በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የላቀ ጥበብ የሚገኝበት በዓይነቱ ልዩ የሆነ ምንጭ

የላቀ ጥበብ የሚገኝበት በዓይነቱ ልዩ የሆነ ምንጭ

ክፍል 3

የላቀ ጥበብ የሚገኝበት በዓይነቱ ልዩ የሆነ ምንጭ

1, 2. መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር ያለብን ለምንድን ነው?

1 መጽሐፍ ቅዱስ ይህ የላቀ ጥበብ ተመዝግቦ የሚገኝበት መጽሐፍ ነውን? ከሕይወት ዓላማ ጋር በተያያዘ ለሚነሱት በጣም አስፈላጊ ለሆኑ ጥያቄዎች እውነተኛ መልስ ሊሰጠን ይችላልን?

2 በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ ልንመረምረው የሚገባ መጽሐፍ ነው። ይህን ልናደርግበት የሚገባው አንዱ ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ዛሬ ድረስ አንድ ላይ ተሰባስበው አንድ መጽሐፍ ከወጣቸው ጽሑፎች ሁሉ ለየት የሚያደርገው ነገር ስላለው ነው፤ ከየትኛውም ሌላ መጽሐፍ በጣም የተለየ ነው። የሚከተሉትን እውነታዎች ተመልከት።

እጅግ ጥንታዊና ከየትኛውም መጽሐፍ ይበልጥ በስፋት የተሰራጨ

3, 4. መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያህል ዕድሜ አለው?

3 መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ዛሬ ከተጻፉት መጻሕፍት ሁሉ እጅግ ጥንታዊ ነው፤ አንዳንድ የመጽሐፉ ክፍሎች የተጻፉት ከ3,500 ዓመታት ገደማ በፊት ነው። ቅዱሳን ናቸው ከሚባሉት ጽሑፎች ሁሉ ብዙ መቶ ዘመናት አስቀድሞ የተጻፈ መጽሐፍ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ከያዛቸው 66 መጻሕፍት መካከል የመጀመሪያው የተጻፈው ከቡድሃና ከኮንፍዩሼስ አንድ ሺህ ዓመታት ገደማ አስቀድሞና ከመሐመድ ሁለት ሺህ ዓመታት ገደማ ቀደም ብሎ ነው።

4 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘው ታሪክ ከሰብዓዊው ቤተሰብ መጀመሪያ አንስቶ ይተርካል፤ በተጨማሪም በምድር ላይ ሕያው ልንሆን የቻልነው እንዴት እንደሆነ ይገልጻል። አልፎ ተርፎም ሰዎች ከመፈጠራቸው በፊት ወደነበረው ጊዜ በመመለስ ስለ ምድር አፈጣጠር ዝርዝር ማብራሪያ ይሰጠናል።

5. በአሁኑ ጊዜ በእጅ ከሚገኙት በጥንት ዘመን የተጻፉ ዓለማዊ ጽሑፎች አንጻር ሲታይ በእጅ የተጻፉ ምን ያህል ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ይገኛሉ?

5 ሌሎች ሃይማኖታዊም ሆኑ ሃይማኖታዊ ያልሆኑ ጽሑፎች በጥንት ዘመን በእጅ ከተጻፉት ቅጂዎቻቸው መካከል በአሁኑ ጊዜ የሚገኙት ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። ወደ 11,000 የሚጠጉ በዕብራይስጥና በግሪክኛ ቋንቋዎች በእጅ የተጻፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ቅጂዎች ይገኛሉ፤ ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ የተጻፉበት ዘመን የመጀመሪያው ቅጂ ወደተጻፈበት ዘመን ይጠጋል። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥፋት ይህ ነው የማይባል ከፍተኛ ጥረት የተደረገ ቢሆንም እነዚህ ቅጂዎች ሊተርፉ ችለዋል።

6. መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያህል በስፋት ተሰራጭቷል?

6 በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ በስፋት በመሰራጨት ረገድ በታሪክ ዘመናት ሁሉ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት መጽሐፍ ነው። ሦስት ቢልዮን ገደማ የሚሆኑ መጽሐፍ ቅዱሶች ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ከሁለት ሺህ በሚበልጡ ቋንቋዎች ታትመው ተሰራጭተዋል። ከሰብዓዊው ቤተሰብ መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝብ መጽሐፍ ቅዱስን በራሱ ቋንቋ ማግኘት እንደሚችል ይነገራል። በዚህ መልኩ የተሰራጨ አንድም ሌላ መጽሐፍ የለም።

7. ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛነት ምን ሊባል ይችላል?

7 ከዚህም በተጨማሪ በትክክለኛነት ረገድ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ሊወዳደር የሚችል ጥንታዊ መጽሐፍ የለም። ሳይንቲስቶች፣ ታሪክ ጸሐፊዎች፣ አርኪኦሎጂስቶች፣ የጂኦግራፊ ጠበብቶች፣ የቋንቋ ሊቃውንትና ሌሎችም የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ትክክለኛ እንደሆኑ በየጊዜው ያረጋግጣሉ።

ሳይንሳዊ ትክክለኛነት

8. መጽሐፍ ቅዱስ ሳይንሳዊ ጉዳዮችን በተመለከተ የሚሰጠው ሐሳብ ምን ያህል ትክክል ነው?

