ሕይወት ታላቅ ዓላማ አለው
ክፍል 5
ሕይወት ታላቅ ዓላማ አለው
1, 2. አምላክ እንደሚያስብልን እንዴት ልናውቅ እንችላለን? ከሕይወት ጋር ለተያያዙ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ትኩረታችንን ወዴት ማዞር ይኖርብናል?
1 ምድርም ሆነች በውስጧ ያሉት ሕያዋን ነገሮች የተፈጠሩበት መንገድ ፈጣሪያቸው አሳቢ የሆነ የፍቅር አምላክ እንደሆነ ያመለክታል። ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስም አሳቢ የሆነ አምላክ እንደሆነ ይገልጻል። በምድር ላይ የተፈጠርነው ለምንድን ነው? ወደፊትስ ምን ይጠብቀናል? ለሚሉት ጥያቄዎች መጽሐፍ ቅዱስ ከሁሉ የላቀውን መልስ ይሰጠናል።
2 እነዚህን መልሶች ለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር አለብን። የአምላክ ቃል “ብትፈልጉትም ይገኝላችኋል፤ ብትተዉት ግን ይተዋችኋል” ይላል። (2 ዜና መዋዕል 15:2) እንግዲያው በአምላክ ቃል ላይ የምናደርገው ምርምር አምላክ ለእኛ ያለውን ዓላማ በተመለከተ ምን ነገር ይገልጽልናል?
አምላክ ሰዎችን የፈጠረበት ምክንያት
3. አምላክ ምድርን የፈጠረው ለምንድን ነው?
3 መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ምድርን ያዘጋጀው ሰዎችን በአእምሮው ይዞ እንደሆነ ያመለክታል። ኢሳይያስ 45:18 ምድርን በተመለከተ ሲናገር አምላክ ‘ምድርን የፈጠረው መኖሪያ እንድትሆን እንጂ ለከንቱ እንዳልሆነ’ ይገልጻል። በተጨማሪም ምድርን ያዘጋጀው ሰዎች ለመኖር ብቻ ሳይሆን ሕይወትንም ሙሉ በሙሉ ለማጣጣም የሚያስችሏቸውን ነገሮች በሙሉ በማሟላት ነው።—ዘፍጥረት ምዕራፍ 1 እና 2
4. አምላክ የመጀመሪያዎቹን ሰዎች የፈጠረው ለምንድን ነው?
4 አምላክ የመጀመሪያዎቹን ሰዎች ማለትም አዳምንና ሔዋንን እንደፈጠረና ለሰብዓዊው ቤተሰብ ያለው ዓላማ ምን እንደሆነ በቃሉ አማካኝነት ገልጾልናል። እንዲህ አለ:- “ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፣ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፣ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ።” (ዘፍጥረት 1:26) ሰዎች “ምድርን ሁሉ” እና በውስጧ ያሉትን እንስሳት በበላይነት እንዲያስተዳድሩ የአምላክ ዓላማ ነበር።
5. የመጀመሪያዎቹን ሰዎች ያስቀመጣቸው የት ነበር?
5 አምላክ በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኝ ኤደን ተብሎ በሚጠራ ቦታ አንድ መናፈሻ መሰል ሰፊ የአትክልት ሥፍራ አዘጋጀ። ከዚያም “ሰውን ወስዶ ያበጃትም ይጠብቃትም ዘንድ በዔድን ገነት አኖረው።” የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ለመብላት የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ሁሉ አሟልታ የያዘች ገነት ነበረች። በውስጧም ‘ለማየት ደስ የሚያሰኙና ለመብላት መልካም የሆኑ ዛፎች’ እንዲሁም ሌሎች አትክልቶችና በጣም ደስ የሚሉ ብዙ ዓይነት እንስሳት ነበሩ።—ዘፍጥረት 2:7-9, 15
6. ሰዎች የተፈጠሩት የትኞቹን አእምሯዊና አካላዊ ባሕርያት ይዘው ነው?
6 የመጀመሪያዎቹ ሰዎች አካላቸው ፍጹም ሆኖ የተፈጠረ ስለነበረ አይታመሙም ነበር፤ እርጅናና ሞት የሚባል ነገርም አልነበረም። በተጨማሪም እንደ ነጻ ምርጫ ያሉ ሌሎች ባሕርያትም ነበሯቸው። የተፈጠሩበት ሁኔታ ዘፍጥረት 1:27 ላይ ተገልጿል:- “እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።” በአምላክ መልክ የተፈጠርን እንደመሆናችን መጠን አካላዊና አእምሮአዊ ባሕርያት ብቻ ሳይሆን ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶችም ተሰጥተውናል፤ እውነተኛ ደስታ ማግኘት እንድንችል ደግሞ እነዚህ ፍላጎቶች መሟላት አለባቸው። አምላክ እነዚህን ፍላጎቶችም ሆነ የምግብ፣ የውኃና የአየር ፍላጎቶቻችንን የሚያሟላበት መንገድ አዘጋጅቷል። ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳለው “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም።”—ማቴዎስ 4:4
7. የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ምን ሥራ ተሰጥቷቸው ነበር?
