በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 28

ሕፃኑ ሙሴ ከሞት የዳነበት ሁኔታ

ሕፃኑ ሙሴ ከሞት የዳነበት ሁኔታ

የሴትዮዋን ጣት ይዞ የሚያለቅሰውን ሕፃን ተመልከት። ይህ ሕፃን ሙሴ ነው። ይህች ቆንጆ ሴት ማን እንደሆነች ታውቃለህ? ግብፃዊት ልዕልት ናት፤ የራሱ የፈርዖን ልጅ ነች።

የሙሴ እናት ልጅዋ በግብፃውያን እንዲገደል ስላልፈለገች ሦስት ወር እስኪሞላው ድረስ ደብቃ አቆየችው። ይሁን እንጂ ሙሴን ሊያገኙት እንደሚችሉ ስላወቀች እርሱን ከሞት ለማዳን ስትል የሚከተለውን ነገር አደረገች።

በሣጥን መልክ የተዘጋጀ ቅርጫት ወሰደችና ውኃ እንዳያስገባ አድርጋ ሠራችው። ከዚያም ሙሴን እዚያ ውስጥ አስገባችውና በናይል ወንዝ አጠገብ ረጃጅም ሣር ባለበት ቦታ አስቀመጠችው። የሙሴ እህት ሚርያም በአቅራቢያው ቆማ የሚሆነውን ሁኔታ እንድትከታተል ታዝዛ ነበር።

ብዙም ሳይቆይ የፈርዖን ሴት ልጅ ልትታጠብ ወደ ናይል ወንዝ መጣች። ድንገት ይህን ቅርጫት በረጃጅም ሣር መካከል ተቀምጦ አየችው። ከአገልጋዮችዋ መካከል አንዷን ጠርታ ‘ሂጂና ያንን ቅርጫት አምጪልኝ’ አለቻት። ልዕልቷ ቅርጫቱን ስትከፍተው አንድ ቆንጆ ሕፃን አየች! ሕፃኑ ሙሴ እያለቀሰ ነበር፤ ልዕልቲቱ አዘነችለት። እንዲገደል አልፈለገችም።

ከዚያ በኋላ ሚርያም ወደ እነርሱ ተጠጋች። ሥዕሉ ላይ ልታያት ትችላለህ። ሚርያም የፈርዖንን ሴት ልጅ ‘ሕፃኑን የምታጠባልሽ እስራኤላዊት ሴት ልጥራልሽ?’ ብላ ጠየቀቻት።

ልዕልቲቱም ‘እባክሽ፣ ጥሪልኝ’ አለቻት።

ሚርያም ለእናቷ ለመንገር እየሮጠች ሄደች። የሙሴ እናት ወደ ልዕልቲቱ ስትመጣ ልዕልቲቱ ‘ይህን ሕፃን ውሰጂና አጥቢልኝ፤ ያሳደግሽበትን ዋጋ እከፍልሻለሁ’ አለቻት።

ስለዚህ የሙሴ እናት የራሷን ልጅ ማሳደግ ጀመረች። ከጊዜ በኋላ ሙሴ በደንብ ሲያድግ እናቱ ሙሴን የራስዋ ልጅ አድርጋ ለወሰደችው ለፈርዖን ልጅ ሰጠቻት። ሙሴ በፈርዖን ቤት ሊያድግ የቻለው በዚህ መንገድ ነበር።