8 ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ምንም እንኳ የሳይንስ መማሪያ መጽሐፍ እንዲሆን ተደርጎ የተጻፈ ባይሆንም ስለ ሳይንሳዊ ጉዳዮች የሚገልጻቸው ነገሮች ከእውነተኛ ሳይንስ ጋር የሚስማሙ ናቸው። እንደ ቅዱስ ተደርገው የሚታዩት ሌሎች ጥንታውያን መጻሕፍት ግን ሳይንሳዊ ተረቶችን፣ የተሳሳቱ ሐሳቦችንና ሙሉ በሙሉ ሐሰት የሆኑ መረጃዎችን የያዙ ናቸው። ሳይንሳዊ ጉዳዮችን በተመለከተ የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛነት ከሚያሳዩት ብዙ ምሳሌዎች መካከል አራቱን ብቻ ተመልከት:-

9, 10. መጽሐፍ ቅዱስ ምድርን ደግፎ ያቆማትን ነገር በተመለከተ በዘመኑ የነበሩትን ሳይንሳዊ ያልሆኑ አመለካከቶች ከማንጸባረቅ ይልቅ ምን ይላል?

9 ምድር በጠፈር ውስጥ የምትገኝበት ሁኔታ። መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት በጥንት ዘመን ምድር በጠፈር ውስጥ ስለምትገኝበት ሁኔታ ብዙ ግምታዊ ሐሳቦች ይሰጡ ነበር። አንዳንዶች በአንድ ትልቅ የባሕር ዔሊ ላይ የቆሙ አራት ዝሆኖች ምድርን ደግፈው እንዳቆሟት አድርገው ያስቡ ነበር። በአራተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የግሪክ ፈላስፋና የሳይንስ ሊቅ የነበረው አርስቶትል ምድር በባዶ ቦታ ላይ ተንጠልጥላ ልትቆም አትችልም ሲል አስተምሮ ነበር። ከዚህ ይልቅ ሰማያዊ አካላት ጠጣርና ብርሃን አስተላላፊ ከሆኑ ክብ አካላት ጋር የተያያዙ እንደሆኑ ገልጿል። በተጨማሪም እነዚህ ብርሃን አስተላላፊ አካላት አንዳቸው በሌላው ላይ የተነባበሩ እንደሆኑ ተናግሯል። ምድር ያለችው በውስጠኛው ክብ አካል ላይ ሲሆን የላይኛው ክብ አካል ደግሞ ከዋክብትን እንደያዘ ተደርጎ ይታመን ነበር።

10 ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ፣ በተጻፈበት ዘመን የነበረውን ግምታዊና ኢ-ሳይንሳዊ አመለካከት ከማንጸባረቅ ይልቅ (ከዘአበ በ1473 ገደማ) “[አምላክ] ምድሪቱንም በታችዋ አንዳች አልባ ያንጠለጥላል” በማለት በአጭሩ ገልጿል። (ኢዮብ 26:7፤ ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።) በጥንቱ የዕብራይስጥ ቋንቋ እዚህ ላይ “አንዳች አልባ” ለሚለው አነጋገር የገባው ቃል “ምንም ነገር ሳይኖር” ማለት ነው፤ ይህ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የገባው እዚህ ቦታ ላይ ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ምድር በባዶ ቦታ የተንጠለጠለች መሆኗን መግለጹ በዚያ ዘመን ከነበረው ሁኔታ አንጻር እጅግ አስደናቂ ራእይ እንደነበር ምሁራን አምነው ተቀብለዋል። ቲኦሎጂካል ወርድ ቡክ ኦቭ ዚ ኦልድ ቴስታመንት እንዲህ ይላል:- “ኢዮብ 26:7 በዚያ ዘመን የነበረው ዓለም በባዶ ቦታ ላይ የተንጠለጠለ እንደሆነ በሚያስገርም ሁኔታ በመግለጽ ወደፊት አዲስ ሳይንሳዊ ግኝት ላይ እንደሚደረስ አመላክቷል።”

11, 12. ሰዎች ኢዮብ 26:7 ላይ የሚገኘው ሐሳብ እውነት መሆኑን የተረዱት መቼ ነው?

11 መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ትክክለኛ መግለጫ የሰጠው አርስቶትል በሕይወት ከነበረበት ዘመን 1,100 ዓመታት በላይ አስቀድሞ ነው። ሆኖም የአርስቶትል እምነት እሱ ከሞተም በኋላ ወደ 2,000 ለሚጠጉ ዓመታት ያህል እንደ ሐቅ ተደርጎ ሲታይ ቆይቷል! በመጨረሻ በ1687 እዘአ ሰር አይዛክ ኒውተን ምድር ከሌሎች ሰማያዊ አካላት ጋር እርስ በርስ በመሳሳብ ማለትም በስበት ኃይል በባዶ ቦታ ላይ የተንጠለጠለች መሆኗን የሚያመለክቱ ግኝቶቹን በመጽሐፍ አሳትሞ አወጣ። ሆኖም ይህ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ምድር “አንዳች አልባ” የተንጠለጠለች መሆኗን እጅግ ቀላል በሆነ መንገድ ከገለጸ ወደ 3,200 የሚጠጉ ዓመታት ካለፉ በኋላ ነው።

