በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሕዝበ ክርስትና አምላክንና መጽሐፍ ቅዱስን ክዳለች

ሕዝበ ክርስትና አምላክንና መጽሐፍ ቅዱስን ክዳለች

ክፍል 4

ሕዝበ ክርስትና አምላክንና መጽሐፍ ቅዱስን ክዳለች

1, 2. አንዳንድ ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት የሌላቸው ለምንድን ነው? ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

1 በብዙ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንከተላለን በሚሉ ሰዎች መጥፎ ምግባር የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ጎን ገሸሽ ከማድረጋቸውም በላይ ለመጽሐፉ አክብሮት የላቸውም። በአንዳንድ አገሮች ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ለጦርነት መንስኤ እንደሆነ፣ የነጮች መጽሐፍ እንደሆነና ቅኝ አገዛዝን የሚደግፍ መጽሐፍ እንደሆነ ተደርጎ ሲነገር ቆይቷል። ሆኖም እነዚህ የተሳሳቱ አመለካከቶች ናቸው።

2 በመካከለኛው ምሥራቅ የተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ በክርስትና ስም ለረጅም ጊዜ የተካሄዱትን የቅኝ ግዛት ጦርነቶችም ሆነ በስግብግብነት የሌሎችን ሀብትና ጉልበት ያላግባብ በመጠቀም የተደረገውን ብዝበዛ አይደግፍም። ከዚህ በተቃራኒው መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብና ኢየሱስ ያስተማረውን የእውነተኛ ክርስትና ትምህርት በመማር መጽሐፍ ቅዱስ ጦርነትን፣ የሥነ ምግባር ብልግናንና የሌሎችን ሀብትና ጉልበት አላግባብ መበዝበዝን አጥብቆ እንደሚያወግዝ መረዳት ትችላለህ። ስህተቱ የስግብግብ ሰዎች እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ አይደለም። (1 ቆሮንቶስ 13:1-6፤ ያዕቆብ 4:1-3፤ 5:1-6፤ 1 ዮሐንስ 4:7, 8) ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚሰጠው ጥሩ ምክር ተቃራኒ የሆነ ኑሮ የሚኖሩ ራስ ወዳድ የሆኑ ሰዎች መጥፎ ምግባር ከመጽሐፍ ቅዱስ ውድ ሀብት እንዳትጠቀም እንቅፋት እንዲሆኑብህ መፍቀድ የለብህም።

3. የታሪክ ሐቅ ስለ ሕዝበ ክርስትና ምን ይመሰክራል?

3 የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ከማይከተሉት ሰዎች መካከል የሕዝበ ክርስትና ሰዎችና አገሮች ይገኙበታል። “ሕዝበ ክርስትና” የሚለው ሐረግ ክርስትና ያለበት የዓለም ክፍል የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። ይህ ሐረግ በአመዛኙ የምዕራቡን ዓለም ያመለክታል፤ በዚህ የዓለም ክፍል ከአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ አካባቢ ጀምሮ የጎላ ሥፍራ የያዘ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ተንሠራፍቶ ይገኛል። ሕዝበ ክርስትና መጽሐፍ ቅዱስ በእጅዋ ከገባ ብዙ መቶ ዘመናት ተቆጥረዋል፤ ቀሳውስቷም መጽሐፍ ቅዱስን እንደሚያስተምሩና የአምላክ ወኪሎች እንደሆኑ ይናገራሉ። ሆኖም የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስትና ሚስዮናውያን እውነትን ያስተምራሉን? ድርጊታቸው በእርግጥ አምላክንና መጽሐፍ ቅዱስን ይወክላልን? በእርግጥ ክርስትና በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ይንጸባረቃልን? በፍጹም። ሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቷ ጎልቶ መታየት ከጀመረበት ከአራተኛው መቶ ዘመን ጀምሮ የአምላክም ሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጠላት መሆኗን አስመስክራለች። አዎን፣ ሕዝበ ክርስትና አምላክንና መጽሐፍ ቅዱስን እንደካደች የታሪክ ሐቅ ይመሰክራል።

መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ መሠረተ ትምህርቶች

4, 5. አብያተ ክርስቲያናት የትኞቹን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ትምህርቶች ያስተምራሉ?

