በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 101

ኢየሱስ ተገደለ

ኢየሱስ ተገደለ

እየተፈጸመ ያለውን አሳዛኝ ድርጊት ተመልከት! ኢየሱስ ሊገደል ነው። እንጨት ላይ ሰቅለውታል። እጆቹና እግሮቹ በምስማር ተመተዋል። በኢየሱስ ላይ ይህን የመሰለ ድርጊት የሚፈጸመው ለምንድን ነው?

ይህ የሆነው ኢየሱስን የሚጠሉ ስላሉ ነው። እነዚህ እነማን እንደሆኑ ታውቃለህ? ከእነዚህ መካከል አንዱ ክፉው መልአክ ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። ሰይጣን አዳምና ሔዋን ይሖዋን እንዳይታዘዙ ያደረገው ክፉ መልአክ ነው። በተጨማሪም ሰይጣን የኢየሱስ ጠላቶች ይህን አሳዛኝ ወንጀል እንዲፈጽሙ እያደረገ ነው።

ኢየሱስ በእንጨት ላይ ከመሰቀሉ በፊት እንኳ ጠላቶቹ በጣም አሠቃይተውታል። ወደ ጌቴሴማኒ የአትክልት ቦታ እንዴት እንደመጡና እንዴት እንደወሰዱት ታስታውሳለህ አይደል? እነዚያ ጠላቶቹ እነማን ነበሩ? አዎ፣ የሃይማኖት መሪዎቹ ነበሩ። ከዚያ በኋላ ምን እንደተፈጸመ እስቲ እንመልከት።

የሃይማኖት መሪዎቹ ኢየሱስን ሲወስዱት ሐዋርያቱ ሸሹ። በጣም ስለ ፈሩ ኢየሱስን ከጠላቶቹ ጋር ብቻውን ጥለውት ሄዱ። ሆኖም ሐዋርያው ጴጥሮስና ሐዋርያው ዮሐንስ ብዙ ርቀው አልሄዱም። ኢየሱስ ምን እንደሚደርስበት ለማየት ተከተሏቸው።

ካህናቱ ኢየሱስን ሐና ወደሚባል አንድ ሽማግሌ ሰው ቤት ይዘውት ሄዱ። ይህ ሰው ቀደም ሲል ሊቀ ካህናት ነበር። ሕዝቡ እዚህ ብዙ አልቆዩም። ቀጥሎ ኢየሱስን በወቅቱ ሊቀ ካህናት ወደነበረው ወደ ቀያፋ ቤት ወሰዱት። በቀያፋ ቤት ውስጥ ብዙ የሃይማኖት መሪዎች ተሰብስበው ነበር።

በዚህ በቀያፋ ቤት ውስጥ ኢየሱስን ለፍርድ አቀረቡት። በኢየሱስ ላይ በሐሰት የሚመሰክሩ ሰዎችን ወደ ውስጥ አስገቡ። የሃይማኖት መሪዎቹ በሙሉ ‘ኢየሱስ መገደል አለበት’ አሉ። ከዚያም ተፉበት፤ በጥፊም መቱት።

ይህ ሁሉ ሲሆን ጴጥሮስ ግቢው ውስጥ ነበር። ሌሊቱ በጣም ይበርድ ስለነበረ ሰዎቹ እሳት አቀጣጠሉ። በእሳቱ ዙሪያ ተቀምጠው እየሞቁ ሳለ አንዲት ሠራተኛ ጴጥሮስን ተመለከተችና ‘ይህ ሰው ከኢየሱስ ጋር ነበር’ አለች።

ጴጥሮስ ‘በፍጹም፣ እኔ ከእሱ ጋር አልነበርኩም!’ ሲል መለሰ።

ሰዎች ሦስት ጊዜ ጴጥሮስን አንተ ከኢየሱስ ጋር ነበርክ ብለውታል። ሆኖም ጴጥሮስ በሦስቱም ጊዜያት እኔ ከእሱ ጋር አልነበርኩም አለ። ጴጥሮስ በሦስተኛው ጊዜ እንዲህ ብሎ ሲናገር ኢየሱስ ዞር ብሎ ተመለከተው። ጴጥሮስ በመዋሸቱ በጣም አዘነ፤ ወደ ውጪ ወጥቶም አለቀሰ።

አርብ ጠዋት ፀሐይ መውጣት ስትጀምር ካህናቱ ኢየሱስን ወደ ትልቁ መሰብሰቢያቸው ወደ ሳንሄድሪን አዳራሽ ወሰዱት። እዚያ ከወሰዱት በኋላ ምን እንደሚያደርጉት ተወያዩ። የይሁዳ አገረ ገዥ ወደሆነው ወደ ጰንጤናዊው ጲላጦስ ወሰዱት።

ካህናቱ ጲላጦስን ‘ይህ መጥፎ ሰው ነው። መገደል አለበት’ አሉት። ጲላጦስ ኢየሱስን አንዳንድ ጥያቄዎች ከጠየቀው በኋላ ‘ምንም ጥፋት አላገኘሁበትም’ አላቸው። ከዚያም ጲላጦስ ኢየሱስን ወደ ሄሮድስ አንቲጳስ ላከው። ሄሮድስ የገሊላ ገዥ የነበረ ሲሆን በወቅቱ ኢየሩሳሌም ውስጥ ነበር። ሄሮድስም በኢየሱስ ላይ ምንም ጥፋት ስላላገኘበት መልሶ ወደ ጲላጦስ ላከው።

ጲላጦስ ኢየሱስን ሊለቀው ፈልጎ ነበር። የኢየሱስ ጠላቶች ግን በእርሱ ፋንታ ሌላ እስረኛ እንዲፈታላቸው ፈለጉ። እንዲፈታላቸው የፈለጉት በርባን የተባለውን ሌባ ነበር። ጲላጦስ ኢየሱስን ወደ ውጪ ሲያወጣው እኩለ ቀን ገደማ ሆኖ ነበር። ጲላጦስ ሰዎቹን ‘እነሆ፣ ንጉሣችሁ!’ አላቸው። የካህናት አለቆቹ ግን ‘አስወግደው! ግደለው! ግደለው’ እያሉ ጮኹ። ስለዚህ ጲላጦስ በርባን እንዲፈታ አደረገና ኢየሱስን ለመግደል ይዘውት ሄዱ።

አርብ እኩለ ቀን ላይ ኢየሱስ እንጨት ላይ በምስማር ተቸነከረ። ሥዕሉ ላይ ልታያቸው ባትችልም እንኳ በኢየሱስ ግራና ቀኝ ሁለት ወንጀለኞች በእንጨት ላይ ተሰቅለው ነበር። ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ከወንጀለኞቹ አንዱ ‘በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ’ አለው። ኢየሱስም ‘ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ’ ብሎ ቃል ገባለት።

ይህ አስደሳች ተስፋ አይደለም? ኢየሱስ የተናገረው ስለየትኛዋ ገነት እንደሆነ ታውቃለህ? አምላክ በመጀመሪያ ያዘጋጃት ገነት የት ነበረች? አዎ፣ ምድር ላይ ነበረች። ኢየሱስ በሰማይ ንጉሥ ሆኖ ሲገዛ ይህን ሰው ከሞት በማስነሳት በምድር ላይ በአዲሲቱ ገነት ውስጥ እንዲኖር ያደርገዋል። ይህ አያስደስትም?