12 አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ወደ 3,500 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት ምድር በሚታይ ነገር የተደገፈች አለመሆኗን በትክክል በመግለጽ በቅርብ ጊዜ ከተደረሰባቸው የስበት ኃይልና የእንቅስቃሴ ሕጎች ጋር የሚስማማ ሐቅ ተናግሯል። አንድ ምሁር “ቅዱስ ጽሑፉ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መሆኑን አምነው የማይቀበሉ ሰዎች ኢዮብ እውነታውን ሊያውቅ የቻለው እንዴት ነው? የሚለው ጥያቄ በቀላሉ አይፈታላቸውም” ሲሉ ገልጸዋል።

13. ሰዎች ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት ስለ ምድር ቅርጽ ምን አመለካከት ነበራቸው? ሆኖም አመለካከታቸውን እንዲለውጡ ያደረጋቸው ምንድን ነው?

13 የምድር ቅርጽ። ዚ ኢንሳይክሎፔድያ አሜሪካና እንዲህ ብሏል:- “በጥንት ዘመን ሰዎች ምድር በአጽናፈ ዓለም መካከል የምትገኝ ጠፍጣፋና ዝርግ የሆነች ጠጣር ነገር ነች ብለው ያምኑ ነበር። . . . ምድር ክብ ነች የሚለው ጽንሰ ሐሳብ የሥልጣኔ ዘመን እስከ ጀመረበት ጊዜ ድረስ በሰፊው ተቀባይነት አላገኘም ነበር።” እንዲያውም አንዳንድ የጥንት ባሕረተኞች በባሕር ላይ ሲቀዝፉ ጠፍጣፋዋን ምድር ለቅቀን ልንወጣ እንችላለን የሚል ስጋት ነበረባቸው። ሆኖም ኮምፓስ የተባለው አቅጣጫ የሚጠቁም መሣሪያና ሌሎች አዳዲስ ግኝቶች ሥራ ላይ ሲውሉ በውቅያኖሶች ላይ ከበፊቱ ይበልጥ ረጅም ጉዞዎች ማድረግ ተቻለ። እነዚህ “አዳዲስ ነገሮች የተገኙባቸው ጉዞዎች ዓለም ቀደም ሲል አብዛኞቹ ሰዎች ያምኑት እንደነበረው ጠፍጣፋ ሳይሆን ክብ መሆኑን አመልክተዋል” ሲል አንድ ሌላ ኢንሳይክሎፔድያ ገልጿል።

14. መጽሐፍ ቅዱስ የምድርን ቅርፅ የሚገልጸው እንዴት ነው? ይህንንስ የገለጸው መቼ ነው?

14 ሆኖም እንዲህ ዓይነቶቹ ረጅም የባሕር ላይ ጉዞዎች ከመካሄዳቸው ወደ 2,700 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት መጽሐፍ ቅዱስ “እርሱ በምድር ክበብ ላይ ይቀመጣል” ሲል ገልጿል። (ኢሳይያስ 40:22፤ ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።) እዚህ ላይ “ክበብ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል የተለያዩ የማመሳከሪያ ጽሑፎች እንደሚገልጹት “ድቡልቡል” ማለትም ሊሆን ይችላል። በዚህም ምክንያት ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “በምድር ሉል” (ዱዌይ ቨርሽን) እና “ክብ በሆነችው ምድር” (ሞፋት) ብለው ተርጉመውታል።

15. መጽሐፍ ቅዱስ ምድርን በተመለከተ የነበሩት ሳይንሳዊ ያልሆኑ አመለካከቶች ተጽእኖ ያላሳደሩበት ለምንድን ነው?

15 ምድርን ደግፎ ያቆማትን ነገርና ቅርጿን በተመለከተ በዚያ ዘመን ተስፋፍተው የነበሩት ሳይንሳዊ ያልሆኑ አመለካከቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ምንም ተጽእኖ አላሳደሩም። ይህ የሆነበት ምክንያት ግልጽ ነው:- መጽሐፍ ቅዱስን የደረሰው የአጽናፈ ዓለም ፈጣሪ ስለሆነ ነው። ምድርን የፈጠረው እሱ ነው፤ ስለዚህ ያንጠለጠላት ነገር ምን እንደሆነና ቅርጿ ምን እንደሚመስል ያውቃል። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈሱ አማካኝነት እንዲጻፍ ሲያደርግ በዚያ ዘመን ሰዎች ያምኑባቸው የነበሩ ብዙ ሳይንሳዊ ያልሆኑ አመለካከቶች የነበሩ ቢሆንም እንኳ አንድም ሳይንሳዊ ያልሆነ ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ እንዳይገባ አድርጓል።

16. ሕያዋን ነገሮች የተሠሩበት ነገር ከመጽሐፍ ቅዱስ አባባል ጋር የሚስማማው እንዴት ነው?

