በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 95

ኢየሱስ ያስተማረበት መንገድ

ኢየሱስ ያስተማረበት መንገድ

ከዕለታት አንድ ቀን ኢየሱስ ባልንጀራህን እንደ ራስህ መውደድ አለብህ ብሎ ለአንድ ሰው ነገረው። ሰውየው ኢየሱስን ‘ባልንጀራዬ ማን ነው?’ ሲል ጠየቀው። ኢየሱስ ይህ ሰው ምን አስተሳሰብ እንዳለው ያውቅ ነበር። ሰውየው ባልንጀሮቹ የራሱ ወገን የሆኑና እሱ የሚከተለውን ሃይማኖት የሚከተሉ ሰዎች ብቻ እንደሆኑ አድርጎ ያስብ ነበር። ኢየሱስ ምን እንዳለው እስቲ እንመልከት።

አንዳንድ ጊዜ ኢየሱስ አንድ ታሪክ በመናገር ያስተምር ነበር። አሁንም ያደረገው እንዲሁ ነው። ስለ አንድ አይሁዳዊና ስለ አንድ ሳምራዊ የሚገልጽ አንድ ታሪክ ተናገረ። አብዛኞቹ አይሁዳውያን ሳምራውያንን እንደማይወዷቸው ቀደም ሲል ተምረናል። ኢየሱስ የተናገረው ታሪክ የሚከተለው ነው:-

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አይሁዳዊ ተራራ አቋርጦ ወደ ኢያሪኮ በሚወስድ መንገድ እየተጓዘ ነበር። ሆኖም ዘራፊዎች በድንገት ያዙት። ገንዘቡን ወሰዱበትና ለሞት እስኪቃረብ ድረስ ደበደቡት።

በኋላ አንድ አይሁዳዊ ካህን በዚያ መንገድ መጣ። የተደበደበውን ሰው አየው። ምን ያደረገ ይመስልሃል? ራቅ ብሎ እንዳላየ ሆኖ አልፎት ሄደ። ከዚያም ሌላ በጣም ሃይማኖተኛ የሆነ ሰው መጣ። ይህ ሰው ሌዋዊ ነበር። እርሱስ ቆሞ ይሆን? በፍጹም፣ እርሱም ቢሆን የተደበደበውን ሰው ለመርዳት አልቆመም። ካህኑና ሌዋዊው በርቀት በመንገዱ ላይ ሲጓዙ ሥዕሉ ላይ መመልከት ትችላለህ።

ይሁን እንጂ ከተደበደበው ሰው ጋር ያለው ማን እንደሆነ ተመልከት። ሳምራዊ ነው። አይሁዳዊውን እየረዳው ነው። ቁስሎቹ ላይ መድኃኒት አደረገለት። ከዚያም አይሁዳዊውን ማረፍና ደህና መሆን ወደሚችልበት ቦታ ወሰደው።

ኢየሱስ ታሪኩን ከጨረሰ በኋላ ጥያቄውን የጠየቀውን ሰው ‘ከእነዚህ ሦስት ሰዎች መካከል ለተደበደበው ሰው ባልንጀራ የሆነው ማን ይመስልሃል? ካህኑ ነው፣ ሌዋዊው ነው፣ ወይስ ሳምራዊው?’ አለው።

ሰውየው ‘ሳምራዊው ነው። የተደበደበውን ሰው ረድቶታል’ ብሎ መለሰ።

ኢየሱስ ‘ልክ ነህ። አንተም ሂድና ለሌሎች እርሱ እንዳደረገው አድርግ’ አለው።

ኢየሱስ ያስተማረበት መንገድ አያስደስትም? ኢየሱስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተናገረውን የምንሰማ ከሆነ በጣም ጠቃሚ የሆኑ ብዙ ነገሮች ልንማር እንችላለን፤ አንችልም እንዴ?