በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 59

ዳዊት መሸሽ የነበረበት ለምንድን ነው?

ዳዊት መሸሽ የነበረበት ለምንድን ነው?

ዳዊት ጎልያድን ከገደለ በኋላ የእስራኤል ሠራዊት አለቃ የነበረው አበኔር ዳዊትን ሳኦል ፊት አቀረበው። ሳኦል በዳዊት በጣም ተደሰተ። በሠራዊቱ ላይ አለቃ አድርጎ ሾመው፤ በዚያው በንጉሡ ቤት እንዲኖርም አስቀረው።

ከጊዜ በኋላ ሠራዊቱ ከፍልስጤማውያን ጋር ተዋግቶ ሲመለስ ሴቶቹ ‘ሳኦል ሺህ ገደለ፤ ዳዊት ግን አሥር ሺህ ገደለ’ ብለው ዘመሩ። ዳዊት ከሳኦል የበለጠ ክብር ስለተሰጠው ሳኦል ቅናት አደረበት። የሳኦል ልጅ ዮናታን ግን ቀናተኛ አልነበረም። ዳዊትን በጣም ይወደው ነበር፤ ዳዊትም ዮናታንን ይወደው ነበር። ስለዚህ ምን ጊዜም ጓደኛሞች ሆነው ለመኖር ሁለቱም እርስ በርሳቸው ቃል ገቡ።

ዳዊት በገና ሲጫወት በጣም ጎበዝ ነበር፤ ሳኦልም ዳዊት የሚጫወተውን ሙዚቃ መስማት ይወድ ነበር። ይሁን እንጂ ከዕለታት አንድ ቀን ሳኦል ያደረበት ቅናት አንድ መጥፎ ድርጊት እንዲፈጽም አደረገው። ዳዊት በገናውን እየመታ ሳለ ሳኦል ‘ዳዊትን ከግድግዳው ጋር አጣብቀዋለሁ!’ ብሎ ጦሩን አነሳና ወረወረው። ይሁን እንጂ ዳዊት ዞር ስላለ ጦሩ ሳተው። በሌላ ጊዜም ሳኦል ጦሩን እንደገና በዳዊት ላይ ወርውሮ ስቶታል። በዚህ ጊዜ ዳዊት በጣም መጠንቀቅ እንዳለበት ተገነዘበ።

ሳኦል ቃል ገብቶ የነበረውን ነገር ታስታውሳለህ? ጎልያድን ለገደለ ሰው ልጁን ሚስት አድርጎ እንደሚድርለት ተናግሮ ነበር። በመጨረሻ ሳኦል ዳዊትን ልጁን ሜልኮልን ማግባት እንዲችል በመጀመሪያ ጠላቶቻቸው ከሆኑት ከፍልስጤማውያን መካከል 100 ሰዎችን መግደል እንዳለበት ነገረው። እስቲ አስበው! ሳኦል ፍልስጤማውያን ዳዊትን ይገድሉታል ብሎ ተማምኖ ነበር። ሆኖም አልገደሉትም፤ ስለዚህ ሳኦል ልጁን ለዳዊት ሚስት አድርጎ ሰጠው።

ከዕለታት አንድ ቀን ሳኦል ዳዊትን መግደል እንደሚፈልግ ለዮናታንና ለአገልጋዮቹ ሁሉ ነገራቸው። ይሁን እንጂ ዮናታን ለአባቱ ‘ዳዊትን አትግደለው። ምንም ያደረገህ ነገር የለም። እንዲያውም እሱ ያደረገው ነገር ሁሉ በጣም ጠቅሞሃል። ጎልያድን በገደለ ጊዜ ሕይወቱን አደጋ ላይ ጥሎ ነበር፤ አንተም በዚያ ጊዜ ስታየው ደስ ብሎህ ነበር’ አለው።

ሳኦል ልጁ ያለውን ሰምቶ ዳዊትን እንደማይገድለው ቃል ገባ። ዳዊት ተመለሰና ቀድሞ ያደርግ እንደነበረው እንደገና ሳኦልን በቤቱ ውስጥ ማገልገል ጀመረ። ይሁን እንጂ አንድ ቀን ዳዊት ሙዚቃ እየተጫወተ እያለ ሳኦል እንደገና ዳዊትን ለመምታት ጦሩን ወረወረበት። ዳዊት ጦሩን ዞር ብሎ ሲያሳልፈው ግድግዳው ላይ ተሰካ። ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ነበር! በዚህ ጊዜ ዳዊት መሸሽ እንዳለበት ተገነዘበ!

በዚያ ቀን ማታ ዳዊት ወደ ራሱ ቤት ሄደ። ይሁን እንጂ ሳኦል ዳዊትን እንዲገድሉት የተወሰኑ ሰዎች ላከ። ሜልኮል አባቷ ምን ለማድረግ እንዳቀደ ታውቅ ነበር። ስለዚህ ባሏን ‘ዛሬ ሌሊት ሸሽተህ ካላመለጥክ ነገ ትገደላለህ’ አለችው። በዚያ ቀን ሌሊት ሜልኮል ዳዊት በመስኮት ወጥቶ እንዲያመልጥ ረዳችው። ዳዊት ለሰባት ዓመታት ያህል ሳኦል እንዳያገኘው ቦታ እየቀያየረ መደበቅ አስፈልጎት ነበር።