በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 36

ከወርቅ የተሠራው ጥጃ

ከወርቅ የተሠራው ጥጃ

እንዴ! እንዴ! ሰዎቹ ምን እያደረጉ ነው? ለአንድ ጥጃ እየጸለዩ ነው! ይህን እያደረጉ ያሉት ለምንድን ነው?

ሙሴ ተራራው ላይ ወጥቶ ረጅም ጊዜ ሲቆይ ሕዝቡ ‘ሙሴ ምን እንደደረሰበት አናውቅም። ስለዚህ ከዚህ ምድር የሚያወጣን አምላክ እንሥራ’ አሉ።

የሙሴ ወንድም የሆነው አሮን ‘እሺ፣ የወርቅ ጉትቻዎቻችሁን አውልቃችሁ ስጡኝ’ አላቸው። ሕዝቡ ጉትቻዎቻቸውን አውልቀው ሲሰጡት አሮን ጉትቻዎቹን አቀለጣቸውና አንድ የወርቅ ጥጃ ሠራ። ሕዝቡም ‘ከግብፅ ምድር ያወጣን አምላካችን ይህ ነው!’ አሉ። ከዚያም እስራኤላውያን ትልቅ ድግስ አዘጋጁና ከወርቅ የተሠራውን ጥጃ አመለኩ።

ይሖዋ ይህን ሲመለከት በጣም ተቆጣ። ስለዚህም ሙሴን ‘ፈጥነህ ውረድ። ሕዝቡ ኃጢአት ሠርተዋል። ሕጎቼን ችላ ብለው ለአንድ የወርቅ ጥጃ እየሰገዱ ነው’ አለው።

ሙሴ ከተራራው ፈጥኖ ወረደ። ሕዝቡ ወዳሉበት ቦታ ሲደርስ የተመለከተው ይህን ነበር። ሕዝቡ ከወርቅ በተሠራው ጥጃ ዙሪያ እየዘፈኑ ይጨፍሩ ነበር! ሙሴ በጣም ስለተናደደ ሕጎቹ ተጽፎባቸው የነበሩትን ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ሲወረውራቸው ተሰባበሩ። ከዚያም ከወርቅ የተሠራውን ጥጃ ወስዶ አቀለጠው። ከዚያ በኋላም ዱቄት እስኪሆን ድረስ ፈጨው።

ሕዝቡ በጣም መጥፎ የሆነ ድርጊት ፈጽመው ነበር። ስለዚህ ሙሴ የተወሰኑ ሰዎች ሰይፋቸውን እንዲታጠቁ ነገራቸው። ‘ከወርቅ የተሠራውን ጥጃ ያመለኩ ክፉ ሰዎች መሞት አለባቸው’ ሲል ሙሴ ተናገረ። ስለዚህ ሰይፋቸውን የታጠቁት ሰዎች 3, 000 ሰዎች ገደሉ! ይህ ሁኔታ ማንኛውንም ዓይነት የሐሰት አማልክት ማምለክ እንደሌለብንና ይሖዋን ብቻ ማምለክ እንዳለብን አያሳይምን?