በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክ ዓላማ በቅርቡ ይፈጸማል

የአምላክ ዓላማ በቅርቡ ይፈጸማል

ክፍል 7

የአምላክ ዓላማ በቅርቡ ይፈጸማል

1, 2. አምላክ ክፋትንና መከራን ለማስወገድ እርምጃ እንደሚወስድ እርግጠኞች ልንሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

1 ምንም እንኳ ከሰው አመለካከት አንጻር ሲታይ አምላክ አለፍጽምናና መከራ ለረጅም ጊዜ እንዲኖሩ የፈቀደ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ያሉት መጥፎ ሁኔታዎች ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቀጥሉ አይፈቅድም። አምላክ እነዚህ ነገሮች እንዲደርሱ የፈቀደው ለተወሰነ ጊዜ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል።

2 “ለሁሉ ዘመን አለው።” (መክብብ 3:1) አምላክ ክፋትና መከራ እንዲኖር የፈቀደበት የተወሰነ ጊዜ ሲያበቃ በሰው ልጅ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ ይገባል። ክፋትንና መከራን በማስወገድ ምድር ፍጹማን በሆኑና በገነት ውስጥ የተሟላ ሰላምና ኢኮኖሚያዊ ዋስትና አግኝተው በሚኖሩ ደስተኛ ሰብዓዊ ቤተሰቦች እንድትሞላ በማድረግ የመጀመሪያ ዓላማውን ይፈጽማል።

የአምላክ ፍርድ

3, 4. የምሳሌ መጽሐፍ የአምላክ ጣልቃ ገብነት የሚያስገኛቸውን ውጤቶች የሚገልጸው እንዴት ነው?

3 የአምላክ ጣልቃ ገብነት ማለትም ፍርዶቹ የሚያስከትሏቸው ውጤቶች በቅርቡ ለሰብዓዊው ቤተሰብ ምን ትርጉም እንደሚኖራቸው ከሚገልጹት ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች መካከል ጥቂቶቹን ተመልከት:-

4 “ቅኖች በምድር ላይ ይቀመጣሉና፣ ፍጹማንም በእርስዋ ይኖራሉና፤ ኀጥኣን ግን ከምድር ይጠፋሉ፣ ዓመፀኞችም ከእርስዋ ይነጠቃሉ።”​—ምሳሌ 2:21, 22

5, 6. መዝሙር 37 አምላክ ጣልቃ በሚገባበት ጊዜ የሚከሰተውን ሁኔታ የሚያመለክተው እንዴት ነው?

5 “ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን እነርሱ ምድርን ይወርሳሉ። ገና ጥቂት፣ ኃጢአተኛም አይኖርም፤ . . . ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።”​—መዝሙር 37:9-11

6 “እግዚአብሔርን ደጅ ጥና፣ መንገዱንም ጠብቅ፣ ምድርንም ትወርስ ዘንድ ከፍ ከፍ ያደርግሃል፤ ኃጢአተኞችም ሲጠፉ ታያለህ። ቅንነትን ጠብቅ፣ ጽድቅንም እይ፤ ለሰላም ሰው ቅሬታ አለውና። በደለኞች በአንድነት ይጠፋሉ፤ የኃጢአተኞች ቅሬታ ይጠፋል።”​—መዝሙር 37:34, 37, 38

7. የአምላክ ቃል ምን ጥሩ ምክር ይሰጠናል?

7 ስለዚህ ሁሉን ቻይ የሆነው ፈጣሪ ያለውን የመግዛት መብት አምነው የሚቀበሉ ሰዎች የሚጠብቃቸውን ግሩም ተስፋ ግምት ውስጥ በማስገባት የሚከተለው ማሳሰቢያ ተሰጥቶናል:- “ልብህም ትእዛዛቴን ይጠብቅ። ብዙ ዘመናትና ረጅም ዕድሜ ሰላምም ይጨምሩልሃልና።” እንዲያውም የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ የሚመርጡ ሰዎች የዘላለም ሕይወትም ያገኛሉ! ስለዚህ የአምላክ ቃል እንዲህ ሲል ይመክረናል:- “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል።”​—ምሳሌ 3:1, 2, 5, 6

ሰማያዊው የአምላክ አገዛዝ

8, 9. አምላክ ምድርን የሚያጸዳው በምን አማካኝነት ነው?

