ማን ሊነግረን ይችላል?
ክፍል 2
ማን ሊነግረን ይችላል?
1, 2. አንድ ነገር ለምን ዓላማ እንደተነደፈ ማወቅ የሚቻልበት ከሁሉ የተሻለ መንገድ ምንድን ነው?
1 የሕይወት ዓላማ ምን እንደሆነ ማን በትክክል ሊነግረን ይችላል? የማሽን ንድፍ አውጪ ወደሆነ ሰው ብትሄድና ምን እንደሆነ ሊገባህ ያልቻለ የአንድ በጣም ውስብስብ የሆነ ማሽን ንድፍ ሲያወጣ ብትመለከት መሣሪያው ለምን ዓላማ የሚያገለግል መሆኑን ልታውቅ የምትችለው እንዴት ነው? ከሁሉ የተሻለው መንገድ ንድፍ አውጪውን መጠየቅ ነው።
2 እንግዲያው ከትንሿ ሕያው ሕዋስ አንስቶ ባሉት ሕያዋን ነገሮች ላይ በጠቅላላው የሚታየውን ንድፍ ጨምሮ በምድር ላይ በዙሪያችን ስለምናየው እጅግ አስደናቂ የሆነ ንድፍ ምን ማለት ይቻላል? በሕዋስ ውስጥ ያሉት በጣም አነስተኛ የሆኑ ሞለኪዩሎችና አተሞች እንኳ አስደናቂ ንድፍ ያላቸውና በሚገባ የተደራጁ ናቸው። ዕጹብ ድንቅ ንድፍ ስላለው የሰው አእምሮስ ምን ማለት ይቻላል? ፕላኔታችን ያለችበት ሥርዓተ ፀሐይ፣ ፍኖተ ሐሊባችንና ጽንፈ ዓለምስ? እነዚህ እጅግ አስደናቂ ንድፍ ያላቸው ነገሮች ንድፍ አውጪ አያስፈልጋቸውምን? ይህ ንድፍ አውጪ እነዚህን ነገሮች የሠራው ለምን እንደሆነ ሊነግረን እንደሚችል ጥርጥር የለውም።
ሕይወት የተገኘው በአጋጣሚ ነውን?
3, 4. ሕይወት በአጋጣሚ ሊገኝ የሚችልበት ዕድል ምን ያህል ነው?
3 ዚ ኢንሳይክሎፔድያ አሜሪካና “በሕያዋን ፍጥረታት ላይ የሚታየውን እጅግ ውስብስብ የሆነ አሠራርና አደረጃጀት” በመጥቀስ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “አበቦችን፣ ትናንሽ ነፍሳትን ወይም አጥቢ እንስሳትን በጥልቀት ስንመረምር የአካል ክፍሎቻቸው አቀማመጥ ለማመን በሚያዳግት ሁኔታ እንከን የማይወጣለት ሆኖ እናገኘዋለን።” እንግሊዛዊው የከዋክብት ተመራማሪ ሰር በርናርድ ሎቭል የሕያዋን ዘአካላትን (ኦርጋኒዝምስ) ኬሚካላዊ ውህደት በመጥቀስ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በጣም አነስተኛ ከሆኑት የፕሮቲን ሞለኪዩሎች መካከል አንዱን ሊያስገኝ የሚችለው አጋጣሚ . . . ሊከሰት የሚችልበትን ሁኔታ መገመት አዳጋች ነው። . . . እንዲያውም ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው።”
4 በተመሳሳይም የከዋክብት ተመራማሪ የሆኑት ፍሬድ ሆይል እንዲህ ብለዋል:- “የባዮሎጂ መሠረታዊ ትምህርት አሁንም ሕይወት የተገኘው እንዲሁ በአጋጣሚ ነው የሚለውን አቋም እንደያዘ ነው። ሆኖም ባዮኬሚስቶች እጅግ አስደናቂ ስለሆነው የሕይወት ውስብስብነት
ተጨማሪ ግኝቶች ላይ እየደረሱ በሄዱ መጠን ሕይወት በአጋጣሚ ተገኘ የሚባልባቸው ሁኔታዎች በጣም እያነሱ በመሄድ ከናካቴው እንደሚጠፉ ግልጽ ነው። ሕይወት በአጋጣሚ ሊገኝ አይችልም።”5-7. ሕያዋን ነገሮች በአጋጣሚ ሊገኙ እንደማይችሉ ሞለኪዩላር ባዮሎጂ የሚያረጋግጠው እንዴት ነው?