16 ሕያዋን ፍጥረታት የተሠሩባቸው ነገሮች። ዘፍጥረት 2:7 “እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው” ሲል ይገልጻል። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ “ሕያዋን ነገሮች የተሠሩባቸው ኬሚካላዊ ንጥረ ነገሮች በሙሉ ሕይወት በሌለው ቁስ አካል ውስጥም ይገኛሉ” ይላል። ስለዚህ ሰውን ጨምሮ ሕያዋን ዘአካሎች የተሠሩባቸው መሠረታዊ የሆኑ ኬሚካሎች በሙሉ በምድር ውስጥም ይገኛሉ። ይህም አምላክ ሰዎችንና ሌሎች ሕያዋን ነገሮችን በሙሉ ለመፍጠር የተጠቀመበትን ነገር ለይቶ ከሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ጋር ይስማማል።

17. ሕያዋን ነገሮች ወደ ሕልውና የመጡበትን መንገድ በተመለከተ እውነታው ምንድን ነው?

17 “እንደ ወገኑ።” አምላክ የመጀመሪያዎቹን ሰብዓዊ ባልና ሚስት እንደፈጠረና ሌሎቹ ሰዎች በሙሉ ከእነርሱ እንደመጡ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ዘፍጥረት 1:26-28፤ 3:20) እንደ ዓሦች፣ አዕዋፍና አጥቢ እንስሳት ያሉት ሌሎቹ ሕያዋን ነገሮችም ‘እንደ ወገናቸው’ እንደመጡ ይናገራል። (ዘፍጥረት 1:11, 12, 21, 24, 25) ሳይንቲስቶች በፍጥረት ሥራ ውስጥ የተመለከቱት ነገርም ይኸው ነው፤ እያንዳንዱ ሕያው ነገር የመጣው መሰሉ ከሆነ ወላጅ እንደሆነ ተገንዝበዋል። በፍጥረት ሥራ ውስጥ ከዚህ ደንብ ውጪ የሆነ ምንም ነገር የለም። ይህን በተመለከተ የፊዚክስ ሊቅ የሆኑት ሬሞ እንዲህ ብለዋል:- “ሕይወት ሕይወትን ያስገኛል፤ ይህ በየትኛውም ሕዋስ ውስጥ ምንጊዜም የሚከሰት ነገር ነው። ሕይወት የሌለው ነገር ግን እንዴት ሕያው ነገር ሊያስገኝ ይችላል? ይህ በባዮሎጂ መልስ ካላገኙት ትልልቅ ጥያቄዎች መካከል አንዱ ነው፤ እስካሁንም ድረስ የባዮሎጂ ሊቃውንት የተምታታ ግምታዊ መልስ ከመስጠት የተሻለ ምንም ነገር ማድረግ አልቻሉም። ሕይወት የሌለው ቁስ አካል በሆነ መንገድ ራሱን በማደራጀት ሕይወት ያለው ነገር መሆን ችሏል ይላሉ። . . . ሆኖም ሁኔታውን የዘፍጥረት መጽሐፍ ደራሲ በትክክል የገለጸው ይመስላል።”

ታሪካዊ ትክክለኛነት

18. አንድ ሕግ ዐዋቂ የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪካዊ ትክክለኛነት በተመለከተ ምን ብለዋል?

18 መጽሐፍ ቅዱስ በውስጡ የያዘው ጥንታዊ ታሪክ በዛሬው ጊዜ የሚገኝ የትኛውም መጽሐፍ ከያዘው ጥንታዊ ታሪክ ይበልጥ ትክክለኛ ነው። አንድ ሕግ ዐዋቂ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያደረጉት ምርምር (A Lawyer Examines the Bible) የተባለው መጽሐፍ ታሪካዊ ትክክለኛነቱን በዚህ መንገድ ጎላ አድርጎ ገልጾታል:- “ስለ ፍቅር የተጻፉ ልብ ወለድ መጽሐፎች፣ አፈ ታሪኮችና የሐሰት ማስረጃዎች በውል በማይታወቅ ሥፍራና በአንድ ያልተወሰነ ጊዜ ላይ የተፈጸሙ ነገሮችን አንድ በአንድ በዝርዝር የሚገልጹ ቢሆንም እኛ የሕግ ሰዎች አንድ ሰው የሚሰጠው ቃል ‘ጊዜውንና ቦታውን የሚገልጽ መሆን አለበት’ ብለን የምናምንበትን የመጀመሪያውን ደንብ የሚጥሱ ናቸው፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ታሪኮች ግን ሁኔታዎቹ የተፈጸሙበትን ጊዜና ቦታ በትክክል ይገልጹልናል።”

19. አንድ ጽሑፍ መጽሐፍ ቅዱስ በዝርዝር የሚያቀርባቸውን ታሪካዊ ክንውኖች በተመለከተ ምን አስተያየት ሰጥቷል?

19 አዲሱ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት (The New Bible Dictionary) የተባለው መጽሐፍ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል:- “[የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ጸሐፊ] ታሪኩን የጻፈው በዚያው ዘመን ከነበረው ታሪክ ጋር ጎን ለጎን በማስኬድ ነው፤ የከተማ የሕግ ባለሥልጣናት፣ አገረ ገዥዎች፣ ነገሥታትና እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮች በመጽሐፉ ውስጥ ብዙ ጊዜ ተጠቅሰዋል። በመጽሐፉ ውስጥ የተጠቀሱት እነዚህ ነገሮች የተፈጸሙበት ቦታና ጊዜ በሙሉ ትክክል እንደሆነም ተረጋግጧል።”

20, 21. አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ምን ብለዋል?