8 አምላክ ምድርን የሚያጸዳው የሰው ልጅ ፈጽሞ አግኝቶት በማያውቅ ከሁሉ የተሻለ መንግሥት አማካኝነት ነው። ይህ መንግሥት በአምላክ አመራር ሥር ሆኖ ከሰማይ የሚያስተዳድር በመሆኑ ሰማያዊ ጥበብን የሚያንጸባርቅ ነው። ይህ ሰማያዊ መንግሥት ሁሉንም ዓይነት ሰብዓዊ አገዛዝ ከምድር ላይ ያስወግዳል። ሰዎች ራሳቸውን ከአምላክ አግልለው በገዛ ፈቃዳቸው ራሳቸውን ለማስተዳደር ሙከራ የሚያደርጉበት ሌላ አማራጭ አያገኙም።

9 ይህን በተመለከተ በዳንኤል 2:44 ላይ ያለው ትንቢት እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “በእነዚያም ነገሥታት [በአሁኑ ጊዜ ባሉት መንግሥታት] ዘመን የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት [በሰማይ] ያስነሣል፤ ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት ይሆናል [ሰዎች ዳግመኛ ራሳቸውን ከአምላክ አግልለው በገዛ ፈቃዳቸው ራሳቸውን እንዲገዙ አይፈቀድላቸውም]፤ እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ [በአሁኑ ጊዜ ያሉትን] ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፣ ለዘላለምም ትቆማለች።”​—በተጨማሪም ራእይ 19:11-21ንና 20:4-6ን ተመልከት።

10. በአምላክ ሰማያዊ መንግሥት አገዛዝ ሥር የአስተዳደር ብልሹነት እንደማይኖር እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

10 ስለዚህ አምላክ ይህን ሥርዓት ካጠፋ በኋላ ከእሱ ውጪ የሆነ ሰብዓዊ አገዛዝ ዳግመኛ ስለማይኖር የሰው ልጅ ብልሹ የሆኑ የአገዛዝ ዓይነቶች ዳግመኛ አይገጥሙትም። በሰማይ ሆኖ የሚያስተዳድረውን መንግሥት የሚያቋቁመውና አቋሙን ጠብቆ እንዲቀጥል የሚያደርገው አምላክ ስለሆነ ይህ መንግሥት አስተዳደራዊ ብልሽት አይደርስበትም። ከዚህ ይልቅ ለምድራዊ ተገዥዎቹ የተሻለ ጥቅም በሚያስገኝ መንገድ ያስተዳድራል። በዚያን ጊዜ የአምላክ ፈቃድ በሰማይ እንደሆነ ሁሉ በመላዋ ምድርም ላይ ይፈጸማል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለው ወደ አምላክ እንዲጸልዩ ያስተማራቸው ለዚህ ነው።​—ማቴዎስ 6:10

ምን ያህል ቀርበናል?

11. ወደዚህ ሥርዓት መጨረሻ ምን ያህል እንደቀረብን ለማወቅ የሚረዱንን ትንቢቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የት ቦታዎች ላይ እናገኛለን?

11 ይህ መጥፎ የነገሮች ሥርዓት ወደሚያከትምበትና አምላክ የሚያመጣው አዲሱ ዓለም ወደሚጀምርበት ጊዜ ምን ያህል ተቃርበናል? የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መልሱን በግልጽ ይነግረናል። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ‘የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ’ ብሎ የገለጸውን ጊዜ በተመለከተ ምን ደረጃ ላይ እንዳለን ለይተን ማወቅ እንድንችል ልንመለከታቸው የሚገቡ ነገሮችን አስቀድሞ ተናግሯል። ይህ በማቴዎስ ምዕራፍ 24 እና 25፣ በማርቆስ 13 እና በሉቃስ 21 ላይ ተመዝግቦ ይገኛል። በተጨማሪም በ2ኛ ጢሞቴዎስ ምዕራፍ 3 ላይ እንደተመዘገበው ሐዋርያው ጳውሎስ በጊዜ ሂደት ውስጥ የትኛው ወቅት ላይ እንዳለን ተጨማሪ ማረጋገጫ የሚሰጡ የተለያዩ ሁኔታዎች የሚፈጸሙበት የ“መጨረሻው ቀን” ተብሎ የሚጠራ ጊዜ እንደሚኖር አስቀድሞ ተናግሯል።

12, 13. ኢየሱስና ጳውሎስ ስለ መጨረሻው ጊዜ ምን ብለዋል?

12 ኢየሱስ በዚህ ወቅት መጀመሪያ ላይ የሚከተሉት ነገሮች እንደሚፈጸሙ ተናግሯል:- “ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፣ ራብም . . . የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል።” (ማቴዎስ 24:7) ሉቃስ 21:11 ኢየሱስ “በልዩ ልዩ ስፍራ ቸነፈር” ይከሰታል ብሎ እንደተናገረም ያመለክታል። በተጨማሪም ‘ዓመፅ እንደሚበዛ’ ተናግሯል።​—ማቴዎስ 24:12

13 ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ተንብዮአል:- “ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ . . . ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች፣ እያሳቱና እየሳቱ፣ በክፋት እየባሱ ይሄዳሉ።”​—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5, 13

14, 15. በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን የተፈጸሙት ነገሮች በእርግጥም በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ እየኖርን እንዳለን የሚያረጋግጡት እንዴት ነው?

