ጥያቄ 1
ሕይወት የተገኘው እንዴት ነው?
ልጅ ሳለህ ወላጆችህን “ልጅ የሚመጣው ከየት ነው?” ብለህ በመጠየቅ አስገርመሃቸው ታውቃለህ? ምን ብለው መለሱልህ? እንደ ዕድሜህ መጠንና እንደ ወላጆችህ ባሕርይ ጥያቄውን ችላ ብለው አልፈውት ወይም እንደ ማፈር ብለው ደበስበስ ያለ መልስ ሰጥተውህ ይሆናል። አሊያም ደግሞ የፈጠራ ታሪክ ነግረውህ ትልቅ ከሆንክ በኋላ ውሸት መሆኑን ደርሰህበት ይሆናል። ይዋል ይደር እንጂ አንድ ልጅ ለአካለ መጠን ደርሶ ትዳር ለመያዝ ሲዘጋጅ ድንቅ ስለሆነው የመራባት ሂደት ማወቁ የግድ ነው።
ብዙ ወላጆች ልጅ ከየት እንደሚመጣ ማብራራት እንደሚከብዳቸው ሁሉ አንዳንድ ሳይንቲስቶችም ‘ሕይወት ከየት ተገኘ?’ ለሚለው ይበልጥ መሠረታዊ የሆነ ጥያቄ መልስ መስጠት የሚከብዳቸው ይመስላል። ለዚህ ጥያቄ አሳማኝ የሆነ መልስ ማግኘት አንድ ሰው ለሕይወት በሚኖረው አመለካከት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ታዲያ ሕይወት የተገኘው እንዴት ነው?
ብዙ ሳይንቲስቶች ምን ይላሉ? በዝግመተ ለውጥ የሚያምኑ ብዙ ሰዎች ሕይወት ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው በቢሊዮን ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ማዕበል በፈጠረው ኩሬ ላይ ወይም ጥልቅ በሆነ ውቅያኖስ ውስጥ እንደሆነ ይናገራሉ። እነዚህ ሰዎች፣ እንዲህ ባለ ቦታ ላይ ኬሚካሎች በድንገት ተዋሕደው አረፋ የመሰለ ነገር በመፍጠር ውስብስብ የሆኑ ሞለኪውሎችን እንዳስገኙና በኋላም ሞለኪውሎቹ መባዛት እንደጀመሩ ያምናሉ። በምድር ላይ ሕይወት በድንገት የተገኘው አንድ ወይም ከዚያ በላይ ቁጥር ካላቸው እንዲህ ካሉ “ውስብስብነት የሌላቸው” የመጀመሪያ ሴሎች በመነሳት እንደሆነ ይናገራሉ።
ከላይ የተጠቀሱትን ያህል ተደማጭነት ያላቸው ዝግመተ ለውጥን የሚደግፉ ሌሎች ሳይንቲስቶች በዚህ አይስማሙም። የመጀመሪያዎቹ ሴሎች ወይም ደግሞ ቢያንስ የሴሎቹ ዋና ዋና ክፍሎች ከሕዋ ወደ ምድር መጥተዋል የሚል መላምት ይሰነዝራሉ። እንዲህ እንዲሉ ያደረጋቸው ምንድን ነው? ሳይንቲስቶች ምንም ያህል ጥረት ቢያደርጉ ሕይወት ከሌላቸው ሞለኪውሎች ሕይወት ያለው ነገር ሊገኝ እንደሚችል ማረጋገጥ አለመቻላቸው ነው። በ2008፣ የባዮሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት 1
አሌክሳንድረ ሜኔዥ ይህን ጉዳይ አስመልክተው ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፦ “ሕይወት ያለው ነገር በምድር ላይ በድንገት የተገኘው ሕይወት ከሌላቸው ሞለኪውሎች ነው የሚለውን መላምት የሚደግፍ ምንም ዓይነት ተጨባጭ ማስረጃ [ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ] አልተገኘም፤ እንዲሁም ይህን ሐሳብ የሚያጠናክር ሳይንሳዊ እድገት የለም።”ማስረጃው ምን ያመለክታል? ‘ልጅ የሚመጣው ከየት ነው?’ የሚለው ጥያቄ በበቂ ማስረጃ የተደገፈና የማያወዛግብ መልስ አለው። ምንጊዜም ቢሆን ሕይወት የሚገኘው ቀድሞ ከነበረ ሕይወት ያለው ነገር ነው። ይሁን እንጂ ረጅም ዘመናት ወደኋላ ብንመለስ ይህ መሠረታዊ ሕግ ተጥሶ ሕይወት ያለው ነገር ሕይወት ከሌላቸው ኬሚካሎች በድንገት ሊገኝ የቻለበት ሁኔታ ይኖር ይሆን? እንዲህ ያለው ሁኔታ ሊፈጠር የሚችልበት አጋጣሚ ምን ያህል ነው?
