ጥያቄ 4
ሕይወት ያለው ነገር ሁሉ ከአንድ አካል እየተሻሻለ የመጣ ነው?
ዳርዊን ሕይወት ያለው ነገር ሁሉ ከአንድ አካል እየተሻሻለ የመጣ ነው የሚል አመለካከት ነበረው። በምድር ላይ የሚገኙ ሕይወት ያላቸው ነገሮች አመጣጥ ከአንድ ትልቅ ዛፍ ጋር እንደሚመሳሰል አድርጎ ያስብ ነበር። በኋላ ላይ ደግሞ ሌሎች ሰዎች፣ ይህ “የሕይወት ዛፍ” መጀመሪያ ላይ አንድ ነጠላ ግንድ እንደነበረና ይህ ግንድ የመጀመሪያዎቹን ውስብስብ ያልሆኑ ሴሎች እንደሚያመለክት አድርገው ማመን ጀመሩ። ከዚህ ግንድ አዳዲስ ዝርያዎች የበቀሉ ሲሆን ቅርንጫፍ ወይም የዕፅዋትና የእንስሳት ቤተሰቦች ሆኑ፤ ከዚያም በአሁኑ ጊዜ ያሉት በዕፅዋትና በእንስሳት ቤተሰቦች ውስጥ የሚመደቡት የተለያዩ ዝርያዎች በሙሉ እንደ ቀንበጥ በቀሉ። በእርግጥ የተፈጸመው እንዲህ ያለ ነገር ነው?
ብዙ ሳይንቲስቶች ምን ይላሉ? ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ ከአንድ አካል ተሻሽለው የመጡ ናቸው የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ከቅሪተ አካላት በተገኙ ማስረጃዎች የተደገፈ እንደሆነ ብዙዎቹ ይናገራሉ። በተጨማሪም ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ ተመሳሳይ “የኮምፒውተር ቋንቋ” ወይም ዲ ኤን ኤ ስለሚጠቀሙ ሕይወት ሁሉ ከአንድ አካል ተሻሽሎ የመጣ መሆን አለበት ይላሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? የዘፍጥረት ታሪክ ዕፅዋት፣ የባሕር ፍጥረታት፣ የየብስ እንስሳትና አእዋፍ “እንደየወገናቸው” እንደተፈጠሩ ይናገራል። (ዘፍጥረት 1:12, 20-25) ይህ አገላለጽ በእያንዳንዱ ‘ወገን’ ውስጥ ልዩነት ሊኖር እንደሚችል የሚያሳይ ቢሆንም እያንዳንዱን ወገን ከሌላው የሚለይ ሊጣስ የማይችል ድንበር እንዳለ ያመለክታል። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ የፍጥረት ዘገባ፣ ሙሉ አካል ያላቸው አዲስ ዓይነት ፍጥረታት በቅሪተ አካላት ስብስብ ውስጥ በድንገት ሊገኙ እንደሚችሉ ይጠቁማል።
ማስረጃው ምን ያመለክታል? ማስረጃው መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ የሚሰጠውን መግለጫ ይደግፋል? ወይስ ዳርዊን ትክክል ነበር? ባለፉት 150 ዓመታት የተገኙት ማስረጃዎች ምን ያረጋግጣሉ?
