በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 39

የአሮን በትር አበባ አወጣች

የአሮን በትር አበባ አወጣች

በዚህ በትር ወይም ዱላ ላይ የበቀለውን አበባና የበሰለ ለውዝ ተመልከት። ይህ የአሮን በትር ነው። ይህ አበባና የበሰለ ፍሬ በአሮን በትር ላይ የበቀለው በአንድ ሌሊት ነው! ይህ የሆነበትን ምክንያት እንመልከት።

እስራኤላውያን በምድረ በዳ እየተቅበዘበዙ የተወሰነ ጊዜ አሳልፈዋል። አንዳንድ ሰዎች ሙሴ መሪ መሆን የለበትም፤ አሮንም ቢሆን ሊቀ ካህን መሆን የለበትም ብለው አሰቡ። ይህ አስተሳሰብ ካደረባቸው ሰዎች አንዱ ቆሬ ነበር፤ ዳታን አቤሮንና 250 የሕዝብ አለቆችም ይህ አስተሳሰብ አድሮባቸው ነበር። እነዚህ ሁሉ ተሰበሰቡና ወደ ሙሴ መጥተው ‘ራስህን በእኛ ላይ መሪ አድርገህ የሾምከው ለምንድን ነው?’ አሉት።

ሙሴ ቆሬንና ተከታዮቹን ‘ነገ ጠዋት ጥናዎችን ውሰዱ፤ ዕጣንም አድርጉባቸው። ከዚያም ወደ ማደሪያው ድንኳን ኑ። ይሖዋ ማንን እንደሚመርጥ እናያለን’ አላቸው።

በሚቀጥለው ቀን ቆሬና 250 ተከታዮቹ ወደ ማደሪያው ድንኳን መጡ። ሌሎች ብዙዎችም እነዚህን ሰዎች ለመደገፍ አብረዋቸው መጡ። ይሖዋ በጣም ተቆጣ። ‘ከእነዚህ ክፉ ሰዎች ድንኳኖች ራቁ። የእነርሱ የሆነውን ማንኛውንም ነገር አትንኩ’ ሲል ሙሴ ተናገረ። ሰዎቹም የተባሉትን ሰምተው ከቆሬ፣ ከዳታንና ከአቤሮን ድንኳኖች ራቁ።

ከዚያም ሙሴ ‘ምድር ተከፍታ እነዚህን ክፉ ሰዎች ትውጣቸዋለች። ይሖዋ ማንን እንደመረጠ በዚህ ታውቃላችሁ’ አለ።

ልክ ሙሴ ተናግሮ እንደጨረሰ ምድር ተከፈተች። የቆሬ ድንኳንና ያለው ንብረት ሁሉ፣ ዳታንና አቤሮን እንዲሁም ከእነርሱ ጋር የነበሩት ሁሉ ወደ ውስጥ ገቡ፤ ምድርም በላያቸው ላይ ተዘጋችባቸው። ሕዝቡ ወደ መሬት የገቡትን ሰዎች ጩኸት ሲሰሙ ‘ምድሪቱ እኛንም እንዳትውጠን እንሽሽ!’ አሉ።

በዚህ ጊዜ ቆሬና 250 ተከታዮቹ በማደሪያው ድንኳን አጠገብ ቆመው ነበር። ይሖዋ እሳት አወረደባቸውና ሁሉም በእሳት ተቃጥለው ጠፉ። ከዚያም ይሖዋ የአሮን ልጅ አልዓዛር የሞቱትን ሰዎች ጥናዎች አቅልጦ መሠዊያውን በስሱ እንዲለብጥባቸው አዘዘው። መሠዊያው የተለበጠው ከአሮንና ከልጆቹ በስተቀር ማንም ሰው የይሖዋ ካህን ሆኖ መሥራት እንደሌለበት ለእስራኤላውያን ማስጠንቀቂያ ሆኖ እንዲያገለግል ተብሎ ነው።

ይሁን እንጂ ይሖዋ ካህናት አድርጎ የመረጣቸው አሮንንና ልጆቹን እንደሆነ በግልጽ ለማሳወቅ ፈልጎ ነበር። ስለዚህም ሙሴን እንዲህ አለው:- ‘እያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ አለቃ በትሩን ያምጣ። ከሌዊ ነገድ አሮን በትሩን ያምጣ። ከዚያም እነዚህን በትሮች በማደሪያው ድንኳን ውስጥ በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ለፊት አስቀምጣቸው። ካህን አድርጌ የመረጥሁት ሰው በትር አበባ ታወጣለች።’

በሚቀጥለው ቀን ጠዋት ሙሴ ሲመለከት የአሮን በትር ይህን አበባና የበሰለ ለውዝ አፍርታ ነበር! ይሖዋ የአሮን በትር አበባ እንድታወጣ ያደረገበት ምክንያት አሁን ግልጽ ሆነልህ?