5 በቅርብ ጊዜ ከተደረሰባቸው የሳይንስ ዘርፎች አንዱ የሆነው ሞለኪዩላር ባዮሎጂ በጂን፣ በሞለኪዩልና በአተሞች ደረጃ ባሉ ሕያዋን ነገሮች ላይ የሚደረግ ጥናት ነው። የሞለኪዩላር ባዮሎጂ ሊቅ የሆኑት ሚካኤል ዴንተን በተደረሰበት ግኝት ላይ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል:- “ከሚታወቁት ሕዋሶች ሁሉ በውስብስብነቱ ዝቅተኛ ደረጃ የሚሰጠው ሕዋስ እንኳ እጅግ ውስብስብ በመሆኑ እንዲህ ዓይነቱ ነገር በአንድ እንግዳ በሆነና ፈጽሞ በማይመስል አጋጣሚ ድንገት ተገኘ ብሎ ማመን የማይቻል ነገር ነው።” “ሆኖም ነገሩን ለማመን እጅግ አስቸጋሪ የሚያደርገው እነዚህ ሕያዋን ነገሮች ውስብስብ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ብዙውን ጊዜ በንድፋቸው ላይ የሚንጸባረቀው እጅግ የረቀቀ የፈጠራ ችሎታም ጭምር ነው።” “ታላቅ የባዮሎጂ ንድፍ የታየውና የተገኙት ውጤቶች ፍጹምነት ይበልጥ የተንጸባረቀው . . . በሞለኪዩል ደረጃ ባሉት ነገሮች ላይ ነው።”
6 ዴንተን በመቀጠል እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “በየትኛውም አቅጣጫ ብንመለከት፣ የቱንም ያህል ጠልቀን ብንመረምር በአጋጣሚ የተገኘ ነው የሚለውን ሐሳብ ተቀባይነት የሚያሳጣ ከፍተኛ የብቃት ደረጃ የሚታይበትና እጅግ የሚማርክ የፈጠራ ችሎታ እናገኛለን። በአጋጣሚ የተከሰቱ ሂደቶች ከእኛ የፈጠራ ችሎታ በላይ የሆነን በጣም የተወሳሰበ ነገር፣ በአጋጣሚ ከሚገኙ ነገሮች ፍጹም ተቃራኒ የሆነን ነገርና በሰው የማሰብ ችሎታ ከተሠሩት ነገሮች ሁሉ በማንኛውም መንገድ የሚልቀውን እጅግ አነስተኛ የሆነ ንጥረ ነገር ማለትም ራሱን የቻለ ሥራ የሚያከናውን ፕሮቲን ወይም ጂን ሊያስገኙ ይችላሉ ብሎ ማመን ይቻላልን?” በተጨማሪም እንዲህ ብለዋል:- “በአንድ ሕያው ሕዋስና የከበሩ ድንጋዮችን በመሰሉ በጣም የረቀቀ አሠራር ባላቸው ሕይወት የሌላቸው ነገሮች መካከል ግልጽ የሆነ ሰፊ ልዩነት አለ።” የፊዚክስ ፕሮፌሰር የሆኑት ቼት ሬሞ ደግሞ “እያንዳንዱ ሞለኪዩል ሥራውን በሚገባ እንዲያከናውን ታልሞ ተአምራዊ በሆነ መንገድ የተሠራ መሆኑ . . . በጣም ያስደንቀኛል” ሲሉ ገልጸዋል።
7 የሞለኪዩላር ባዮሎጂ ሊቅ የሆኑት ዴንተን “አሁንም ግትር አቋም ይዘው ይህ ሁሉ አዲስ ነገር እንዲሁ በአጋጣሚ የተገኘ ነው ብለው የሚከራከሩ ሰዎች” በተረት የሚያምኑ ናቸው የሚል የመደምደሚያ ሐሳብ ሰጥተዋል። እንዲያውም ሕያዋን ነገሮች የተገኙት በአጋጣሚ ነው የሚለውን የዳርዊን እምነት “ስለ አጽናፈ ዓለም አመጣጥ የተነገረ የሃያኛው መቶ ዘመን ታላቅ ተረት” ብለው ጠርተውታል።