20 ኤስ ኦስቲን አልቦን ዘ ዩኒየን ባይብል ካምፓንየን በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ሰር አይዛክ ኒውተንም . . . በጥንት ጽሑፎች ላይ ሂስ በመስጠት የታወቀ ነው፤ ቅዱሳን ጽሑፎችንም ከፍተኛ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ መርምሯል። በዚህ ነጥብ ላይ የደረሰበት መደምደሚያ ምንድን ነው? ‘ከማንኛውም የ[ዓለማዊ] ታሪክ መጽሐፍ ይበልጥ በውስጡ ስለያዘው ታሪክ እውነተኛነት አስተማማኝ ማስረጃ ያገኘሁት በአዲስ ኪዳን ውስጥ ነው’ ብሏል። ዶክተር ጆንሰን፣ ጁሊየስ ቄሣር ሮም በሚገኘው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት እንደሞተ ከሚያመለክተው ማስረጃ የበለጠ ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌሎች ውስጥ እንደተገለጸው በጎልጎታ እንደሞተ የሚያረጋግጡ ብዙ ማስረጃዎች አሉን። አዎን፣ ከዚያ የበለጡ ማስረጃዎች አሉን ብለዋል።”

21 ይህ ጽሑፍ እንዲህ ሲል አክሎ ይገልጻል:- “የወንጌልን ታሪክ እውነተኝነት እጠራጠራለሁ የሚለውን ማንኛውንም ሰው ቄሣር በሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ውስጥ መሞቱን ወይም ደግሞ በ800 ንጉሠ ነገሥት ሻርለማኝ የምዕራቡ ክፍል ንጉሠ ነገሥት እንዲሆን በሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ መቀባቱን እንዲያምን ያደረገው ምን እንደሆነ ጠይቁት። . . . ቀዳማዊ ቻርልስ የሚባል [የእንግሊዝ] ሰው በሕይወት ይኖር እንደነበረና አንገቱ ተቀልቶ ኦሊቨር ክሮምዌል የሚባል ገዥ በቦታው እንደተተካ እንዴት ልታውቅ ቻልክ? በሉት። . . . የስበትን ሕግ ያገኘው ሰር አይዛክ ኒውተን እንደሆነ ይነገራል . . . ስለ እነዚህ ሰዎች የተነገረውን ሁሉ እናምናለን፤ ምክንያቱም እውነተኝነታቸውን የሚመሰክሩ ታሪካዊ ማስረጃዎች አሉን። . . . እንዲህ ዓይነት ማስረጃዎች እያሉም የሚነገረውን ነገር አላምንም የሚሉ ሰዎች ካሉ ነገር የማይዋጥላቸው ደረቆች ወይም ፈጽሞ የማይገባቸው ደንቆሮዎች ናቸው ብለን ከመተው ሌላ ምንም ልናደርግ አንችልም።”

22. አንዳንዶች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነተኝነት አንቀበልም የሚሉት ለምንድን ነው?

22 ከዚያም ይህ ጽሑፍ እንዲህ በማለት ይደመድማል:- “ታዲያ ቅዱሳን ጽሑፎች የያዙት ታሪክ ትክክለኛ መሆኑን የሚያሳዩ ብዙ ማስረጃዎች ቢቀርቡም እንኳ ለማመን አሻፈረኝ የሚሉትን ሰዎች በተመለከተ ምን ለማለት እንችላለን? . . . ችግር ያለው አእምሯቸው ውስጥ ሳይሆን ልባቸው ውስጥ ነው ብለን እንድንደመድም ያደርገናል፤ ክብራቸውን ዝቅ የሚያደርግና አኗኗራቸውን እንዲለውጡ የሚያስገድድ ነገር አምነው መቀበል አይፈልጉም።”

እርስ በርሱ ያለው ስምምነትና ግልጽነቱ

23, 24. መጽሐፍ ቅዱስ በውስጡ የያዘው ሐሳብ እርስ በርሱ የሚስማማ መሆኑ አስገራሚ የሆነው ለምንድን ነው?

