ክፍል 4
አምላክ ከአብርሃም ጋር ቃል ኪዳን ገባ
አብርሃም አምላክን በእምነት በመታዘዙ ይሖዋ እንደሚባርከውና ዘሩንም እንደሚያበዛለት ቃል ገባለት
በኖኅ ዘመን ከመጣው የጥፋት ውኃ በኋላ ወደ 350 የሚጠጉ ዓመታት አለፉ። የቤተሰብ ራስ የነበረው አብርሃም፣ ዑር (በዛሬዋ ኢራቅ ውስጥ ትገኛለች) በምትባል የበለጸገች ከተማ ውስጥ ይኖር ነበር። አብርሃም ታላቅ እምነት ያለው ሰው ነበር። ይሁን እንጂ እምነቱን የሚፈትን ነገር አጋጠመው።
ይሖዋ፣ አብርሃም የተወለደበትን አገር ትቶ ከነዓን ወደሚባል ባዕድ አገር እንዲሄድ ነገረው። አብርሃምም ያለማወላወል ታዘዘ። ሚስቱን ሣራንና የወንድሙን ልጅ ሎጥን ጨምሮ ቤተሰቡን በመያዝ ረጅም ጉዞ ካደረገ በኋላ በከነዓን ምድር በድንኳን ውስጥ መኖር ጀመረ። ይሖዋ አብርሃምን ታላቅ ሕዝብ እንደሚያደርገው፣ የምድር ሕዝቦች በሙሉ በእሱ አማካኝነት እንደሚባረኩ እንዲሁም ዘሩ የከነዓንን ምድር እንደሚወርስ በመግለጽ ከእሱ ጋር ቃል ኪዳን ገባ።
አብርሃምና ሎጥ ብዙ የበጎችና የከብቶች መንጋ ያላቸው ባለጸጎች ሆኑ። ራስ ወዳድ ያልሆነው አብርሃም፣ የሚፈልገውን አካባቢ እንዲመርጥ ለሎጥ ፈቀደለት። ሎጥ በዮርዳኖስ ወንዝ አካባቢ ያለውን ለምለም ቦታ በመምረጥ በሰዶም ከተማ አቅራቢያ ሰፈረ። የሰዶም ሰዎች ግን መጥፎ ሥነ ምግባር ያላቸውና በይሖዋ ፊት እጅግ ኃጢአተኞች ነበሩ።
ይሖዋ አምላክ፣ የአብርሃም ዘሮች እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደሚበዙ ለአብርሃም አረጋገጠለት። አብርሃምም ይሖዋ በሰጠው በዚህ ተስፋ አመነ። ሆኖም የሚወዳት ሚስቱ ሣራ መካን ነበረች። አብርሃም 99 ዓመት ሲሆነው ሣራ ደግሞ 90 ዓመት ሊሞላት ሲቃረብ አምላክ ወንድ ልጅ እንደሚወልዱ ለአብርሃም ነገረው። አምላክ እንደተናገረውም ሣራ ይስሐቅን ወለደች። አብርሃም ሌሎች ልጆች የነበሩት ቢሆንም በኤደን ተስፋ የተሰጠበት አዳኝ የሚመጣው በይስሐቅ በኩል ነበር።
በዚህ ጊዜ ሎጥና ቤተሰቡ የሚኖሩት በሰዶም ነበር፤ ያም ቢሆን ጻድቁ ሎጥ በከተማዋ የነበሩትን መጥፎ ሥነ ምግባር ያላቸው ሰዎች አልተከተለም። ይሖዋ ሰዶምን ለማጥፋት በወሰነ ጊዜ ስለሚመጣው ጥፋት ሎጥን እንዲያስጠነቅቁት መላእክትን ላከ። መላእክቱ፣ ሎጥንና ቤተሰቡን ከሰዶም እንዲሸሹና ወደኋላቸው እንዳይመለከቱ አሳስበዋቸው ነበር። ከዚያም አምላክ በሰዶምና በአቅራቢያዋ በምትገኘው ገሞራ የተባለች ክፉዎች የሞሉባት ከተማ ላይ እሳትና ዲን በማዝነብ ነዋሪዎቹን በሙሉ አጠፋቸው። ሎጥና ሁለቱ ሴት ልጆቹ ከጥፋቱ ዳኑ። የሎጥ ሚስት ግን ትታው ስለመጣችው ነገር በማሰብ ሳይሆን አይቀርም ወደኋላ ዞራ ተመለከተች። ባለመታዘዟም ሕይወቷን አጣች።
—በዘፍጥረት 11:10 እስከ 19:38 ላይ የተመሠረተ።