አንድ ንድፍ የራሱ ንድፍ አውጪ ያስፈልገዋል
8, 9. እያንዳንዱ ንድፍ የግድ አንድ ንድፍ አውጪ እንደሚያስፈልገው የሚያሳይ ምሳሌ ስጥ።
8 ሕይወት የሌለው ነገር እንዲሁ በአጋጣሚ ፈጽሞ ሕያው ሊሆን አይችልም። እያንዳንዱ ንድፍ የግድ አንድ ንድፍ አውጪ የሚያስፈልገው በመሆኑ በምድር ላይ ያሉት በጣም አስደናቂ የሆነ ንድፍ ያላቸው ሕያዋን ነገሮች በሙሉ በድንገተኛ አጋጣሚ ሊመጡ አይችሉም። ያለ ንድፍ አውጪ የተገኘ ንድፍ ልትጠቅስ ትችላለህን? አንድም የለም። ንድፉ ይበልጥ ውስብስብ በሆነ መጠን የንድፍ አውጪው ችሎታም የዚያኑ ያህል የላቀ ይሆናል።
9 ሁኔታውን በሚከተለውም መንገድ በምሳሌ ማስረዳት ይቻላል:- አንድ ቅብ ስንመለከት ቅቡ አንድ ቀለም ቀቢ እንዳለ የሚመሰክር መሆኑን አምነን እንቀበላለን። አንድ መጽሐፍ ስናነብ አንድ ደራሲ እንዳለው እናምናለን። አንድ ቤት ስንመለከት ቤቱን የሠራ ሰው እንዳለ እናምናለን። የትራፊክ መብራት ስንመለከት አንድ ሕግ አውጪ አካል እንዳለ እናምናለን። ሠሪዎቻቸው እነዚህን ነገሮች ሁሉ የሠሩት በዓላማ ነው። እነዚህን ነገሮች ስለሠሩት ሰዎች ጠንቅቀን የማናውቅ ቢሆንም እንኳ ሰዎቹ መኖራቸውን እንደማንጠራጠር የታወቀ ነው።
10. አንድ ታላቅ ንድፍ አውጪ እንዳለ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?
10 በተመሳሳይም በምድር ላይ ያሉትን ሕያዋን ነገሮች ንድፍ፣ አሠራርና ውስብስብነት በመመልከት አንድ የላቀ ችሎታ ያለው ንድፍ አውጪ መኖሩን መረዳት ይቻላል። ሁሉም አንድ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ያለው አካል እንዳለ ያመለክታሉ። እያንዳንዳቸው በቢልዮን የሚቆጠሩ ከዋክብት የያዙ በቢልዮን የሚቆጠሩ የከዋክብት ረጨቶችን ያቀፈው አጽናፈ ዓለም ያለው ንድፍ፣ አሠራርና ውስብስብነትም ይህንኑ የሚመሠክር ነው። ሁሉም ሰማያዊ አካላት የሚመሩት የእንቅስቃሴ፣ የሙቀት፣ የብርሃን፣ የድምፅ፣ የኤሌክትሮማግኔቲዝምና የስበትን ኃይል ሕግ በመሰሉ ዝንፍ በማይሉ ሕጎች አማካኝነት ነው። ሕግ አውጪ ሳይኖር ሕጎች ሊኖሩ ይችላሉን? የሮኬት ሳይንቲስት የሆኑት ዶክተር ቨርንኼር ፎን ብራውን እንዲህ ብለዋል:- “የአጽናፈ ዓለም ሕጎች ፈጽሞ ዝንፍ የማይሉ በመሆናቸው ወደ ጨረቃ የሚመጥቅ መንኮራኩር ለመሥራት ምንም ዓይነት ችግር የማይገጥመን ከመሆኑም በላይ የበረራውን ሰዓት በሰከንድ ክፋይ እንኳን ሳይቀር ለይተን በትክክል ማስቀመጥ እንችላለን። እነዚህን ሕጎች ያወጣ አንድ አካል መኖር አለበት።”
11. ልናየው ስላልቻልን ብቻ አንድ ታላቅ ንድፍ አውጪ መኖሩን ልንክድ የማይገባው ለምንድን ነው?
