ጥያቄ 2
ሕይወት ካላቸው ነገሮች መካከል ውስብስብ ያልሆነ አለ?
አካልህ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከሚገኙት እጅግ ውስብስብ የሆኑ ነገሮች መካከል አንዱ ነው። አካልህ 100 ትሪሊዮን በሚያህሉ ጥቃቅን ሴሎች የተገነባ ነው፤ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል የአጥንት ሴሎች፣ የደም ሴሎችና የአንጎል ሴሎች ይገኙበታል።7 እንዲያውም በአካልህ ውስጥ ከ200 የሚበልጡ የተለያዩ የሴል ዓይነቶች ይገኛሉ።8
እነዚህ ሴሎች ቅርጻቸውና ሥራቸው በጣም የተለያየ ቢሆንም እጅግ ውስብስብ በሆነ መንገድ ተቀናጅተው ይሠራሉ። እጅግ ፈጣን በሆኑ የመረጃ ማስተላለፊያ ሽቦዎች አማካኝነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኮምፒውተሮችን የሚያገናኘው ኢንተርኔትም እንኳ ከእነዚህ ሴሎች ጋር ሲነጻጸር በጣም ቀርፋፋ ነው። የሰው ልጅ የፈለሰፈው የትኛውም ዓይነት የፈጠራ ውጤት፣ ውስብስብነት የለውም በሚባለው ሴል ውስጥ ከሚካሄደው የተራቀቀ አሠራር ጋር እንኳ ሊወዳደር አይችልም። ታዲያ የሰው አካል የተገነባባቸው ሴሎች ወደ ሕልውና የመጡት እንዴት ነው?
ብዙ ሳይንቲስቶች ምን ይላሉ? ሕያው የሆኑ ሴሎች በሙሉ ኒውክሊየስ ያላቸውና ኒውክሊየስ የሌላቸው ተብለው በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ይከፈላሉ። የሰው፣ የእንስሳትና የዕፅዋት ሴሎች ኒውክሊየስ አላቸው። የባክቴሪያ ሴሎች ኒውክሊየስ የላቸውም። ኒውክሊየስ ያላቸው ሴሎች ዩካርዮቲክ ይባላሉ። ኒውክሊየስ የሌላቸው ደግሞ ፕሮካርዮቲክ በመባል ይታወቃሉ። ኒውክሊየስ የሌላቸው ሴሎች ኒውክሊየስ ካላቸው ሴሎች አንጻር ሲታዩ እምብዛም ውስብስብ ስላልሆኑ ብዙዎች የእንስሳትና የዕፅዋት ሴሎች ከባክቴሪያ ሴሎች ተሻሽለው እንደመጡ ያምናሉ።
እንዲያውም አንዳንድ “ውስብስብ ያልሆኑ” ፕሮካርዮቲክ ሴሎች በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዓመታት ሌሎች ሴሎችን እንደዋጧቸው ሆኖም ከሰውነታቸው ጋር እንዳላዋሃዷቸው በርካታ ሰዎች ያስተምራሉ። ከዚህም በላይ የማሰብ ችሎታ የሌለው “ተፈጥሮ” እነዚህ የተዋጡ ሴሎች ሥር ነቀል ለውጥ እንዲያደርጉ ብቻ ሳይሆን “የዋጧቸው” ሴሎች ራሳቸውን በሚተኩበት ጊዜ የተዋጡት ሴሎች እዚያው ባሉበት እንዲቀጥሉ እንደረዳቸው ጽንሰ ሐሳቡ ይናገራል።መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? በምድር ላይ ያሉትን ሕይወት ያላቸውን ነገሮች በሙሉ የፈጠረው የማሰብ ችሎታ ያለው አንድ አካል እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ምክንያታዊ ሐሳብ ልብ በል፦ “በእርግጥ እያንዳንዱ ቤት የራሱ ሠሪ አለው፤ ሁሉን ነገር የሠራው ግን አምላክ ነው።” (ዕብራውያን 3:4) ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ደግሞ እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ሥራህ እንዴት ብዙ ነው! ሁሉን በጥበብ ሠራህ፤ ምድርም በፍጥረትህ ተሞላች። . . . ታላላቅና ታናናሽ እንስሳት፣ ስፍር ቍጥር የሌላቸውም ነፍሳት በውስጧ አሉ።”—መዝሙር 104:24, 25
