በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 116

ለዘላለም መኖር የምንችለው እንዴት ነው?

ለዘላለም መኖር የምንችለው እንዴት ነው?

ትንሿ ልጅና ጓደኞቿ ምን እያነበቡ እንዳሉ ታውቃለህ? አዎ፣ አንተ እያነበብከው ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተባለውን ይህንኑ መጽሐፍ እያነበቡ ነው። እያነበቡት ያሉት ታሪክ ደግሞ “ለዘላለም መኖር የምንችለው እንዴት ነው?” የሚል ርዕስ ያለውን አሁን አንተ እያነበብከው ያለኸውን ታሪክ ነው።

ምን እየተማሩ እንዳሉ ታውቃለህ? ለዘላለም መኖር እንድንችል በመጀመሪያ ደረጃ ስለ ይሖዋና ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ ማወቅ አለብን። መጽሐፍ ቅዱስ ‘የዘላለም ሕይወት ለማግኘት እውነተኛውን አምላክና ወደ ምድር የላከውን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ ያስፈልጋል’ ይላል።

ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተባለውን መጽሐፍ ከዳር እስከ ዳር በማንበብ ነው። ይህ መጽሐፍ ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ ብዙ ነገር ይገልጻል፤ አይገልጽም እንዴ? በተጨማሪም ይሖዋና ኢየሱስ ስላደረጓቸውና ወደፊት ስለሚያደርጓቸው ነገሮችም በስፋት ይገልጻል። ሆኖም ይህን መጽሐፍ ማንበብ ብቻ ሳይሆን ሌላም ልናደርገው የሚገባ ነገር አለ።

ወለሉ ላይ የተቀመጠውን መጽሐፍ አየኸው? መጽሐፍ ቅዱስ ነው። አንድ ሰው በዚህ መጽሐፍ ላይ ያሉት ታሪኮች የተመሠረቱባቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እንዲያነብልህ አድርግ። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን በትክክለኛው መንገድ እንድናገለግለውና የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ የሚያስችለንን የተሟላ እውቀት ይሰጠናል። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ብዙ ጊዜ የማጥናት ልማድ ሊኖረን ይገባል።

ሆኖም ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማወቅ ብቻ በቂ አይደለም። ስለ እነርሱና ስለ ትምህርቶቻቸው በጣም ብዙ እውቀት ቢኖረንም እንኳ የዘላለም ሕይወት ላናገኝ እንችላለን። ከዚህ ሌላ ምን ነገር እንደሚያስፈልግ ታውቃለህ?

ከተማርናቸው ነገሮች ጋር ተስማምተን መኖርም አለብን። አስቆሮቱ ይሁዳን ታስታውሰዋለህ? ኢየሱስ ሐዋርያቱ እንዲሆኑ ከመረጣቸው 12 ሰዎች አንዱ ነበር። ይሁዳ ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ ብዙ እውቀት ነበረው። ይሁን እንጂ ምን ደረሰበት? ከጊዜ በኋላ ራስ ወዳድ ሆነና ኢየሱስን በ30 ብር ለጠላቶቹ አሳልፎ ሰጠው። ስለዚህ ይሁዳ የዘላለም ሕይወት አያገኝም።

ግያዝ የተባለውን በ69ኛው ታሪክ ላይ የተገለጸውን ሰው ታስታውሰዋለህ? የእሱ ያልሆነውን ልብስና ገንዘብ ለመውሰድ ፈለገ። ስለዚህ እነዚህን ነገሮች ለማግኘት ሲል ዋሸ። ሆኖም ይሖዋ ቀጥቶታል። እኛም ሕጎቹን የማናከብር ከሆነ ይቀጣናል።

ይሁን እንጂ ይሖዋን ዘወትር በታማኝነት ያገለገሉ ብዙ ጥሩ ሰዎች አሉ። እኛ እንደ እነሱ መሆን እንፈልጋለን፤ አንፈልግም እንዴ? ትንሽ ልጅ የነበረው ሳሙኤል ልንከተለው የሚገባ ጥሩ ምሳሌ ነው። በ55ኛው ታሪክ ላይ እንዳየነው ሳሙኤል ይሖዋን በማደሪያው ድንኳን ማገልገል ሲጀምር ገና አራት ወይም አምስት ዓመቱ እንደነበረ አስታውስ። ስለዚህ ምንም ያህል ትንሽ ብትሆን ይሖዋን ለማገልገል አታንስም።

እርግጥ ሁላችንም ልንከተለው የሚገባን ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። በ87ኛው ታሪክ ላይ እንደተገለጸው ገና ልጅ ሳለ በቤተ መቅደስ ተቀምጦ ለሌሎች ስለ ሰማያዊ አባቱ ይናገር ነበር። እኛም የእሱን ምሳሌ እንከተል። ስለ ታላቁ አምላካችን ስለ ይሖዋና ስለ ልጁ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የቻልነውን ያህል ለብዙ ሰዎች እንናገር። እነዚህን ነገሮች ካደረግን አምላክ በምድር ላይ በሚያቋቁማት አዲስ ገነት ውስጥ ለዘላለም መኖር እንችላለን።