11 እርግጥ ታላቁን ንድፍ አውጪና ሕግ ሰጪ በሥጋዊ ዓይናችን ማየት አንችልም። ይሁን እንጂ የስበትን፣ የማግኔትን ወይም የኤሌክትሪክን ኃይል ወይም የሬዲዮ ሞገዶችን ልናያቸው ስላልቻልን ብቻ መኖራቸውን እንክዳለንን? የሚያከናውኑትን ነገር ስለምንመለከት መኖራቸውን ፈጽሞ አንክድም። እንግዲያው ታላቁ ንድፍ አውጪና ሕግ ሰጪ ያከናወናቸውን አስደናቂ ነገሮች መመልከት እየቻልን እሱን ልናየው ስላልቻልን ብቻ መኖሩን እንዴት እንክዳለን?
12, 13. ማስረጃው ስለ ፈጣሪ መኖር ምን ምሥክርነት ይሰጣል?
12 የፊዚክስ ፕሮፌሰር የሆኑት ፖል ዴቪስ የሰው ልጅ ወደ ሕልውና የመጣው እንዲሁ ድንገት በተከሰተ አጋጣሚ እንዳልሆነ ተናግረዋል። “ወደ ሕልውና የመጣነው በዓላማ ነው” ሲሉ ገልጸዋል። ስለ አጽናፈ ዓለም ሲናገሩም እንዲህ ብለዋል:- “ያካሄድኩት ሳይንሳዊ ሥራ ግዑዙ አጽናፈ ዓለም እጅግ አስደናቂ በሆነ የፈጠራ ችሎታ የተሠራ መሆኑን ይበልጥ እንዳምን ስላደረገኝ ያላንዳች ዓላማ የሚንቀሳቀስ ነው ብዬ ማመን ያዳግተኛል። ይበልጥ ጥልቀት ያለው ማብራሪያ መኖር ያለበት ይመስለኛል።”
13 ስለዚህ አጽናፈ ዓለም፣ ምድርና በምድር ላይ ያሉት ሕያዋን ነገሮች ሁሉ እንዲሁ በአጋጣሚ የመጡ ነገሮች ሊሆኑ እንደማይችሉ ያሉት ማስረጃዎች ያመለክታሉ። ሁሉም አፍ አውጥተው ባይናገሩም እንኳ አንድ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ያለው ኃያል ፈጣሪ እንዳለ ይመሠክራሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ሐሳብ
14. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፈጣሪ ምን ይላል?
14 ጥንታዊ የሰው ልጅ መጽሐፍ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ይህንኑ ሐሳብ ይሰጣል። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ጳውሎስ በጻፈውና የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በዕብራውያን መጽሐፍ ውስጥ “እያንዳንዱ ቤት በአንድ ሰው ተዘጋጅቶአልና፣ ሁሉን ያዘጋጀ ግን እግዚአብሔር ነው” የሚል ሐሳብ እናገኛለን። (ዕብራውያን 3:4) በሐዋርያው ዮሐንስ የተጻፈው የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍም እንዲህ ይላል:- “አምላካችን ሆይ፣ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል።”— ራእይ 4:11
15. አንዳንዶቹን የአምላክ ባሕርያት ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?
15 መጽሐፍ ቅዱስ ምንም እንኳ አምላክ ሊታይ ባይችልም በሠራቸው ነገሮች አማካኝነት ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ማወቅ እንደሚቻል ያመለክታል። እንዲህ ይላል:- “የማይታየው [የፈጣሪ] ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ግልጥ ሆኖ ይታያል።”— ሮሜ 1:20
16. ሰዎች አምላክን ሊያዩት የማይችሉ መሆናቸው ሊያስደስተን የሚገባው ለምንድን ነው?