4 የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ ትምህርቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሳይሆን በግሪክ፣ በግብፅ፣ በባቢሎንና በሌሎች የጥንት አፈ ታሪኮች ላይ የተመሠረቱ ናቸው። የሰው ነፍስ ያለመሞት ባሕርይ አላት፣ በእሳታማ ሲኦል ውስጥ ለዘላለም መሠቃየት፣ መንጽሔ፣ ሥላሴ (በአንድ አምላክ ሦስት አካላት) እና የመሳሰሉት ትምህርቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኙም።

5 ለምሳሌ ያህል ክፉ ሰዎች በእሳታማ ሲኦል ውስጥ ለዘላለም ይሠቃያሉ የሚለውን ትምህርት ተመልከት። ስለዚህ ትምህርት ምን ይሰማሃል? ብዙዎች በጣም ይዘገንናቸዋል። አምላክ ሰዎችን ለዘላለም እንዲሠቃዩ በማድረግ መቅጣቱ ተገቢ እንዳልሆነ ይሰማቸዋል። “እግዚአብሔር ፍቅር” ስለሆነ እንዲህ ዓይነቱ የጭካኔ አስተሳሰብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተገለጸው አምላክ ተቃራኒ የሆነ ነው። (1 ዮሐንስ 4:8) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነቱ ትምህርት ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ‘በልቡ ያላሰበው’ ነገር እንደሆነ በግልጽ ይናገራል።​—ኤርምያስ 7:31፤ 19:5፤ 32:35

6. መጽሐፍ ቅዱስ ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት ሐሰት መሆኑን የሚያረጋግጠው እንዴት ነው?

6 በዛሬው ጊዜ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናትን ጨምሮ ብዙ ሃይማኖቶች ሰዎች ሲሞቱ ወደ ሰማይ አሊያም ደግሞ ወደ ሲኦል የምትሄድ የማትሞት ነፍስ አለቻቸው ብለው ያስተምራሉ። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አይደለም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል በግልጽ ይናገራል:- “ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም፤ . . . አንተ በምትሄድበት በሲኦል [በመቃብር] ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙም።” (መክብብ 9:5, 10) በተጨማሪም መዝሙራዊው ሰው ሲሞት “ወደ መሬቱም ይመለሳል ያን ጊዜ ምክሩ ሁሉ ይጠፋል” ሲል ገልጿል።​—መዝሙር 146:4

7. አዳምና ሔዋን የአምላክን ሕግ በመጣሳቸው የተበየነባቸው ቅጣት ምንድን ነው?

7 አዳምና ሔዋን የአምላክን ሕግ በጣሱ ጊዜም ቅጣቱ ያለመሞት ባሕርይ እንዲያገኙ ማድረግ እንዳልነበረ አስታውስ። እንደዚያ ቢሆን ኖሮ ቅጣት ሳይሆን ሽልማት ይሆን ነበር! ከዚህ ይልቅ ‘ወደ ወጡበት መሬት እንደሚመለሱ’ ተነግሯቸዋል። አምላክ “አፈር ነህና፣ ወደ አፈርም ትመለሳለህ” በማለት ለአዳም ጠበቅ አድርጎ ገልጾለታል። (ዘፍጥረት 3:19) ስለዚህ ነፍስ ያለመሞት ባሕርይ አላት የሚለው ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም፤ ከዚህ ይልቅ የሕዝበ ክርስትና አባላት ከእነርሱ በፊት ይኖሩ ከነበሩ ክርስቲያን ያልሆኑ ሕዝቦች የወሰዱት ትምህርት ነው።

8. መጽሐፍ ቅዱስ ሕዝበ ክርስትና የምታስተምረው የሥላሴ መሠረተ ትምህርት ሐሰት መሆኑን የሚያረጋግጠው እንዴት ነው?

