በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 91

ኢየሱስ በአንድ ተራራ ላይ ሲያስተምር

ኢየሱስ በአንድ ተራራ ላይ ሲያስተምር

ኢየሱስ ተቀምጦ ይታያል። እነዚህን ሰዎች በገሊላ ውስጥ በሚገኝ አንድ ተራራ ላይ እያስተማረ ነው። ወደ እሱ ቀረብ ብለው የተቀመጡት ደቀ መዛሙርቱ ናቸው። አሥራ ሁለቱን ሐዋርያት አድርጎ መርጧቸዋል። ሐዋርያት የኢየሱስ ልዩ ደቀ መዛሙርት ነበሩ። ስማቸውን ታውቀዋለህ?

ከሐዋርያቱ መካከል ስምዖን ጴጥሮስና ወንድሙ እንድርያስ ይገኙበታል። ወንድማማች የሆኑት ያዕቆብና ዮሐንስም ሐዋርያት ናቸው። ያዕቆብ የሚባል ሌላም ሐዋርያ አለ፤ ሌላው ደግሞ ስምዖን ነው። ይሁዳ ተብለው የሚጠሩ ሁለት ሐዋርያት ነበሩ። አንደኛው አስቆሮቱ ይሁዳ ሲሆን ሌላው ይሁዳ ደግሞ ታዴዎስ የሚል መጠሪያም ነበረው። የተቀሩት ሐዋርያት ደግሞ ፊልጶስና ናትናኤል (በርተሎሜዎስ ተብሎም ይጠራል) እንዲሁም ማቴዎስና ቶማስ ናቸው።

ኢየሱስ ከሰማርያ ከተመለሰ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ‘መንግሥተ ሰማያት ቀርቧል’ እያለ መስበክ ጀመረ። ይህ መንግሥት ምን እንደሆነ ታውቃለህ? እውን የሆነ የአምላክ አስተዳደር ነው። የዚህ መንግሥት ንጉሥ ኢየሱስ ነው። ከሰማይ ሆኖ በመግዛት ለምድር ሰላም ያመጣል። መላዋ ምድር በአምላክ መንግሥት አማካኝነት ውብ ገነት ትሆናለች።

ኢየሱስ ሰዎቹን ስለዚህ መንግሥት እያስተማረ ነው። ‘እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ’ ሲል አስተማራቸው። ‘በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ። መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነ እንዲሁ በምድር ይሁን።’ ብዙ ሰዎች ይህን ጸሎት ‘የጌታ ጸሎት’ ብለው ይጠሩታል። ሌሎች ደግሞ ‘አባታችን ሆይ’ ብለው ይጠሩታል። ጸሎቱን በቃልህ ይዘኸዋል?

በተጨማሪም ኢየሱስ ሰዎቹ አንዳቸው ለሌላው ምን ዓይነት ጠባይ ማሳየት እንዳለባቸው እያስተማራቸው ነው። ‘ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን እናንተም አድርጉላቸው’ አላቸው። ሌሎች የአሳቢነት ጠባይ ሲያሳዩህ ደስ አይልህም? ስለዚህ እኛም ልክ እንደዚሁ ለሌሎች አሳቢነት ማሳየት እንዳለብን ኢየሱስ ተናግሯል። በገነቲቱ ምድር ላይ ሁሉም ሰው ይህን ጠባይ ሲያሳይ የሚኖረው ሁኔታ በጣም የሚያስደስት አይሆንም?