አንድ ሴል በሕይወት እንዲቀጥል ከተፈለገ ቢያንስ ሦስት የሚሆኑ ውስብስብ የሞለኪውል ዓይነቶች ይኸውም ዲ ኤን ኤ (ዲኦክሲራይቦኑክሊክ አሲድ)፣ አር ኤን ኤ (ራይቦኑክሊክ አሲድ) እና ፕሮቲኖች አንድ ላይ ተቀናጅተው መሥራት እንዳለባቸው ተመራማሪዎች ደርሰውበታል። በዛሬው ጊዜ፣ ሕይወት የሌላቸው ኬሚካሎች በአጋጣሚ ተዋሕደው ድንገት አንድ የተሟላ ሴል አስገኝተዋል ብለው የሚያምኑ ሳይንቲስቶች ከስንት አንድ ናቸው። ይሁንና አር ኤን ኤ ወይም ፕሮቲኖች በድንገት ሊገኙ የሚችሉበት አጋጣሚ ምን ያህል ነው? *
ብዙ ሳይንቲስቶች ሕይወት በአጋጣሚ ሊገኝ ይችላል ብለው ሊያምኑ የቻሉት በ1953 ለመጀመሪያ ጊዜ በተገኘ አንድ የቤተ ሙከራ ውጤት የተነሳ ነው። በዚያ ዓመት ስታንሊ ሚለር፣ ምድር ጥንት በነበራት ከባቢ አየር ውስጥ ይገኛሉ ብሎ ባሰባቸው ጋዞች ውስጥ ኤሌክትሪክ እንዲያልፍ በማድረግ ፕሮቲን ለመሥራት የሚያስፈልጉ አንዳንድ አሚኖ አሲዶችን ማስገኘት ችሎ ነበር። ከዚያ ወዲህ አሚኖ አሲዶች በተወርዋሪ ኮከቦችም (meteorite) ላይ ተገኝተዋል። ታዲያ እነዚህ ግኝቶች ሕይወት ለማስገኘት የሚያስፈልጉት መሠረታዊ ነገሮች በሙሉ እንዲሁ በአጋጣሚ ሊገኙ እንደሚችሉ ያሳያሉ?
በኒው ዮርክ ዩኒቨርሲቲ የኬሚስትሪ ፕሮፌሰር የነበሩት ሮበርት ሻፒሮ እንዲህ ብለዋል፦ “አንዳንድ ጸሐፊዎች፣ ሕይወት ለማስገኘት የሚያስፈልጉት መሠረታዊ ነገሮች በሙሉ በተወርዋሪ ኮከቦች ላይ እንዲሁም ሚለር ባካሄደው ሙከራ አማካኝነት በቀላሉ ሊገኙ ይችላሉ ብለው ያምናሉ። ሁኔታው ግን እንደዚያ አይደለም።”2 *
እስቲ አር ኤን ኤ የተባለውን ሞለኪውል እንመልከት። ይህ ሞለኪውል የተሠራው ኑክሊዮታይድ ከሚባሉ ትናንሽ ሞለኪውሎች ነው። ኑክሊዮታይድ ከአሚኖ አሲድ የተለየና ትንሽ ወሰብሰብ ያለ ሞለኪውል ነው። ሻፒሮ “በጋዞች ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያልፍ በማድረግም ሆነ ተወርዋሪ ኮከቦችን በማጥናት ማንኛውም ዓይነት ኑክሊዮታይድ ተገኝቶ አያውቅም” ብለዋል።3 * አክለው ሲናገሩ አንድ ራሱን የሚተካ የአር ኤን ኤ ሞለኪውል በዘፈቀደ ከተከሰቱ ኬሚካሎች ሊገኝ የሚችልበት አጋጣሚ “በጣም፣ እጅግ በጣም አነስተኛ በመሆኑ በሚታየው አጽናፈ ዓለም ውስጥ በማንኛውም ቦታ አንድ ጊዜ ተከስቶ ቢገኝ እንኳ ተወዳዳሪ የሌለው ጥሩ ዕድል ተደርጎ ይቆጠራል” ብለዋል።4
ስለ ፕሮቲን ሞለኪውሎችስ ምን ማለት ይቻላል? በትንሹ ከ50 አንስቶ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አሚኖ አሲዶች ሥርዓት ባለው መንገድ እርስ በርሳቸው ሲተሳሰሩ ፕሮቲኖች ይሠራሉ። “ውስብስብ ባልሆነ” አንድ ሴል ውስጥ የሚገኝ የተለመደ ዓይነት አንድ ፕሮቲን 200 አሚኖ አሲዶች ይኖሩታል። በእነዚህ ሴሎች
ውስጥ እንኳ በሺህ የሚቆጠሩ የተለያዩ ፕሮቲኖች አሉ። አንድ መቶ አሚኖ አሲዶች ያሉት አንድ ነጠላ ፕሮቲን በምድር ላይ በድንገት ሊገኝ የሚችልበት አጋጣሚ ሲሰላ ከአንድ ኳድሪሊዮን (1,000,000,000,000,000) ውስጥ አንድ ብቻ ነው።ውስብስብ የሆኑ ሞለኪውሎችን በቤተ ሙከራ ውስጥ መፍጠር የአንድን ሳይንቲስት የረቀቀ ችሎታ የሚጠይቅ ከሆነ ከዚያ ይበልጥ ውስብስብ የሆኑት በአንድ ሴል ውስጥ የሚገኙ ሞለኪውሎች በአጋጣሚ ሊገኙ ይችላሉ?
