በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 111

ያንቀላፋው ልጅ

ያንቀላፋው ልጅ

ኧረ! ምን ሆነው ነው? መሬት ላይ የወደቀው ልጅ በጣም ተጎድቶ ይሆን? ተመልከት! ከቤቱ ውስጥ እየወጡ ካሉት ሰዎች መካከል አንዱ ጳውሎስ ነው! ጢሞቴዎስንም አየኸው? ልጁ የወደቀው ከመስኮቱ ላይ ነው?

አዎ፣ ከመስኮቱ ላይ ወድቆ ነው። ጳውሎስ በዚህ በጢሮአዳ ውስጥ ለሚገኙ ደቀ መዛሙርት ንግግር እየሰጠ ነበር። በሚቀጥለው ቀን ከተማይቱን ለቆ በጀልባ ስለሚሄድ ከዚህ በኋላ ለረጅም ጊዜ እንደማያያቸው ያውቅ ነበር። ስለዚህ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ንግግሩን እየሰጠ ነበር።

ይህ አውጤኪስ የሚባለው ልጅ መስኮቱ ላይ ተቀምጦ እንቅልፍ ወስዶት ነበር። ሦስተኛ ፎቅ ላይ ካለው መስኮት ወደ መሬት ወደቀ! ስለዚህ ሰዎቹ በጣም የተጨነቁት ለምን እንደሆነ መረዳት ትችላለህ። ሰዎቹ ልጁን ሲያነሱት የፈሩት ነገር ደርሶ ነበር። ሞቶ ነበር!

ጳውሎስ ልጁ መሞቱን ሲያይ ላዩ ላይ ተኝቶ አቀፈው። ከዚያም ‘አይዟችሁ። ደህና ነው!’ አላቸው። እውነትም እንዳለው ሆነ! ተአምር ነበር! ጳውሎስ እንደገና ሕያው አደረገው! ሰዎቹ በአንድ ጊዜ ደስታ በደስታ ሆኑ።

ሁሉም እንደገና ወደ ላይኛው ፎቅ ወጡና እራት በሉ። ጳውሎስ እስኪነጋ ድረስ ንግግሩን ቀጠለ። መቼም አውጤኪስ እንደገና እንደማይተኛ የታወቀ ነው! ከዚያም ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስና አብረዋቸው የሚጓዙት ሰዎች በጀልባ ተሳፈሩ። ወዴት እንደሚሄዱ ታውቃለህ?

ጳውሎስ ሦስተኛውን የስብከት ጉዞውን አጠናቆ ወደ አገሩ እየተመለሰ ነው። ጳውሎስ በዚህኛው ጉዞው በኤፌሶን ከተማ ብቻ ሦስት ዓመታት ቆይቷል። ስለዚህ ይኼኛው ጉዞ ከሁለተኛውም ጉዞ የበለጠ ጊዜ የወሰደ ነበር።

ከጢሮአዳ ከወጡ በኋላ ጀልባዋ በሚሊጢን ለጥቂት ጊዜ ቆመች። ኤፌሶን ከዚህ ብዙም ስለማትርቅ ጳውሎስ ለመጨረሻ ጊዜ ሊያነጋግራቸው እንዲችል በጉባኤው ውስጥ ያሉትን ሽማግሌዎች ወደ ሚሊጢን እንዲመጡ ሰው ላከባቸው። በኋላ ጀልባዋ የምትሄድበት ሰዓት ደርሶ ጳውሎስ ተሰናብቷቸው ሲሄድ ምንኛ አዝነው ይሆን!

በመጨረሻ ጀልባዋ ወደ ቂሣርያ ተመለሰች። ጳውሎስ በዚህች ከተማ በደቀ መዝሙሩ ፊልጶስ ቤት ተቀምጦ ሳለ ነቢዩ አጋቦስ አስጠነቀቀው። ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ እንደሚታሰር ተናገረ። በእርግጥም የተፈጸመው ነገር ይኸው ነበር። ከዚያም ጳውሎስ በቂሣርያ ሁለት ዓመት ታስሮ ከቆየ በኋላ በሮማ ገዥ በቄሣር ፊት ለፍርድ እንዲቀርብ ወደ ሮም ተላከ። ወደ ሮም ሲጓዝ ምን ነገር እንዳጋጠመው እስቲ እንመልከት።