23 አንድ መጽሐፍ በሮማ የግዛት ዘመን መጻፍ ጀምሮ በተለያዩ ጸሐፊዎች አማካኝነት በመካከለኛውም ዘመን ሲጻፍ ከቆየ በኋላ በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ተጽፎ አለቀ እንበል። ጸሐፊዎቹ የተለያየ ሥራ ያላቸው ማለትም ወታደሮች፣ ነገሥታት፣ ካህናት፣ ዓሣ አጥማጆች፣ እረኞችና ሐኪሞች ቢሆኑ መጨረሻ ውጤቱ ምን ይሆናል ብለህ ትገምታለህ? መጽሐፉ እርስ በእርሱ የሚስማማና የሚጣጣም ይሆናል ብለህ ትጠብቃለህ? ‘በፍጹም!’ ብለህ ትመልስ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በእንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ ነው። ሆኖም በአጠቃላይ ሐሳብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ ዝርዝር ሐሳብ እንኳ ሳይቀር ሙሉ በሙሉ እርስ በርሱ የሚስማማ ነው።

24 መጽሐፍ ቅዱስ 40 በሚያክሉ የተለያዩ ጸሐፊዎች አማካኝነት የተጻፈ የ66 መጻሕፍት ስብስብ ነው፤ መጻፍ የጀመረው በ1513 ከዘአበ ሲሆን ተጽፎ ያለቀው ደግሞ በ98 እዘአ ነው። ተጽፎ እስኪያልቅ ድረስ ከ1,600 ዓመታት በላይ ወስዷል። ጸሐፊዎቹ የተለያየ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ሲሆኑ ብዙዎቹ ደግሞ እርስ በርሳቸው አይተዋወቁም ነበር። ሆኖም መጨረሻ ላይ መጽሐፉ ልክ በአንድ አእምሮ እንደተዘጋጀ መጽሐፍ ከዳር እስከ ዳር እርስ በርሱ የሚስማማ አንድ ማዕከላዊ ጭብጥ ያለው መጽሐፍ ሊሆን ችሏል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንዶች እንደሚያምኑት የምዕራባውያን የሥልጣኔ ውጤት ሳይሆን በምሥራቅ ሰዎች የተጻፈ ነው።

25. የመጽሐፍ ቅዱስ ሐቀኝነትና ግልጽነት የትኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አባባል የሚደግፍ ነው?

25 አብዛኞቹ የጥንት ጸሐፊዎች የራሳቸውን ስኬትና በጎ ጎን ብቻ የጻፉ ቢሆንም የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ግን የራሳቸውን ስህተቶችም ሆነ የነገሥታቶቻቸውንና የመሪዎቻቸውን ጉድለት አምነው በመቀበል በግልጽ ጽፈዋል። ዘኁልቁ 20:1-13 እና ዘዳግም 32:50-52 ሙሴ የፈጸማቸውን ስህተቶች ዘግበዋል፤ እነዚህን መጽሐፎች የጻፈው ደግሞ ሙሴ ራሱ ነው። ዮናስ 1:1-3 እና 4:1 የዮናስን ድክመቶች ይገልጻሉ፤ ታሪኮቹን የጻፈው ራሱ ዮናስ ነው። በማቴዎስ 17:18-20፤ 18:1-6፤ 20:20-28 እና 26:56 ላይ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ያሳዩአቸው ተገቢ ያልሆኑ ባሕርያት ተመዝግበው እናገኛለን። ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ሐቀኝነትና ግልጽነት መጽሐፉን የጻፉት በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት እንደሆነ በመግለጽ ለሰጡት ሐሳብ ድጋፍ ይሆናቸዋል።

ይበልጥ ልዩ የሚያደርገው ነገር

26, 27. መጽሐፍ ቅዱስ በሳይንሳዊና በሌሎች ጉዳዮች ረገድ ፍጹም ትክክል የሆነው ለምንድን ነው?

26 መጽሐፍ ቅዱስ በሳይንስ፣ በታሪክና በሌሎችም ጉዳዮች ረገድ የሚያቀርባቸው ዘገባዎች ፍጹም ትክክል ሊሆኑ የቻሉበትን ምክንያትም ሆነ እርስ በርሱ የሚስማማና ሐቁን በግልጽ የሚያስቀምጥ መጽሐፍ ሊሆን የቻለበትን ምክንያት ራሱ ይገልጻል። መጽሐፍ ቅዱስን የደረሰው አጽናፈ ዓለምን የሠራው፣ የሁሉ የበላይና ሁሉን ቻይ አምላክ የሆነው ፈጣሪ እንደሆነ ይገልጻል። አምላክ ሰብዓዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችን በመንፈሱ የገለጠላቸውን ነገር እንዲጽፉ አንቀሳቃሽ በሆነው ታላቅ ኃይሉ አማካኝነት በመገፋፋት እንደ ጸሐፊ አድርጎ ተጠቅሞባቸዋል።

27 ሐዋርያው ጳውሎስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።” በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “ከእኛ የሰማችሁትን የእግዚአብሔርን ቃል በተቀበላችሁ ጊዜ፣ . . . ይህንን ቃል የተቀበላችሁት እንደ ሰው ቃል ሳይሆን ልክ እንደ እግዚአብሔር ቃል አድርጋችሁ ነው፤ በእርግጥም የእግዚአብሔር ቃል ነው።”—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17፤ 1 ተሰሎንቄ 2:13 የ1980 ትርጉም

28. የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲ ማን ነው?

