በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሕይወት ዓላማ አለውን?

ሕይወት ዓላማ አለውን?

ክፍል 1

ሕይወት ዓላማ አለውን?

1. የሕይወትን ዓላማ በተመለከተ ብዙ ጊዜ የሚቀርበው ጥያቄ ምንድን ነው? አንድ ሰው በዚህ ጉዳይ ላይ ሐሳብ የሰጠውስ እንዴት ነው?

እያንዳንዱ ሰው ማለት ይቻላል፣ በሆነ ወቅት ላይ የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው? ብሎ ራሱን መጠየቁ አይቀርም። ኑሮን ለማሻሻል ተግቶ መሥራት፣ ቤተሰባችን የሚያስፈልገውን ነገር ማሟላት፣ ምናልባትም 70 ወይም 80 ዓመት ከኖሩ በኋላ መሞትና በዚያው ለዘላለም ከሕልውና ውጪ ሆኖ መቅረት ነውን? እንዲህ ዓይነት ስሜት የተሰማው አንድ ወጣት ሕይወት “ከመኖር፣ ልጆች ከመውለድ፣ ከመደሰትና ብሎም ከመሞት” የተሻለ ሌላ ዓላማ የለውም ሲል ተናግሯል። ግን ይህ እውነት ነውን? ሁሉ ነገር በሞት ያከትማል ማለት ነውን?

2, 3. ቁሳዊ ሀብት ማካበት የሕይወት ዓላማ ሊሆን የማይችለው ለምንድን ነው?

2 በምሥራቁም ሆነ በምዕራቡ ዓለም የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ዋነኛው የሕይወት ዓላማ ቁሳዊ ሀብት ማካበት እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይህ ደግሞ አስደሳችና ትርጉም ያለው ሕይወት ሊያስገኝ ይችላል የሚል እምነት አላቸው። ይሁን እንጂ ቁሳዊ ሀብት ያላቸው ሰዎች ያሉበት ሁኔታ ምን ይመስላል? ካናዳዊው ጸሐፊ ሃሪ ብሩስ እንዲህ ብለዋል:- “ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የናጠጡ ሀብታሞች ደስተኞች እንዳልሆኑ በተደጋጋሚ ይናገራሉ።” አክለውም “ከሕዝብ የተሰበሰቡ አስተያየቶች እንደሚያመለክቱት በሰሜን አሜሪካ መጥፎ የሆነ አፍራሽ አመለካከት ተስፋፍቷል . . . በዚህ ዓለም ደስተኛ የሆነ ሰው ይገኛልን? ካለ ደስታ ማግኘት የሚቻልበት ቁልፉ ምንድን ነው?” ብለዋል።

3 የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር እንዲህ በማለት ገልጸዋል:- “ቁሳዊ ነገሮችን ማግኘት ወይም በእነሱ መጠቀም ትርጉም ያለው ሕይወት ለማግኘት ያለንን ከፍተኛ ፍላጎት እንደማያረካ ተገንዝበናል። . . . ቁሳዊ ነገሮችን ማካበት ምንም ዓይነት ትምክህት ወይም ዓላማ የሌለውን ባዶ ሕይወት ትርጉም ያለው ሊያደርገው አይችልም።” አንድ ሌላ የፖለቲካ መሪ ደግሞ እንዲህ ብለዋል:- “ራሴንም ሆነ ሕይወቴን በተመለከተ እውነታው ምን እንደሆነ ለማወቅ ለበርካታ ዓመታት ጥልቅ ምርምር ሳደርግ ቆይቻለሁ፤ እኔ የማውቃቸው ሌሎች ብዙ ሰዎችም እንደዚሁ በማድረግ ላይ ናቸው። ከምንጊዜውም የበለጠ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ‘እኛ ማን ነን? የሕይወታችን ዓላማስ ምንድን ነው?’ እያሉ በመጠየቅ ላይ ናቸው።”

ይበልጥ አስቸጋሪ የሆኑ ሁኔታዎች

4. አንዳንዶች ሕይወት ዓላማ ያለው መሆኑ የሚያጠራጥራቸው ለምንድን ነው?

