በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 37

ለአምልኮ የሚያገለግል ድንኳን

ለአምልኮ የሚያገለግል ድንኳን

ይህ ቤት ምን እንደሆነ ታውቃለህ? ለይሖዋ አምልኮ የሚያገለግል ለየት ያለ ድንኳን ነው። የማደሪያው ድንኳን ተብሎም ይጠራል። ሕዝቡ ይህን ድንኳን ሠርተው የጨረሱት ከግብፅ ከወጡ ከአንድ ዓመት በኋላ ነበር። ይህ ድንኳን እንዲሠራ ሐሳብ ያመጣው ማን እንደሆነ ታውቃለህ?

ይህን ሐሳብ ያመጣው ይሖዋ ነው። ሙሴ በሲና ተራራ ላይ ወጥቶ በነበረበት ጊዜ ይሖዋ ድንኳኑ እንዴት መሠራት እንዳለበት ነገረው። በቀላሉ ሊነቃቀል እንደሚችል አድርጎ እንዲሠራው ነግሮት ነበር። በዚህ መንገድ ድንኳኑ የተሠራባቸውን ነገሮች ነቃቅሎ በመለያየት ወደ ሌላ ቦታ ተሸክሞ መሄድና በዚያ ቦታም እንደገና አንድ ላይ ገጣጥሞ መሥራት ይቻላል። ስለዚህ እስራኤላውያን በምድረ በዳ ከቦታ ወደ ቦታ ሲጓዙ ድንኳኑን ይዘውት ይሄዱ ነበር።

በድንኳኑ ጫፍ በሚገኘው አነስተኛ ክፍል ውስጥ ብትመለከት አንድ ሣጥን ማየት ትችላለህ። ይህ የቃል ኪዳኑ ታቦት ተብሎ ይጠራል። ጫፍና ጫፉ ላይ ከወርቅ የተሠሩ ሁለት መላእክት ወይም ኪሩቤሎች አሉት። ሙሴ የመጀመሪያዎቹን ጽላቶች ሰብሯቸው ስለነበረ አምላክ እንደገና አሥርቱን ትእዛዛት በሁለት የድንጋይ ጽላቶች ላይ ጻፋቸው። እነዚህ ጽላቶች በቃል ኪዳኑ ታቦት ውስጥ እንዲቀመጡ ተደረገ። በተጨማሪም መና የያዘ ማሰሮ በውስጡ ተቀመጠ። መና ምን እንደሆነ ታስታውሳለህ አይደል?

ይሖዋ የሙሴን ወንድም አሮንን ሊቀ ካህን አድርጎ መርጦት ነበር። ሕዝቡን ለይሖዋ አምልኮ ያስተባብር ነበር። ወንዶች ልጆቹም ካህናት ነበሩ።

አሁን ደግሞ ሰፋ ያለውን የድንኳኑን ክፍል ተመልከት። የትንሹን ክፍል ሁለት እጥፍ ይሆናል። ጭስ የሚጨስበት አነስተኛ ሣጥን ይታይሃል? ይህ ካህናቱ ደስ የሚል ሽታ ያለውን ዕጣን የተባለ ነገር የሚያጨሱበት መሠዊያ ነው። ከዚህም ሌላ ሰባት መብራቶችን የያዘ መቅረዝ አለ። በክፍሉ ውስጥ ያለው ሦስተኛው ነገር ጠረጴዛ ነው። በጠረጴዛው ላይ 12 ዳቦዎች ተቀምጠዋል።

በማደሪያው ድንኳን ግቢ ውስጥ በውኃ የተሞላ አንድ ትልቅ ሳህን ወይም ገንዳ ነበረ። ካህናቱ ይታጠቡበት ነበር። ትልቁ መሠዊያም በዚሁ ቦታ ይገኛል። የታረዱ እንስሳትን በዚህ መሠዊያ ላይ በማቃጠል ለይሖዋ መሥዋዕት አድርገው ያቀርቡ ነበር። ድንኳኑ በሠፈሩ መካከል ይገኝ ነበር፤ እስራኤላውያን ደግሞ በዙሪያው በድንኳኖቻቸው ውስጥ ይኖሩ ነበር።