በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 109

ጴጥሮስ ወደ ቆርኔሌዎስ ቤት ሄደ

ጴጥሮስ ወደ ቆርኔሌዎስ ቤት ሄደ

የቆመው ሐዋርያው ጴጥሮስ ነው፤ ከኋላው ያሉት ደግሞ ጓደኞቹ ናቸው። ሆኖም ሰውየው ለጴጥሮስ እየሰገደ ያለው ለምንድን ነው? እንደዚህ ማድረጉ ተገቢ ነውን? ይህ ሰው ማን እንደሆነ ታውቃለህ?

ሰውየው ቆርኔሌዎስ ነው። የሮማ ሠራዊት አለቃ ነው። ቆርኔሌዎስ ጴጥሮስን አያውቀውም፤ ሆኖም ወደ ቤቱ እንዲጠራው ተነግሮታል። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ተከታዮች አይሁዳውያን ነበሩ፤ ቆርኔሌዎስ ግን አይሁዳዊ አይደለም። ሆኖም አምላክን ይወድ ነበር፤ ወደ እርሱ ይጸልይ ነበር፤ እንዲሁም ለሰዎች ብዙ ጥሩ ነገሮች ያደርግ ነበር። አንድ ቀን ከሰዓት በኋላ አንድ መልአክ ተገለጠለትና እንዲህ አለው:- ‘አምላክን ደስ ስላሰኘኸው ለጸሎትህ መልስ ይሰጥሃል። ጥቂት ሰዎች ላክና ጴጥሮስ የሚባለውን ሰው ይዘውት እንዲመጡ አድርግ። በኢዮጴ በባሕር አጠገብ በሚኖረው በስምዖን ቤት ውስጥ ተቀምጦአል።’

ቆርኔሌዎስ ወዲያውኑ ጴጥሮስን ፈልገው ይዘውት እንዲመጡ ጥቂት ሰዎች ላከ። በሚቀጥለው ቀን ሰዎቹ ወደ ኢዮጴ ሲቃረቡ ጴጥሮስ በስምዖን ቤት ሰገነት ላይ ተቀምጦ ነበር። እዚያው ላይ እንዳለ አምላክ አንድ ትልቅ ጨርቅ ከሰማይ የወረደ መስሎ እንዲታየው አደረገ። በጨርቁ ውስጥ ብዙ ዓይነት እንስሳት ነበሩ። የአምላክ ሕግ በሚለው መሠረት እነዚህ እንስሳት ርኩስ ስለሆኑ ለምግብነት አይሆኑም ነበር፤ ሆኖም አንድ ድምፅ ‘ጴጥሮስ ሆይ ተነሳና አርደህ ብላ’ አለው።

ጴጥሮስ ‘አይሆንም! ርኩስ የሆነ ነገር በልቼ አላውቅም’ ሲል መለሰ። ሆኖም ድምፁ ጴጥሮስን ‘አምላክ ንጹሕ ነው ያለውን ርኩስ ነው አትበል’ አለው። ይህ ሦስት ጊዜ ተደጋገመ። ጴጥሮስ የዚህ ነገር ትርጉም ምን ይሆን እያለ ሲያስብ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች እዚያ ቤት ደረሱና ጴጥሮስ እንዳለ ጠየቁ።

ጴጥሮስ ወደ ታች ወረደና ‘የምትፈልጉት ሰው እኔ ነኝ። የመጣችሁት ለምንድን ነው?’ አላቸው። ሰዎቹም አንድ መልአክ ጴጥሮስን ወደ ቤትህ አስጠራው ብሎ ለቆርኔሌዎስ እንደነገረው ገለጹለት፤ ጴጥሮስ አብሯቸው ለመሄድ ተስማማ። በሚቀጥለው ቀን ጴጥሮስና ጓደኞቹ በቂሣርያ ወደሚገኘው ወደ ቆርኔሌዎስ ቤት ሄዱ።

ቆርኔሌዎስ ዘመዶቹንና የቅርብ ጓደኞቹን አንድ ላይ ሰብስቦ ነበር። ጴጥሮስ ሲመጣ ቆርኔሌዎስ ተቀበለው። ሥዕሉ ላይ እንደምታየው በጴጥሮስ እግር ሥር ተደፍቶ ሰገደለት። ይሁን እንጂ ጴጥሮስ ‘ተነሳ፤ እኔ ራሴ ሰው ነኝ’ አለው። አዎ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ለሰው መስገድና ሰውን ማምለክ ትክክል እንዳልሆነ ያሳያል። ይሖዋን ብቻ ማምለክ ይኖርብናል።

ጴጥሮስ ተሰብስበው ለነበሩት ሰዎች መስበክ ጀመረ። ‘አምላክ እርሱን ለማገልገል የሚፈልጉትን ሰዎች በሙሉ እንደሚቀበል ተረድቻለሁ’ አለ። እየተናገረ ሳለ አምላክ ቅዱስ መንፈሱን ላከና ሰዎቹ በተለያዩ ቋንቋዎች መናገር ጀመሩ። ከጴጥሮስ ጋር የመጡት አይሁዳውያን ደቀ መዛሙርት አምላክ የሚቀበለው አይሁዳውያንን ብቻ ነው የሚል አመለካከት ስለነበራቸው ይህን ሲያዩ በጣም ተደነቁ። ስለዚህ ይህ ሁኔታ አምላክ የትኛውንም ዘር ከሌላ ዘር አስበልጦ ወይም ከፍ አድርጎ እንደማይመለከት አስተማራቸው። ይህ ሁላችንም ልናስታውሰው የሚገባ ነገር አይደለምን?