8 በተጨማሪም የሕዝበ ክርስትና የሥላሴ ትምህርት አምላክን ሦስትነት በአንድነት የሆነ ምሥጢራዊ አምላክ እንደሆነ አድርጎ ይገልጸዋል። ሆኖም ይኸኛውም ትምህርት ቢሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም። ለምሳሌ ያህል አምላክ በኢሳይያስ 40:25 ላይ “እንግዲህ እተካከለው ዘንድ በማን መሰላችሁኝ?” በማለት በግልጽ ተናግሯል። መልሱ የማያሻማ ነው:- ከእሱ ጋር ሊተካከል የሚችል የለም። በተጨማሪም መዝሙር 83:18 [NW] ‘ስምህ ይሖዋ የሆነው አንተ፣ በምድር ሁሉ ላይ አንተ ብቻ ልዑል ነህ’ በማለት በአጭሩ ይገልጻል።​—በተጨማሪም ኢሳይያስ 45:5ን፤ 46:9ን፤ ዮሐንስ 5:19ን፤ 6:38ንና 7:16ን ተመልከት።

9. ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችና የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ስለሚያስተምሯቸው ትምህርቶች ምን ማለት እንችላለን?

9 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ የሚሰጠው ትምህርት ግልጽ፣ በቀላሉ የሚገባና ምክንያታዊ ነው። የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ትምህርቶች ግን እንደዚህ አይደሉም። እንዲያውም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይጋጫሉ።

አምላካዊ ያልሆኑ ድርጊቶች

10, 11. የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ሲፈጽሙት ከቆዩት ድርጊት ተቃራኒ የሆኑ ነገሮችን እንድናደርግ የሚፈልግብን በምን መንገዶች ነው?

10 ሕዝበ ክርስትና የሐሰት መሠረተ ትምህርቶችን ከማስተማሯም በተጨማሪ አምላክንና መጽሐፍ ቅዱስን በድርጊቶቿ ክዳለች። ቀሳውስትና አብያተ ክርስቲያናት ባለፉት መቶ ዘመናት የፈጸሟቸው ነገሮችና በዘመናችን እየፈጸሟቸው ያሉት ነገሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው አምላክ ከሚፈልገው ነገር ተቃራኒ የሆኑና የክርስትና መሥራች የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ካስተማረው ትምህርት ጋር የሚቃረኑ ናቸው።

11 ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ተከታዮቹ በዓለም ፖለቲካዊ ጉዳዮች ጣልቃ መግባትም ሆነ በጦርነቶች ውስጥም መሳተፍ እንደሌለባቸው አስተምሯቸዋል። በተጨማሪም ሰላም ወዳዶችና ሕግ አክባሪዎች እንዲሆኑ፣ ለሰዎች ከማንኛውም ዓይነት መሠረተ ቢስ ጥላቻ ነፃ የሆነ ፍቅር እንዲኖራቸውና የሌሎችን ሕይወት ከማጥፋት ይልቅ የራሳቸውን ሕይወት ለሌሎች መሥዋዕት ለማድረግ እንኳ ፈቃደኞች እንዲሆኑ አስተምሯቸዋል።​—ዮሐንስ 15:13፤ ሥራ 10:34, 35፤ 1 ዮሐንስ 4:20, 21

12. ኢየሱስ እውነተኛ ክርስቲያኖች በምን ተለይተው እንደሚታወቁ ተናግሯል?

12 እንዲያውም ኢየሱስ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከአስመሳዮቹ ሐሰተኛ ክርስቲያኖች ተለይተው የሚታወቁት ለሌሎች ሰዎች ባላቸው ፍቅር እንደሆነ ገልጿል። ለተከታዮቹ እንዲህ ብሏል:- “እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፣ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ። እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።”​—ዮሐንስ 13:34, 35፤ 15:12

13, 14. የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት አምላክን እንደማይወክሉ የሚያመለክተው ምንድን ነው?