የዝግመተ ለውጥን ትምህርት የሚደግፉት ሁበርት ዮኪ የተባሉ ተመራማሪ አጋጣሚው ከላይ የተገለጸውን ያህል እንኳ እንደማይሆን ተናግረዋል። እንዲህ ብለዋል፦ “ለሕይወት መገኘት መንስኤ የሚሆነው ‘የመጀመሪያው ነገር ፕሮቲን ነው’ ብሎ መደምደም የማይቻል ነው።”5 ፕሮቲኖችን ለመሥራት አር ኤን ኤ የግድ አስፈላጊ ነው፤ ያም ሆኖ አር ኤን ኤ እንዲፈጠር ከሚያስፈልጉት ነገሮች አንዱ ፕሮቲን ነው። አጋጣሚው እጅግ ጠባብ ቢሆንም እንኳ የፕሮቲኖችና የአር ኤን ኤ ሞለኪውሎች በአንድ ቦታ በተመሳሳይ ጊዜ በአጋጣሚ አንድ ላይ ቢገኙስ? እርስ በርሳቸው ተጋግዘው ራሱን የሚተካና ራሱን ለማኖር የሚችል ሕይወት ያለው ነገር ሊያስገኙ የሚችሉበት አጋጣሚ ምን ያህል ይሆናል? በብሔራዊ የበረራና የሕዋ አስተዳደር (NASA) ሥር የአስትሮባዮሎጂ ተቋም ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ካሮል ክሌላንድ * “(ፕሮቲኖችና አር ኤን ኤ በዘፈቀደ ቢቀየጡ እንኳ) እንዲህ ያለ ነገር የመከሰቱ አጋጣሚ በጣም በጣም አነስተኛ ነው ሊባል ይችላል” በማለት ተናግረዋል። እኚህ ሴት አክለውም “ያም ሆኖ አብዛኞቹ ተመራማሪዎች ፕሮቲኖችና የአር ኤን ኤ ሞለኪውሎች ጥንት በነበረው የከባቢ አየር ሁኔታ ራሳቸውን ችለው የተገኙበትን አጋጣሚ መረዳት ከቻሉ እርስ በርስ የሚቀናጁበትን መንገድ መረዳት እንደሚችሉ አድርገው የሚያስቡ ይመስላል” ብለዋል። ሕይወት እንዲገኝ አስፈላጊ የሆኑት እነዚህ ነገሮች እንዴት በድንገት ሊገኙ እንደቻሉ ስለሚገልጹት ጽንሰ ሐሳቦች ዶክተር ክሌላንድ አስተያየታቸውን ሲሰጡ “አንዳቸውም ቢሆኑ ይህ እንዴት ሊሆን እንደቻለ አጥጋቢ ማብራሪያ ሊሰጡን አልቻሉም” ብለዋል።6
ለእነዚህ እውነታዎች ትኩረት መስጠት ለምን አስፈለገ? ሕይወት የተገኘው በአጋጣሚ ነው የሚሉ ተመራማሪዎች ምን ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታ እንደተጋረጠባቸው አስብ። ሕይወት ባላቸው ሴሎች ውስጥ የሚገኙትን አንዳንድ አሚኖ አሲዶች መፍጠር ችለዋል። እንዲሁም በቤተ ሙከራዎቻቸው ውስጥ በጥንቃቄ በተዘጋጁና ብዙ ክትትል በተደረገባቸው ሙከራዎች አማካኝነት ይበልጥ ውስብስብ የሆኑ ሌሎች ሞለኪውሎችን ማግኘት ችለዋል። ውሎ አድሮ ደግሞ “ውስብስብ ባልሆነ” አንድ ሴል ውስጥ የሚገኙትን የተለያዩ ክፍሎች በሙሉ እንሠራለን ብለው ተስፋ ያደርጋሉ። የእነዚህ ሰዎች ሁኔታ በተፈጥሮ የሚገኙትን ንጥረ ነገሮች ወደ ብረት፣ ፕላስቲክ፣ ሲልከንና ሽቦ ከቀየረ በኋላ አንድ ሮቦት ከሚሠራ ሳይንቲስት ጋር ይመሳሰላል። ከዚያም ሮቦቱ ራሱን መተካት እንዲችል ፕሮግራም ያስገባለታል። ይህን ማድረግ መቻሉ ምን ያረጋግጣል? ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ያለው አንድ አካል አስደናቂ የሆነ ማሽን ሊፈጥር እንደሚችል ከማረጋገጥ ሌላ ምን ሊያሳይ ይችላል?