4 ብዙዎች የኑሮ ሁኔታዎች ይበልጥ እየከፉ መሄዳቸውን ሲመለከቱ ሕይወት ዓላማ ያለው ስለ መሆኑ ይጠራጠራሉ። በዓለም ዙሪያ ከአንድ ቢልዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ሥር የሰደደ ሕመም አለባቸው አሊያም የተመጣጠነ ምግብ አያገኙም። በዚህም ሳቢያ በአፍሪካ ብቻ በየዓመቱ አሥር ሚልዮን ገደማ የሚሆኑ ሕፃናት ሕይወታቸው ያልፋል። ወደ 6 ቢልዮን እየተጠጋ ያለው የምድር ሕዝብ ቁጥር በየዓመቱ ከ90 ሚልዮን በላይ በመጨመር ላይ ይገኛል፤ ከዚህ መካከል 90 በመቶው የሚሆነው የሕዝብ ቁጥር ጭማሪ የሚታየው በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ውስጥ ነው። ይህ የሕዝብ ቁጥር ያለማቋረጥ እያደገ በሄደ መጠን የምግብ፣ የቤትና የኢንዱስትሪ ፍላጎትም የዚያኑ ያህል ይጨምራል። ከኢንዱስትሪዎችና ከሌሎች ተቋማት የሚወጡት መርዘኛ ነገሮች ደግሞ መሬቱን፣ ውኃውንና አየሩን ይበልጥ ይበክሉታል።

5. በምድር ዕፅዋት ላይ ምን እየደረሰ ነው?

5 የዓለም ወታደራዊና ማኅበራዊ ወጪዎች 1991 (World Military and Social Expenditures 1991) የተባለው ጽሑፍ እንዲህ ሲል ሪፖርት አድርጓል:- “በየዓመቱ [የታላቋ ብሪታንያን] የቆዳ ስፋት የሚያክል ቦታ የሚሸፍን ደን ይወድማል። (የደን ጭፍጨፋው) በዚህ መጠን ከቀጠለ በ2000 ዓመት ላይ ርጥበት አዘል የአየር ንብረት ባለው የሐሩር ክልል ካለው ደን መካከል 65 በመቶው ይጠፋል።” አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወኪል እንዳለው ከሆነ በእነዚህ ቦታዎች 10 ዛፎች ሲቆረጡ የሚተከለው ግን 1 ዛፍ ነው፤ በአፍሪካ በሬሾ 1 ዛፍ ሲተከል ከ20 በላይ የሚሆኑ ዛፎች ይቆረጣሉ። ስለዚህ በረሃ እየተስፋፋ ነው፤ በየዓመቱ የቤልጅየምን የቆዳ ስፋት የሚያክል ቦታ እየተበላሸ ለእርሻ መሬትነት ወደማያገለግልበት ደረጃ ይለወጣል።

6, 7. ሰብዓዊ መሪዎች ሊፈቷቸው ካልቻሏቸው ችግሮች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? ስለዚህ የትኞቹ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ይኖርባቸዋል?

6 በተጨማሪም በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን በጦርነት የሞቱት ሰዎች ቁጥር ቀደም ባሉት አራት መቶ ዘመናት በሙሉ በጦርነት የሞቱትን ሰዎች ቁጥር አራት እጥፍ ይሆናል። በየትኛውም ቦታ ወንጀል በተለይ ደግሞ በኃይል እርምጃ የሚፈጸም ወንጀል እየጨመረ በመሄድ ላይ ይገኛል። የቤተሰብ መፈራረስ፣ አደንዛዥ ዕፆችን መጠቀም፣ ኤድስ፣ በጾታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎችና ሌሎች ጎጂ ነገሮችም ሕይወትን ይበልጥ አስቸጋሪ እያደረጉት ነው። የዓለም መሪዎችም ሰብዓዊውን ቤተሰብ በማጥቃት ላይ ላሉት ብዙ ችግሮች መፍትሔ ማምጣት አልቻሉም። ስለዚህ ሰዎች የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው? ብለው መጠየቃቸው አያስገርምም።

7 ምሁራንና የሃይማኖት መሪዎች ለዚህ ጥያቄ የሚሰጡት መልስ ምንድን ነው? እነዚህ ሁሉ መቶ ዘመናት ካለፉ በኋላ አጥጋቢ መልስ ማግኘት ችለዋልን?

የሚሰጡት መልስ

8, 9. (ሀ) አንድ የቻይና ምሁር ስለ ሕይወት ዓላማ ምን ብለዋል? (ለ) ከናዚ ማጎሪያ ካምፕ በሕይወት የተረፉ አንድ ሰው ምን ብለዋል?

8 የኮንፍዩሼስ ሃይማኖት ምሁር የሆኑት ዱ ዋ-ሚንግ “የመጨረሻው ከፍተኛ የሕይወት ትርጉም በተለመደው ሰብዓዊ ሕልውናችን ውስጥ ይገኛል” ብለዋል። በዚህ አመለካከት መሠረት ሰዎች መወለዳቸውን፣ በሕይወት ለመኖር ትግል ማድረጋቸውንና መሞታቸውን ይቀጥላሉ ማለት ነው። እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት የተስፋ ጭላንጭል እንኳ አይታይበትም። ደግሞስ ይህ አመለካከት እውነት ነውን?

