በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 46

የኢያሪኮ ግንብ

የኢያሪኮ ግንብ

ይህን የኢያሪኮ ግንብ እንዲፈራርስ እያደረገው ያለው ምንድን ነው? አንድ ትልቅ ቦምብ የመታው ይመስላል። ይሁን እንጂ በዚያ ዘመን የነበሩ ሰዎች ቦምብ አልነበራቸውም፤ ሌላው ቀርቶ ጠመንጃ እንኳ አልነበራቸውም። ይህ ሌላው የይሖዋ ተአምር ነበር! ይህ የተፈጸመው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ይሖዋ ኢያሱን ምን እንዳለው ተመልከት:- ‘አንተና ተዋጊዎችህ ከተማይቱን ትዞራላችሁ። ከተማይቱን ለስድስት ቀናት በቀን አንድ ጊዜ ትዞራላችሁ። የቃል ኪዳኑን ታቦት ይዛችሁ ዙሩ። ሰባት ካህናት ከታቦቱ ፊት እየሄዱ ቀንደ መለከታቸውን ይንፉ።

‘በሰባተኛው ቀን ከተማይቱን ሰባት ጊዜ ትዞራላችሁ። ከዚያም ቀንደ መለከቶቹን ያለማቋረጥ ንፉ፤ ሕዝቡ ሁሉ ታላቅ ጩኸት ያሰሙ። በዚህ ጊዜ ግንቦቹ ይፈራርሳሉ!’

ኢያሱና ሕዝቡ ይሖዋ ያለውን አደረጉ። በሚዞሩበት ጊዜ ሁሉም ጸጥ ብለው ይዞሩ ነበር። አንድም ቃል የሚናገር አልነበረም። የሚሰማ ድምፅ ቢኖር የቀንደ መለከቶቹ ድምፅና ከተማይቱን የሚዞሩት ሰዎች ኮቴ ነበር። በኢያሪኮ የነበሩት የአምላክ ሕዝብ ጠላቶች ሳይፈሩ አይቀርም። አንድ መስኮት ላይ የተንጠለጠለ ቀይ ገመድ ይታይሃል? ይህ የማን መስኮት ነው? አዎ፣ ረዓብ ሁለቱ ሰላዮች ያሏትን አድርጋለች። ቤተሰቦቿ በሙሉ ቤቱ ውስጥ ከእርሷ ጋር ሆነው እየተጠባበቁ ነው።

በመጨረሻ በሰባተኛው ቀን ከተማዋን ሰባት ጊዜ ከዞሩ በኋላ ቀንደ መለከቶቹን ነፉ፣ ተዋጊዎቹ ጮኹ፣ ግንቦቹም ወደቁ። ከዚያም ኢያሱ ‘በከተማይቱ ውስጥ ያሉትን ሁሉ ግደሉ፤ ከተማይቱንም አቃጥሉ። ሁሉንም ነገር አቃጥሉ። ብሩን፣ ወርቁን፣ ነሐሱንና ብረቱን ብቻ አታቃጥሉት፤ ወደ ይሖዋ ድንኳን ግምጃ ቤት አስገቡት’ አላቸው።

ኢያሱ ሁለቱን ሰላዮች ‘ወደ ረዓብ ቤት ሂዱና እሷንና ቤተሰቦቿን አውጧቸው’ አላቸው። ሰላዮቹ ቃል በገቡላት መሠረት ረዓብና ቤተሰቦቿ ከጥፋቱ ተረፉ።