በተመሳሳይም ሳይንቲስቶች ተሳክቶላቸው አንድ ሴል መሥራት ከቻሉ እጅግ ድንቅ የፈጠራ ሥራ አከናወኑ
ማለት ነው፤ ይሁን እንጂ ይህን ማድረግ መቻላቸው አንድ ሴል እንዲሁ በአጋጣሚ ሊፈጠር እንደሚችል የሚያረጋግጥላቸው ይሆናል? እንዲያውም ይህ ነገር የሚያረጋግጠው የዚህን ተቃራኒ ነው።ታዲያ ምን ይመስልሃል? እስከ ዛሬ የተገኘው ሳይንሳዊ መረጃ በሙሉ የሚያመለክተው ሕይወት ሊገኝ የሚችለው ቀደም ሲል ከነበረ ሕይወት ያለው ነገር መሆኑን ነው። አንድ ሰው “ውስብስብ ያልሆነ” ሕያው ሴልም እንኳ ሕይወት አልባ ከሆኑ ኬሚካሎች በአጋጣሚ ተገኘ ብሎ ማመኑ ጭፍን እምነት ይሆንበታል።
እስካሁን ከተመለከትናቸው እውነታዎች አንጻር እንዲህ ያለውን ሐሳብ በጭፍን መቀበልህ ምክንያታዊ ይሆናል? ለዚህ ጥያቄ መልስ ከመስጠትህ በፊት አንድ ሴል እንዴት እንደተዋቀረ በጥልቀት እንድትመረምር እንጋብዝሃለን። እንዲህ ማድረግህ፣ ‘አንዳንድ ሳይንቲስቶች ሕይወት ስለተገኘበት መንገድ የሚያስተምሩት ጽንሰ ሐሳብ ተጨባጭ ነው? ወይስ አንዳንድ ወላጆች ልጅ ከየት እንደመጣ ለልጆቻቸው ለማስረዳት ከሚናገሩት ተረት የማይሻል የፈጠራ ታሪክ ነው?’ ለሚለው ጥያቄ ትክክለኛ መልስ እንድታገኝ ይረዳሃል።
^ አን.8 “መመሪያዎቹ ከየት መጡ?” የሚል ርዕስ ባለው ክፍል 3 ላይ ዲ ኤን ኤ በድንገት ሊገኝ የሚችልበት አጋጣሚ ምን ያህል እንደሆነ ተብራርቷል።
^ አን.10 ፕሮፌሰር ሻፒሮ ሕይወት በፍጥረት እንደተገኘ አያምኑም። እሳቸው የሚያምኑት ሕይወት እስካሁን ሙሉ በሙሉ ባልተረዳነው መንገድ በአጋጣሚ እንደተገኘ ነው።
^ አን.11 በ2009 እንግሊዝ በሚገኘው ማንቸስተር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኙ ሳይንቲስቶች በቤተ ሙከራቸው ውስጥ አንዳንድ ኑክሊዮታይዶችን እንደሠሩ ሪፖርት አድርገዋል። ይሁን እንጂ ሻፒሮ ሳይንቲስቶቹ የተከተሉት መንገድ “አር ኤን ኤ ለመሥራት የሚያስችል ትክክለኛ መንገድ ነው ብዬ ያወጣሁትን መመዘኛ በፍጹም አያሟላም” በማለት ተናግረዋል።
^ አን.13 ዶክተር ክሌላንድ ስለ ፍጥረት በሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ አያምኑም። እኚህ ሴት የሚያምኑት ሕይወት እስካሁን ሙሉ በሙሉ ባልተረዳነው መንገድ በአጋጣሚ እንደተገኘ ነው።