28 ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በአንድ ደራሲ ማለትም በአምላክ አእምሮ ነው። አምላክ ካለው እጅግ ታላቅ የሆነ ኃይል አንጻር መጽሐፉ ሳይበረዝ እንዳለ ተጠብቆ እስከ ዘመናችን ድረስ እንዲዘልቅ ማድረግ ለእሱ ቀላል ነገር ነው። በእጅ በተጻፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ላይ ምርምር ያደረጉት ሰር ፍሬድሪክ ኬንዮን በ1940 እንዲህ ብለዋል:- “ቅዱሳን ጽሑፎች በመጀመሪያ ሲጻፉ የነበራቸው ይዘት ሳይለወጥ እስከ ጊዜያችን ድረስ ተጠብቀው መቆየታቸውን አጠራጣሪ ሊያደርግ ይችል የነበረው የመጨረሻው መሠረት ተወግዷል።”

29. አምላክ ከሰዎች ጋር ግንኙነት ለማድረግ ያለውን ችሎታ እንዴት በምሳሌ ማስረዳት ይቻላል?

29 ሰዎች ከምድር በብዙ ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት በጠፈር ላይ ሆነው አልፎ ተርፎም ከጨረቃ ላይ የሬዲዮና የቴሌቪዥን መልእክቶችን የማስተላለፍ ችሎታ አላቸው። መንኮራኩሮች በመቶ ሚልዮን ማይልስ ርቀት ላይ በሚገኙ ፕላኔቶች ላይ ሆነው ፎቶዎችንና የጽሑፍ መረጃዎችን ወደ ምድር ይልካሉ። የሬዲዮ ሞገዶችን የፈጠረው የሰው ልጅ ፈጣሪ ቢያንስ ይህን ማድረግ አያቅተውም። በእርግጥም ሁሉን ቻይ የሆነውን ኃይሉን በመጠቀም መጽሐፍ ቅዱስን እንዲጽፉ ወደመረጣቸው ሰዎች አእምሮ ቃላትንና ምስሎችን ማስተላለፍ ለእሱ በጣም ቀላል ነበር።

30. አምላክ ሰዎች ለእነርሱ ያወጣውን ዓላማ እንዲያውቁ ይፈልጋልን?

30 ከዚህም በላይ አምላክ ለሰው ልጆች እንደሚያስብ የሚያሳዩ ምድርንም ሆነ በምድር ላይ ያለውን ሕይወት የሚመለከቱ ብዙ ነገሮች አሉ። ስለዚህ አምላክ የእሱን ማንነትና ለሰዎች ያለውን ዓላማ በአንድ መጽሐፍ ማለትም በአንድ ቋሚ የሆነ ሰነድ ውስጥ ቁልጭ አድርጎ በመግለጽ ሰዎች እነዚህን ነገሮች እንዲገነዘቡ ሊረዳቸው እንደሚፈልግ የታወቀ ነው።

31. በመንፈስ አነሳሽነት የተላለፈ በጽሑፍ የሰፈረ መልእክት በአፍ ሲተላለፍ ከቆየ መልእክት እጅግ የላቀ መረጃ የሚሆነው ለምንድን ነው?

31 በተጨማሪም አምላክ የደረሰው መጽሐፍ በሰዎች አንደበት ብቻ ሲተላለፍ ከቆየ መረጃ ጋር ሲወዳደር ምን ያህል የላቀ እንደሆነ አስበው። በአፍ የሚተላለፍ ቃል ሰዎች መልእክቱን በራሳቸው መንገድ ስለሚገልጹትና ከጊዜ በኋላም ትርጉሙ ስለሚዛባ አስተማማኝ ሊሆን አይችልም። በአፍ የሚነገረውን መረጃ እነሱ በመሰላቸው መንገድ ለሌላው ያስተላልፉታል። በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ቋሚ ጽሑፍ ግን እንዲህ ዓይነት ስህተት አይኖረውም። በተጨማሪም አንድ መጽሐፍ የተለያዩ ቋንቋዎች የሚያነቡ ሰዎች መጠቀም እንዲችሉ በሌላ ቅጂ ሊዘጋጅና ሊተረጎም ይችላል። እንግዲያው ፈጣሪያችን መረጃን ለማስተላለፍ በዚህ መንገድ መጠቀሙ ምክንያታዊ አይደለምን? ፈጣሪ ይህን እንዳደረገ የገለጸ በመሆኑ በእርግጥም ይህ ምክንያታዊ መሆኑ ምንም አያጠያይቅም።

ፍጻሜውን ያገኘ ትንቢት

32-34. መጽሐፍ ቅዱስ በሌላ በማንኛውም መጽሐፍ ውስጥ የማይገኝ ምን ነገር ይዟል?

32 ከዚህም ሌላ መጽሐፍ ቅዱስ በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መሆኑን በዓይነቱ እጅግ ልዩ በሆነ መንገድ የሚጠቁም ምልክት ይዟል:- ያላንዳች እንከን ፍጻሜያቸውን ያገኙና ፍጻሜያቸውን በማግኘት ላይ ያሉ ትንቢቶችን የያዘ መጽሐፍ ነው።