13 ሆኖም የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት በታሪክ ዘመናት ሁሉ በፖለቲካ ጉዳዮች ጣልቃ ሲገቡና አገሮቻቸው ያካሄዷቸውን ጦርነቶች ሲደግፉ ኖረዋል። በዚህ መቶ ዘመን በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ላይ እንደታየው በራሳቸው በሕዝበ ክርስትና አገሮች መካከል የተደረጉትን ጦርነቶች እንኳ ሳይቀር ከሁለቱም ጎራዎች ጎን ሆነው ደግፈዋል። በእነዚህ ግጭቶች በሁለቱም ወገኖች በኩል ያሉት ቀሳውስት ድል ለማግኘት ጸልየዋል፤ በተጨማሪም በአንድ አገር ያሉ የአንድ ሃይማኖት አባላት በሌላ አገር የሚኖሩትን የራሳቸውን ሃይማኖት አባላት ገድለዋል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ይህ የአምላክ ልጆች ሳይሆኑ የሰይጣን ልጆች የሚፈጽሙት ድርጊት እንደሆነ ይናገራል። (1 ዮሐንስ 3:10-12, 15) ስለዚህ ምንም እንኳ ቀሳውስቱና ተከታዮቻቸው ክርስቲያኖች ነን ቢሉም ተከታዮቹ ‘ሰይፍ እንዳያነሱ’ ከተናገረው ከኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ጋር የሚጋጭ ድርጊት ፈጽመዋል።​—ማቴዎስ 26:51, 52

14 ላለፉት ብዙ መቶ ዘመናት አብያተ ክርስቲያናት የሕዝበ ክርስትና አገሮች በኢምፔሪያሊዝም ዘመን ሌሎች ሕዝቦችን ድል አድርገው ሲይዙ፣ በባርነት ሲገዟቸውና ሲያዋርዷቸው ከእነዚህ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር አብረዋል። ይህ በአፍሪካ ውስጥ ለብዙ መቶ ዘመናት የተፈጸመ ነገር ነው። ኦፒየም ዎርስ ተብሎ በሚጠራው ጦርነትና ቦክሰር ሪቤልየን ተብሎ በሚጠራው ዓመፅ ወቅት እንደታየው ምዕራባውያን አገሮች በኃይል ተጠቅመው ተጽእኖ ባሳደሩበት ዘመን ቻይናም የዚህ ዕጣ ተቋዳሽ ልትሆን ችላለች።

15. ሕዝበ ክርስትና ምን እኩይ ድርጊት ፈጽማለች?

15 በተጨማሪም የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች የጨለማ ዘመን ተብለው በሚጠሩት በእነዚያ የታሪክ ዘመናት ከእነርሱ ጋር የማይስማሙትን ሰዎች በግንባር ቀደምትነት አሳደዋል፣ አሠቃይተዋል፣ አልፎ ተርፎም ገድለዋል። ለብዙ መቶ ዓመታት በዘለቀው ኢንኩዊዝሽን ሕጋዊ ፈቃድ በመስጠት ማሠቃየትንና መግደልን የመሳሰሉ አረመኔያዊ ድርጊቶች መልካም ምግባር ባላቸውና ምንም ወንጀል ባልሠሩ ሰዎች ላይ እንዲፈጸም ተደርጓል። ይህን ድርጊት የፈጸሙት ክርስቲያን ነን የሚሉት ቀሳውስትና ተከታዮቻቸው ናቸው። እንዲያውም ተራው ሕዝብ መጽሐፍ ቅዱስን እንዳያነብ መጽሐፉን ለማጥፋት ጥረት አድርገዋል።

ክርስቲያን አይደሉም

16, 17. አብያተ ክርስቲያናት ክርስቲያኖች አይደሉም ማለት የምንችለው ለምንድን ነው?