ማስረጃው ምን ያመለክታል? በማይክሮባዮሎጂ መስክ የተገኘው እድገት ውስብስብ ያልሆኑ ፕሮካርዮቲክ ሴሎችን ውስጣዊ ክፍል በጥልቀት ለመመልከት አስችሏል። የዝግመተ ለውጥን ጽንሰ ሐሳብ የሚያራምዱ ሳይንቲስቶች የመጀመሪያዎቹ ሕያው ሴሎች ከፕሮካርዮቲክ ሴሎች ጋር እንደሚመሳሰሉ ያስተምራሉ።10
የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ እውነት ከሆነ የመጀመሪያው “ውስብስብ ያልሆነ” ሴል እንዴት በአጋጣሚ እንደተገኘ አሳማኝ የሆነ ማብራሪያ መስጠት ነበረበት። በአንጻሩ ደግሞ ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ከሆነ በጣም ትንሽ በሚባለው ፍጥረት ላይ እንኳ ሳይቀር የተራቀቀ ንድፍ መንጸባረቅ ይኖርበታል። አንድን የፕሮካርዮቲክ ሴል ለምን አትጎበኝም? በምትጎበኝበት ጊዜ ‘እንዲህ ያለው ሴል እንዲሁ በአጋጣሚ ሊገኝ ይችላል?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ።
የሴል “አጥር”
በአንድ ፕሮካርዮቲክ ሴል ውስጥ ገብተህ ለመጎብኘት የሰውነትህ መጠን ከአንዲት ትንሽ ነጥብ በብዙ መቶዎች እጥፍ ማነስ ይኖርበታል። ሆኖም ጠንካራ የሆነውና የመተጣጠፍ ባሕርይ ያለው የሴሉ ሽፋን ወደ ውስጥ እንዳትገባ ይከለክልሃል፤ ይህ ሽፋን የሚያከናውነው ተግባር ከጡብና ከሲሚንቶ ከተገነባ የአንድ ፋብሪካ አጥር ጋር ይመሳሰላል። ወደ 10,000 የሚጠጉ የሴል ሽፋኖች ቢነባበሩ እንኳ የሚኖራቸው ውፍረት ከአንድ ወረቀት ውፍረት አያልፍም። ይሁን እንጂ የሴል ሽፋን ከጡብ ከተሠራ አጥር የበለጠ የተወሳሰበ ነው። እንዴት?
እንደ አንድ የፋብሪካ አጥር ሁሉ የሴል ሽፋንም በሴሉ ውስጥ ያሉትን ነገሮች በዙሪያው ካሉ ጎጂ ነገሮች ይጠብቃቸዋል። ይሁንና ሽፋኑ ድፍን ያለ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ እንደ ኦክስጅን ያሉ ጥቃቅን ሞለኪውሎች እንዲገቡና እንዲወጡ በማድረግ ሴሉ “እንዲተነፍስ” ያስችለዋል። ያም ሆኖ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ይበልጥ ውስብስብ የሆኑ ሞለኪውሎች ከሴሉ ፈቃድ ውጭ እንዳይገቡ ይከላከላል። ከዚህም በላይ ጠቃሚ የሆኑ ሞለኪውሎች ከሴሉ አፈትልከው እንዳይወጡ ያደርጋል። የሴሉ ሽፋን ይህን ሥራ የሚያከናውነው እንዴት ነው?
እስቲ አሁን ደግሞ ስለ ፋብሪካው አስብ። ፋብሪካው ወደ ውስጥ የሚገቡትንም ሆነ የሚወጡትን ምርቶች የሚቆጣጠሩ ጠባቂዎች ሊኖሩት ይችላሉ።
በተመሳሳይም የሴሉ ሽፋን አንደ በርና እንደ ጠባቂ ሆነው የሚያገለግሉ ለየት ያሉ የፕሮቲን ሞለኪውሎች አሉት።ከእነዚህ ፕሮቲኖች መካከል አንዳንዶቹ (1) የተወሰኑ የሞለኪውል ዓይነቶችን ብቻ ሊያስገቡና ሊያስወጡ የሚችሉ ቀዳዳዎች አሏቸው። ሌሎች ፕሮቲኖች ደግሞ በአንድ በኩል ክፍት (2) ሲሆኑ በሌላው በኩል ዝግ ናቸው። እነዚህ ፕሮቲኖች ከሚያልፈው ንጥረ ነገር ጋር የሚመሳሰል ቅርጽ ያለው የመጫኛ ጣቢያ (3) አላቸው። ይህ ንጥረ ነገር በመጫኛው በኩል ከገባ በኋላ ሌላኛው የፕሮቲን በር ተከፍቶ ጭነቱ በዚያ በኩል ይራገፋል። (4) ይህ ሁሉ እንቅስቃሴ በጣም ያልተወሳሰቡ በሚባሉ ሴሎች ውስጥ ሳይቀር ይከናወናል።
