በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 34

አዲስ ዓይነት ምግብ

አዲስ ዓይነት ምግብ

ሰዎቹ ከመሬት እየለቀሙት ያሉት ነገር ምን እንደሆነ ታውቃለህ? አመዳይ የሚመስል ነገር ነው። ነጭ ነው፤ እንዲሁም ስስና ቅርፊት የሚመስል ነገር ነው። አመዳይ ግን አይደለም፤ የሚበላ ነገር ነው።

እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ ገና አንድ ወር ገደማ መሆኑ ነበር። በዚህ ጊዜ በምድረ በዳ ነበሩ። በዚህ ቦታ እህል የማይበቅል በመሆኑ ሕዝቡ ‘ይሖዋ በግብፅ ሳለን ቢገድለን ይሻለን ነበር። እዚያ ሳለን ሌላው ቢቀር የፈለግነውን ምግብ ሁሉ እናገኝ ነበር’ በማለት አጉረመረሙ።

ስለዚህም ይሖዋ ‘ከሰማይ ምግብ አዘንባለሁ’ ሲል ተናገረ። ይሖዋ የተናገረውን ፈጽሟል። በሚቀጥለው ቀን ጠዋት እስራኤላውያን ከሰማይ የዘነበ ነጭ ነገር መሬት ላይ ሲመለከቱ ‘ይህ ምንድን ነው?’ እያሉ እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ።

ሙሴም ‘ይህ ይሖዋ እንድትበሉት የሰጣችሁ ምግብ ነው’ አላቸው። ሕዝቡም ምግቡን መና ብለው ጠሩት። ጣዕሙም በማር እንደተሠራ ቂጣ ነበር።

ሙሴ ሕዝቡን ‘እያንዳንዱ ሰው መብላት የሚችለውን ያህል ይልቀም’ አላቸው። ስለዚህ ሕዝቡ በየዕለቱ ጠዋት ጠዋት እንደተባሉት ያደርጉ ነበር። ከዚያም የፀሐይ ሙቀት እየጨመረ ሲሄድ በመሬት ላይ የቀረው መና ይቀልጥ ነበር።

በተጨማሪም ሙሴ ‘ማንም ሰው መናውን አስተርፎ ለሚቀጥለው ቀን ማሳደር የለበትም’ በማለት ተናግሮ ነበር። አንዳንድ ሰዎች ግን አልታዘዙም። ምን ሁኔታ እንደተፈጠረ ታውቃለህ? በሚቀጥለው ቀን ጠዋት ያስተረፉት መና ትል በትል ሆነና ሸተተ!

ይሁን እንጂ ሕዝቡ በሳምንት አንድ ቀን ሁለት እጥፍ አድርገው እንዲሰበስቡ ይሖዋ አዟቸው ነበር። ይህ ስድስተኛው ቀን ነበር። በተጨማሪም ይሖዋ በዚህ ቀን ከሰበሰቡት መና ላይ ለሚቀጥለው ቀን እንዲያስተርፉ ነግሯቸዋል፤ ምክንያቱም በሰባተኛው ቀን መና አያዘንብም ነበር። መናውን ለሰባተኛው ቀን ሲያስተርፉ አልተላም፤ እንዲሁም አልሸተተም ነበር! ይህ ሌላ ተአምር ነው!

እስራኤላውያን በምድረ በዳ በነበሩባቸው ዓመታት ሁሉ ይሖዋ መና መግቧቸ⁠ዋል።