9 በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ብዙ ሰዎች ካለቁባቸው የናዚ ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ በሕይወት የተረፉት ኤሊ ቪዝል እንዲህ ብለዋል:- “‘በሕይወት የምንኖረው ለምንድን ነው?’ የሚለው ጥያቄ የሰው ልጅ መልስ ሊሰጠው የሚገባ እጅግ አንገብጋቢ የሆነ ጥያቄ ነው። . . . ትርጉም የለሽ ሞት ያየሁ ቢሆንም እንኳ ሕይወት ትርጉም እንዳለው አምናለሁ።” ሆኖም የሕይወት ትርጉም ምን እንደሆነ መናገር አልቻሉም።

10, 11. (ሀ) አንድ የመጽሔት አዘጋጅ የሰው ልጅ ለጥያቄዎቹ መልስ እንዳላገኘ የገለጹት እንዴት ነው? (ለ) አንድ የዝግመተ ለውጥ ሳይንስ ሊቅ የሰጡት አስተያየት አጥጋቢ ያልሆነው ለምንድን ነው?

10 የአንድ መጽሔት አዘጋጅ የሆኑት ቨርማንት ሮይስተር እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “ስለ ራሱ ስለ ሰው፣ . . . በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ስላለው ቦታ ስናስብ ያለን እውቀት ጊዜ ሲጀምር ከነበረው እውቀት እምብዛም ዕድገት አላሳየም። አሁንም ቢሆን እኛ ማን ነን? በሕይወት የምንኖረው ለምንድን ነው? ወደፊትስ ምን ይጠብቀናል? ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ አላገኘንም።”

11 የዝግመተ ለውጥ ሳይንስ ሊቅ የሆኑት ስቲፈን ጄይ ጎልድ “‘የላቀ’ መልስ ለማግኘት እንጓጓ ይሆናል፤ ሆኖም አናገኝም” ብለዋል። ለእንዲህ ዓይነቶቹ የዝግመተ ለውጥ አማኞች ሕይወት ከአካባቢ ሁኔታ ጋር ተስማምቶ በሕልውና ለመቀጠል የሚደረግ ትግል ነው፤ ሁሉም ነገር በሞት ያከትማል። ይኸኛውም አመለካከት ምንም የተስፋ ጭላንጭል አይታይበትም። ይህ አመለካከትስ እውነት ነውን?

12, 13. የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ያሏቸው አመለካከቶች ምንድን ናቸው? የእነርሱ አመለካከቶችስ ዓለማዊ ሰዎች ከሰጧቸው አመለካከቶች የተሻሉ ናቸውን?

12 ብዙ የሃይማኖት መሪዎች የሕይወት ዓላማ አንድ ሰው ሲሞት ነፍሱ ወደ ሰማይ ሄዳ በዚያ ለዘላለም መኖር እንድትችል ጥሩ የአኗኗር መንገድ መከተል ነው ይላሉ። መጥፎ ለሆኑ ሰዎች የቀረበው አማራጭ እሳታማ በሆነ ሲኦል ውስጥ ለዘላለም መሠቃየት ነው። ሆኖም በዚህ እምነት መሠረት በምድር ላይ በታሪክ ዘመናት ሁሉ የታየው አጥጋቢ ያልሆነ ኑሮ እንዳለ ይቀጥላል ማለት ነው። ሆኖም የአምላክ ዓላማ ሰዎች ልክ እንደ መላእክት በሰማይ እንዲኖሩ ከነበረ ለመላእክት እንዳደረገው ሰዎችንም መጀመሪያውኑ ለምን በሰማይ እንዲኖሩ አድርጎ አልፈጠራቸውም?

13 ቀሳውስትም እንኳ እንዲህ ዓይነቶቹ አመለካከቶች ግራ ያጋቧቸዋል። በለንደን የሚገኘው የቅዱስ ጳውሎስ ካቴድራል የቀድሞ ዲን የነበሩት ዶክተር ደብልዩ አር ኢንጅ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር:- “በሕይወት ዘመኔ ሁሉ የሕይወትን ዓላማ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት አድርጌያለሁ። ምንጊዜም መሠረታዊ ነገሮች ናቸው ብዬ አምንባቸው የነበሩ ሦስት ጥያቄዎችን ለመፍታት ሞክሬያለሁ፤ እነርሱም:- ዘላለማዊነት፣ የሰውን ሁለንተናዊ ባሕርይና ክፋትን የሚመለከቱ ጥያቄዎች ናቸው። ሆኖም ጥረቴ አልተሳካም። ለአንዳቸውም መልስ አላገኘሁም።”

ውጤቱ

14, 15. እርስ በርሳቸው የሚጋጩት ሐሳቦች በብዙ ሰዎች ላይ ምን ውጤት አስከትለዋል?