14 ኢየሱስና ጳውሎስ የተነበዩአቸው እነዚህ ነገሮች በዘመናችን ተፈጽመዋልን? አዎን፣ በሚገባ ተፈጽመዋል። አንደኛው የዓለም ጦርነት ከዚያ በፊት ከተካሄዱት ጦርነቶች ሁሉ እጅግ የከፋ ነበር። የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ሲሆን በዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ ያስከተለ ጦርነት ነው። የምግብ እጥረት፣ ወረርሽኝ በሽታዎችና ሌሎች መቅሰፍቶችም ከጦርነቱ ጋር አብረው ተከስተው ነበር። ከ1914 ጀምሮ የተከሰቱት እነዚህ ነገሮች ኢየሱስ እንደገለጸው “የምጥ ጣር መጀመሪያ” ናቸው። (ማቴዎስ 24:8) አስቀድሞ በተነገረለት የ“መጨረሻው ቀን” ተብሎ በተጠራው ዘመን መጀመሪያና አምላክ ክፋትና መከራ እንዲቀጥል በፈቀደበት በመጨረሻው ትውልድ መጀመሪያ ላይ የተፈጸሙ ነገሮች ናቸው።

15 በ20ኛው መቶ ዘመን ውስጥ የተከናወኑትን ነገሮች በሚገባ ሳታውቅ አትቀርም። ምን ዓይነት ዝብርቅ እንደተከሰተ ታውቃለህ። በተካሄዱት ጦርነቶች ከ100 ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ተገድለዋል። ሌሎች በመቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብና በበሽታ ሞተዋል። የምድር ነውጥ ሥፍር ቁጥር የሌላቸውን ሰዎች ሕይወት ቀጥፏል። ሰዎች ለሕይወትና ለንብረት ያላቸው አክብሮት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ በመሄድ ላይ ነው። ወንጀል የፈጠረው ሥጋት የዕለታዊው ኑሮ ክፍል ሆኗል። ሰዎች የሥነ ምግባር መሥፈርቶችን አሽቀንጥረው ጥለዋቸዋል። የሕዝብ ቁጥር ፍንዳታ መፍትሔ ያልተገኘላቸው ችግሮች አስከትሏል። ብክለት የሕይወትን የጥራት ደረጃ እያበላሸ ከመሆኑም በላይ የጥፋት አደጋ እንዲያጠላበት አድርጎታል። በእርግጥም ከ1914 ጀምሮ በመጨረሻዎቹ ቀኖች ውስጥ እየኖርን ነው፤ በተጨማሪም ያለንበትን ጊዜ አስመልክቶ የተተነበዩት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ሙሉ በሙሉ ፍጻሜያቸውን ወደሚያገኙበት ጊዜ እየተቃረብን ነው።

16. የመጨረሻዎቹ ቀናት ምን ያህል ይቆያሉ?

16 እነዚህ የመጨረሻ ቀኖች የሚቆዩት ምን ያህል ጊዜ ነው? ኢየሱስ ከ1914 ጀምሮ “የምጥ ጣር መጀመሪያ” የሆኑት ነገሮች የሚፈጸሙበትን ዘመን አስመልክቶ ሲናገር “ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም” ብሏል። (ማቴዎስ 24:8, 34-36) ስለዚህ የመጨረሻዎቹ ቀናት ገጽታዎች በሙሉ በተወሰነ የጊዜ ርዝመት ውስጥ የሚፈጸሙ ናቸው። ራእይ 12:12 ሰይጣን ወደ ምድር አካባቢ ከተጣለ በኋላ የሚቀረው ጊዜ አጭር እንደሆነ ይገልጻል።

17, 18. ወደዚህ ዓለም መጨረሻ በጣም እንደቀረብን የሚያሳየው የትኛው ትንቢት ነው?

