በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 50

ሁለት ደፋር ሴቶች

ሁለት ደፋር ሴቶች

እስራኤላውያን ችግር ሲያጋጥማቸው ወደ ይሖዋ ጮኹ። ይሖዋ ልመናቸውን በመስማት እነርሱን የሚረዱ ደፋር መሪዎች ሰጣቸው። መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን መሪዎች መሳፍንት ብሎ ይጠራቸዋል። የመጀመሪያው መስፍን ኢያሱ ነበር፤ ከእሱ በኋላ ከተነሱት መሳፍንት መካከል ጎቶንያል፣ ናዖድና ሰሜጋር ይገኙበታል። ይሁን እንጂ እስራኤላውያንን ከረዷቸው ሰዎች መካከል ዲቦራና ኢያዔል የሚባሉ ሁለት ሴቶች ይገኛሉ።

ዲቦራ ነቢይት ነበረች። ይሖዋ ወደፊት ስለሚሆነው ነገር ይነግራት ነበር፤ ከዚያም ይሖዋ ያለውን ነገር ለሕዝቡ ትናገር ነበር። ዲቦራ ፈራጅም ነበረች። በኮረብታማው አገር ከአንድ የዘንባባ ዛፍ ሥር ትቀመጣለች፤ ሕዝቡም ችግሮቻቸውን እንድትፈታላቸው ወደ እርሷ ይመጡ ነበር።

በዚህ ወቅት ኢያቢስ የከነዓን ንጉሥ ነበር። 900 የጦር ሠረገሎች ነበሩት። ሠራዊቱ በጣም ኃይለኛ ስለነበረ ብዙዎቹ እስራኤላውያን የኢያቢስ አገልጋዮች ለመሆን ተገደው ነበር። የንጉሥ ኢያቢስ ሠራዊት አለቃ ሲሣራ የሚባል ሰው ነበር።

አንድ ቀን ዲቦራ ‘ይሖዋ “10, 000 ሰዎች ይዘህ ወደ ታቦር ተራራ ውጣ። ሲሣራ አንተን ለመውጋት ወደዚያ እንዲመጣ አደርጋለሁ። በእሱና በሠራዊቱም ላይ ድል አቀዳጅሃለሁ” ሲል አዝዞሃል’ ብላ ወደ መስፍኑ ባርቅ መልእክተኛ ላከች።

ባርቅ ዲቦራን ‘አንቺ ከእኔ ጋር የምትሄጂ ከሆነ እሄዳለሁ’ አላት። ዲቦራ ከእርሱ ጋር ሄደች፤ ሆኖም ባርቅን ‘ይሖዋ ሲሣራን በሴት እጅ እንዲገደል ስለሚያደርግ ድሉ ለአንተ ክብር አይሆንም’ አለችው። በኋላም የተፈጸመው ሁኔታ ይኸው ነበር።

ባርቅ ከሲሣራ ወታደሮች ጋር ለመገናኘት ከታቦር ተራራ ወረደ። ይሖዋ በድንገት ጎርፍ አመጣባቸውና ብዙዎቹን የጠላት ወታደሮች ጠራረጋቸው። ሲሣራ ግን ከሰረገላው ላይ ወረደና ሸሸ።

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሲሣራ ወደ ኢያዔል ድንኳን ደረሰ። ወደ ውስጥ እንዲገባ ጋበዘችውና ወተት ሰጠችው። ይህም እንቅልፍ አመጣበት፤ ብዙም ሳይቆይ እንቅልፍ ድብን አድርጎ ወሰደው። ከዚያም ኢያዔል አንድ የድንኳን ካስማ አነሳችና በዚህ መጥፎ ሰው ጭንቅላት ላይ ቸከለችው። በኋላ ባርቅ ሲመጣ የሲሣራን ሬሳ አሳየችው! ዲቦራ የተናገረችው ነገር እንደተፈጸመ መረዳት ትችላለህ።

በመጨረሻ ንጉሥ ኢያቢስም ተገደለ፤ እስራኤላውያንም እንደገና ለተወሰነ ጊዜ ሰላም አገኙ።