በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 40

ሙሴ አለቱን መታ

ሙሴ አለቱን መታ

ዓመታት እያለፉ ሄዱ፤ 10 ዓመት፣ 20 ዓመት፣ 30 ዓመት ብሎም 39 ዓመት አለፈ! በዚህም ጊዜ ቢሆን እስራኤላውያን ገና በምድረ በዳ ነበሩ። ይሁን እንጂ በእነዚህ ዓመታት ሁሉ ይሖዋ ለሕዝቡ አስፈላጊውን እንክብካቤ አድርጎላቸዋል። መና መግቧቸዋል። ቀን በደመና ዓምድ ሌሊት ደግሞ በእሳት ዓምድ ይመራቸው ነበር። በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ልብሳቸው አላለቀም፤ እግራቸውም አልቆሰለም።

አሁን ጊዜው ከግብፅ የወጡበት 40ኛ ዓመት የመጀመሪያው ወር ነበር። እስራኤላውያን እንደገና በቃዴስ ሰፈሩ። ይህ ቦታ ወደ 40 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት የከነዓንን ምድር እንዲሰልሉ 12 ሰላዮች በተላኩበት ጊዜ እስራኤላውያን ሰፍረውበት የነበረው ቦታ ነው። የሙሴ እህት ሚርያም በቃዴስ ሞተች። ልክ እንደቀድሞው አሁንም በዚህ ቦታ ችግር ተፈጠረ።

ሕዝቡ ምንም ውኃ ማግኘት አልቻሉም። በዚህም ምክንያት እንዲህ ሲሉ በሙሴ ላይ አጉረመረሙ:- ‘አስቀድሞ ሞተን ቢሆን ኖሮ ይሻለን ነበር። ከግብፅ ምድር አውጥተህ ምንም ነገር ወደማይበቅልበት ወደዚህ አስቸጋሪ ቦታ ለምን አመጣኸን? እህልና በለስ፣ ወይንም፣ ሮማንም የለም። የሚጠጣ ውኃ እንኳ የለም።’

ሙሴና አሮን ለመጸለይ ወደ ማደሪያው ድንኳን ሲሄዱ ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው:- ‘ሕዝቡን አንድ ላይ ሰብስብ። እዚያም በእነርሱ ሁሉ ፊት ሆነህ ያንን አለት ተናገረው። ለሕዝቡና ለእንስሶቻቸው በሙሉ የሚበቃ ውኃ ይወጣል።’

ሙሴ ሕዝቡን ሰበሰበና ‘እናንተ በአምላክ የማትታመኑ ሰዎች ስሙ! አሮንና እኔ ከዚህ አለት ውኃ እንድናወጣላችሁ ትፈልጋላችሁ?’ አላቸው። ከዚያም ሙሴ በበትር አለቱን ሁለት ጊዜ ሲመታው ከአለቱ ውስጥ ብዙ ውኃ ፈሰሰ። ለሰዎቹና ለእንስሳቱ በሙሉ የሚበቃ ውኃ ነበር።

ሆኖም ይሖዋ በሙሴና በአሮን ላይ ተቆጣ። ለምን እንደሆነ ታውቃለህ? ይሖዋ የተቆጣው ሙሴና አሮን ውኃውን ከአለቱ ውስጥ የሚያወጡት እነርሱ እንደሆኑ አድርገው በመናገራቸው ነበር። ውኃውን ያወጣው ግን ይሖዋ ነበር። ሙሴና አሮን እውነቱን ባለመናገራቸው ይሖዋ እንደሚቀጣቸው ተናገረ። ‘ሕዝቤን ወደ ከነዓን ምድር ይዛችሁ አትገቡም’ አላቸው።

ብዙም ሳይቆይ እስራኤላውያን ከቃዴስ ወጡ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደ ሖር ተራራ ደረሱ። በዚህ ቦታ በተራራው ጫፍ ላይ አሮን ሞተ። አሮን ሲሞት 123 ዓመት ሆኖት ነበር። እስራኤላውያን በጣም በማዘናቸው ሕዝቡ ሁሉ ለአሮን 30 ቀን አለቀሱ። ልጁ አልዓዛር የእስራኤል ሕዝብ ሊቀ ካህን ሆኖ ተተካ።