33 ለምሳሌ ያህል የጥንቷ ጢሮስ መጥፋት፣ የባቢሎን መውደቅ፣ የኢየሩሳሌም ዳግመኛ ግንባታና የሜዶንና የፋርስ እንዲሁም የግሪክ ነገሥታት መነሳትና መውደቅ በመጽሐፍ ቅዱስ አንድ በአንድ በዝርዝር ተተንብዮ ነበር። ትንቢቶቹ ፍጹም ትክክል በሆነ መንገድ በመፈጸማቸው አንዳንድ ተቺዎች ትንቢቶቹ የተጻፉት ሁኔታዎች ከተከሰቱ በኋላ ነው በማለት ተቀባይነት የሌለው ምክንያት ለማቅረብ ሞክረው ነበር።—ኢሳይያስ 13:17-19፤ 44:27 እስከ 45:1፤ ሕዝቅኤል 26:3-6፤ ዳንኤል 8:1-7, 20-22

34 ኢየሱስ በ70 እዘአ ኢየሩሳሌም እንደምትጠፋ የተናገራቸው ትንቢቶች በትክክል ተፈጽመዋል። (ሉቃስ 19:41-44፤ 21:20, 21) ኢየሱስና ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ “መጨረሻው ቀን” የተናገሯቸው ትንቢቶች በዘመናችን አንድ በአንድ በመፈጸም ላይ ናቸው።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5, 13፤ ማቴዎስ 24፤ ማርቆስ 13፤ ሉቃስ 21

35. የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ከፈጣሪ ብቻ የመጣ ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

35 የትኛውም የሰው አእምሮ የቱንም ያህል ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ቢኖረው እንኳ ወደፊት የሚፈጸሙ ነገሮችን ፍጹም ትክክል በሆነ መንገድ ሊተነብይ አይችልም። በ2 ጴጥሮስ 1:20, 21 ላይ እንደተገለጸው ይህን ማድረግ የሚችለው ሁሉን ማድረግ የሚያስችል ኃይልና ጥበብ ያለው የአጽናፈ ዓለሙ ፈጣሪ አእምሮ ብቻ ነው:- “በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፤ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፣ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።”

መልሱን ይሰጣል

36. መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይነግረናል?

36 መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ የታላቁ አካል ቃል እንደሆነ በብዙ መንገዶች ያሳያል። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች በምድር ላይ የተፈጠሩት ለምን እንደሆነ፣ መከራ የበዛው ለምን እንደሆነ፣ ወደፊት ምን እንደሚጠብቀንና አሁን ያሉት ሁኔታዎች እንዴት እንደሚሻሻሉ ይነግረናል። ሰዎችንና ይህችን ምድር በዓላማ የፈጠረ አንድ ታላቅ አምላክ እንዳለና ዓላማውም እንደሚፈጸም ይገልጽልናል። (ኢሳይያስ 14:24) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛው ሃይማኖት የቱ እንደሆነና እንዴት ልናገኘው እንደምንችል ይገልጽልናል። ስለዚህ በሕይወት ውስጥ ለሚነሱት አንገብጋቢ ጥያቄዎች ሁሉ እውነተኛ መልስ ሊሰጠን የሚችለው ከሁሉ የላቀው የጥበብ ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው።—መዝሙር 146:3፤ ምሳሌ 3:5፤ ኢሳይያስ 2:2-4

37. ሕዝበ ክርስትናን በተመለከተ ምን ጥያቄ መነሳት አለበት?

37 መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛና እውነተኛ መጽሐፍ መሆኑን የሚያሳዩ ብዙ ማስረጃዎች ቢኖሩም መጽሐፍ ቅዱስን እናምንበታለን የሚሉ ሁሉ ትምህርቱን ይከተላሉን? ለምሳሌ ያህል ክርስትናን እንከተላለን የሚሉትን ሕዝቦች ማለትም ሕዝበ ክርስትናን ተመልከት። መጽሐፍ ቅዱስን ካገኙ ብዙ መቶ ዘመናት ተቆጥረዋል። ይሁን እንጂ አስተሳሰባቸውና ድርጊታቸው በእርግጥ የአምላክን የላቀ ጥበብ ያንጸባርቃልን?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 11 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ሰር አይዛክ ኒውተን ምድር ከሌሎች ሰማያዊ አካላት ጋር በስበት ኃይል በመሳሳብ በባዶ ቦታ ላይ የተንጠለጠለች መሆኗን ያምን ነበር

መጽሐፍ ቅዱስ ምድር በባዶ ቦታ የተንጠለጠለች መሆኗን መግለጹ በዚያ ዘመን ከነበረው ሁኔታ አንጻር እጅግ አስደናቂ ራእይ እንደነበር ምሁራን አምነው ተቀብለዋል

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንዳንድ የጥንት ባሕረተኞች በባሕር ላይ ሲቀዝፉ ጠፍጣፋዋን ምድር ለቅቀን ልንወጣ እንችላለን የሚል ስጋት ነበረባቸው

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ እንደኖረ የሚያሳየው ማስረጃ ጁልየስ ቄሣር፣ ንጉሠ ነገሥት ሻርለማኝ፣ ኦሊቨር ክሮምዌል ወይም ደግሞ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ሦስተኛ በሕይወት እንደነበሩ ከሚያሳየው ማስረጃ ይበልጣል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሮም ውስጥ የሚገኘው የቲቶ ሐውልት ኢየሱስ በ70 እዘአ በኢየሩሳሌም ላይ ስለደረሰው ጥፋት የተናገራቸው ትንቢቶች እንደተፈጸሙ ያረጋግጣል