በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 107

እስጢፋኖስ በድንጋይ ተወገረ

እስጢፋኖስ በድንጋይ ተወገረ

ተንበርክኮ የሚታየው ይህ ሰው እስጢፋኖስ ነው። የኢየሱስ ታማኝ ደቀ መዝሙር ነው። ይሁን እንጂ አሁን ምን እየተፈጸመበት እንዳለ ተመልከት! እነዚህ ሰዎች ትልልቅ ድንጋይ እየወረወሩበት ነው። እንዲህ ያለ የጭካኔ ድርጊት እስኪፈጽሙበት ድረስ እስጢፋኖስን በጣም የጠሉት ለምንድን ነው? እስቲ እንመልከት።

አምላክ እስጢፋኖስ አስደናቂ ተአምራት እንዲፈጽም አድርጎት ነበር። እነዚህ ሰዎች እንዲህ ማድረጉን አልወደዱትም፤ ስለዚህ ለሕዝቡ እውነትን በማስተማሩ ይከራከሩት ጀመር። ሆኖም አምላክ ለእስጢፋኖስ ታላቅ ጥበብ ሰጠው። እነዚህ ሰዎች የሚያስተምሩት ትምህርት ሐሰት መሆኑን ገለጸ። ይህ ከበፊቱ ይበልጥ አናደዳቸው። ስለዚህ ያዙትና ሰዎች በእሱ ላይ በሐሰት እንዲመሰክሩ አደረጉ።

ሊቀ ካህናቱ እስጢፋኖስን ‘ይህ ነገር እውነት ነውን?’ ሲል ጠየቀው። እስጢፋኖስ ከመጽሐፍ ቅዱስ እየጠቀሰ ጥሩ ንግግር በመስጠት መለሰ። በንግግሩ መጨረሻ ላይ ከብዙ ዘመናት በፊት ክፉ ሰዎች የአምላክን ነቢያት እንዴት ይጠሉ እንደነበረ ገለጸ። ከዚያም ‘እናንተ ልክ እንደነዚህ ሰዎች ናችሁ። የአምላክን አገልጋይ ኢየሱስን ገድላችኋል፤ የአምላክን ሕጎች አላከበራችሁም’ አላቸው።

ይህ እነዚህን የሃይማኖት መሪዎች በጣም አናደዳቸው! በንዴት ጥርሳቸውን አፋጩበት። ይሁን እንጂ እስጢፋኖስ ወደ ላይ ቀና አለና ‘እነሆ፣ ኢየሱስ በሰማይ በአምላክ ቀኝ ቆሞ አያለሁ’ አለ። በዚህ ጊዜ እነዚህ ሰዎች ጆሮዎቻቸውን በእጆቻቸው ደፍነው ወደ እስጢፋኖስ ሮጡ። ያዙትና እየጎተቱ ከከተማይቱ ውጪ አወጡት።

ከዚያም ከላይ የደረቡትን ልብስ አወለቁና እንዲጠብቅላቸው ሳውል ለተባለ አንድ ወጣት ሰጡት። ሳውልን አየኸው? ከዚያ በኋላ ሰዎቹ እስጢፋኖስን በድንጋይ መምታት ጀመሩ። ሥዕሉ ላይ እንደምታየው እስጢፋኖስ ተንበረከከና ‘ይሖዋ ሆይ፣ ይህን መጥፎ ነገር በመሥራታቸው አትቅጣቸው’ ሲል ወደ አምላክ ጸለየ። አንዳንዶቹ ይህን ያደረጉት በሃይማኖት መሪዎቹ ተታልለው እንደሆነ ያውቅ ነበር። ከዚያ በኋላ እስጢፋኖስ ሞተ።

ሰዎች አንድ መጥፎ ነገር ሲፈጽሙብህ እነርሱን መልሰህ ለመጉዳት ትሞክራለህ? ወይም ደግሞ አምላክ እንዲቀጣቸው ትለምነዋለህ? እስጢፋኖስና ኢየሱስ እንዲህ አላደረጉም። የጭካኔ ድርጊት ለፈጸሙባቸው ሰዎች እንኳ ያስቡ ነበር። የእነርሱን ምሳሌ ለመኮረጅ እንጣር።