16 ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ውጤቱንም ሆነ ለተገኘው ውጤት ምክንያት የሆነውን ነገር ይገልጽልናል። ውጤቱ ማለትም የተሠሩት እጅግ አስደናቂ የሆኑ ነገሮች ለእነርሱ መፈጠር ምክንያት የሆነ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ያለው ታላቅ አምላክ እንዳለ ይመሠክራሉ። አምላክ የማይታይ በመሆኑ አመስጋኞች ልንሆን ይገባናል። አምላክ መላውን አጽናፈ ዓለም የፈጠረ እንደ መሆኑ መጠን እጅግ ታላቅ ኃይል እንዳለው ምንም አያጠራጥርም። ስለዚህ ዘጸአት 33:20 የ1980 ትርጉም
ሥጋና ደም የለበሱ ሰዎች እሱን አይተው በሕይወት ሊቀጥሉ አይችሉም። መጽሐፍ ቅዱስም የሚለው ይህንኑ ነው:- “[አምላክን] አይቶ በሕይወት መኖር የሚቻለው የለም።”—17, 18. ፈጣሪ አለ የሚለው ጽንሰ ሐሳብ የሚጠቅመን ለምንድን ነው?
17 ታላቅ ንድፍ አውጪ የሆነ አንድ የበላይ አካል ማለትም አምላክ አለ የሚለው ጽንሰ ሐሳብ በጣም ይጠቅመናል። ወደ ሕልውና የመጣነው በአንድ ፈጣሪ አማካኝነት ከሆነ እንግዲያው ይህ ፈጣሪ እኛን የፈጠረበት አንድ ምክንያት ወይም ዓላማ እንደሚኖረው የተረጋገጠ ነው። የተፈጠርነው በዓላማ እንድንኖር ከሆነ ደግሞ ወደፊት ሁኔታዎች ይሻሻሉልናል ብለን ተስፋ የምናደርግበት በቂ ምክንያት ይኖረናል ማለት ነው። አለዚያ ግን እንዲሁ ለተወሰነ ጊዜ እንኖርና ያላንዳች ተስፋ እንሞታለን ማለት ነው። ስለዚህ አምላክ ለእኛ ያለውን ዓላማ ማወቃችን በጣም አስፈላጊ ነው። ከዚያ በኋላ ከእሱ ዓላማ ጋር ተስማምተን መኖር እንፈልግ እንደሆነና እንዳልሆነ መወሰን እንችላለን።
18 መጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪ ስለ እኛ እጅግ የሚያስብ አፍቃሪ አምላክ እንደሆነ ይገልጻል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ስለ እናንተ ያስባል” ብሏል። (1 ጴጥሮስ 5:7፤ በተጨማሪም ዮሐንስ 3:16ንና 1 ዮሐንስ 4:8, 16ን ተመልከት።) አምላክ ምን ያህል እንደሚያስብልን ማወቅ የምንችልበት አንዱ መንገድ በአእምሮም ሆነ በአካል እኛን የሠራበትን አስደናቂ መንገድ በመመርመር ነው።
“ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁ”
19. መዝሙራዊው ዳዊት የትኛውን እውነታ እንድናስብ ያደርገናል?
19 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መዝሙራዊው ዳዊት “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁ” ሲል ገልጿል። (መዝሙር 139:14) የሰው አንጎልም ሆነ አካል በታላቁ ንድፍ አውጪ እጅግ በሚያስደንቅ ሁኔታ የተነደፈ በመሆኑ ይህ አባባል በእርግጥም ትክክል ነው።
20. አንድ ኢንሳይክሎፔድያ የሰውን አንጎል የገለጸው እንዴት ነው?
20 ለምሳሌ ያህል አንጎልህ ከየትኛውም ኮምፒዩተር እጅግ በላቀ ሁኔታ የተወሳሰበ ነው። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “በሥርዓተ ነርቭ ውስጥ የሚተላለፈው መረጃ በስልክ መስመሮች ከሚደረገው ከፍተኛ የመረጃ ልውውጥ ይበልጥ የተወሳሰበ ነው፤ የሰው አንጎል የሚፈታው ችግር ከፍተኛ ኃይል ካላቸው ኮምፒዩተሮች አቅም እጅግ የላቀ ነው።”
21. አንጎል የሚያከናውነውን ሥራ ስንመለከት ምን ብለን መደምደም ይኖርብናል?