የዳርዊን ዛፍ ተገነደሰ
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሳይንቲስቶች የበርካታ ባለ አንድ ሴል ነፍሳትን እንዲሁም የዕፅዋትንና የእንስሳትን ጄኔቲክ ኮዶች ማነጻጸር ችለዋል። እንዲህ ያለውን ንጽጽር ማድረጋቸው ዳርዊን ስለ “ሕይወት ዛፍ” የተናገረውን መላምት ያረጋግጣል ብለው አስበው ነበር። ይሁን እንጂ እንዳሰቡት አልሆነም።
ምርምሩ ያስገኘው ውጤት ምንድን ነው? የሥነ ሕይወት ተመራማሪ የሆኑት ማልኮም ጎርደን በ1999 እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ሕይወት ያላቸው ነገሮች ከተለያዩ ምንጮች የተገኙ ይመስላል። ሕይወት ያላቸውን ነገሮች በሙሉ የሚወክለው ዛፍ ከአንድ ነጠላ ሥር የተገኘ አይመስልም።” ዋነኞቹ የሕይወት ቅርንጫፎች በሙሉ ዳርዊን ያምን እንደነበረው ከአንድ ነጠላ ግንድ የበቀሉ እንደሆኑ የሚያረጋግጥ ማስረጃ አለ? ጎርደን በማከል እንዲህ ብለዋል፦ “ሕይወት ያላቸው ነገሮች ከአንድ አካል ተሻሽለው የመጡ ናቸው የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ዛሬ ከተገኙት ማስረጃዎች አንጻር ሲታይ በኪንግደም 29 *
ላይ የሚሠራ አይመስልም። ምናልባትም በሁሉም ሊባል ባይችል እንኳ በብዙዎቹ ፋይለሞች እንዲሁም በአንድ ፋይለም ውስጥ በሚገኙ በርካታ መደቦች (classes) ውስጥ ላይሠራ ይችላል።”በቅርቡ የተደረጉ ምርምሮችም ከዳርዊን ጽንሰ ሐሳብ ጋር ይቃረናሉ። ለምሳሌ በኒው ሳይንቲስት መጽሔት ላይ በ2009 የወጣ አንድ ጽሑፍ፣ የዝግመተ ለውጥ ሳይንቲስት የሆኑት ኤሪክ ባቴስት “የሕይወት ዛፍ [ጽንሰ ሐሳብ] እውነትነት እንዳለው የሚያሳይ ምንም ዓይነት ማስረጃ የለንም” እንዳሉ ጠቅሷል።30 ይኸው ጽሑፍ የዝግመተ ለውጥ ባዮሎጂስት የሆኑት ማይክል ሮዝ እንዲህ በማለት እንደተናገሩ ገልጿል፦ “የሕይወት ዛፍ ብዙ ድምፅ ሳያሰማ ወደ መቃብር በመውረድ ላይ መሆኑን ሁላችንም እናውቃለን። ከባዮሎጂ ጋር በተያያዘ ያለንን መሠረታዊ አመለካከት መለወጥ እንዳለብን ለመቀበል ግን ተቸግረናል።”31 *
የቅሪተ አካላት ማስረጃዎችስ?
በርካታ ሳይንቲስቶች ሕይወት ያላቸው ነገሮች ከአንድ አካል ተሻሽለው የመጡ ናቸው የሚለው ጽንሰ ሐሳብ በቅሪተ አካላት ማስረጃዎች የተደገፈ እንደሆነ ይናገራሉ። ለምሳሌ፣ የቅሪተ አካላት ማስረጃዎች ዓሦች ተለውጠው አምፊቢያን፣ በደረታቸው የሚሳቡ እንስሳት ደግሞ አጥቢ እንስሳት ሆነዋል የሚለውን ሐሳብ እንደሚደግፉ በመግለጽ ይከራከራሉ። ይሁን እንጂ ከቅሪተ አካላት የተገኘው ማስረጃ ምን ያሳያል?
