በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም ኑር

ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም ኑር

ክፍል 8

ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም ኑር

1, 2. በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ምን ዓይነት ሕይወት ይኖራል?

1 አምላክ ክፋትንና መከራን ከምድር ላይ አስወግዶ በሰማያዊ መንግሥቱ ፍቅራዊ አመራር የሚተዳደረውን አዲሱን ዓለም ሲያመጣ ሕይወት ምን መልክ ይኖረው ይሆን? አምላክ ‘እጁን እንደሚከፍትና ሕይወት ላለው ሁሉ መልካምን እንደሚያጠግብ’ ቃል ገብቷል።​—መዝሙር 145:16

2 የአንተ ምኞት ምንድን ነው? አስደሳች የሆነ ሕይወት፣ ዋጋማ ሥራ፣ የተትረፈረፈ ቁሳዊ ሀብትና ውብ ሠፈር ማግኘትና በሁሉም ሰዎች መካከል ሰላም ሰፍኖ ማየት እንዲሁም ከግፍ፣ ከበሽታ፣ ከመከራና ከሞት ነፃ መውጣት አይደለምን? አስደሳች የሆነ መንፈሳዊ ተስፋ ማግኘትስ አትፈልግምን? እነዚህ ነገሮች ሁሉ በቅርቡ በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ይፈጸማሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በዚያ አዲስ ዓለም ውስጥ ስለሚኖሩት አስደሳች በረከቶች ምን እንደሚሉ ተመልከት።

የሰው ልጆች ፍጹም የሆነ ሰላም ያገኛሉ

3-6. ሰዎች በአዲሱ ዓለም ውስጥ ሰላም እንደሚያገኙ ምን ማረጋገጫ አለን?

3 “[አምላክ] እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ጦርነትን ይሽራል፤ ቀስትን ይሰብራል፣ ጦርንም ይቆርጣል፣ በእሳትም ጋሻን ያቃጥላል።”​—መዝሙር 46:9

4 “ሰይፋቸውንም ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፣ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም።”​—ኢሳይያስ 2:4

5 “ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።”​—መዝሙር 37:11

6 “ምድርም ሁሉ ዐርፋ በጸጥታ ተቀምጣለች እልልም ብላለች።”​—ኢሳይያስ 14:7

በሰውና በእንስሳት መካከል ሰላም ይኖራል

7, 8. በሰዎችና በእንስሳት መካከል ምን ዓይነት ሰላም ይኖራል?

7 “ተኩላ ከበግ ጠቦት ጋር ይቀመጣል፣ ነብርም ከፍየል ጠቦት ጋር ይተኛል፤ ጥጃና የአንበሳ ደቦል ፍሪዳም በአንድነት ያርፋሉ፤ ታናሽም ልጅ ይመራቸዋል። ላምና ድብ አብረው ይሰማራሉ፣ ግልገሎቻቸውም በአንድነት ያርፋሉ፤ አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል። የሚጠባውም ሕፃን በእባብ ጉድጓድ ላይ ይጫወታል፣ ጡት የጣለውም ሕፃን በእፉኝት ቤት ላይ እጁን ይጭናል። . . . አይጐዱም አያጠፉምም።”​—ኢሳይያስ 11:6-9

8 “በዚያም ቀን ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች ከመሬትም ተንቀሳቃሾች ጋር ቃል ኪዳን አደርግላቸዋለሁ፤ . . . ተከልለውም እንዲኖሩ አስተኛቸዋለሁ።”​—ሆሴዕ 2:20

ፍጹም ጤናና የዘላለም ሕይወት

9-14. በአዲሱ ዓለም ውስጥ የሚኖረውን የጤንነት ሁኔታ ግለጽ።

9 “በዚያን ጊዜም የዕውሮች ዓይን ይገለጣል የደንቆሮዎችም ጆሮ ይከፈታል። በዚያን ጊዜ አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘልላል፣ የድዳም ምላስ ይዘምራል።”​—ኢሳይያስ 35:5, 6

10 “[አምላክ] እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም።”​—ራእይ 21:4

11 “በዚያም የሚቀመጥ:- ታምሜአለሁ አይልም።”​—ኢሳይያስ 33:24

12 “ሥጋው እንደ ሕፃን ሥጋ ይለመልማል፤ ወደ ጉብዝናውም ዘመን ይመለሳል።”​—ኢዮብ 33:25

13 “የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው።”​—ሮሜ 6:23

14 “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት [ያገኛል]።”​—ዮሐንስ 3:16

ሙታን እንደገና ሕያው ይሆናሉ

15-17. ሙታን ምን ተስፋ አላቸው?

15 “ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን [ይነሳሉ]።”​—ሥራ 24:15

16 “በመታሰቢያ መቃብር [በአምላክ አእምሮ] ውስጥ ያሉት ሁሉ ድምፁን ሰምተው የሚወጡበት ሰዓት ይመጣል።”​—ዮሐንስ 5:28, 29 NW

17 “ባሕርም በእርሱ ውስጥ ያሉትን ሙታን ሰጠ፣ ሞትና ሲኦልም [መቃብር] በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ።”​—ራእይ 20:13

ምድር የተትረፈረፈ ምርት የሞላባት ገነት ትሆናለች

18-22. መላዋ ምድር ወደ ምን ትለወጣለች?

18 “በቂ ዝናም በመስጠት እባርካቸዋለሁ፤ ዛፎች ያፈራሉ፤ እርሻዎች በቂ የእህል ምርት ይሰጣሉ፤ እያንዳንዱም በገዛ ራሱ ምድር በሰላም ይኖራል።”​—ሕዝቅኤል 34:26, 27 የ1980 ትርጉም

19 “በዚያን ጊዜ ምድር ብዙ ፍሬ ትሰጣለች፤ እግዚአብሔር አምላካችን ይባርከናል።”​—መዝሙር 67:6 የ1980 ትርጉም

20 “ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፣ በረሀውም ሐሤት ያደርጋል እንደ ጽጌ ረዳም ያብባል።”​—ኢሳይያስ 35:1

21 “ተራሮችና ኮረብቶች በፊታችሁ እልልታ ያደርጋሉ፣ የሜዳም ዛፎች ሁሉ ያጨበጭባሉ። በእሾህም ፋንታ ጥድ በኩርንችትም ፋንታ ባርሰነት ይበቅላል።”​—ኢሳይያስ 55:12, 13

22 “ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ።”​—ሉቃስ 23:43

ሁሉም ሰው ጥሩ ቤት ይኖረዋል

23, 24. ሁሉም ሰው ጥሩ መኖሪያ እንደሚያገኝ ምን ማረጋገጫ አለን?

23 “ቤቶችንም ይሠራሉ ይቀመጡባቸውማል፤ . . . ሌላ እንዲቀመጥበት አይሠሩም፣ ሌላም እንዲበላው አይተክሉም፤ . . . እኔም የመረጥኋቸው በእጃቸው ሥራ ረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋልና። . . . በከንቱ አይደክሙም ለጥፋትም አይወልዱም።”​—ኢሳይያስ 65:21-23

24 “ሰው እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፣ የሚያስፈራውም የለም።”​—ሚክያስ 4:4

በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ

25. የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ምን ግሩም ተስፋ አለን?

25 እንዴት ያለ ግሩም ተስፋ ነው! በዛሬው ጊዜ ያሉት ችግሮች በሙሉ አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ጊዜ ያለፈባቸው ነገሮች ሆነው እንደሚቀሩ በሚገልጸው ጠንካራ ተስፋ ላይ መልሕቅ በመጣል በአሁኑ ጊዜ እውነተኛ ዓላማ ያለው ሕይወት መኖር ይቻላል! “የቀደሙትም አይታሰቡም፣ ወደ ልብም አይገቡም።” (ኢሳይያስ 65:17) በዚያን ጊዜ ሕይወት ዘላለማዊ እንደሚሆን ማወቁ ምንኛ የሚያጽናና ነው:- “[አምላክ] ሞትን ለዘላለም ይውጣል።”​—ኢሳይያስ 25:8

26. አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም ለመኖር ቁልፉ ምንድን ነው?

26 በጣም በቀረበው በዚያ ገነታዊ አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም መኖር ትፈልጋለህን? ‘በዚህ ዓለም መጨረሻ ላይ የአምላክን ሞገስ እንዳገኝና እርሱ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ መኖር እንድችል ምን ማድረግ ያስፈልገኛል?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ኢየሱስ ለአምላክ ባቀረበው ጸሎት ላይ የጠቀሰውን ነገር ማድረግ ይኖርብሃል:- “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።”​—ዮሐንስ 17:3

27. በአምላክ ዓላማ ውስጥ ለመካፈል ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

27 ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ፈልግና በዚህ ብሮሹር ውስጥ ያነበብከው ነገር እውነት መሆኑን አረጋግጥ። እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች የሚያጠኑና የሚያስተምሩ ሰዎችን ፈልግ። መጽሐፍ ቅዱስን የሚቃረኑ ነገሮችን ከሚያስተምሩና ከሚያደርጉ ግብዝ ሃይማኖቶች ራቅ። የአምላክን ፈቃድ እያደረጉ ካሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ጋር አምላክ የሰው ልጆች ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ ለማድረግ ባለው ዓላማ ውስጥ እንዴት ተካፋይ መሆን እንደምትችል ተማር። በተጨማሪም በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ቃል በቅርቡ ስለሚፈጸመው ነገር የሚሰጠውን የሚከተለውን ሐሳብ ልብ በል:- “ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚ​ያደ⁠ርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።”​—1 ዮሐንስ 2:17

[የግርጌ ማስታወሻ]

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ ምድራዊውን ገነት እንደገና ለመመለስ ያለው ዓላማ በቅርቡ ይፈጸማል