7 ከዚህም በተጨማሪ አምላክ የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት በኤደን በነበሩበት ጊዜ “ብዙ፣ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት” በማለት አንድ ግሩም የሆነ ሥራ ሰጣቸው። ዘፍጥረት 1:28) ስለዚህ መባዛትና ፍጹም የሆኑ ልጆች መውለድ ይችላሉ ማለት ነው። የሰብዓዊው ኅብረተሰብ ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ ደግሞ በኤደን ትገኝ የነበረችውን የመጀመሪያዋን መናፈሻ መሰል ገነት ወሰኖች የማስፋት አስደሳች ሥራ ይኖራቸዋል። በመጨረሻ መላዋ ምድር ፍጹም በሆኑና ለዘላለም መኖር በሚችሉ ደስተኛ ሰዎች የተሞላች ገነት ትሆናለች። በዚህ መንገድ ሁሉንም ነገር መስመር ካስያዘ በኋላ “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፣ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ” ሲል መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጽልናል።—ዘፍጥረት 1:31፤ በተጨማሪም መዝሙር 118:17ን ተመልከት።
(8. ሰዎች ምድርን እንዴት መያዝ ይጠበቅባቸው ነበር?
8 ሰዎች የሚገዟትን መሬት ለራሳቸው ጥቅም በሚያስገኝ መንገድ እንደሚጠቀሙባት ግልጽ ነው። ሆኖም ይህን የሚያከናውኑት በኃላፊነት ስሜት ሊሆን ይገባል። ሰዎች ምድርን ማበላሸት ሳይሆን በእንክብካቤ መያዝ ይጠበቅባቸው ነበር። በዛሬው ጊዜ የምንመለከተው የምድር ብክለት የአምላክን ፈቃድ የሚጻረር ነው፤ ይህን የሚያደርጉ ሰዎች፣ ሕይወት በምድር ላይ የተፈጠረበትን ዓላማ የሚጻረር ድርጊት እየፈጸሙ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ‘ምድርን የሚያጠፉትን እንደሚያጠፋ’ ስለሚናገር ለዚህ ድርጊታቸው ተገቢውን ቅጣት ያገኛሉ።—ራእይ 11:18
የአምላክ ዓላማ አሁንም አልተለወጠም
9. የአምላክ ዓላማ እንደሚፈጸም እርግጠኞች የምንሆነው ለምንድን ነው?
9 ስለዚህ ከመጀመሪያው ጀምሮ የአምላክ ዓላማ ፍጹም የሆነ ሰብዓዊ ቤተሰብ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም እንዲኖር ነበር። አሁንም ይህ ዓላማው አልተለወጠም! ይህ ዓላማው ያላንዳች ጥርጥር ይፈጸማል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ምሎአል:- እንደ ተናገርሁ በእርግጥ ይሆናል፣ እንደ አሰብሁም እንዲሁ ይቆማል።” “ተናግሬአለሁ እፈጽምማለሁ፤ አስቤአለሁ አደርግማለሁ።”—ኢሳይያስ 14:24፤ 46:11
10, 11. ኢየሱስ፣ ጴጥሮስና መዝሙራዊው ዳዊት ስለ ገነት የተናገሩት እንዴት ነው?
10 ኢየሱስ ክርስቶስ ለወደፊቱ ጊዜ ተስፋ እንዲሰጠው ለጠየቀው ሰው “ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ባለው ጊዜ አምላክ ምድርን መልሶ ገነት ለማድረግ ስላለው ዓላማ ተናግሯል። (ሉቃስ 23:43) ሐዋርያው ጴጥሮስም እንደሚከተለው በማለት አስቀድሞ በተናገረ ጊዜ ስለ መጪው አዲስ ዓለም ገልጿል:- “ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና [ከሰማይ ሆኖ የሚገዛ አዲስ መንግሥታዊ መዋቅር] አዲስ ምድር [አዲስ ምድራዊ ኅብረተሰብ] እንደ [አምላክ] ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን።”—2 ጴጥሮስ 3:13
11 መዝሙራዊው ዳዊትም ስለ መጪው አዲስ ዓለምና ይህ ዓለም የሚቆይበትን የጊዜ ርዝመት አስመልክቶ ጽፏል። “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ” ሲል አስቀድሞ ተናግሯል። (መዝሙር 37:29) ኢየሱስ “የዋሆች ብፁዓን [“ደስተኞች፣” NW] ናቸው፣ ምድርን ይወርሳሉና” የሚል ተስፋ የሰጠው ለዚህ ነው።—ማቴዎስ 5:5
12, 13. አምላክ ለሰው ልጆች ያለውን ታላቅ ዓላማ በአጭሩ ግለጽ።
12 ከማንኛውም ክፋት፣ ወንጀል፣ በሽታ፣ ሐዘንና ሥቃይ ነፃ ሆኖ ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም መኖር እንዴት ያለ ታላቅ ተስፋ ነው! በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው የመጨረሻ መጽሐፍ ላይ ያለው የአምላክ ትንቢታዊ ቃል ይህን ታላቅ ዓላማ እንዲህ ሲል ጠቅለል አድርጎ ይገልጸዋል:- “[አምላክ] እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።” አክሎም እንዲህ ይላል:- “በዙፋንም የተቀመጠው:- እነሆ፣ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ አለ። ለእኔም:- እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸውና ጻፍ አለኝ።”—ራእይ 21:4, 5
13 አዎን፣ አምላክ ታላቅ ዓላማ አለው። የተናገረውን መፈጸም የሚችለውና ደግሞም የሚፈጽመው አምላክ አስቀድሞ በተናገረው መሠረት ጽድቅ የሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ማለትም ዘላለማዊ ገነት ያመጣል። ቃሎቹ “የታመኑና እውነተኛዎች ናቸውና።”
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 20, 21 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
አምላክ ሰዎች ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ ዓላማው ነበር። ይህ ዓላማው አሁንም አልተለወጠም
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንድ አከራይ ቤቱን ያበላሹትን ተከራዮች በኃላፊነት ሊጠይቃቸው ይችላል