16 የሕዝበ ክርስትና አገሮችና አብያተ ክርስቲያናት ክርስቲያኖች አልነበሩም፤ አሁንም አይደሉም። የአምላክ አገልጋዮች አይደሉም። አምላክ በመንፈሱ አነሳሽነት ያስጻፈው ቃሉ ስለ እነሱ ሲናገር እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔርን እንዲያውቁ በግልጥ ይናገራሉ፣ ዳሩ ግን የሚያስጸይፉና የማይታዘዙ ለበጎ ሥራም ሁሉ የማይበቁ ስለ ሆኑ፣ በሥራቸው ይክዱታል።”​—ቲቶ 1:16

17 ኢየሱስ የሐሰት ሃይማኖት በሚያፈራው ፍሬ ተለይቶ ሊታወቅ እንደሚችል ተናግሯል። እንዲህ አለ:- “የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ። ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። . . . መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፣ ክፉም ዛፍ ክፉ ፍሬ ያደርጋል። መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ ማፍራት፣ ወይም ክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ ማፍራት አይቻለውም። መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል ወደ እሳትም ይጣላል። ስለዚህም [የሐሰት ነቢያትን] ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ።”​—ማቴዎስ 7:15-20

18. የሕዝበ ክርስትና ትምህርትና ድርጊት ምን ውጤት አስከትሏል?

18 ስለዚህ የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች በመጽሐፍ ቅዱስ እናምናለን፣ ፈሪሃ አምላክ አለን፣ እንዲሁም ክርስቲያኖች ነን ቢሉም የሚያስተምሩት ትምህርትና የሚሠሩት ሥራ ይህ አባባላቸው ሐሰት መሆኑን ያሳያል። አምላክንና መጽሐፍ ቅዱስን ክደዋል። ይህንንም በማድረጋቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ጥላቻ እንዲያድርባቸውና የሁሉ የበላይ በሆነው አካል ላይ እምነት እንዲያጡ አድርገዋል።

19. የሕዝበ ክርስትና ጉድለት አምላክና መጽሐፍ ቅዱስ ጉድለት አለባቸው ሊያሰኝ ይችላልን?

19 ይሁን እንጂ የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስትና አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም ከሕዝበ ክርስትና ውጪ ያሉ የሌሎች ሃይማኖቶች ጉድለት የመጽሐፍ ቅዱስ ጉድለት ነው ማለት አይደለም። የአምላክ ጉድለት ነው ሊባልም አይችልም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እኛና ወደፊት ስለሚያጋጥመን ሁኔታ የሚያስብ አንድ ታላቅ አካል እንዳለ ይነግረናል። ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ የሚፈልጉትንና ፍትሕና ሰላም በመላዋ ምድር ላይ እንዲሰፍን የሚሹትን ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች እንዴት እንደሚክሳቸው ይገልጻል። በተጨማሪም አምላክ ክፋትና መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምን እንደሆነና በሰዎች ላይ ጉዳትን የሚያደርሱትንም ሆነ እሱን እናመልካለን የሚሉትን ቃል አባዮች እንዴት ከምድር ላይ እንደሚያስወግድ ይገልጻል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የዳንቴ “ገሃነመ እሳት”

[ምንጭ]

Doré’s illustration of Barrators—Giampolo for Dante’s Divine Comedy

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሕዝበ ክርስትና ሥላሴ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሂንዱ ሥላሴ

[ምንጭ]

Courtesy of The British Museum

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የግብጻውያን ሥላሴ

[ምንጭ]

Museo Egizio, Turin

[በገጽ 18 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ከኢየሱስ ትምህርቶች ተቃራኒ በሆነ መንገድ በሁለቱም ጎራዎች ያሉ ቀሳውስት ጦርነቶችን ደግፈዋል

[ምንጭ]

U.S. Army photo