በቅሪተ አካል ጥናት ላይ የተሠማሩት ዴቪድ ራውፕ የተባሉ የዝግመተ ለውጥ ምሑር እንዲህ ብለዋል፦ “በዳርዊን ዘመን የነበሩ ጂኦሎጂስቶችም ሆኑ የዘመናችን ጂኦሎጂስቶች ያገኙት ነገር ሕይወት ያላቸው ነገሮች ቀስ በቀስ እየተለወጡ እንደመጡ የሚያሳይ ማስረጃ ሳይሆን የተዘበራረቀና ወጥነት የሌለው ነው፤ አንዳንድ ዝርያዎች በቅሪተ አካላት ስብስብ ቅደም ተከተል ውስጥ ድንገት ብቅ ይሉና በኖሩባቸው ዘመናት በሙሉ ይህ ነው የሚባል ለውጥ ሳያሳዩ ወይም ምንም ዓይነት ለውጥ ሳይከሰትባቸው ድንገት ይጠፋሉ።”32
እንደ እውነቱ ከሆነ አብዛኞቹ ቅሪተ አካላት የሚያረጋግጡት፣ የተለያዩ ፍጥረታት ለረጅም ዘመን ምንም ለውጥ ሳይታይባቸው እንደኖሩ ነው። የተገኘው ማስረጃ፣ አንድ ዓይነት ፍጥረት ተሻሽሎ ወደ ሌላ ዓይነት ፍጥረት እንደተለወጠ አያሳይም። ከዚህ ይልቅ በዓይነታቸው ልዩ የሆኑ አካላዊ ንድፎች በድንገት ብቅ ይላሉ። ከዚህም በላይ አዳዲስ ገጽታዎች በድንገት ይከሰታሉ። ለምሳሌ በድምፅ ሞገዶች በመጠቀም የአንድን ነገር አቅጣጫና ርቀት የመለየት ችሎታ ያላቸው የሌሊት ወፎች ቅሪተ አካላት፣ ቀደም ባሉት ዘመናት ከነበሩት እንስሳት ጋር ዝምድና እንዳላቸው የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ የለም።
እንዲያውም የእንስሳት ሕይወት ከተከፋፈለባቸው ዋና ዋና ምድቦች ውስጥ ከግማሽ የሚበልጡት ብቅ ያሉት በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይመስላል። በዓይነታቸው ለየት ያሉና አዳዲስ የሆኑ በርካታ ሕያዋን ነገሮች በቅሪተ አካላት ስብስብ ውስጥ ብቅ ያሉት በድንገት በመሆኑ የቅሪተ አካል ጥናት ተመራማሪዎች ይህ የሆነበትን ዘመን “የካምብሪያን ፍንዳታ” ብለውታል። የካምብሪያን ዘመን የተባለው የትኛው ዘመን ነው?
የተመራማሪዎቹ ግምት ትክክል ነው እንበል። እነሱ እንደሚሉት ቢሆን ምድር የኖረችበት ዘመን የእግር ኳስ ሜዳ ከሚያክል የጊዜ ርዝመት ጋር ልናመሳስለው እንችላለን (1)። በዚህ መሥፈርት መሠረት የቅሪተ አካል ጥናት ተመራማሪዎች የካምብሪያን ዘመን በሚሉት ዘመን ላይ ለመድረስ የሜዳውን ሰባት ስምንተኛ የሚያህል ርቀት መጓዝ ይኖርብሃል (2)። የእንስሳት ሕይወት የተከፋፈለባቸው ዋና ዋና ምድቦች በቅሪተ አካላት ስብስብ ውስጥ ብቅ ማለት የሚጀምሩት በካምብሪያን ዘመን ውስጥ በሚገኝ አጭር ጊዜ ውስጥ ነው። ቅሪተ አካላቱ መታየት የሚጀምሩበት ጊዜ ምን ያህል አጭር ነው? በኳስ ሜዳው ላይ መሄድህን ስትቀጥል እነዚህ ሁሉ የተለያዩ ፍጥረታት ብቅ የሚሉት ከአንድ እርምጃ በሚያንስ ርቀት ውስጥ ነው!
