በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 113

ጳውሎስ በሮም

ጳውሎስ በሮም

ጳውሎስ የታሰረበትን ሰንሰለትና እሱን እየጠበቀ ያለውን የሮማ ወታደር ተመልከት። ጳውሎስ በሮም ታስሯል። የሮማ ቄሣር የሚሰጠውን ፍርድ እየተጠባበቀ ነው። እስረኛ ሆኖ ሳለ ሰዎች እንዲጠይቁት ተፈቅዶላቸው ነበር።

ጳውሎስ ወደ ሮም ከተወሰደ ከሦስት ቀናት በኋላ የአይሁድ መሪዎች መጥተው እንዲያነጋግሩት መልእክት ላከባቸው። በዚህም ምክንያት በሮም የሚኖሩ ብዙ አይሁዶች መጡ። ጳውሎስ ስለ ኢየሱስና ስለ አምላክ መንግሥት ሰበከላቸው። አንዳንዶቹ አመኑና ክርስቲያኖች ሆኑ፤ ሌሎቹ ግን አላመኑም።

በተጨማሪም ጳውሎስ እሱን የመጠበቅ ሥራ ለነበራቸው የተለያዩ ወታደሮች ሰብኳል። ጳውሎስ በዚህ ቦታ ለሁለት ዓመታት ታስሮ ሲቆይ ላገኘው ሰው ሁሉ ይሰብክ ነበር። በዚህም ምክንያት ሌላው ቀርቶ የቄሣር ቤተሰቦች እንኳን የመንግሥቱን ምሥራች ሰምተው አንዳንዶቹ ክርስቲያኖች ሆነዋል።

ጳውሎስን ለመጠየቅ የመጣውና ጠረጴዛው ላይ አስደግፎ እየጻፈ ያለው ማን ነው? እስቲ ገምት? አዎ፣ ጢሞቴዎስ ነው። ጢሞቴዎስም ስለ አምላክ መንግሥት በመስበኩ ታስሮ ነበር፤ ሆኖም በኋላ ተለቋል። እዚህ የመጣው ጳውሎስን ለመርዳት ነው። ጢሞቴዎስ ምን እየጻፈ እንዳለ ታውቃለህ? እስቲ እንመልከት።

በ110ኛው ታሪክ ላይ የተገለጹትን ፊልጵስዩስ እና ኤፌሶን የተባሉ ከተሞች ታስታውሳለህ? ጳውሎስ በእነዚህ ከተሞች የክርስቲያን ጉባኤዎች እንዲቋቋሙ አስተዋጽኦ አድርጓል። አሁን በእስር ላይ እያለ ጳውሎስ ለእነዚህ ክርስቲያኖች ደብዳቤዎች ጻፈላቸው። ደብዳቤዎቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ኤፌሶንና ፊልጵስዩስ ተብለው ይጠራሉ። ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ለሚገኙ ክርስቲያን ጓደኞቻቸው ምን ብሎ እንደሚጽፍ ለጢሞቴዎስ እየነገረው ነው።

በፊልጵስዩስ የሚገኙ ክርስቲያኖች ጳውሎስን በጣም ያስቡለት ነበር። እዚህ እስር ቤት እያለ ስጦታ ልከውለታል፤ ስለዚህ ጳውሎስ ለስጦታው እያመሰገናቸው ነው። ስጦታውን ያመጣው አፍሮዲጡ የሚባል ሰው ነው። ሆኖም በጣም ታሞ ሊሞት ደርሶ ነበር። አሁን ተሽሎት ወደ አገሩ ሊመለስ ነው። ወደ ፊልጵስዩስ ሲመለስ ይህን ደብዳቤ ከጳውሎስና ከጢሞቴዎስ ተቀብሎ ይዞ ይሄዳል።

ጳውሎስ በእስር ቤት እያለ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናገኛቸውን ሁለት ተጨማሪ ደብዳቤዎች ጽፏል። አንዱ በቆላስይስ ከተማ ለሚገኙ ክርስቲያኖች የተጻፈ ነው። ይህ ደብዳቤ ምን ተብሎ እንደሚጠራ ታውቃለህ? ቆላስይስ ተብሎ ይጠራል። ሌላው በቆላስይስ ለሚኖረው የቅርብ ጓደኛው ለፊልሞና የተላከ የግል ደብዳቤ ነው። ደብዳቤው የፊልሞና አገልጋይ የሆነውን አናሲሞስን የሚመለከት ነው።

የፊልሞና አገልጋይ የሆነው አናሲሞስ ጠፍቶ ወደ ሮም መጥቶ ነበር። አናሲሞስ ጳውሎስ ሮም ውስጥ መታሰሩን በሆነ መንገድ ሰምቶ ነበር። አናሲሞስ ሊጠይቀው ሲመጣ ጳውሎስ ሰበከለት። ብዙም ሳይቆይ አናሲሞስም ክርስቲያን ሆነ። በዚህ ጊዜ አናሲሞስ ጠፍቶ በመምጣቱ አዘነ። ስለዚህ ጳውሎስ በዚህ ደብዳቤ ለፊልሞና ምን ብሎ እንደጻፈለት ታውቃለህ?

ጳውሎስ፣ ፊልሞና አናሲሞስን ይቅር እንዲለው ለመነው። ‘መልሼ ወደ አንተ ልኬዋለሁ፤ ሆኖም አሁን አገልጋይህ ብቻ ሳይሆን ጥሩ ክርስቲያን ወንድምህም ነው’ ሲል ጻፈለት። አናሲሞስ ወደ ቆላስይስ ሲመለስ እነዚህን ሁለት ደብዳቤዎች አንዱን ለቆላስይስ ክርስቲያኖች ሌላውን ደግሞ ለፊልሞና ይዞ ሄደ። ፊልሞና አገልጋዩ ክርስቲያን እንደሆነ ሲሰማ ምን ያህል እንደሚደሰት መገመት እንችላለን።

ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖችና ለፊልሞና የጻፋቸው ደብዳቤዎች ምሥራች የያዙ ነበሩ። ‘ጢሞቴዎስን እልክላችኋለሁ። እኔም በቅርብ ጊዜ እጎበኛችኋለሁ’ በማለት ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ገልጾላቸዋል። ለፊልሞናም ‘የማርፍበት ቦታ አዘጋጅልኝ’ ሲል ጽፎለታል።

ጳውሎስ ሲፈታ በብዙ ቦታዎች የሚገኙ ክርስቲያን ወንድሞችንና እህቶችን ጎብኝቷል። በኋላ ግን ጳውሎስ እንደገና በሮም ታሰረ። በዚህ ጊዜ እንደሚገደል አውቆ ነበር። ስለዚህ ወደ ጢሞቴዎስ ደብዳቤ ጻፈና በፍጥነት እንዲመጣ ጠየቀው። ጳውሎስ ‘ለአምላክ ታማኝ ሆኛለሁ፤ አምላክም ይሸልመኛል’ ሲል ጽፏል። ጳውሎስ ከተገደለ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ኢየሩሳሌም እንደገና ጠፋች፤ በዚህ ጊዜ የጠፋችው በሮማውያን ነበር።

ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጹ ሌሎች ነገሮችም አሉ። ይሖዋ አምላክ ሐዋርያው ዮሐንስን የራእይ መጽሐፍን ጨምሮ የመጨረሻዎቹን መጻሕፍት እንዲጽፍ አድርጎታል። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የራእይ መጽሐፍ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ይናገራል። ወደፊት ምን ነገሮች እንደሚፈጸሙ እስቲ እንመልከት።