በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 49

ፀሐይ ባለችበት ቦታ ቆመች

ፀሐይ ባለችበት ቦታ ቆመች

ኢያሱን ተመልከተው። ‘ፀሐይ ትቁም!’ እያለ ነው። ፀሐይዋ ቆመች። በሰማይ መካከል አንድ ሙሉ ቀን ቆመች። ይሖዋ ፀሐይዋ እንድትቆም አደረገ! ይሁን እንጂ ኢያሱ ፀሐይ ብርሃንዋን መስጠትዋን እንድትቀጥል የፈለገበት ምክንያት ምን እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

በከነዓን ምድር የነበሩት አምስቱ መጥፎ ነገሥታት ገባዖናውያንን መውጋት ሲጀምሩ ገባዖናውያን ኢያሱ እንዲረዳቸው ለመጠየቅ ሰው ላኩ። መልእክተኛው ‘በፍጥነት ድረስልን! አድነን! በኮረብታማው አገር የሚኖሩ ነገሥታት በሙሉ አገልጋዮችህን ለመውጋት መጥተዋል’ አለው።

ወዲያውኑ ኢያሱና ተዋጊዎቹ በሙሉ ሄዱ። ሙሉ ሌሊት ተጓዙ። ገባዖን ሲደርሱ የአምስቱ ነገሥታት ወታደሮች ፈሩና መሸሽ ጀመሩ። ከዚያም ይሖዋ ትልልቅ የበረዶ ድንጋይ ከሰማይ አዘነበ፤ በበረዶው ድንጋይ ተመትተው የሞቱት ወታደሮች የኢያሱ ተዋጊዎች ከገደሏቸው ይበልጡ ነበር።

ኢያሱ ፀሐይ የምትጠልቅበት ጊዜ እየተቃረበ እንዳለ ተገንዝቦ ነበር። ቀኑ ይጨልምና ብዙዎቹ የአምስቱ መጥፎ ነገሥታት ወታደሮች ያመልጣሉ። ኢያሱ ወደ ይሖዋ በመጸለይ ‘ፀሐይ ትቁም!’ ያለው በዚህ ምክንያት ነበር። ፀሐይ ብርሃን መስጠቷን ስትቀጥል እስራኤላውያን ውጊያውን በአሸናፊነት ማጠናቀቅ ይችላሉ።

የአምላክን ሕዝብ የሚጠሉ ሌሎች ብዙ መጥፎ ነገሥታት በከነዓን ምድር ይገኙ ነበር። ኢያሱና ሠራዊቱ በዚያ ምድር ይኖሩ የነበሩትን 31 ነገሥታት ድል ለማድረግ ወደ ስድስት ዓመታት ገደማ ወስዶባቸዋል። ይህ ከሆነ በኋላ ኢያሱ የከነዓን ምድር ርስት ላላገኙት ነገዶች እንዲከፋፈል አደረገ።

ብዙ ዓመታት አለፉ፤ በመጨረሻም ኢያሱ በ110 ዓመቱ ሞተ። እሱና ጓደኞቹ በሕይወት በነበሩበት ዘመን ሁሉ ሕዝቡ ይሖዋን ይታዘዙ ነበር። እነዚህ ጥሩ ሰዎች ሲሞቱ ግን ሕዝቡ መጥፎ ነገሮች መሥራት ጀመሩና ችግር ውስጥ ገቡ። በዚህ ወቅት የአምላክን እርዳታ ማግኘት ያስፈልጋቸው ነበር።