በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 65

የእስራኤል መንግሥት ተከፋፈለ

የእስራኤል መንግሥት ተከፋፈለ

ይህ ሰው ልብሱን እየቀዳደደ ያለው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ? ይሖዋ እንዲህ እንዲያደርግ ስላዘዘው ነው። ይህ ሰው አኪያ የሚባል የአምላክ ነቢይ ነው። ነቢይ ምን እንደሆነ ታውቃለህ? አምላክ ወደፊት የሚሆነውን ነገር አስቀድሞ የሚነግረው ሰው ነው።

አኪያ ኢዮርብዓምን እያነጋገረው ነው። ኢዮርብዓም ሰሎሞን በተወሰነ የግንባታ ሥራው ላይ ሃላፊ አድርጎ የሾመው ሰው ነበር። አኪያ ኢዮርብዓምን እዚህ መንገድ ላይ ሲያገኘው አንድ ያልተለመደ ነገር አደረገ። የለበሰውን አዲስ ልብስ አወለቀና 12 ቦታ ቀዳደደው። ኢዮርብዓምን ‘አሥሩን ቁርጥራጭ ልብሶች ውሰድ’ አለው። አኪያ አሥሩን የልብስ ቁርጥራጮች ለኢዮርብዓም የሰጠው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?

ይሖዋ መንግሥቱን ከሰሎሞን ሊወስደው መሆኑን አኪያ ገልጿል። አኪያ ይሖዋ አሥሩን ነገዶች ለኢዮርብዓም ሊሰጠው መሆኑን ተናገረ። በዚህም መሠረት የሰሎሞን ልጅ ሮብዓም የሚገዛቸው ሁለት ነገዶች ብቻ ይሆናሉ ማለት ነው።

ሰሎሞን አኪያ ለኢዮርብዓም የነገረውን ነገር ሲሰማ በጣም ተቆጣ። ኢዮርብዓምን ለመግደል ሞከረ። ሆኖም ኢዮርብዓም ወደ ግብፅ ሸሸ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሰሎሞን ሞተ። ሰሎሞን ለ40 ዓመታት ነግሦአል፤ ከዚህ በኋላ ግን ልጁ ሮብዓም ነገሠ። ኢዮርብዓም በግብፅ ምድር ሳለ ሰሎሞን እንደሞተ ስለ ሰማ ወደ እስራኤል ተመለሰ።

ሮብዓም ጥሩ ንጉሥ አልነበረም። እንዲያውም ከአባቱ ከሰሎሞን ይበልጥ ክፉ ሆነባቸው። ኢዮርብዓምና ሌሎች ጥቂት ታላላቅ ሰዎች ወደ ንጉሥ ሮብዓም ሄዱና ለሕዝቡ ደግና አሳቢ እንዲሆን ጠየቁት። ሮብዓም ግን አልተቀበላቸውም። እንዲያውም ከበፊቱ ይበልጥ ክፉ ሆነባቸው። ስለዚህ ሕዝቡ ኢዮርብዓምን በ10 ነገዶች ላይ አነገሡት፤ ሁለቱ የብንያምና የይሁዳ ነገዶች ግን በንጉሥ ሮብዓም ሥር ሆኑ።

ኢዮርብዓም ሕዝቡ በይሖዋ ቤተ መቅደስ በሚካሄደው የአምልኮ ሥነ ሥርዓት ለመካፈል ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄዱ አልፈለገም። ስለዚህ ሁለት የወርቅ ጥጃዎችን ሠራና በአሥሩ ነገድ መንግሥት ሥር ያለው ሕዝብ እነዚህን ጥጃዎች እንዲያመልኩ አደረገ። ብዙም ሳይቆይ ምድሪቱ በወንጀልና በዓመፅ ተሞላች።

የሁለቱ ነገድ መንግሥትም ችግር አጋጥሞታል። ሮብዓም ከነገሠ በኋላ አምስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የግብጽ ንጉሥ ኢየሩሳሌምን ለመውጋት መጣ። በይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ የነበሩትን ብዙ ውድ ነገሮች ወሰደ። ስለዚህ ቤተ መቅደሱ ሲሠራ የነበረውን ሁኔታ እንደያዘ የቆየው ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነበር።