በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 66

ክፉዋ ንግሥት ኤልዛቤል

ክፉዋ ንግሥት ኤልዛቤል

ንጉሥ ኢዮርብዓም ከሞተ በኋላ 10 ነገዶች ያቀፈውን ሰሜናዊውን የእስራኤል መንግሥት የገዙት ነገሥታት በሙሉ መጥፎ ነገሥታት ነበሩ። ንጉሥ አክዓብ ደግሞ ከሁሉ የከፋ ነበር። ለምን እንደሆነ ታውቃለህ? አንዱ ትልቁ ምክንያት የራሱ ሚስት ክፉዋ ንግሥት ኤልዛቤል ነበረች።

ኤልዛቤል እስራኤላዊት ሴት አይደለችም። የሲዶን ንጉሥ ልጅ ናት። በኣል የተባለውን የሐሰት አምላክ ታመልክ ነበር፤ አክዓብና ብዙ እስራኤላውያንም በኣልን እንዲያመልኩ አድርጋለች። ኤልዛቤል ይሖዋን ትጠላ ነበር፤ ብዙ የይሖዋ ነቢያትንም ገድላለች። ሌሎቹ ነቢያት ደግሞ እንዳይገደሉ በዋሻዎች ውስጥ መደበቅ አስፈልጓቸው ነበር። ኤልዛቤል አንድ ነገር ለማግኘት ከፈለገች ያንን ነገር ለማግኘት ስትል ሰውን ከመግደል ወደ ኋላ የማትመለስ ሴት ነበረች።

አንድ ቀን ንጉሥ አክዓብ በጣም አዝኖ ነበር። በመሆኑም ኤልዛቤል ‘ዛሬ ያስከፋህ ነገር ምንድን ነው?’ ብላ ጠየቀችው።

አክዓብ ‘ናቡቴ አናዶኝ ነው። የወይን እርሻህን ልግዛህ አልኩት። እሱ ግን አይቻልም ብሎ ከለከለኝ’ አላት።

ኤልዛቤል ‘አይዞህ፤ እኔ አሰጥሃለሁ’ አለችው።

ኤልዛቤል ይህ ናቡቴ የተባለው ሰው በሚኖርበት ከተማ ውስጥ ለሚገኙ አለቆች ደብዳቤ ጻፈች። ‘ጥቂት ምናምንቴ ሰዎች ናቡቴ አምላክንና ንጉሡን ሰድቧል ብለው እንዲመሠክሩበት አድርጉ። ከዚያም ናቡቴን ከከተማ አውጡና በድንጋይ ወግራችሁ ግደሉት’ አለቻቸው።

ኤልዛቤል ናቡቴ መገደሉን እንዳወቀች ወዲያውኑ አክዓብን ‘አሁን ሂድና የናቡቴን የወይን እርሻ ውሰድ’ አለችው። ኤልዛቤል እንዲህ ያለ መጥፎ ድርጊት በመፈጸሟ መቀጣት ያለባት አይመስልህም?

ስለዚህ ይሖዋ ከጊዜ በኋላ እሷን ለመቅጣት ኢዩ የተባለ ሰው ላከ። ኤልዛቤል ኢዩ እየመጣ መሆኑን ስትሰማ ዓይኖቿን ተኳኩላ ቆንጆ ለመምሰል ሞከረች። ይሁን እንጂ ኢዩ ሲመጣና ኤልዛቤልን በመስኮት ሲያያት ቤተ መንግሥቱ ውስጥ የነበሩትን ሰዎች ‘ወደ ታች ወርውሯት!’ አላቸው። ሥዕሉ ላይ እንደምታየው ሰዎቹ የታዘዙትን አደረጉ። ወደ ታች ወረወሯትና ሞተች። ክፉዋ ንግሥት ኤልዛቤል በዚህ መንገድ ጠፋች።