14 የሕይወት ዓላማን በተመለከተ በተነሳው ጥያቄ ላይ ምሁራንና የሃይማኖት መሪዎች የሚሰጧቸው ብዙ የተለያዩ ሐሳቦች ምን ውጤት አስከትለዋል? ብዙዎች የሚሰጡት ምላሽ አንድ በዕድሜ የገፉ ሰው እንዲህ በማለት ከሰጡት አስተያየት ጋር የሚመሳሰል ነው:- “በአብዛኛው የሕይወት ዘመኔ የሕይወቴ ዓላማ ምንድን ነው እያልኩ ስጠይቅ ኖሬያለሁ። አሁን ግን ሕይወት ዓላማ ኖረውም አልኖረው ግድ የለኝም።”

15 በዓለም ሃይማኖቶች ውስጥ ብዙ ዓይነት አመለካከቶች እንዳሉ የተረዱ በርካታ ሰዎች አንድ ሰው ምንም ዓይነት እምነት ቢኖረው የሚያመጣው ለውጥ የለም የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። ሃይማኖት አንድ ሰው የሕይወትን ውጣ ውረድ መቋቋም እንዲችል የሚረዳውን መጠነኛ የአእምሮ ሰላምና መጽናኛ የሚሰጥ ሕሊናን የሚያሳርፍ ነገር ነው የሚል እምነት አላቸው። ሌሎች ደግሞ ሃይማኖት ከአጉል እምነት ተነጥሎ የማይታይ ነገር ነው ብለው ያስባሉ። ለብዙ መቶ ዘመናት ሲሰጡ የኖሩት ግምታዊ የሆኑ ሃይማኖታዊ ሐሳቦች የሕይወት ዓላማን በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄ መልስ ካለመስጠታቸውም በላይ የተራውን ሕዝብ ሕይወት እንዳላሻሻሉ ይሰማቸዋል። እንዲያውም የዚህ ዓለም ሃይማኖቶች በአብዛኛው የሰውን ልጅ ዕድገት ወደኋላ እንደጎተቱና ለከረረ ጥላቻና ለጦርነት መንስኤ እንደሆኑ ታሪክ ያሳያል።

16. የሕይወትን ዓላማ ማወቅ ምን ያህል ጠቃሚ ሊሆን ይችላል?

16 ይህም ሆኖ ግን ስለ ሕይወት ዓላማ እውነታውን ማወቁ አስፈላጊ ነውን? የሥነ አእምሮ ጠበብት የሆኑት ቪክቶር ፍራንክል የሚከተለውን መልስ ሰጥተዋል:- “አንድን ሰው የሕይወትን ትርጉም ለማግኘት የሚያደርገውን ጥረት ያህል ለሥራ የሚያንቀሳቅሰው ኃይል የለም። . . . አንድ ሰው ሕይወት ትርጉም እንዳለው ማወቁ ሌላው ቀርቶ እጅግ አስከፊ የሆኑ ሁኔታዎችን እንኳ ሳይቀር በሚገባ መቋቋም እንዲችል በዓለም ላይ ካለው ከማንኛውም ነገር በላይ ሊረዳው እንደሚችል ለመናገር እደፍራለሁ።”

17. አሁን የትኞቹን ጥያቄዎች ማንሳት አለብን?

17 ሰብዓዊ ፈላስፎችና ሃይማኖቶች የሕይወት ዓላማ ምን እንደሆነ አጥጋቢ በሆነ መንገድ ሊገልጹልን አልቻሉም፤ ታዲያ የሕይወትን ዓላማ እንዴት ልናውቅ እንችላለን? ስለዚህ ጉዳይ እውነቱን ሊነግረን የሚችል የላቀ ጥበብ ያለው አካል ይኖራልን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“በየዓመቱ [የታላቋ ብሪታንያን] የቆዳ ስፋት የሚያክል ቦታ የሚሸፍን ደን ይወድማል”

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“በአብዛኛው የሕይወት ዘመኔ የሕይወቴ ዓላማ ምንድን ነው እያልኩ ስጠይቅ ኖሬያለሁ”