዶች ጠንቋዮች የሚጠቀሙበትን ከመስተዋት የተሠራ ድቡልቡል የሆነ ነገር በመጠቀም ወደፊት የሚሆኑትን ሁኔታዎች መመልከት፣ ለመናፍስትነት ድርጊቶች በሚገለገሉባቸው የተለያዩ ምልክቶች ባሉባቸው ሰሌዳዎች መጠቀም፣ በሌላ ተጨማሪ የማስተዋል የስሜት ሕዋስ መጠቀምን፣ በአሻራ መጠንቆልንና ኮከብ ቆጠራን የሚያጠቃልሉ ናቸው። አጋንንቶች የራሳቸው ክልል ባደረጓቸው ቤቶች ውስጥም ድምፆችን ሊያሰሙና ሌላ በዓይን የሚታይ ድርጊት ሊፈጽሙ ይችላሉ።

ከዚህም በተጨማሪ ክፉ መናፍስት ብልሹና ከተፈጥሮ ውጪ የሆነ የጾታ ግንኙነት ባሕርይን የሚያንጸባርቁ ጽሑፎች፣ ፊልሞችና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች እንዲስፋፉ በማድረግ የሰው ልጆችን ደካማ ጎን ይኸውም የኃጢአተኝነት ዝንባሌ ይጠቀሙበታል። መጥፎ ሐሳቦች ከአእምሮ ካልተወገዱ በየጊዜው ሥር እየሰደዱ በመሄድ በመጨረሻው መፋቅ ወደማይችሉበት ደረጃ ሊደርሱና ሰዎች ልክ እንደ አጋንንት በጣም የረከሱ ሊሆኑ እንደሚችሉ አጋንንት ያውቃሉ።—ዘፍጥረት 6:1, 2፤ 1 ተሰሎንቄ 4:3–8፤ ይሁዳ 6

እውነት ነው፣ ብዙዎች ይህን ዓለም የሚገዙት ክፉ መናፍስት ናቸው በሚለው ሐሳብ ያላግጡ ይሆናል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና” በማለት ስለሚናገር አለማመናቸው የሚያስደንቅ ነገር አይደለም። (2 ቆሮንቶስ 11:14) እጅግ የረቀቀ የማታለያ ዘዴው ብዙዎች እሱም ሆነ አጋንንቱ የመኖራቸውን ሐቅ እንዳይቀበሉ አሳውሯቸዋል። አይታለሉ! ዲያብሎስና አጋንንቱ በእርግጥ አሉ፤ ያለማቋረጥ ሊከላከሏቸው ይገባል።—1 ጴጥሮስ 5:8, 9

ሰይጣንና ግብረ አበሮቹ የሚጠፉበት ጊዜ መቅረቡ ደስ ያሰኛል! “ዓለሙም [ገዢዎቹ የሆኑትን አጋንንት ጨምሮ] . . . ያልፋሉ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” ሲል መጽሐፍ ቅዱስ ማረጋገጫ ይሰጣል። (1 ዮሐንስ 2:17) ያ መጥፎ ተጽዕኖ ሲወገድ እንዴት ያለ እፎይታ ይሆናል! እንግዲያው እኛ የአምላክን ፈቃድ ከሚያደርጉትና ጽድቅ በሚሰፍንበት የአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት ከሚያገኙት ሰዎች መካከል የምንሆን ያድርገን!—መዝሙር 37:9–11, 29፤ 2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 21:3, 4

ሌላ መግለጫ ካልተሰጠ በስተቀር የተጠቀሱት ጥቅሶች የተወሰዱት በ1954 ከተተረጐመው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ነው።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰይጣን እነዚህ የዓለም መንግሥታት በሙሉ የእርሱ ባይሆኑ ኖሮ ኢየሱስን ልስጥህ ሊለው ይችል ነበርን?