21 በአንጎልህ ውስጥ በመቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ መረጃዎችና አእምሮህ የቀረጻቸው ምስሎች ተቀምጠዋል፤ ሆኖም አንጎል እንዲሁ የመረጃዎች መከማቻ ብቻ አይደለም። በአንጎልህ አማካኝነት እንዴት ማፏጨት፣ ዳቦ መጋገር፣ የውጪ ቋንቋዎች መናገር፣ ኮምፒዩተር መጠቀም ወይም አውሮፕላን ማብረር እንደምትችል ትማራለህ። የእረፍት ጊዜህ ምን እንደሚመስል ወይም ደግሞ አንድ ፍሬ ምን ያህል ጣፋጭ እንደሆነ በአእምሮህ መገመት ትችላለህ። ነገሮችን ማገናዘብና መሥራት ትችላለህ። በተጨማሪም ዕቅድ ማውጣት፣ ማድነቅ፣ ማፍቀርና አሳብህን ካለፈው፣ በወቅቱ ካለውና ከወደፊቱ ጊዜ ጋር ማዛመድ ትችላለህ። እኛ የሰው ልጆች የሰውን አንጎል የመሰለ እጅግ አስደናቂ የሆነ ነገር መንደፍ የማንችል በመሆኑ አንጎልን የነደፈው አካል በእርግጥም ከማንኛውም ሰው የላቀ ጥበብና ችሎታ እንዳለው ግልጽ ነው።
22. ሳይንቲስቶች የሰውን አንጎል በተመለከተ የትኛውን ሐቅ አምነው ተቀብለዋል?
22 አንጎልን በተመለከተ ሳይንቲስቶች የሚከተለውን ሐቅ አምነው ተቀብለዋል:- “እነዚህ ነገሮች በዚህ እጅግ አስደናቂ የሆነ ንድፍና አሠራር ባለውና በጣም በተወሳሰበ መሣሪያ አማካኝነት የሚከናወኑት እንዴት እንደሆነ በፍጹም አይታወቅም። . . . የሰው ልጆች በአንጎል ውስጥ የሚታየውን እያንዳንዱን እንቆቅልሽ የሆነ ነገር ሁሉ መቼም ቢሆን ላይፈቱት ይችላሉ።” (ሳይንቲፊክ አሜሪካን) የፊዚክስ ፕሮፌሰር የሆኑት ሬሞ ደግሞ እንዲህ ብለዋል:- “እውነቱን ለመናገር ከሆነ እስከ አሁንም ድረስ የሰው ልጅ አንጎል መረጃዎች የሚያስቀምጠው እንዴት እንደሆነ ወይም ደግሞ ያለፉ ነገሮችን በፈለገበት ጊዜ ማስታወስ የሚችለው እንዴት እንደሆነ ብዙም የምናውቀው ነገር የለም። . . . በሰው ልጅ አንጎል ውስጥ ቁጥራቸው እስከ መቶ ቢልዮን የሚደርስ በጣም ብዛት ያላቸው የነርቭ ሕዋሳት ይገኛሉ። እያንዳንዱ ሕዋስ
ሲናፕስ ተብለው በሚጠሩ የዛፍ ዓይነት መልክ ባላቸው ብዛት ያላቸው ነገሮች በሺህ ከሚቆጠሩ ሌሎች ሕዋሳት ጋር ይገናኛል። እርስ በርስ ግንኙነት የሚያደርጉባቸው መንገዶች እጅግ የተራቀቁ ናቸው።”23, 24. አስደናቂ ንድፍ ካላቸው የሰውነት ክፍሎች መካከል አንዳንዶቹን ጥቀስ፤ አንድ መሐንዲስ ምን አስተያየት ሰጥቷል?