“ማስረጃው” ያሉበት ችግሮች
ዓሦች ወደ አምፊቢያን፣ በደረታቸው የሚሳቡ እንስሳት ደግሞ ወደ አጥቢ እንስሳት እንደተለወጡ ለማሳየት እንደ ማስረጃ የሚቀርቡት ቅሪተ አካላትስ? ለዝግመተ ለውጥ ሂደት አሳማኝ ማስረጃ ይሆናሉ? ጠለቅ ብለን ስንመረምራቸው በርካታ ችግሮች ገሃድ ይወጣሉ።
አንደኛ፣ በደረታቸው ከሚሳቡ እንስሳት አንስቶ እስከ አጥቢ እንስሳት ድረስ ያለውን ቅደም ተከተል ለማሳየት ሲባል በመማሪያ መጻሕፍት ላይ የሚቀርበው የእነዚህ እንስሳት የመጠን ልዩነት አንዳንድ ጊዜ ትክክል አይደለም። በዚህ ቅደም ተከተል ውስጥ ያሉት እንስሳት መጠናቸው ተመሳሳይ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ አንዳንዶቹ እጅግ ትላልቅ ሌሎቹ ደግሞ ትናንሽ ናቸው።
ሁለተኛውና ይበልጥ ተፈታታኝ የሆነው ጉዳይ እነዚህ ፍጥረታት እርስ በርሳቸው እንደሚዛመዱ የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የሌለ መሆኑ ነው። በቅሪተ አካል ስብስብ ውስጥ የተካተቱት እነዚህ ናሙናዎች በተመራማሪዎች ግምት መሠረት በሚሊዮን ዓመታት የሚቆጠር የጊዜ ልዩነት አላቸው። ሄንሪ ጂ የተባሉ የሥነ እንስሳት ተመራማሪ፣ በአብዛኞቹ ቅሪተ አካላት መካከል ስላለው የጊዜ ልዩነት ሲናገሩ “በቅሪተ አካላቱ መካከል ያለው የጊዜ ልዩነት በጣም ብዙ በመሆኑ ምንም ዓይነት የትውልድም ሆነ የዘር ሐረግ ዝምድና እንዳላቸው በእርግጠኝነት መናገር አንችልም” ብለዋል።34 *
የሥነ ሕይወት ተመራማሪ የሆኑት ማልኮም ጎርደን የዓሦችንና የአምፊቢያኖችን ቅሪተ አካላት አስመልክተው አስተያየት ሲሰጡ፣ የተገኙት ቅሪተ አካላት “በእነዚህ ቡድኖች ውስጥ የተካተተውን በዚያ ዘመን የኖረውን ብዝሐ ሕይወት ናሙና የሚወክሉት [በጥቂቱ ብቻ] ነው፤ ምናልባትም ጨርሶ ላይወክሉ ይችላሉ” በማለት ተናግረዋል። አክለውም “እነዚህ ሕያዋን ነገሮች ከእነሱ በኋላ ለተገኘው እድገት ያበረከቱት ድርሻ ይኖር እንደሆነ አሊያም እርስ በርሳቸው ምን ዝምድና ሊኖራቸው እንደሚችል ማወቅ የሚቻልበት ምንም መንገድ የለም” ብለዋል።“ፊልሙ” ምን ያሳያል?
በ2004 በናሽናል ጂኦግራፊክ ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ፣ የቅሪተ አካላትን ስብስብ ፊልም በሚቀናበርበት ክፍል ውስጥ እየተዘጋጀ ካለ የዝግመተ ለውጥ ፊልም ጋር ያመሳሰለው ሲሆን ይህን ፊልም ለማዘጋጀት ከሚያስፈልገው “ከእያንዳንዱ 1,000 ተከታታይ ምስል ውስጥ 999 ያህሉ ጠፍቷል።”36 ይህ ምሳሌ ምን አንድምታ እንደሚኖረው ተመልከት።
መጀመሪያ ላይ 100,000 ተከታታይ ምስሎች ከነበሩት አንድ ፊልም ውስጥ 100 የሚሆኑትን ምስሎች አገኘህ እንበል። በእነዚህ ምስሎች ተመሥርተህ የፊልሙን ታሪክ ማወቅ ትችላለህ? ታሪኩ እንዲህ መሆን አለበት ብለህ አስቀድመህ ገምተሃል እንበል፤ ሆኖም ካገኘሃቸው 100 ምስሎች መካከል የአንተን ግምት እንዲደግፉ ተደርገው ሊቀናበሩ የሚችሉት 5ቱ ብቻ ቢሆኑና የቀሩት 95ቱ ምስሎች አንተ ከገመትከው የተለየ ታሪክ የሚናገሩ ቢሆንስ? አምስቱ ምስሎች መጀመሪያ ላይ ስለ ታሪኩ የነበረህን ግምት እንደሚያረጋግጡ በመግለጽ ብትከራከር ምክንያታዊ ይሆናል? አምስቱን ምስሎች በዚህ ቅደም ተከተል ያስቀመጥከው የአንተን ሐሳብ ስለሚደግፍልህ ብቻ ሊሆን አይችልም? አመለካከትህ በተቀሩት 95 ምስሎች ላይ የተመሠረተ ቢሆን ይበልጥ ምክንያታዊ አይሆንም?
ይህ ምሳሌ የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ አራማጆች ስለ ቅሪተ አካላት ማስረጃዎች ካላቸው አመለካከት ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው? አብዛኞቹ ቅሪተ አካላት ማለትም 95ቱ የፊልሙ ምስሎች፣ ዝርያዎቹ በዘመናት ሂደት ውስጥ ምንም ዓይነት ለውጥ እንደማይታይባቸው የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ተመራማሪዎች ለበርካታ ዓመታት ሳይቀበሉ ቆይተዋል። እንዲህ ያለ አሳማኝ ማስረጃ እያለ ዝምታን የመረጡት ለምንድን ነው? ሪቻርድ ሞሪስ የተባሉት ደራሲ እንዲህ 37
ብለዋል፦ “የቅሪተ አካል ጥናት ተመራማሪዎች ሥር የሰደደውን የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ የተቀበሉ ሲሆን ወደ ተቃራኒው አቅጣጫ የሚጠቁም ማስረጃ ባገኙበት ጊዜም እንኳ ይህን ጽንሰ ሐሳብ ሙጭጭ አድርገው የያዙ ይመስላል። የቅሪተ አካላት ማስረጃዎችን ተቀባይነት ካገኘው የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ አንጻር ለመተርጎም ሲሞክሩ ቆይተዋል።”“በቅደም ተከተል የተቀመጡ ቅሪተ አካላትን ወስዶ የዘር ሐረግን ያመለክታሉ ማለት በሙከራ ሊረጋገጥ የሚችል ሳይንሳዊ ጽንሰ ሐሳብ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ሕፃናትን ለማስተኛት ከሚነበብ ተረት ተለይቶ አይታይም፤ አዝናኝ ምናልባትም ትምህርት ሰጪ ሊሆን ቢችልም ሳይንሳዊ አይደለም።”—ኢን ሰርች ኦቭ ዲፕ ታይም—ቢዮንድ ዘ ፎሲል ሪከርድ ቱ ኤ ኒው ሂስትሪ ኦቭ ላይፍ፣ በሄንሪ ጂ የተዘጋጀ ከገጽ 116-117
በአሁኑ ጊዜ ስላሉት የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ አራማጆችስ ምን ማለት ይቻላል? ዛሬም ቅሪተ አካላትን በተወሰነ ቅደም ተከተል ማስቀመጣቸውን የቀጠሉት፣ እንዲህ ያለው ቅደም ተከተል በቅሪተ አካላትና በጄኔቲክ ማስረጃዎች የተደገፈ ስለሆነ ሳይሆን እንዲህ ማድረጋቸው በአሁኑ ጊዜ ተቀባይነት ካገኘው የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ጋር የሚስማማ ስለሆነ ብቻ ይሆን? *
ታዲያ ምን ይመስልሃል? ከማስረጃው ጋር ይበልጥ የሚስማማው የትኛው መደምደሚያ ነው? እስካሁን የተመለከትናቸውን እውነታዎች ልብ በል።
-
በመጀመሪያ በምድር ላይ የነበረው ሕይወት ያለው ነገር “ያልተወሳሰበ” አልነበረም።
-
የአንድ ሴል የተለያዩ ክፍሎች እንኳ በአጋጣሚ ሊገኙ የሚችሉበት ዕድል እጅግ የመነመነ ነው።
-
ሴሎች ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ የሚያደርግ “የኮምፒውተር ፕሮግራም” ወይም ኮድ የሆነው ዲ ኤን ኤ እጅግ በጣም ውስብስብ በመሆኑ የትኛውም ዓይነት ሰው ሠራሽ የኮምፒውተር ፕሮግራም ወይም መረጃ የሚይዝ መሣሪያ ሊወዳደረው የማይችል ከፍተኛ ጥበብ የታየበት ነው።
-
የጄኔቲክ ምርምር ሕይወት ያለው ነገር ከአንድ አካል ተሻሽሎ የመጣ አለመሆኑን አረጋግጧል። በተጨማሪም የእንስሳት ሕይወት የተከፋፈለባቸው ዋና ዋና ምድቦች በቅሪተ አካል ስብስብ ውስጥ ብቅ ያሉት በድንገት ነው።
ከእነዚህ እውነታዎች አንጻር ሲታይ ማስረጃዎቹ መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወት ስለተገኘበት መንገድ ከሚሰጠው ማብራሪያ ጋር ይስማማሉ ብሎ መደምደም ምክንያታዊ አይመስልህም? ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘው አብዛኛው የፍጥረት ዘገባ ከሳይንስ ጋር እንደሚጋጭ ይናገራሉ። ይህ እውነት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ ምን ይላል?
^ አን.9 ፋይለም የሚለው የባዮሎጂ ቃል አንድ ዓይነት አካላዊ ንድፍ ያላቸውን በርካታ እንስሳት ያቀፈ ቡድን ያመለክታል። ሳይንቲስቶች ሕይወት ያላቸውን ነገሮች በሙሉ ከሚከፋፍሉባቸው ዘዴዎች አንዱ ሰባት ደረጃዎች ያሉት ሲሆን ደረጃዎቹ ከላይ ወደታች እየጠበቡ ይሄዳሉ። የመጀመሪያው ደረጃ በስፋቱ ከሁሉ የሚበልጠው ኪንግደም የተባለው ክፍል ነው። ከዚያም ፋይለም፣ ክላስ፣ ኦርደር፣ ፋሚሊ፣ ጂነስ እና ስፒሽስ የተባሉት ክፍሎች ይከተላሉ። ለምሳሌ ፈረስ በሚከተለው መንገድ ይመደባል፦ ኪንግደም፣ አኒማልያ፤ ፋይለም፣ ኮርዳታ፤ ክላስ፣ ማማልያ፤ ኦርደር፣ ፐሪሶዳክቲላ፤ ፋሚሊ፣ ኤክዊዴ፤ ጂነስ፣ ኤክዉስ፤ ስፒሽስ፣ ካባለስ።
^ አን.10 ኒው ሳይንቲስት የተሰኘው መጽሔትም ሆነ ባቴስትና ሮዝ ይህን የገለጹት የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ስህተት ነው ለማለት ፈልገው እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል። ከዚህ ይልቅ ሁለቱም ሊያስገነዝቡ የፈለጉት የዳርዊን ጽንሰ ሐሳብ ዋነኛ ክፍል የሆነው የሕይወት ዛፍ በማስረጃ የተደገፈ አለመሆኑን ነው። እንደነዚህ ያሉ ሳይንቲስቶች ስለ ዝግመተ ለውጥ ሌላ ማብራሪያ ለማግኘት አሁንም ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።
^ አን.21 ሄንሪ ጂ ይህን የተናገሩት የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ስህተት እንደሆነ ለማመልከት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይህን አስተያየት የሰጡት ከቅሪተ አካላት ስብስብ የሚገኘው ግንዛቤ ውስን እንደሆነ ለመግለጽ ነው።
^ አን.22 ማልኮም ጎርደን የዝግመተ ለውጥን ትምህርት የሚደግፉ ሰው ናቸው።
^ አን.27 ለዚህ ምሳሌ እንዲሆንህ “ ስለ ሰው ዝግመተ ለውጥ ምን ማለት ይቻላል?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
^ አን.50 ማሳሰቢያ፦ በዚህ ሣጥን ውስጥ ከተጠቀሱት ተመራማሪዎች መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፍጥረት የሚያስተምረውን ትምህርት አያምኑም። ሁሉም የዝግመተ ለውጥን ትምህርት የሚቀበሉ ናቸው።
^ አን.54 “ሆሚኒድ” የሚለው ቃል የዝግመተ ለውጥ ተመራማሪዎች የሰውን ዘርና በቅድመ ታሪክ ዘመናት የኖሩትን ሰው መሰል ዝርያዎች ለማመልከት የሚጠቀሙበት ቃል ነው።