“የፋብሪካው” የውስጠኛ ክፍል
“ጠባቂዎቹ” እንድታልፍ ፈቅደውልህ አሁን ሴሉ ውስጥ ነው ያለኸው እንበል። የፕሮካርዮቲክ ሴል ውስጠኛ ክፍል አልሚ ምግቦችን፣ ጨዎችንና ሌሎች ንጥረ ነገሮችን በያዘ ፈሳሽ የተሞላ ነው። ሴሉ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማምረት እነዚህን ንጥረ ነገሮች ይጠቀማል። ይሁን እንጂ ሥራው በዘፈቀደ የሚከናወን አይደለም። ጥሩ የሥራ አመራር እንዳለው ፋብሪካ ሁሉ ሴሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ኬሚካላዊ ሂደቶች በተወሰነላቸው ቅደም ተከተልና በተመደበላቸው ጊዜ እንዲከናወኑ ያደራጃቸዋል።
አንድ ሴል አብዛኛውን ጊዜውን የሚያሳልፈው ፕሮቲኖችን በመሥራት ነው። ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ሴሉ 20 የሚያህሉ የተለያዩ አሚኖ አሲዶችን ሲሠራ ትመለከታለህ፤ እነዚህ አሚኖ አሲዶች ፕሮቲን ለመሥራት የሚያገለግሉ መሠረታዊ ነገሮች ናቸው። ለግንባታ የሚያስፈልጉት እነዚህ መሠረታዊ ነገሮች ወደ ራይቦዞሞች (5) ይወሰዳሉ፤ ራይቦዞም አሚኖ አሲዶች በተወሰነላቸው ቅደም ተከተል ተጣምረው ራሱን የቻለ አንድ ፕሮቲን እንዲያስገኙ የሚያደርግ አውቶማቲክ ማሽን ነው ሊባል ይችላል። የአንድ ፋብሪካ የሥራ ሂደት ማዕከላዊ በሆነ የኮምፒውተር ፕሮግራም እንደሚመራ ሁሉ በሴል ውስጥ የሚከናወኑት ብዙዎቹ ተግባሮችም የሚመሩት ዲ ኤን ኤ (6) በሚባል “የኮምፒውተር ፕሮግራም” ወይም ኮድ አማካኝነት ነው። ራይቦዞም የትኞቹን ፕሮቲኖች መሥራት እንዳለበትና በምን ዓይነት መንገድ (7) እንደሚሠራቸው የሚገልጽ ዝርዝር መመሪያ ከዲ ኤን ኤ ይቀበላል።
ፕሮቲን ከተሠራ በኋላ የሚከናወነው ነገር በጣም የሚያስደንቅ ነው! እያንዳንዱ ፕሮቲን ይተጣጠፍና በዓይነቱ ልዩ የሆነ ባለ ሦስት ገጥ (three-dimensional) ቅርጽ (8) ይይዛል። ፕሮቲን የሚያከናውነውን ተግባር የሚወስነው ይህ ቅርጽ ነው። * የመኪና ሞተር ክፍሎች የሚገጣጠሙበትን ክፍል በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። ሞተሩ እንዲሠራ ከተፈለገ እያንዳንዱ ክፍል በትክክል መሠራት ይኖርበታል። በተመሳሳይም አንድ ፕሮቲን በትክክል ካልተሠራና ተገቢው ቅርጽ እንዲኖረው ተደርጎ ካልተጣጠፈ የሚፈለግበትን ተግባር በተገቢው ሁኔታ ማከናወን የማይችል ከመሆኑም በላይ ሴሉ ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል።
ፕሮቲኑ ከተሠራበት ቦታ ተነስቶ ወደሚፈለግበት ቦታ የሚደርሰው እንዴት ነው? በሴል ውስጥ የሚመረተው እያንዳንዱ ፕሮቲን፣ የት መሄድ እንዳለበት የሚገልጽ “አድራሻ” አለው። በእያንዳንዱ ደቂቃ በሺህ የሚቆጠሩ ፕሮቲኖች ተሠርተው ወደሚፈለጉበት ቦታ የሚደርሱ ቢሆንም አንዳቸውም እንኳ ወደ ተሳሳተ ቦታ አይሄዱም።
