ክፍል 11
በመንፈስ መሪነት የተጻፉ አጽናኝና ትምህርት አዘል መዝሙሮች
ዳዊትና ሌሎች፣ በይሖዋ አምልኮ የሚጠቀሙባቸውን መዝሙሮች አቀናብረዋል። ከእነዚህ መካከል የ150ዎቹ ግጥሞች በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ ይገኛሉ
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካሉት መጻሕፍት ሁሉ ትልቁ፣ ቅዱስ መዝሙሮችን የያዘው መጽሐፍ ነው። ይህ መጽሐፍ ተጽፎ ለማለቅ 1,000 የሚያህሉ ዓመታት ፈጅቶበታል። እነዚህን መዝሙሮች ያቀናበሩት ሰዎች እምነታቸውን የገለጹበት መንገድ እስከ ዛሬ በጽሑፍ ከሰፈሩት ሐሳቦች ሁሉ ይልቅ ጥልቅና ስሜት የሚነካ ነው። በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ እንደ ደስታ፣ ውዳሴና ምስጋና ወይም እንደ ሐዘንና ጸጸት ያሉ በጣም የተለያዩ ሰብዓዊ ስሜቶች ተገልጸዋል። መዝሙሮቹን ያቀናበሩት ሰዎች በአምላክ እንደሚተማመኑና ከእሱ ጋር የቅርብ ዝምድና እንዳላቸው በግልጽ ይታያል። እነዚህ መዝሙሮች ከሚያስተላልፏቸው መልእክቶች መካከል እስቲ አንዳንዶቹን እንመልከት።
ይሖዋ የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥ የመሆን መብት አለው፤ እንዲሁም ሊመለክና ሊወደስ ይገባዋል። መዝሙር 83:18 [NW] “ሰዎች ሁሉ ስምህ ይሖዋ የሆነው አንተ፣ በምድር ሁሉ ላይ አንተ ብቻ ልዑል እንደሆንክ [ይወቁ]” ይላል። በርካታ መዝሙሮች በከዋክብት ስለተሞሉት ሰማያት፣ በምድር ላይ ስላለው አስደናቂ ሕይወትና ግሩም ስለሆነው የሰው አካል እንዲሁም እነዚህን ስለመሳሰሉት የይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች በማንሳት አምላክን ያወድሱታል። (መዝሙር 8, 19, 139 እና 148) አንዳንዶቹ መዝሙሮች ደግሞ ይሖዋ ለእሱ ታማኝ የሆኑትን ሰዎች ለማዳንና ከጥቃት ለመጠበቅ ሲል እርምጃ የሚወስድ አምላክ እንደሆነ በመጥቀስ ያሞግሱታል። (መዝሙር 18, 97 እና 138) ሌሎቹ መዝሙሮች ይሖዋ ለተጨቆኑት እፎይታ የሚሰጥና በክፉዎች ላይ ቅጣትን የሚያመጣ የፍትሕ አምላክ እንደሆነ በመግለጽ ከፍ ከፍ ያደርጉታል።—መዝሙር 11, 68 እና 146
ይሖዋ ለሚወዱት እርዳታና መጽናናት ይሰጣል። ዳዊት በጎቹን እንደሚመራ፣ ጥበቃ እንደሚያደርግላቸውና እንደሚንከባከባቸው አፍቃሪ እረኛ አድርጎ ይሖዋን የገለጸበት 23ኛው መዝሙር ከሌሎች መዝሙሮች ሁሉ ይልቅ ታዋቂ ሳይሆን አይቀርም። መዝሙር 65:2 ይሖዋ ‘ጸሎትን የሚሰማ’ አምላክ መሆኑን ለይሖዋ አምላኪዎች ያስታውሳቸዋል። ከባድ ኃጢአት የፈጸሙ ብዙ ሰዎች፣ ዳዊት በፈጸመው ከባድ ኃጢአት ከልቡ መጸጸቱንና ይሖዋ ምሕረት እንደሚያደርግለት ያለውን እምነት የገለጸባቸውን መዝሙር 39ን እና 51ን ማንበባቸው በጣም አጽናንቷቸዋል። መዝሙር 55:22 በይሖዋ እንድንተማመንና ሸክማችንን በሙሉ በእሱ ላይ እንድንጥል ያበረታታናል።
ይሖዋ፣ መሲሑ በሚያስተዳድረው መንግሥት አማካኝነት ዓለምን ይለውጣል። በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ የሰፈሩ በርካታ ሐሳቦች ከመሲሑ ማለትም አስቀድሞ ከተነገረለት ንጉሥ ጋር በቀጥታ የተያያዙ ናቸው። መዝሙር 2 ይህ ንጉሥ የሚቃወሙትን ክፉ መንግሥታት እንደሚያጠፋ ተንብዮአል። መዝሙር 72 ይህ ንጉሥ፣ ረሃብንና የፍትሕ መዛባትን እንዲሁም ጭቆናን እንደሚያስቀር ይገልጻል። መዝሙር 46:9 መሲሑ በሚገዛበት መንግሥት አማካኝነት አምላክ ጦርነትን እንደሚያስወግድና ሌላው ቀርቶ የጦር መሣሪያዎችን በሙሉ እንደሚያጠፋ ይናገራል። በመዝሙር 37 ላይ ክፉዎች እንደሚወገዱና ጻድቃን ግን ዓለም አቀፍ ሰላምና ስምምነት በሠፈነበት ሁኔታ በምድር ላይ ለዘላለም እንደሚኖሩ እናነባለን።
—በመዝሙር መጽሐፍ ላይ የተመሠረተ።