23 ዓይኖችህ ከየትኛውም ካሜራ የበለጠ ጥራት ያላቸውና ራሳቸውን እንደ ሁኔታው በሚገባ የሚያስተካክሉ ናቸው፤ እንዲያውም ሙሉ በሙሉ አውቶማቲክ የሆኑ፣ ራሳቸውን አስተካክለው በተፈለገው ነገር ላይ በሚገባ የሚያነጣጥሩና ባለ ቀለም ተንቀሳቃሽ ምስሎችን የሚያነሱ ካሜራዎች ናቸው። ጆሮዎችህ የተለያዩ ዓይነት ድምፆች መለየት የሚችሉ ከመሆናቸውም በላይ አቅጣጫህንና ሚዛንህን እንድታስተካክል ያደርጉሃል። ልብህ ከፍተኛ ችሎታ አላቸው የሚባሉ መሐንዲሶች እንኳ አስመስለው ሊሠሩት ያልቻሉት ከፍተኛ ብቃት ያለው ፓምፕ ነው። ሌሎች የሰውነት ክፍሎችም በጣም አስደናቂ ናቸው፤ ከእነዚህም መካከል አፍንጫህ፣ ምላስህና እጆችህ እንዲሁም ደምህ የሚዘዋወርባቸውና ምግብ የሚፈጭባቸው ሥርዓቶች ጥቂቶቹ ናቸው።
24 በመሆኑም አንድ ትልቅ ኮምፒዩተር እንዲነድፍና እንዲሠራ የተቀጠረ አንድ መሐንዲስ የሚከተለውን ምክንያታዊ የሆነ ሐሳብ ሰንዝሯል:- “የእኔ ኮምፒዩተር አንድ ንድፍ አውጪ ካስፈለገው፣ ወሰን የሌለው የታላቁ አጽናፈ ዓለም እጅግ አነስተኛ ክፍል የሆነውና ውስብስብ የሆነው ፊዚካላዊ፣ ኬሚካላዊና ባዮሎጂያዊ መሣሪያ ማለትም ሰብዓዊ አካሌ ይበልጥ ታላቅ የሆነ ንድፍ አውጪ አያስፈልገውምን?”
25, 26. ታላቁ ንድፍ አውጪ የትኛውን ነገር ሊነግረን መቻል ይኖርበታል?
25 ሰዎች አውሮፕላኖችን፣ ኮምፒዩተሮችን፣ ብስክሌቶችንና ሌሎች መሣሪያዎችን የሚሠሩት በአእምሯቸው አንድ ዓላማ ይዘው እንደሆነ ሁሉ የሰዎች አንጎልና አካል ንድፍ አውጪም የፈጠረን አንድ ዓላማ ኖሮት መሆን እንዳለበት ግልጽ ነው። ማንኛችንም ብንሆን የእሱን ንድፎች አስመስለን መሥራት የማንችል በመሆኑ ይህ ንድፍ አውጪ ከሰዎች የላቀ ጥበብ ያለው መሆን አለበት። እንግዲያው ለምን እንደሠራን፣ ለምን በምድር ላይ እንድንኖር እንዳደረገንና ወደፊት ምን እንደሚጠብቀን ሊነግረን የሚችለው እሱ መሆን አለበት ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ነው።
26 እነዚህን ነገሮች ማወቅ ስንችል አምላክ የሰጠንን አስደናቂ አንጎልና አካል የተፈጠርንበትን ዓላማ በሚያሟላ መንገድ ልንጠቀምባቸው እንችላለን። ይሁን እንጂ የአምላክን ዓላማዎች ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? ይህን መረጃ የሚሰጠንስ በምን አማካኝነት ነው?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንድ ነገር የተነደፈበትን ዓላማ ለማወቅ የሚያስችለው ከሁሉ የተሻለ መንገድ ንድፍ አውጪውን መጠየቅ ነው
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሕያዋን ነገሮችን ውስብስብነትና ንድፍ በዲ ኤን ኤ ሞለኪዩል ውስጥ ማየት ይቻላል
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“የሰው አንጎል የሚፈታው ችግር ከፍተኛ ኃይል ካላቸው ኮምፒዩተሮች አቅም እጅግ የላቀ ነው”