ለእነዚህ እውነታዎች ትኩረት መስጠት ለምን አስፈለገ? ያልተወሳሰበ በሚባለው ሕይወት ያለው ነገር ውስጥ የሚገኙት ውስብስብ ሞለኪውሎች ብቻቸውን ቢሆኑ ሊባዙ አይችሉም። ከሴሉ ውጭ ከሆኑ ይፈራርሳሉ። በሴሉ ውስጥ ቢሆኑም በሌሎች ውስብስብ የሆኑ ሞለኪውሎች ካልታገዙ መባዛት አይችሉም። ለምሳሌ አዴኖሲን ትራይፎስፌት (ኤ ቲ ፒ) የሚባለውን ልዩ የሆነ የኃይል ሞለኪውል ለመሥራት ኢንዛይሞች የሚያስፈልጉ ሲሆን ኢንዛይሞችን ለመሥራት ደግሞ ከኤ ቲ ፒ የሚገኘው ኃይል ያስፈልጋል። በተመሳሳይም ኢንዛይሞችን ለመሥራት ዲ ኤን ኤ (ክፍል 3 ስለዚህ ሞለኪውል ያብራራል) ሲያስፈልግ ዲ ኤን ኤ ለመሥራት ደግሞ ኢንዛይሞች ያስፈልጋሉ። በተጨማሪም ሌሎች ፕሮቲኖች በሴል ብቻ ሊመረቱ ይችላሉ፤ ይሁን እንጂ አንድ ሴል ሊመረት የሚችለው በፕሮቲኖች ብቻ ሊሆን ይችላል። *
ራዱ ፖፓ የተባሉ ማይክሮባዮሎጂስት ስለ ፍጥረት በሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ አያምኑም። ሆኖም በ2004 እንዲህ ሲሉ ጠይቀዋል፦ “የተሟላ ቁጥጥር በሚደረግበት ቤተ ሙከራ ውስጥ ሕይወት ያለው ነገር ማስገኘት ካልቻልን ተፈጥሮ በራሱ እንዴት ሕይወት ያለው ነገር ሊያስገኝ ይችላል?”13 አክለውም “አንድ ሕያው ሴል ተግባሩን እንዲያከናውን የሚያስፈልጉት ሂደቶች እጅግ ውስብስብ በመሆናቸው ሁሉም በአጋጣሚ በአንድ ጊዜ ይገኛሉ ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው” ብለዋል።14
ታዲያ ምን ይመስልሃል? የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ አራማጆች በምድር ላይ ሕይወት የተገኘው ያለ መለኮት ጣልቃ ገብነት እንደሆነ በመናገር ሰዎችን ለማሳመን ይሞክራሉ። ይሁን እንጂ ሳይንቲስቶች ስለ ሕያዋን ነገሮች ይበልጥ ባወቁ መጠን ሕይወት እንዲሁ በአጋጣሚ ሊገኝ እንደማይችል ግልጽ እየሆነላቸው መጥቷል። አንዳንድ የዝግመተ ለውጥ ሳይንቲስቶች እውነታውን ላለመጋፈጥ ሲሉ የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብና ሕይወት ስለተገኘበት መንገድ የሚነሳው ጥያቄ ሁለት የተለያዩ ነገሮች እንደሆኑ አድርገው ለማቅረብ ይሞክራሉ። ይሁንና እንዲህ ያለው አካሄድ ምክንያታዊ ይመስልሃል?
የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ የተመሠረተው ‘ሕይወት የተገኘው ለረጅም ዓመታት በአጋጣሚ በተከናወኑ ክስተቶች አማካኝነት ነው’ በሚለው መላምት ላይ ነው። ጽንሰ ሐሳቡ በመቀጠል በዘፈቀደ የሚከሰቱ ድንገተኛ አጋጣሚዎች ዓይነታቸው የበዛና እጅግ ውስብስብ የሆኑ ሕይወት ያላቸው ነገሮችን እንዳስገኙ ለማብራራት ይሞክራል። ይሁን እንጂ የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ምንም መሠረት ከሌለው፣ በዚህ መላምት ላይ የተገነቡት ጽንሰ ሐሳቦች መጨረሻቸው ምን ይሆን? መሠረት የሌለው ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ መፍረሱ እንደማይቀር ሁሉ ስለ ሕይወት አመጣጥ ማብራሪያ መስጠት ያልቻለው የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብም መንኮታኮቱ አይቀርም።
የአንድን “ውስብስብ ያልሆነ” ሴል አወቃቀርና ተግባሩን የሚያከናውንበትን መንገድ በአጭሩ ከተመለከትክ በኋላ ከመረጃዎቹ ምን አስተዋልክ? ሕይወት በአጋጣሚ በተከናወኑ በርካታ ክስተቶች መገኘቱን ወይስ የተራቀቀ ንድፍ ያለው መሆኑን? አሁንም እርግጠኛ ካልሆንክ የሁሉንም ሴሎች አሠራር ስለሚቆጣጠረው “ዋነኛ ፕሮግራም” በዝርዝር እንድትመረምር እንጋብዝሃለን።