17 የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ በጣም እንደቀረበ የሚያሳየውን ሌላ ትንቢት ደግሞ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል አስቀድሞ ገልጾታል:- “የጌታ ቀን፣ ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ፣ እንዲሁ ይመጣል . . . ሰላምና ደኅንነት ነው ሲሉ፣ ያን ጊዜ . . . ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል ከቶም አያመልጡም።”​—1 ተሰሎንቄ 5:2, 3፤ በተጨማሪም ሉቃስ 21:34, 35ን ተመልከት።

18 በዛሬው ጊዜ ቀዝቃዛው ጦርነት ያበቃ በመሆኑ ዓለም አቀፍ ጦርነት ሊነሳ ይችላል የሚለው ስጋት ቀንሶ ይሆናል። ስለዚህ ብሔራት ወደ አዲስ ዓለም ሥርዓት በጣም እንደተቃረቡ ሆኖ ሊሰማቸው ይችላል። ሆኖም ጥረቶቻቸው እየተሳኩ እንዳሉ ሆኖ ሲሰማቸው ሁኔታው የተገላቢጦሽ ይሆናል፤ ምክንያቱም ይህ ሁኔታ አምላክ ያለንበትን ሥርዓት የሚያጠፋበት ጊዜ በጣም እንደተቃረበ የሚያሳይ የመጨረሻው ምልክት ነው። የፖለቲካ ድርድሮችና ስምምነቶች በሰዎች ላይ ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ለውጥ እንዳላመጡ አትዘንጋ። ሰዎች እርስ በርሳቸው እንዲፋቀሩ አላደረጉም። የዓለም መሪዎችም ወንጀልን ማቆምም ሆነ በሽታንና ሞትን ማስወገድ አልቻሉም። ስለዚህ የሰው ልጆች ሰላምና ደህንነት ለማምጣት በሚያደርጉት ማንኛውም ጥረት አትታመን፤ በተጨማሪም ይህ ዓለም ያሉበትን ችግሮች መፍታት የሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል ብለህ አታስብ። (መዝሙር 146:3) ስለ ሰላምና ደህንነት የሚሰማው ጩኸት ይህ ዓለም የሚጠፋበት ጊዜ እንደተቃረበ የሚያመለክት ነው።

የምሥራች ስብከት

19, 20. በአሁኑ ጊዜ እየተፈጸመ ያለው በመጨረሻዎቹ ቀናት የሚካሄደውን የስብከት ሥራ አስመልክቶ የተተነበየው የትኛው ትንቢት ነው?

19 ከ1914 ጀምሮ በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ እየኖርን እንዳለን የሚያሳየው ሌላው ትንቢት ኢየሱስ “አስቀድሞም ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ይሰበክ ዘንድ ይገባል” ሲል የተናገረው ነው። (ማርቆስ 13:10) ይህንን ማቴዎስ 24:14 እንዲህ ሲል ገልጾታል:- “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።”

20 በዛሬው ጊዜ በታሪክ ዘመናት ሁሉ ታይቶ በማያውቅ ሁኔታ ስለዚህ ዓለም መጨረሻና በአምላክ መንግሥት ስለምትተዳደረው ስለ መጪዋ የአ​ዲስ ዓለም ገነት የሚገልጸው ምሥራች በምድር ዙሪያ በመሰበክ ላይ ነው። ይህን የምሥራች እየሰበኩ ያሉት እነማን ናቸው? በሚልዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። በምድር ላይ በሚገኝ በየትኛውም አገር በመስበክ ላይ ናቸው።

21, 22. የይሖዋ ምሥክሮች እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆናቸውን ለይቶ የሚያሳውቀው በተለይ ምንድን ነው?

21 የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አምላክ መንግሥት ከሚያካሄዱት የስብከት ሥራ በተጨማሪ የክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች እንደሆኑ ለይቶ የሚያሳውቅ ምግባር ያሳያሉ፤ ምክንያቱም ክርስቶስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል። ስለዚህ የይሖዋ ምሥክሮች አንድ ዓለም አቀፋዊ የወንድማማች ማኅበር በመሆን በማይበጠስ የፍቅር ማሰሪያ ተሳስረዋል።​—ዮሐንስ 13:35፤ በተጨማሪም ኢሳይያስ 2:2-4ን፤ ቆላስይስ 3:14ን፤ ዮሐንስ 15:12-14ን፤ 1 ዮሐንስ 3:10-12ን፤ 4:20, 21ንና ራእይ 7:9, 10ን ተመልከት።

22 የይሖዋ ምሥክሮች የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ አባባል ያምናሉ:- “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ [ነው]።” (ሥራ 10:34, 35) በሁሉም አገሮች የሚገኙትን መሰሎቻቸው የሆኑትን ምሥክሮች ምንም ዓይነት ዘርና ቀለም ቢኖራቸው እንደ መንፈሳዊ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው አድርገው ይመለከቷቸዋል። (ማቴዎስ 23:8) በዛሬው ጊዜ ባለው ዓለም ውስጥ እንዲህ ዓይነት ዓለም አቀፋዊ ወንድማማችነት መኖሩ የአምላክ ዓላማ በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንደሚፈጸም የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ነው።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአዲሱ ዓለም የሰው ልጆችን የሚገዛው ፍጹሙ የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ብቻ ነው